>

ስለ ሪል እስቴት በጨረፍታ (ከይኄይስ እውነቱ)

ስለ ሪል እስቴት በጨረፍታ

ከይኄይስ እውነቱ


ሪል እስቴት የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ፊደል ብንጽፈውም ቃሉ እንግሊዝኛ ነው፡፡ የአማርኛ አቻ ጠፍቶለት ይሁን ወይም ጽንሰ ሃሳቡን በበቂ ሁናቴ አለመረዳት ወይም ተለምዶና ለአጠቃቀም ቀሎ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ቋንቋችን ውስጥ በተውሶ እንደሚገኙ ሌሎች ባዕዳን ቃሎች ይህም ቦታ አግኝቶ በይፋ እየተጠቀምንበት ነው፡፡  ቃሉን ባለሙያዎች በሙያ መስካቸው ለመግባባት በሚጠቀሙበት (technical term) ዓውድ በተለይም በሕግ አግባብ ስናየው የተለየ አረዳድ ይኖረዋል፡፡ እኛ አገር በተለምዶ ሪል እስቴት የምንለው ለመኖሪያም ሆነ ለንግድ የሚገነቡ ሕንፃዎችን ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የኢንቨስትመንት ደንብ ሪል እስቴትን የሕንፃ ግንባታ ሥራ በሚል ነው የወሰደው፡፡ የሪል እስቴት ልማት እንደ አንድ የኢንቨስትመንት የሥራ መስክ በ1990ዎቹ አካባቢ ተጀምሮ፣ በስፋት የተገባበት በወቅቱ የነበረው አገዛዝ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ግንባታ ከጀመረ ወዲህ ነው፡፡

ባለፉት 50 ዓመታት የመሬት ሥሪት ሥርዓት ተቀይሮ ሕዝብ የመሬት ባለቤትነቱን መብት ሙሉ በሙሉ ቢነጠቅም ሪል እስቴት መሬትና ከመሬት ጋር በቋሚነት የተያያዙ መዋቅሮችን ይመለከታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕግ ባለሙያዎች ዘንድ በሚታወቀውና ‹‹BLACK’S LAW DICTIONARY›› በሚባለው የሕግ መዝገበ ቃላት ሪል እስቴትን በሚከተለው መልኩ ይበይነዋል፤ ‹‹Real Property [Real Estate]: Land and anything growing on, attached to, or erected on it, excluding anything that may be severed without injury to the land.›› መሬት እና በመሬት ላይ የበቀሉ፣ የተያያዙ ወይም የቆሙ ማናቸውም ንብረቶች ሆኖ፣ መሬቱ ሳይጎዳ ሊለያዩ የሚችሉ ማናቸውንም ነገሮች አይጨምርም፡፡

በ1952 ዓ.ም. በወጣው የፍትሐብሔር ሕጋችን ሪል እስቴት ለሚለው በተወሰነ ደረጃ ተቀራራቢ የሚሆነው ‹‹የማይንቀሳቀስ ንብረት›› የሚለው ሐረግ ነው፡፡ በዚህ ሕግ ለሪል እስቴት የተሰጠ ትርጓሜ የለም፡፡ ይሁን እንጂ በሕጉ ከቊ. 1281 እስከ 1308 ያሉት ድንጋጌዎች ለመኖሪያ በተሠሩ ሕንፃዎች (አፓርትመንት) ውስጥ ለመኖሪያ የተመደቡ ክፍሎች ባለሀብትነትን በሚመለከት፤

1/ የጋራ/የአንድነት ሀብት ሆነው ስለሚቈጠሩ የሕንፃው ክፍሎች፤

2/ ስለ ጋራ ንብረቱ አስተዳደር ስምምነትና ስለ ስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች፤

3/ የመኖሪያ ቤት ሕንፃው (የአፓርትመንቱ) የጋራ ስላልሆኑት ክፍሎች፤

4/ የጋራ/አንድነት የሆነው ንብረት አገልግሎት፣ አስተዳደርና ስለሚያስፈልገው ወጪ፤

5/ ከቤቶቹ ባለቤቶች ተውጣጥቶ ስለሚቋቋመው የጋራ ባለሀብቶች ማኅበር፤ የማኅበሩ ሥልጣንና ተግባር፣ የአባላቱ መብትና ግዴታ፣ ስብሰባና ውሳኔ፤

6/ ስለ ማኅበሩ ሥራ አመራር አሰያየም፣ ሥልጣንና ተግባር፣ ኃላፊነት፣ የአገልግሎት ክፍያ፤

7/ በንብረቱ ላይ ስለሚደርስ አደጋና መልሶ ማቋቋም፤

የሚመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎች አሉት፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች በዓዋጅ ቊ.370/1995 ዓ.ም. የጋራ ሕንፃ ባለቤትነትን (ኮንዶሚኒየም) ከሚመለከተው ዓዋጅ በስተቀር ሪል እስቴት ላይ ተፈጻሚ ናቸው፡፡ 

በቅርቡ በወጣው የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው ዓዋጅ ቊ. 1263/2014 አንቀጽ 31 (ጠ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል፤

‹‹የሪል ስቴት ልማትን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ሕጎችን ያመነጫል፤ ሲጸድቅም ተግባራዊነቱን ይከታተላል፡፡›› የሚለው ነው፡፡

የሚኒስቴሩ መ/ቤት የሪል እስቴት ልማትን በሚመለከት ፖሊሲና ሕግ እስከሚያወጣ ድረስ ሥራ ላይ ያለውና ከፍ ብለን የጠቀስነው የመኖሪያ ቤት ሕንፃዎችን (አፓርትመንት) የሚመለከቱት የፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህ ድንጋጌዎች ማንኛውም በሪል እስቴት ልማት ላይ በተሠማራ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብት ላይ ተፈጻሚነት አላቸው ማለት ነው፡፡ 

ከፍ ብለን የዘረዘርናቸውን የሕግ ማዕቀፎች እንደ መነሻ (background) ይዘን የሪል እስቴት ልማት እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በግልም ሆነ በማኅበር ተደራጅቶ የሪል እስቴት ልማት ላይ የተሠማራ ባለሀብት አሠራር ምን ይመስላል? መሬት ከማግኘት ጀምሮ፣ የሕንፃ ግንባታው ወጪ ምንጭ፣ የገዥዎች የክፍያ ሥርዓት፣ ስምምነት በተደረሰበት ጊዜ የመኖሪያ ቤቶቹን ስለማስረከብ፣ የሕንፃዎቹ አስተዳደር ወዘተ. በጥቅሉ በመመልከት በዚህ የሥራ መስክ የሚታየውን ትዝብቴን በጥቂቱ አካፍላለሁ፡፡

የሪል እስቴት ልማት መሠረታዊ የሆነውን የቤት እጦት ችግር በማቃለል ረገድ የራሱ ድርሻ እንዳለው የሚታመን ቢሆንም፣ በሕግና በሥርዓት ካልተመራ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ መሀከለኛ መደብ (middle class) የሚባል የኅብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ ከወታደራዊው ደርግ ጀምሮ ባለፉት 50 ዓመታት የተፈራረቁት ወንጀለኛ የአገዛዝ ሥርዓቶች ላገርና ለወገን ዕድገትና ልማት ደንታ የሌላቸው መሆኑን በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ደርግ ያልገባውንና ባዕድ የሆነውን የኅብረተሰባዊነት ፍልስምና አሰፍናለሁ ብሎ በንጉሡ ዘመን እያቆጠቆጠ ያለውን ኢኮኖሚ አሽመድምዶ ሁሉም ዜጋ ተካክሎ ደሀ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የኋለኞቹ ሁለት አገዛዞች ካንድ ኩሬ የተቀዱ አገርንና ሕዝብን ለማዋረድና ለማጥፋት ያለሙ በመሆናቸው፤ በሚከተሉት የጐሣ ፖለቲካ ምክንያት ዜጎች ባገራቸው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሊሠሩ ባለመቻላቸው ኢኮኖሚው ባለበት መቆም ሳይሆን ወደ ጥልቁ በርባሮስ ወርዷል፡፡ ከእጅ ወዳፍ የሚባለውን ኑሮ የሚመራውን ሕዝብ የሚላስ የሚቀመስ አሳጥተውታል፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛው (80 ከመቶ በላይ የሚሆነው የገጠር ነዋሪና 15 በመቶ ገደማ የሚሆነው የከተማው ደሀ) ከድኅነት ወለል የበታች በታች ሲገኝ፣ የወንጀል ሥርዓቱ የፈጠራቸው ጥቂት ‹ሀብታሞች› እና ባገዛዝ ሥርዓቱ በጎ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ነጋዴዎች ያሉበት የኅብረተሰብ ክፍፍል ተፈጥሯል፡፡ በመላ አገራችን ከ1ሚሊየን ጥቂት ከፍ የሚለው አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደግሞ ከእጅ ወዳፍ የሚለውን ኑሮ የሚመራ ነው፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ከሚያገኘው ደመወዝ 35 በመቶ የገቢ ግብር፣ ማባሪያ የሌለው የግዴታ መዋጮ (ደርግ ‹የእናት ሀገር ጥሪ› በሚል የጀመረውን ያለ ተጠያቂነት አሁንም በተለያየ ስም በግዳጅ የቀጠለወ)፣ የጡረታ መዋጮ፣ ተገቢ ሕክምና ለማያገኝበት የጤና ኢንሹራንስ መዋጮ ወዘተ. ተቀንሶ በእጁ የሚቀረው ቤት ኪራይ፣ ቀለቡን፣ ልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍያዎችና የልጆቹን ትምህርት ወጪ የሚሸፍን አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት በሚያገኘው ደመወዝ እንኳን በሪል እስቴት የሚሸጠውን አፓርትመንት የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን አይችልም፡፡ ከደመወዙ አይደለም ቁጠባ ሊታሰብ የቅድሚያ የደመወዝ ክፍያ እየወሰደም ከወር እስከ ወር መድረስ ተስኖታል፡፡ ቁጠባ ከሌለ ደግሞ ስለ ዕድገት ማሰብ ምኞት ብቻ ይሆናል፡፡ ተጠያቂነት በሌለበት የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ጥቂቱ የኅበረተሰብ ክፍል በቁጠባ በባንኮች የሚያስቀምጠው ገንዘብ ለምን እንደሚውል በውል አይታወቅም፡፡ ዛሬ መንግሥታዊ ባንኮች በጠራራ ፀሐይ የሚዘረፉበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አመራራቸው ዕውቀትና ልምድ በሌላቸው ተረኞች ተሞልቶ የተረኞችን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ እየሠሩ ይገኛል፡፡ በመሀሉ ቆጣቢው ኅብረተሰብ ገንዘቡን ባንክ በማስቀመጡ የሚያገኘው ብቸኛ ዋስትና ከዝርፊያ መጠበቅ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የማይረባውን ወለድ ትተን ያስቀመጠው ገንዘብ በግሽበትና በኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት በማያቋርጥ ሁናቴ እየቀነሰ መሄዱ የኢኮኖሚ ጠበብትነትን አይጠይቅም፡፡ መንግሥታዊ ባልሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ተቀጥሮ የሚሠራው የኅብረተሰብ ክፍል እጅግ ጥቂት በመሆኑ አጠቃላይ ሥዕሉን ለመረዳት ግምት ውስጥ የምናስገባው አይደለም፡፡ የቀረው የኅብረተሰብ ክፍል በባህላዊው የ‹ጉልት ንግድ› እና በቀን ሥራ የተሠማራ እንዲሁም ጥገኛ ሆኖ አብዛኛው የሥራ አጥ ሠራዊት ጎራ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ስለ መሀከለኛ መደብ ማውራት ፌዝ ይሆናል፡፡  የመሀከለኛ መደብ ከሌለ ደግሞ የሪል እስቴት ልማት ተጠቃሚዎች ሊሆኑ የሚችሉት ዘርፈውም ሆነ ነግደው (ትላልቆቹን ነጋዴዎች ማለቴ ነው) ጥሪት የያዙ ጥቂት የኅብረተሰቡ ክፍሎችና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያኖች ናቸው፡፡ አብዛኛውን ኅብረተሰብ እያስለቀሱት ባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለቤት ለመሆን መቆጠብ ያቃተውና በደቀቁ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ረሃቡን ታግሦ እያኗኗረ ያለ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን ላይ ባለፉት 32 ዓመታት በሠለጠነው ንቅዘት የተሞላበት ሥርዓት በብልሹ አሠራርና ይሉኝታ ባጣ የሞራል ልሽቀት ያልተነካ መንግሥታዊ ተቋም፣ እንደ ሃይማኖትና በጎ አድራጎት ያሉ ማኅበራዊ ድርጅቶች፣ የግል የንግድ ድርጅቶችና ግለሰብ ፈልጎ ለማግኘት በእጅጉ ይቸግራል፡፡ ከደሙ ንጹሕ ነኝ የሚሉ ጥቂት ግለሰቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመት ስለ ልዩ ሁናቴው (exception) ሳይሆን ስለ አጠቃላዩ ደንብ (general rule) መነጋገራችን እንቀጥላለን፡፡ ባገራዊው የንቅዘት ባሕር ውስጥ ተዘፍቀው ከሚገኙት፣ ዜጋን ከሚያስለቅሱትና በመጥፎ ስም (infamy) ከሚታወቁት የንግድ ማኅበራት ወይም ግለሰብ ‹ባለሀብቶች› መካከል በሪል እስቴት የተሰማሩት ይጠቀሳሉ፡፡ በዘመነ ወያኔም ሆነ በወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ የዜና አውታሮችን፣ ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን፣ የፍርድ ቤት ውሎዎችን የተከታተለ ዜጋ ለዚህ አባባል እንግዳ አይሆንም፡፡ አንዳንዶች የቤት ገዢዎችን ገንዘብ ሰብስበው እብስ ያሉ፣ በፍርድ ቤት ሙግት የገጠሙ፣ ዓመታትን አስቆጥረው ቤቶቹን በጅምር ያስቀሩ፣ ወዘተ. ይገኛሉ፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ እንዳይሳሳት የምፈልገው በቤት ገዢዎች ዘንድ ችግር የለም እያልሁ አይደለም፡፡ ትኩረቴ አልሚዎቹ ላይ በመሆኑ እንጂ፡፡

1/ ለሪል እስቴት ልማት የሚውል መሬት

ሀ) ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የሚመደብ መሬት

በዚህ ረገድ የንቅዘት አሠራሩ እንዳለ ሆኖ፣ ቀደም ሲል የነበረውም ሆነ አሁን ያለው አገዛዝ ለሪል እስቴት አልሚዎች በሊዝ ሥርዓት መሬት መስጠቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ መልኩ መሬት ወስደው ለዓመታት ያላለሙ፣ መሬቱን ለሌላ ዓላማ የተጠቀሙበትና አልፎ ተርፎም በሕገ ወጥ አሠራር መሬት ‹ሽጠው› ያስተላለፉ ‹ባለሀብቶች› እንዳሉ ይህ ጸሐፊ ሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ የታዘበው ነው፡፡ 

ለ) ከተማ ዳር ከሚገኙ ቦታዎች ለአርሶ አደሮች ካሣ በመክፈል በግዢ የሚገኝ መሬት፤ እና

ሐ) ከተማ ውስጥ ከግለሰቦች በግዢ ወይም ‹‹በጋራ ማልማት›› በሚል አሠራር የሚገኝ ቦታ፤

‹‹በጋራ ማልማት›› የሚለውን አሠራር ለመረዳት ከተወሰኑ የሪል እስቴት አልሚዎች ባሰባሰብነው መረጃ መሠረት መሬቱ ለሚገኝበት የቤት ባለቤት ከሚገነባው ሕንፃ አጠቃላይ ግምት 15 በመቶ የሚሆነውን በየዓይነት (የመኖሪያ ክፍሎች) መስጠት ወይም ቦታውን አሳልፎ የሚሰጠው ግለሰብ የቤቱን የገበያ ግምት 50 በመቶ በጥሬ ገንዘብ ክፍያና ቀረውን 50 በመቶ የሕንፃው ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ በዓይነት (የመኖሪያ ክፍሎች) የሚሰጡበት አሠራር ነው፡፡ ሁለቱም የአሠራር ዘይቤዎች አሁን የምንቀበለው ገንዘብ ለወደፊት ከምንቀበለው አንድ ዓይነት የገንዘብ መጠን  የበለጠ ጠቀሜታ አለው የሚለውን የኢኮኖሚ እሳቤ (time value of money) እና የገንዘብን ግሽበት (inflation) ግምት ውስጥ ያላስገቡ በመሆናቸው ቦታውን አሳልፎ የሚሰጠው ግለሰብ ተገቢውን/ተመጣጣኝ ዋጋ ስለማግኘቱ ዋስትና የለም፡፡

2/ የሪል እስቴት አልሚዎች የገንዘብ ምንጭ

ሀ) በዋናነት የመኖሪያ ቤቶቹ ባለቤቶች ከሚሆኑት ግለሰቦች በቅድሚያ ከሚገኝ የሽያጭ ክፍያ፤

ለ) አልፎ አልፎ ከአልሚዎች የሚመደብ መነሻ ገንዘብ፤ እና

ሐ) ከባንኮች የሚገኝ ብድር፤ 

የኋለኞቹ ሁለቱ ምንጮች እምብዛም ሥራ ላይ የዋሉ አይደሉም፡፡

3/ የሪል እስቴት አልሚዎች ከቤት ገዢዎች ጋር የሚያደርጉት ስምምነት

እስካሁን ባለኝ መረጃ ሪል ስቴት ለማልማት ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ፈቃድ አግኝቶ በመስኩ የተሠማራ ባለሀብት ሥራ ላይ ያለውንና አግባብነት ያላቸውን የፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች አክብሮ የሚሠራ የለም፡፡ እስከነአካቴው በሪል ስቴት ልማት ላይ ተፈጻሚ የሆነ ሕግ እንዳለም የማያውቁት ቊጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ በግዢ ባለቤቶች የሚሆኑትም አብዛኛዎቹ ግለሰቦች አልሚዎቹ ባዘጋጁት ደንብና ሁናቴ (terms and conditions) ከመስማማት በስተቀር (እውነቱን ለመናገር ሰነዱን በቅጡ አንብቦ የሚፈርም የለም) ስለሚኖሩበት ቤትና በጋራ ስለሚጠቀሙበት ንብረት ገዢ ሕግ ስለመኖሩ የሚያውቁት ጉዳይ የለም፡፡ የሚገርመው ከቤት ገዢ ደንበኞች ጋር ከሚደረገው ስምምነት አንሥቶ፣ ቤቶቹ ተጠናቅቀው ርክክብ ከተፈጸመ በኋላ ስላለው አስተዳደራዊ ጉዳይ በአልሚዎቹ ፈቃድና ውሳኔ የሚፈጸም ነው፡፡ በሪል እስቴት አልሚዎች የሚዘጋጁ ስምምነቶች ወጥነት የሌላቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጡ የውኃና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ስምምነቶች ባንደኛው ወገን ብቻ ተዘጋጅተው ሌላኛው ፈርሞ ከመቀበል ውጪ የመደራደር መብት የማይሰጡ ውሎች (adhesive contracts) ጠባይ ያላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ የከፋው ደግሞ እነዚህ ውሎች ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁናቴ የአልሚውን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቁ፣ አልሚው ሲያጠፋ ተጠያቂነትን የማያስከትሉ፣ በገዢዎች ላይ ቀምበር የሚጭኑና በየትኛውም መመዘኛ ሲታዩ በሕጉ ኢፍትሐዊ፣ ኢሞራላዊ እና በተለይም አሮጌ ጎጆአቸውን የቀለሱበትን ቦታ ለሪል እስቴት አልሚዎች የሚሸጡ ግለሰቦችን ተስፋ ማጣት (desperation) በማየት፣ የሚያስደነግጥና በሞራል ረገድ ተቀባይነት የሌለው (unconscionable) እና ባጠቃላይ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም (undue advantage) የሚያገኙበት ዓይነት ውል/ስምምነት ነው፡፡ መንግሥት አለ የምንል ከሆነ የሚመለከተው አካል ኅብረተሰቡን ከእንደዚህ ዓይነት የረቀቁ ዘራፊዎች ሊጠብቅ ይገባል፡፡ ግለሰቦች በሚያደርጉት ውል ውስጥ እየገባ ይፈትፍት እያልን አይደለም፡፡ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ሊጎዳ የሚችል እንደ ሪል እስቴትና ሌሎች መሰል ተግባራትን አሠራር በሚመለከት ስታንዳርድ በማውጣትና በመቆጣጠር ሥርዓት እንዲያስይዝ ይጠበቃል፡፡ የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች አንዱና ዋነኛ ተግባራቸውም ይሄው ነውና፡፡ 

ከዚህ ቀደም Pick Pick ICT Technologies የሚባል ድርጅት በላይ አብ ሞተርስ ከሚባል ድርጅት ጋር በቅንጅት ሆነው (በወቅቱ በሚዲያ እንደተነገረው ማስታወቂያ ከሆነ Pick Pick ICT Technologies የበላይ አብ ሞተርስ እኅት ኩባንያ እንደሆነ የሚገልጽ ነበር) ግለሰቦችን የታክሲ ተሽከርካሪ ባለቤቶች እናደርጋችኋለን በሚል (ከባንክ ጋር በማስተሳሰር) ማስተባበር ይጀምራሉ፡፡ መተዳደሪያ ይሆነኛል ብለው ካሰቡ ካንዳንድ ዝቅተኛ ኑሮ ካለቸው ግለሰቦችና በዐቅዱ ተጠቃሚ ልንሆን እንችላለን ብለው ኢንቨስት ካደረጉ ግለሰቦች የመኪናውን ጠቅላላ ዋጋ 30 በመቶ ከሰበሰቡ በኋላ ገንዘቡን ዘርፈው ካገር መጥፋታቸው ይታወሳል፡፡ በመጨረሻም በላይ አብ ሞተርስ የግለሰቦቹን ገንዘብ እንዲመልስ ሲጠየቅ፣ Pick Pick ICT Technologies ለቴክኖሎጂ መግዣ በሚል ከእያንዳንዱ ግለሰብ ብር 10ሺህ የወሰደ በመሆኑ ይህንን ቀንሶ እንደሚሰጣቸው ለባለገንዘቦቹ ይነግራል፡፡ ባለገንዘቦቹም በላይ አብ ሞተርስ ለተባለው የቴክኖሎጂ ግዢ Pick Pick ICT Technologies በድምሩ ብር 10 ሚሊየን ማስተላለፉን የሚያሳይ ሕጋዊ ደረሰኝ (ማስረጃ) ካቀረበ ቀሪውን ለመቀበል ፈቃደኛ እንደሆኑ ይገልጹለታል፡፡ ይሁን እንጂ በላይ አብ ሞተርስ ማስረጃው ባለመኖሩ ይሁን ወይም ከእነ አካቴው የቴክኖሎጂ ግዢ የተባለው ሐሰት በመሆኑ ማስረጃውን ለማሳየት ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል፡፡ ከዚያም አንዳንድ ባለገንዘቦች ለ10ሺህው ብር በፍርድ ቤት ክስ እንመሠርታለን፤ ቀሪውን ስጡን ሲሏቸው የተስማሙ ይመስሉና ገንዘቡን ከመቀበላቸው በፊት ድርጅቱ አንድ የግዴታ ወረቀት አዘጋጅቶ ፈርሙ ይላቸዋል፡፡ ግዴታው ይህን ያህል ገንዘብ መቀበላችንን በፊርማችን እናረጋግጣለን የሚል ብቻ ሳይሆን፣ በላይ አብ ሞተርስ ለPick Pick ICT Technologies ድርጅት የቴክኖሎጂ መግዣ ከእያንዳንዱ ግለሰብ በቅድሚያ ከተከፈለው ገንዘብ ብር 10 ሺህ ማስተላለፉን በሚገባ ተገንዝቤ የሚል ሐረግ እንዳለበት ባለገንዘቦቹ ይረዳሉ፡፡ በዚህ መልኩ የዐቅዱ ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው ታክሲውንም ሳያገኙ ከብር 10 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ገንዘብ በሁለቱ ድርጅቶች መመሳጠር ተዘርፈዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሸፍጥ የፈጸሙና እየፈጸሙ ያሉ ኅብረተሰቡን በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፉ ድርጅቶች ያለምንም ተጠያቂነት ሕጋዊ መስለውና መልካም ስም እንዳላቸው ተቈጥሩ እየሠሩ ያሉበት አገር ውስጥ ነው የምንገኝ፡፡ መብቱን ለማስከበር በጋራ የማይቆም ኅብረተሰብ ሁሌም የአጭበርባሪዎች ሰለባ ከመሆን አያመልጥም፡፡ ባነሣነው ጉዳይ ባለገንዘቦቹ ባንድነት ሆነው ክስ እንመሠርታለን ቢሉና የሐሰት የግዴታ ወረቀቱን ባይፈርሙ ፍትሕ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ለወደፊቱም ሌሎች አጭበርባሪዎች ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስተማሪ ከመሆኑም በተጨማሪ ኋላ ለሚወሰድ ተግባርና ውሳኔ መልካም ምሳሌነትን (precedence) ያስቀምጥ ነበር፡፡ 

4/ በሪል እስቴት ልማት የተሠሩ ቤቶች አስተዳደር

ይህ ንዑስ ርእሰ ጉዳይ የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ ትኩረት ሲሆን መጣጥፉንም ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነኝ ይኸው አልሚዎች ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ ሪል እስቴቶችን በግዢ ለባለቤቶቹ ካስተላለፉ በኋላ የቤቶቹን ባለቤቶች መብት ነጥቀው በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን አስተዳደሪ አድርገው መሰየማቸው ነው፡፡ ለመሆኑ ለመኖሪያ ቤት የሚሆን ሪል እስቴት ያለማ ባለሀብት ቤቶቹንና የጋራ መጠቀሚያዎቹን በግዢ ባለቤቶቹ ለሆኑት ነዋሪዎች ካስተላለፈ በኋላ የትኛው ሕግ ነው ራሱን በአስተዳዳሪነት ሰይሞ ቋሚ የአገልግሎት ክፍያ እያስከፈለ ነዋሪዎችን ‹እንዲበዘብዝ› እና እንዲቆጣጠር መብት የሚሰጠው? 

በጋራ የመኖሪያ ቤቶች ባለቤትነት (ኮንዶሚኒየም) ዓዋጅም ሆነ በዚህ ጽሑፍ በተጠቀሰውና ለሪል እስቴት ተፈጻሚነት ባለው የፍትሐብሔር አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች መኖሪያ ቤቶቹ ተሽጠው ከተጠናቀቁ እና የቤቱ ገዥዎች የባለቤትነት መብት ካገኙ በኋላ አልሚው ሠርቶ ባስረከበው ሕንፃና የጋራ አገልግሎት አጠቃቀም፣ ባጠቃላይ የቤቶቹ አስተዳደር ላይ ምንም መብት የለውም፡፡ የአስተዳደሩ መብት የመኖሪያ ባለቤቶቹ ሲሆን፣ ይህም የሚፈጸመው ሁሉም ባለቤቶች አባል የሚሆኑበት ማኅበር በማቋቋም፣ ጠቅላላ ጉባኤው በመረጣቸው አመራሮች አማካይነት ይሆናል፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙን ከባለቤቶቹ መካከል የሕግ ባለሙያ ካለ (በሌላም መስክ ፕሮፌሽናሎች ካሉ) ተመካክረው የሚፈጽሙት ይሆናል፡፡ የራሱን መብትና ግዴታ ጠንቅቆ የማያውቅና የማያስከብር ዜጋ ከራሱ አልፎ እንዴት ላገር ሊተርፍ ይችላል?

ለማጠቃለል፤

1ኛ/ ኅብረተሰቡን ከሕገ ወጦች የረቀቀ ብዝበዛ (ዘረፋ) ለመከላከልና ለመጠበቅ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ደንቦችንና ስታንዳርድ በማውጣት በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚነኩና በግል ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቊጥጥርና ክትትል የማድረግ ሥራ እንዲሠራ ይጠበቅበታል፡፡ በበጀት የሚተዳደሩ መ/ቤቶች የገቢ ምንጫቸው ግብር ከፋዩ ዜጋ እንደሆነ ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል፡፡

2ኛ/ ኅብረተሰቡን በሕጋዊነትና በድርጅት ስም ከተከለሉ ጩልሌዎች ለመጠበቅ፣ መብቱና ግዴታውን ለይቶ እንዲያወቅ፣ የመብት ጥሰትም ሲደርስበት በጋራ በመቆም መብቱን እንዲያስከብር መደበኛነትና ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ዘርግቶ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በሥራ ላይ ያሉ ሀገር-በቀል፣ የአካባቢን ማኅበረሰብ ጥቅምና ፍላጎት ለማራመድ የተቋቋሙ የማኅበረሰብ ተቋማት (የሲቪክ ማኅበራት) ካሉ ለተወሰነ የጋራ ዓላማ ወይም ፖሊሲ የኅብረተሰቡን ድጋፍ የማስተባበር ሥራ (advocacy work) በስፋት መሥራት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ትናንሽ ከሚመስሉን የመብት ማሳወቅ ሥራ ጀምረን ግንዛቤ መፍጠር ከቻልን ለትልቅ አገራዊ ጉዳይ የሚቆም፣ መብቱንና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ንቁና ብቁ ዜጋ መፍጠር ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ እኅቴ ለሥራ ጉዳይ ሩዋንዳ ሄዳ የታዘበችውን ገጠመኝ ማንሣት የሲቪክ ማኅበራት የኅብረተሰቡን ጠባይ በበጎ መልኩ ቅርፅ በማስያዝ ረገድ ያላቸውን ዓይነተኛ ሚና በማሳየት አብነት ይሆናል፡፡ የሲቪክ ማኅበሩ ባገር ደረጃ በተለይም በዋና ከተማው የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ 50 በመቶ ለመቀነስ በማለም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መደበኛና ተከታታይ በሆነ መልኩ ይሰጣል፡፡ ዕቅዱን ለማሳካት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ 5 ዓመት ቢሆንም የሚፈለገው ውጤት ላይ በአንድ ዓመት ጊዜ ሊደርስ ችሏል፡፡

Filed in: Amharic