>
5:26 pm - Saturday September 17, 0355

እቴጌ ጣይቱ ብጡል ማን ናቸው? (ምኒልክ ቴሌቪዥን)

እቴጌ ጣይቱ ብጡል ማን ናቸው?

ምኒልክ ቴሌቪዥን


*… የእቴጌ ጣይቱ 182ኛ ዓመት ልደት መታሰቢያ !!

«ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም እና ከእናታቸው ወይዘሮ የውብዳር በነሐሴ12ቀን1832 ዓ.ም በጌምድር ውስጥ ደብረታቦር ከተማ ተወለዱ።

በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት መሠረት በተወለዱ በ 80 ቀናቸው ጥቅምት 23 ቀን1833 ዓ.ም በደብረ ታቦር እየሱስ ቤተክርስቲያን ክርስትና ተነሱ። በልጅነት ዘመናቸው በዚሁ ደብር ውስጥ ዳዊት ደገሙ። ከዚያም በጊዜው ይሰጡ የነበሩትን ሌሎች የሃይማኖት ትምህርቶች በየታላላቅ አድባራት በመዘዋወር ያጠናቀቁ ስለመሆናቸው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።

የተማሩባቸውም መጻሕፍት የተጻፉት በግዕዝ ቋንቋ ስለነበር ቋንቋውን አጣርተው ያውቁ ነበር። እናታቸው ወይዘሮ የውብዳር ባለቤታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም ከሞቱ በኋላ በጅሮንድ መዩ የተባሉትን የአፄ ቴዎድሮስ ባለሟልን አግብተው ነበር። እርሳቸውም ጣይቱ ብጡል ትምህርት እንዲቀስሙ ለማድረግ ልዩ መምህር ቀጥረውላቸዋል።

እቴጌ ጣይቱ በማኅደረ ማርያም ሆነው ይማሩና መፃሕፍትን ይቀጽሉ በነበሩበት ጊዜ ለቤተክርስቲያን መጋረጃ መሥሪያ በትርፍ ጊዜያቸው ፈትል እየፈተሉ ያቀርቡ ነበር። በበገና ቅኝትና ድርደራም በኩል የታወቁ ባለሙያ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።

የጣይቱና የምኒልክ ጋብቻ

የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ በሸዋ የአፄ ቴዎድሮስ እንደራሴ ከነበሩት አቶ በዛብህ ጋር ነሐሴ 17 ቀን 1857 ዓ.ም በጋዲሎ አካባቢ በተደረገው ጦርነት ድል አድርገው ወደ አንኮበር ገቡ። በነሐሴ 24 ቀን ነገሡ። በነገሡም በአሥራ ሁለት ዓመታቸው የፋሲካን በዓል በባሕር ዳር አቅራቢያ ሱሉልታ ላይ ዋሉና ደብረ መይ በጣይቱ ብጡል እናት በወይዘሮ የውብዳር ቤት ከጣይቱ ጋር ተጫጭተው ስለጋብቻቸው ተነጋገሩ። ከዚያም ዋና ከተማቸው ወደነበረችው ደብረ ብርሃን ተመለሱ።

ከተጫጩ ከሁለት ዓመት በኋላ ወይዘሮ ጣይቱን ለማስመጣት በቤተ መንግሥቱ በተደረገው ምክር መሠረት አለቃ ተክለማርያም ወልደ ሚካኤል ደብዳቤ ተሰጥቷቸው ተላኩ። በዚያም አስፈላጊው ሁሉ በተፋጠነ ሁኔታ ተሟልቶ በጐጃም በኩል አድርገው ወደ ሽዋ ጉዞውን ጀመሩ።

ደብረ ብርሃንም በገቡ ጊዜ ንጉሡ ምኒልክ ታላቅ አቀባበል አደረጉላቸው። ከዚያም ጣይቱ ወንድማቸው ራስ ወሌ ብጡል ዘንድ ለጥቂት ዓመታት ተቀምጠው ከቆዩ በኋላ የጋብቻቸው ሥነ-ሥርዓት የፋሲካ ዕለት ሚያዝያ 25 ቀን1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ተጋቡ።

አፈወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ «ዳግማዊ አጼ » በተባለው መጽሐፋቸው ከገጽ39 እስከ 41ላይ «አጼ ምኒሊክ ከልጅነት ጀምረው ሲመኟት እንደ ህልም ሲአልሟት ትኖር የነብረችው ጣይቱ ብጡል በ18 75ዓ.ም ደብረ ብርሃን ገባች። ንግሥተ ሸዋ ሆነች ወዲያው የፋሲካ ዕለት አንኮበር መድኃኔዓለም ቆርበው ተጋቡ። … ፀሐይቱ ለማለት ጣይቱ ተባለች ነገር ግን ከጣይቱ እጣይቱ ለመባል ይገባታል» ይላሉ።

«ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ»

ንጉሡ «አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» የሚለውን ስም በተቀዳጁ በማግሥቱ ጥቅምት 27 ቀን 1882ዓ.ም ወይዘሮ ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ። የሥርዓተ ዘውዱ አፈፃፀም በከፍተኛ መሰናዶ የተጠናቀቀ በመሆኑ እጅግ ደማቅ እንደነበር ከተፃፉ ጽሑፎች ለማወቅ ይቻላል። እቴጌ ጣይቱም ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ የተቀበሉትን ዘውድ ደፉላቸው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታወቁበት «እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» በሚል የክብር ስም ማኅተም ተቀረፀላቸው። እነዚሁ ታሪካዊ ሂደቶች እቴጌዪቱን በኢትዮጵያ ዱኛዊ፣ ወታደራዊና ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ከፍተኛና ብሩህ ሚና ለመጫወት የቻሉ አድርጓቸዋል።

ፖለቲካዊ ተግባራት

እቴጌ ጣይቱ በዱኛ አስተዳደር አንፃር የነበራቸው ችሎታና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በታሪክ አዋቂዎች ዘንድ ተደናቂነትን አትርፎላቸዋል። በየጊዜው ይነሱ በነበሩ የሀገር ጉዳዮች ላይ ይይዙት የነበረው አቋም፣ ይሰጡት የነበረው ውሳኔና ያስተላልፉ የነበረው ትዕዛዝ ተሰሚነትና ተቀባይነት እያገኘ እንደመሄዱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄድ ለነበረው የዱኛ ሥልጣናቸው ዓይነተኛ ምክንያት ነበር።

እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ዱኛ ተሳትፏቸው የገነነውና በአገር አስተዳደርም ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት የጀመሩት፤ ኢትዮጵያ ሚያዝያ 25ቀን 1981ዓ.ም በውጫሌ ላይ ከኢጣሊያ ጋር በተፈራረመችው ውል ውስጥ በኢጣሊያንኛው ትርጉም ሀገሪቷን ነፃነት እንደሌላት ጥገኛ በማስመሰል ዓላማ ላይ የተመረኮዘ ውንብድና መኖሩ ከታወቀ ወዲህ ነው።

ይህ ለአድዋ ጦርነት መነሳት ምክንያትና ዋነኛ መንስዔ የሆነው ጉዳይ ሊታወቅ የቻለው እቴጌ ጣይቱ የውጫሌ ውል አንቀፅ 17ላይ አለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ የተባሉት ቋንቋ አዋቂ አፄ ምኒልክ በሰጧቸው ትዕዛዝ መሠረት ነው። ያኔ የውሉን ሰነድ በመመርመር የውሉ 17ኛ አንቀፅ የያዘውን የትርጉም መዛባት ያለበት መሆኑን አሳወቁ። ጉዳዩ ኢትዮጵያ የምትጐዳበት ስለመለሆኑ ጭምር በማስረዳት በሰጡት ቃል እቴጌ ጣይቱ በጥንቃቄ ተመለከቱት።

ጉዳዩን አፄ ምኒልክ በመጀመሪያ ሳይረዱ አለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ እንዲታሰሩ ቢያደርጉም እቴጌ ጣይቱ ግን እኚህ ሰው ትክክለኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆናቸውን ለአፄ ምኒልክ በማስረዳት ከሦስት ዓመታት እስራት በኋላ ማስፈታታቸው ይታወቃል። በዚህ በኩል ሲታይ እቴጌ ጣይቱ የምኒልክ የቅርብ አማካሪ በመሆን በፖለቲካ ተግባሮች ምን ያህል አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ መገንዘብ ይቻላል።

እቴጌ እንደተናገሩትም «ዓፅመ ጊዮርጊስ ቢታሰር ቢፈታም ለሀገሩ የሚገባውን ሠርቶ ነው። ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ዮሴፍ፣ ኢጣሊያኖች በተንኮል ገብተው በማታለል ይህን የመሰለ ሥራ ሲሠሩ አነጋጋሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ሳያስጠነቅቅዎ ቀረ?» በማለት የእቴጌ ጣይቱ የቁጣ መዓት ወደ ዮሴፍ ዞረ።

ከዚያም ጨምረው «ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ፣ ሥር የሚነቅል፣ መሠረት የሚያፈርስ ጉዳዩን ሁሉ እኔ ሳላየው እንዳያልፍ ይፍቀዱልኝ» ብለው ለንጉሡ ባመለከቱት መሠረት «አንቺ ሳታይው ሳትመረምሪው አያልፍም» በማለት ፈቀዱላቸው። ይህ ሁኔታ የሚያመለክተው እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው ቦታ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ነው። ውሉንም ለማስተካከል አፄ ምኒልክ ያደረጉት የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ሚኒስትሮች የጦር አለቆችና መኳንንት የሚገኙበት ጉባዔ እንዲጠራ አደረጉ።

እያንዳንዱ ሰው ስለተነሳው ችግር ያለውን አስተያየት የሀገር ፍቅር በተሞላበት አንደበትና የጋለ መንፈስ ሲገለፅ ቆየ። እቴጌ ጣይቱም «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» የሚል አቋማቸው በታሪክ ቅርስነቱ ለትውልድ ትተውት ያለፉት አባባል ዘመን ተለውጦ ዘመን እየተተካ በሄደ ቁጥር የሚነገር ሆነ።

ስለዚህ የእቴጌን ጀግንነት የቁርጠኛ ኢትዮጵያዊ ልጅ ለመሆናቸው ሌላ ማረጋገጫ ማቅረብ አያስፈልግም። እቴጌ ጣይቱ ወንድማቸው ራስ ወሌን አተኩረው በማየት በታወቀው ጀግና አንደበታቸው የተሰበሰበውን ሕዝብ ስሜት ለመቀስቀስ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ማድረጋቸው ይነገራል።

በዚያች ደቂቃ እቴጌ ጣይቱ ስማቸውን የሚያስጠራ ታሪካቸውን የሚያስታውስ አንድ የምኒልክ የደም ቋጠሮ ሀረግ ሳያሠሩ ማለፋቸው ሳያሳዝናቸው እንዳልቀረ መገመቱ ቀላል ነው። ይህንም ሀዘን ለግዞት ወደ እንጦጦ ከመውጣታቸው ጥቂት ጊዜ በፊት ሊሸኟቸው በተሰበሰቡት መኳንንትና ወይዛዝርት ፊት የገጠሙት ግጥም አንጀት የሚበላ ነበር።

«ተወዶ ከመኖር ተጠልቶ መውለድ

ማን ያይብኝ ነበር ይህን ሁሉ ጉድ»

Filed in: Amharic