ንጉሥ ሚዳስና አፄ አቢይ አህመድ አሊ
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ባለፉና አሁን ባሉ የሀገራት መሪዎች መካከል የሚስተዋሉ በርካታ ተመሳስሎዎች አሉ – በደጉም በክፉም፡፡ አሁን የማነሳው በግሪክ ሥነ ቃላት የሚወሳው ንጉሥ ሚዳስና የኛው አፄ ቦካሣ – ማነው – አፄ አቢይ አህመድ አሊን የሚያመሳስላቸው ከዚህ በታች የምጠቅሰው የስግብግብነት ጠባይ ደግሞ በአስደናቂነቱ ለዬት ይላል፡፡
ሚዳስ የተባለው የሀገረ ግሪክ ምናባዊ ንጉሥ እጅግ ሀብታም ነበረ፡፡ ከነሐስ እስከብርና ወርቅ እንዲሁም ዕንቁና አልማዝ ድረስ “ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ” የሆነ ምንም የማይጎድለው በዘመናችን አገላለጽ ቱጃር ነበር – ባለጸጋ እንዳላልኩ ግና ግምት ውስጥ ይግባልኝ ታዲያ፡፡ ይሁንና ንጉሥ ሚዳስ በዚያ ሁሉ ወርቅና ሀብት ንብረቱ ሊረካ ያልቻለ የገብጋባነትና ያልተገራ ፍላጎት መፍለቂያ ዋሻ ነበረ፡፡
ለፍላጎታችን ገደብ ካላደረግንለት አደገኛ ነው ወንድም እህቶቼ፡፡ ፍላጎታቸውን ለከት ያሳጡ የምድራችን ዜጎች ከላይ እስከታች ተቆጣጥረውን ዓለማችንን አሣሯን እያበሏት ነው፡፡ በሀብትም ይሁን በሥልጣን አንድ ሰው ፍላጎቱንና ምኞቱን ድንበር ካላበጀለት ደግሞ አገርንና ሐዝብን ጭምር መቀመቅ እንደሚከት አሁን የምናነሳው የሁለቱ መሪዎች የጋራ ጠባይ ዋና ማሳያ ነው፡፡
በንጉሥ ሚዳስ ቤተ መንግሥት ውስጥ በሚገኝ የአትክልት ሥፍራ በአማልክት ጣዖታቱ ዓለም የዘማዊነትና የጠጭነት ተምሣሌት የሆነ ሳይሊነስ የሚባል አማልክት ሰክሮ ተጋድሞ ይገኛል፡፡ ንጉሡም የዚያ አማልክት ወዳጅና ጓደኛ መሆን የሚያስገኘውን ቁሣዊ ትሩፋት በሚገባ ያውቅ ነበርና አማልክቱ ከስካሩ እስኪነቃ ተንከባክቦ በተኛበት ያቆየዋል፡፡ ዘማዊውና ሰካራሙ አማልክት ከተኛበት እንደነቃ ወደ ንጉሡ ዘንድ ቀርቦ ንጉሡ ባለውለታው እንደሆነ በመግለጽ ምን ሊያደርግለት እንደሚሻ ይጠይቀዋል፡፡ ንጉሡም ምንም ባልጎደለበት ቤተ መንግሥቱ ተንቀባርሮ እየኖረ ሳለ ነገር ግና አዱኛ አትጠገብምና በእጁ የሚነካው ሁሉ ወደ ወርቅነት እንዲለወጥለት ያደርገው ዘንድ አማልክቱን ይጠይቀዋል፡፡ አንዳችም ነገር ማድረግ የማይሳነው አማልክቱ ሳይሊነስም ምንም እንኳን ንጉሡ የጠየቀውን ጥያቄ ባይደግፈውም አንዴውኑ ቃል ገብቷልና ይፈቅድለታል፡፡
ንጉሥ ሚዳስ የሚነካው ሁሉ በቅጽበት ወደወርቅነት መለወጡን ቀጠለ፡፡ ሚዳስ በደስታ ቦረቀ፡፡ የቤተ መንግሥቱ ድንጋይና ሣር ቅጠል ሁሉ ሣይቀር በአንዴ ወርቅና አልማዝ መሆን ጀመረ፡፡ ሚዳስ በደስታ እየተፍነከነከ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ግን አንድ አሳዛኝ ነገር ተፈጠረ፡፡ እርሱም እጅግ የሚወዳት ሴት ልጁ ስትክለፈለፍ መጥታ ስትጠመጠምበትና በእጁ ሲጨብጣት ከመቅጽበት ወደግዑዝ ወርቅነት መለወጧ ነበር፡፡ ያላሰበው ነገር ስለገጠመው ጭንቀት ጥበቱ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ሆነ፡፡ ወዲያውኑም ለአማልክቱ ብርቱ ተማፅኖ አድርጎ ያን ጦሰኛ ስጦታ አስነሳ፡፡ ልጁንም በብዙ ልመናና ደጅ ጥናት ከወርቅነት ወደ ሰውነት አስለወጠ፡፡
አፄ አቢይ አህመድ ሥልጣን ከያዘባት ከዚያች ከዕለታት ሁሉ እጅጉን የተረገመች መጋቢት 24 ቀን 2010 ጀምሮ ስንትና ስንት ታላላቅ ዜጎች በዚህ ሰውዬ እጆች ተነክተው እንደበከቱብን አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ አፄ አቢይ አንድን ሰው ነካው ማለት፣ አንድን ዜጋ አቅፎ ሣመ ወይም አስጠግቶ በአስመሳይ ቅጥፍጥፍ ምላሱ አነጋገረ ማለት በቁሙ ገደለው ማለት ነው፡፡ ይህ ሰይጣናዊ ፍጡር ምን ትብታብ ይዞብን እንደመጣ ባላውቅም እርሱ ወደሥልጣን ማማ ከወጣ ወዲህ የደረሰብንን ሁሉ ለመጻፍና ለመናገር ግን አራት ዓመታትም አይበቁንም፡፡ ያገሬ ሰው ይህን መሰሉን የሰይጣን ውላጅ “የሰንበት ጽንስ” የሚለው ወዶ አይደለም፡፡
አቢይ ወደውጪ ሲወጣ ሰዎች ይገደላሉ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ራሱን ከሰወረም ብርቅዬ ዜጎች እየታደኑ ወደ ዘብጥያ ይወርዳሉ፡፡ ኦሮምያን በዋናነት ጨምሮ አንዳንድ ክልሎች እንደፈለጉ ያሽቃንጣሉ፡፡ በክልላቸው የሚገኙ የሌላ ዘውግ አባላትን በተለይም አማሮችን እንዳሻቸው ይገድላሉ፤ ያስራሉ፤ ያንገላታሉ፤ ያፈናቅላሉ፤ ይዘርፋሉ፤ መዝረፍ ያልቻሉትን ሀብት ንበረት ያወድማሉ፤ በጥቅሉ ምስኪኖቹ ዜጎች መፈጠራቸውን እስኪራገሙ ድረስ መከራና ስቃያቸውን ያበዙባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ከአፄው ቡራኬና ፍቃድ ውጪ እንደማይሆን በፍቅሩ የደነዘዙ/ የነሆለሉ መረዳት ባይፈልጉም እኛ ግን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ቅቤው አፄ ቦካሣ ሰውን ሲጨብጥ በተቆራኘው የአጋንንት መንፈስ ሳቢያ የሚነካው ሰው ሁሉ ይፈዝና ልክ ቡዳ እንደበላውና ወደጋንነት ወይም እንሥራነት ተለውጦ ዞምቤ እንደሚሆነው በድን ሰው ሁሉ የርሱ ቅን ታዛዥ ይሆናል፡፡ አሁን አሁን እርሱን ላለማየትና ላለመጨባበጥ የሚፈራ የሚጠነቀቅም ሰው ሳይበዛ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ “እባብ ያየ በልጥ በረዬ” እንዲሉ ነውና እነዳንኤል ክብረትንና እነታማኝ በየነን የተመለከተ አፄ አቢይን ሲያይ የሚገባበት ቢጠፋው አይፈረድበትም፡፡ እኔ ለምሣሌ አይበልብኝና አቢይ ባለበት አካባቢ ዝር ማለትን በፍጹም አልሻም፡፡
በተረፈ እንግዲህ ስንጮህበት ከነበረው ነገር ሁሉ አብዛኛው ስለታዬ ጎርፉ እስኪያልፍ እንደምንም ቻል ማድረግ ነው፡፡ መታወቂያ እየታዬ ወደ አዲስ አበባ የሚገባና የማይገባ ሰው መለየቱ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ይዞታዎች ወደ “ታላቋ ኦሮምያ” መጠቃለላቸውም እንደዚሁ ከመጨረሻው መጀመሪያዎች የሚካተት ነው፡፡ እኔ ይህን ዓይነት ኦሮሙማዊ ትንግርት ስመለከት እነታዬ ቦጋለንና እነታምራት ነገራን፣ ከቀድሞዎቹ ደግሞ እነአፄ ኃይለ ሥላሤንና እነመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን የመሳሰሉ ድንቅ ድንቅ ኦሮሞዎችን ማወቄ ጠቀመኝ እንጂ ፈጣሪየን “እንኳን ኦሮሞ አድርገህ አልፈጠርከኝ!” ብዬ ምሥጋና ማቅረብ ከጅሎኝ ነበር፡፡ አንድ ፈረንጅኛ ፈሊጥ እዚህ ላይ ባስታውስ ቅር የሚልብኝ ሰው አይኖርም መቼም፡፡ “ብላክሽፕ” ይባላል፡፡ “ማፈሪያ” እንደማለት ነው በቁም ትርጉሙ፡፡ አዎ፣ በቤተሰብም፣ በአካባቢም፣ በማኅበረሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ … አንዳንድ ማፈሪያዎች መኖራቸው ገሃድ እውነት ነው፡፡ አማራው – ለምሣሌ ነው የምልህ – ከሚያፍርባቸው መካከል በደምሳሳው የብአዴን አባላትና በተናጠል ደግሞ ገነት ዘውዴን፣ አገኘሁ ተሻገርን፣ ሙሉጌታ አሥራተ ካሣን፣ ደመቀ መኮንንን፣ ተመስገን ጥሩነህን፣ ላቀ አያሌውን ወዘተ. መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከኦሮሞም በዚህ በአሁኑ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ተሰልፈው ወጧ እንዳማረላት ሴት ይሠሩትን ያጡትን ኦሮሞዎች በማፈሪያነትና በነገው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ታሪክ ላይ የማይሽር ጠባሳ በማስቀመጥ ረገድ ቢጠቀሱ ነውር የለበትም፡፡ ሁላችንም ማፈሪያዎች አሉን፡፡ ወንጀልንና ክፋትን በመከፋፈል ረገድ መበላለጥ ይኖር እንደሆነ እንጂ በሁሉም ዘውግ ውስጥ እጅግ የምናፍርባቸው ሆዳሞችና ዘረኞች አሉን፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር መሆኑ የሚነገረውም ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሰዎች ይህኛውን ወይንም ያኛውን መሆን አለመሆንን ቢመኙ በሰውኛ አካሄድ ስህተት የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ቢቻለኝማ ካናዳዊ በሆንኩ በወደድኩ፡፡ ሸፋፋው ዕድሌ ግን የሰውን ደም ካልጠጡ፣ ነገድን ከነገድ ካላባሉ ሀገር መምራት የሚቻል የማይመስላቸው ማይማን ወደሚመሯት አገር አመጣና ጣለኝ፡፡ የማታፍርባቸው መሪዎችና የማታፍርበት ሀገር ይስጥህ ወንድሜ፡፡
ከፍ ሲል የጠቀስኩትን ምሥጋናዊ ጸሎት ወይንም ጸሎታዊ ምሥጋና ይበልጥ እንድገፋበት የሞራል ብርታት የሰጠኝ ደግሞ የዛሬ ሁለት ይሁን ሦስት ዓመታት ገደማ “ውጣልኝ!” በሚል ርዕስ በዩቲብ የወጣው የኦሮሙማ ክሊፕ ነው፡፡ በዚያ ክሊፕ ውስጥ በጣም ብዙ ሰው ተሳትፏል፤ አንዳችም ሳያፍሩ ነው ታዲያ፡፡ ደራሲውም፣ አቀናባሪዉም፣ ዘፋኙም፣ ሙዚቀኞቹም፣ አጃቢዎቹም፣ ጨፋሪዎቹም … ምንም አያፍሩም፤ እኔ ግን ስለነሱ የምገባበትን አጣሁ፡፡ ያን ክሊፕ ያዬ ጤናማ ሰው – ኦሮሞም ይሁን ትግሬ ወይም ሌላ – ኦሮሙማዎች ምንኛ በዘረኝነት ደዌ እንደሚሰቃዩ ይረዳል፡፡ አሁን ባለኝ የአስተሳሰብና የአመለካከት ይዞታ ላይ እንዳለሁ ኦሮሞ ብሆን ኖሮ ያን ክሊፕ ሳዳምጥ ምን ይውጠኝ ነበር ብዬ ሳስብ አለማሰቡን ብቻ መረጥኩ ወንድማለም፡፡ በዘፈኑ ርዕስ ጉግል አድርጉና ያን ብዙ ኦሮሞ በደስታ ሲቃ እያነባ የሚዘፍነውንና የሚጨፍርበትን ዘፈን አድምጡት – አማራን አሁን በምናየው ፍጥነት ከአዲስ አበባ ለማውጣት ነው የዘፈኑ ማዕከላዊ ጭብጥ፤ በዘፈኑ የተገለጸው ቁም ነገር እኮ ነው እየተተገበረ ያለው በነገራችን ላይ – የሽመልስ ትንቢትና ፖለቲካዊ ዕቅድ እኮ ነው አሁን በተግባር እየተገለጠ የሚገኘው – ለታዛቢ ቀልድ ሊመስል ይችላል፡፡ ግን እውነት ነው፡፡ የኦሮሙማ አስፈሪ ገጽታ ደግሞ ይሄ ነው፡፡
ዘፈኑን ስሙት ብያችኋለሁ፡፡ ያኔ – ዘፈኑን ስትሰሙት – ኦሮሙማ ማለት – ጽንሰ ሃሳቡ ራሱ – ከጥልቁ የዲያቢሎስ ጽልመታዊ መንግሥት እንደመጣ ትረዳላችሁ፡፡ ያኔ አቢይና ሽመልስ የጥልቁ ተወካዮች ብቻ ሳይሆኑ ሊቀ ሣጥናኤል በሰው አምሳል ኢትዮጵያ ውስጥ በነሱ አካል በግልጽ እንደተከሰተ ትገነዘባላችሁ፡፡
ለማንኛውም ጨለማ ሲጠነክር የተረገዘ ብርሃን ሳይወድ በግዱ አፈትልኮ መውጣቱ ያለና የነበረ ነውና ለብርሃናማው ዘመን እንዘጋጅ፤ ብዙም ተስፋ አንቁረጥ፡፡ ተስፋችንም የአዳምና የሄዋን፣ የአደምና የሀዋ ፈጣሪ የሆነው ኅው እግዚአብሔር ነው፡፡ አንተ አላህ ብትለው የምቀበልህ በደስታ ነው፤ ምክንያቱም ፈጣሪ በቋንቋዎቻችን ልክ ቢያንስ ከሰባት ሽህ አንድ መቶ በላይ ስሞች አሉትና፡፡ የነዚህን ገልቱዎች ነገር ለአራሹና ለጎልጓዩ ታሪክ እንተወው፡፡ በቅርቡ ሰደቃቸውን አብልቶ ወደመጡበት የጨለማው ግዛት ይሰዳቸዋል፡፡ ያኔ ታዲያ እውነተኛ የሃይማኖትና የመንግሥት መሪዎችን እናገኛለን፡፡ ቢሆንም ግን በምኞት ብቻ የሚሣካ ነገር እንደሌለ ደግሞ መረዳት ጠቃሚ ነው፡፡ ቢያንስ ግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዘህ የማትቀበለው ትንሣኤም ሆነ ነፃነት ዋጋ እንደሌለው ካለፈ ታሪካችን መማር አለብህ፡፡ እንደስካሁኑ ከተኛን አሁንም መጪውን ትንሣኤ የሚነጥቀን ተኩላና ቀበሮ አይጠፋምና ከፊት ለፊት የሚገኘውን ብሩኅ ዘመን የመጨረሻው እንዲያደርግልን በየእምነታችን አጥብቀን እንጸልይ፡፡ ሃይማኖታችንም ፖለቲካችንም እንዳይሆኑ ሆነው በጨለማው ገዢ ተጠልፈዋልና ፈጣሪ በቶሎ ይድረስልን፡፡ መስዋዕትነቱንም ያቅልልልን፤ ያሣለፍነውን መከራ ቆጥሮ ምሕረቱን በአፋጣኝ ይላክልን፡፡
እኛ ደግሞ ሰውነትን በማስቀደም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንከባበር፡፡ የሃይማኖት ልዩነትን መሠረት አድርገን – ቅንጣት በማያገባን እየገባን – ጽድቅንና ኩነኔን አንዳችን ላንዳችን እያደልን በከንቱ አንመፃደቅ፡፡ በፈጣሪ ሥራ አንግባ፡፡ ኃላፊነትና ግዴታችንን እንወቅ፡፡ የአንድኛችን ሃይማኖት መጽሐፍ “ዕርፍ እሚያህል ጉድፍ በራስህ ዐይን ውስጥ እያለ በሰው ዐይን ውሰጥ የምትገኝን አነስተኛ ጉድፍ ለማውጣት የምትጣደፍ አንተ ማን ነህና….” ይላልና ራሳችንን በመፈተሽ ዘመናችንን በሚዋጅ ዕውቀትና ጥበብ አእምሯችንን እንገንባ፡፡ ፍርድን ለፈራጅ እንተው፡፡ ክፋትን፣ ምቀኝነትንና ተንኮልን እንጠየፍ፡፡ አዲሱ ዓመት እንደክፉዎች ምኞት ሳይሆን ደጋጎች እንደሚጠብቁት የብሩኅ ተስፋና የእውነተኛ ትንሣኤ ዘመን ይሁንልን፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ፡፡