>

ደምበጫ ከተማን በጨረፍታ (ጌታ በለጠ ደበበ)

ደምበጫ ከተማን በጨረፍታ

ጌታ በለጠ ደበበ


በሐገራችን የጉዞ ማስታወሻ መያዝ እና ለሰዎች ማካፈል በብዙ አልተለመደም። ሰዎችም ለእንዲህ አይነት ነገር ትኩረት ሰጥተው አያዳምጡም። በየኼዱበት የጉዞ ማስታወሻ ይዞ ትዝብትን ማካፈል ሸጋ ነገር ነው። በተለይ የጉዞ ማስታወሻው አላማ አንድ የአካባቢ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ የታሪክ እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ የሚያሳይ ከሆነ ሊደመጥ የተገባ ነው።የዚህ ማስታወሻ አላማ በጎጃም፣ደንበጫ ከተማ በአጋጣሚ በኼድሁበት ወቅት ያየሁትንና የሰማሁትን ብሎም በታሪክ ድርሳናት ያነበብሁትን ለሌሎች ማካፈል ነው። በእኔ ውስን አዕምሮ አቅም ልክ ያለውን በአጭሩ አቀረብሁ እንጅ የደንበጫ ታሪክ በዚህ የሚወሰን አይደለም።ሥለሆነም የጎደለው ሞልቶ፣ የተጣመመውን አቃንቶ ታሪኩን ማዳበር የተመልካች መብት ነው።
ደንበጫ ከተማ የማውቃት ከዛሬ ብዙ ዓመታት በፊት ቢሆንም ያስተዋልኋት እና ታሪኳን በመጠኑም ቢሆን ያጠነኋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። በዚህ ሳምንት ለአንድ ጉዳይ ወደ ከተማዋ ጎራ ብዬ ነበር፡፡ ከተማዋ ከጦቢያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ (በረራ) በ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ትገኛለች። በውስጥ ብዙ የታሪክ አሻራዎችን የያዘችው ከተማ “ደንበጫ” ስለሚለው ስያሜዋ የተለያዩ መላምቶች ይነገራሉ። ከነዚህ መላምቶች መካከል ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው። የመጀመሪያው መላምት ደንበጫን “ደንብ መውጫ” ከሚል ሥም ጋር ያገናኛታል። ነገሩ እንዲህ ነው። ጥንት ዕለት የዳሞት መቀመጫ (መዲና) ደንበጫ ላይ ሆኖ ነበር። ደንበጫ የገዥዎች መቀመጫ በመሆኗ ደንብ እና መመሪያዎች የሚወጡት ከመዲናዋ በመሆኑ “ደንብ ማውጫ” እንደተባለች፣ በሂደትም ሥሟ ደንበጫ ተብሎ እንደተቀየረ የሚነግረን ነው።
ሁለተኛው መላምት ደንበጫን “ደም ቢጫ” ወደሚል ሥያሜ ይወስዳታል። በዚህ መላምት መሰረት አንድ መነኩሴ መስቀል ይዘው እንዳሉ በአካባቢው በተተኮሰች ጥይት ሲመቱ ከተለመደው ቀይ ቀለም ውጭ የሆነ ቢጫ መልክ ያለው ደም ፈሰሳቸው፡፡ ሰዎችም የመነኩሴው ደም ቢጫ ሆነ ለማለት ደም ቢጫ አሏት፡፡ በሂደትም ደንበጫ ሆነ የሚል ነው፡፡ የሆነ ሆነና ሁለቱም መላምቶች በመሆናቸው የጠራ አቋም ለመያዝ ሰፊና ጥልቅ ምርምር ይጠይቃል። መላ- ምት ማለት በመላ (በብልሃት) አንድ ነገር እንደዚህ ወይም እንደዚያ ሊሆን ይችላል ብሎ ሳይንሳዊ ያልሆነ ብያኔ መስጠት ነው።
ደንበጫ በአንድ ወቅት ከጎንደር እሰክ ሊሙ ኢናሪያ የተዘረጋው የንግድ ትስስር መሸጋገሪያ መስመር ነበረች፡፡በሐገር ውስጥም ቢሆን ከደንበጫ ተነስቶ ወደ ቡሬ፣ ደብረ ኤልያስ እና ሞጣ ደረስ የሚዘልቅ የንግድ ትስስር ተፈጥሮ ነበር፡፡ በአጭሩ ከተማዋ የአንድ ዘመን የንግድ መነኸሪያ ነበረች፡፡
በከተማዋ ውስጥ አንድ ጥንታዊ ደብር አለ።እሱም ቅዲስ ሚካኤል ደብር ነው። የተመሰረተው በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። በወጋችን ላይ ቅዱስ ሚካኤል ደብር ከመደበሩ ቀደም ብሎ በ12ኛው መቶ ክፍለዘመን የተመሰረተ የሥላሴን ቤተ ክርሰቲያን አለ። ሲመሰረትም “ጉብሪት ሥላሴ” ተብሎ ነው። የቅዱስ ሚካኤል ደብር በአሰራሩ እጅግ ውብ የሆነ፣ ቅጥር ግቢው በዛፎች የተከበበ ሲሆን በውስጡ ብዙ ታሪካዊ እና ሐይማኖታዊ ቅርሶችን አካትቶ ይዟል፡፡ በደብሩ ብዙ መፅሐፍት፣ ድርሳናት እና ሐተታዎች ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደብሩ የራሱ ሙዚየም ያለው በመሆኑ ታሪክ መመርመር የፈለገ፣ የአባቶችን እውቀት ለመሸመት የጓጓው ሰው ቢኖር ወደ ከተማዋ ጎራ ብሎ ተዝቆ ከማያልቀው ታሪክ መቆድስ ይቸላል፡፡
በከተማው መሐል አንድ የመንግስት ንዋዬ ቤት (የንግድ ባንክ) ቅርንጫፍ በአንድ ታላቅ ሐገረ ገዥ ስም ተሰይሞ ይገኛል። እሱም “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ቅርንጫፍ” ይላል። የሕዝብ ተቋማት በጀግኖች እና ሐገረ ገዥዎች ስም ተሰይሞ ማዬት ምንኛ ደስ ይላል፡፡ ባንኩ ላይ ያነበብሁት ስም የደጃዘማች ጎሹን የጀግንነት ታሪክ ተመልሼ እንዳስታውስ ገፋፋኝ፡፡ ባሻዬ! ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ማን ናቸው የሚለውን አስመልክቶ ትቂት ላውጋ!ደጃዝማች ዘውዴ የዳሞት ባላባት እና ገዥ ነበሩ። ጥንት ጊዜ ጋብቻ የሚመሰረተው ርስተ- ጉልት ተጠንቶ፣ የገዥነት መደብ ተመርምሮ በመሆኑ ደጃዝማች ዘውዴ የጎጃሙን ባላባት የታላቁ ራስ ኃይሉ ዮሴዴቅን ልጅ የሆነችውን ወይዘሮ ድንቅነሽ ኃይሉን አገቡ። ዳሞትን ደጃዝማች ዘውዴ፣ ጎጃምን የታላቁ ራስ ኃይሉ ዮሴዴቅ ወንድ ልጅ ደጃዝማች መርዕድ እየገዙ ባሉበት ወቅት ደጃዝማች ዘውዴ የሚስቱን አገር ደርበው መግዛት ፈለጉና ከደጃዝማች መርዕድ ጋር መግጠም አሰበ።
እቅዱ ወደ ተግባር አልተለወጠም። ራስ መርዕድ አምቻውን (ደጃዝማች ዘውዴን) ሞጣ ቀራንዮ አካባቢ በግዞት አስቀመጡት። ወይዘሮ ድንቅነሽ ባሏን በታሰረበት ልታዬው በኼደች ጊዜ ጭኗን በፍቅር ጎበኘው። በዚህ ጊዜ ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ተፀነሰ። በኋላም ደጃዝማች ዘውዴ ከግዞት ወጥተው ወደ ግዛታቸው ተመለሱ። ቆይቶ ደጃዝማች ዘውዴ ከራስ ጉግሳ ጋር ባደረጉት ጦርነት ተሰው። አልጋውንም ልጃቸው ደጃዝማች ጎሹ ተረከቡት።ደጃች ጎሹ አልጋ ሲይዝ የደጃች ዘውዴ የእህት ልጅ የሆኑት መምህር አምኃ አምሳ ጎበዥ (ወጣቶች) አስከትለው የደጃች ዘውዴን አፅም ለማምጣት ወደ የጁ ኼዱ። አፅሙን አምጥተው በክብር ሳጥን ሆኖ ደንበጫ ተቀመጠ።
ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴም የዳሞት ገዥ የነበሩ እና የጎጃሙ ገዥ የንጉስ ተክለሃይማኖት አያት ናቸው። ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴም ካሳ ኃይሉ ( በኋላ አፄ ቴዎድሮስ) ሲዋጉ ጉራምባ ላይ ቆስለው በኋላ ሞቱ። እዚህ ላይ ዳሞት እና ጎጃምን ለየብቻ መጥራቴ ዳሞት የጎጃም አካል አይደለም የሚል መነሻ ይዤ እንዳልሆነ ይያዝልኝ። ከታላቁ ኃይሉ ዮሴዴቅ ሞት በኋላ ገዥዎች ጎጃምን ከፋፍለው ይገዙት ነበር። በመሆኑም በጊዜው አነጋገር “ጎጃም” ተብሎ የሚጠራው አሁን ምስራቅ ጎጃም ተብሎ የሚታወቀው የጎጃም ክፍል መሆኑን ልብ በሉ።
በእያንዳንዱ ዘመን ያለውን የደንበጫ ታሪክ ለመዘርዘር በመፅሐፍ መልክ ካልሆነ የሚቻል አይሆንም፡፡አሁን በጣሊያን ዘመን የነበረውን የአረበኞች ተጋድሎ በጨርፍታ እንመልከት፡፡ በጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት ከፍተኛ ተጋድሎ ከተደረገባቸው የጎጃም አካባቢዎች አንዱ ደንበጫ ነው፡፡ ከአጎራባች አካባቢ አርበኞች ጋር በመሆን የደንበጫ አርበኞች ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ከደንበጫ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘው የጨረቃ የተባለው የጦር አውድማ በታሪክ ጉልህ ቦታ አለው፡፡ የጨረቃ የደጋ ዳሞት አርበኞች (ደንበጫን ጨምሮ) ከፍተኛ የጦር ጀብዱ የፈፀሙበት ድንቅ ምድር ነው። ደም ተገብሮ ሰው ነፃ የሆነበት ምድር። በቦታውም በፊታውራሪ ኃይለየሱስ ፍላቴ ስም የመታሰቢያ ሐውልት ተቀርጿል። ሐውልቱ ውስጥ ለነፃነት የተከፈለው መስዋዕትነት ቁልጭ ብሎ ይታያል። እኒያ የጣሊያንን ባንዳ እንደ አንበሳ ተቆጥተው፣እንደ ንብ ተናድፈው ያባራሩት ጀግና ፊታውራሪ ኃይለየሱስ ፍላቴ (አባ ሻውል) የጦር መነፀራቸውን በአንገታቸው አፊታውራሪ ” ጅንን” ብለው ቆመዋል። አባ ሽውል የጨረቃ ላይ ሐውልት ይቁምላቸው እንጅ በብዙ የጦር አውድማዎች እየተዘዋወሩ ታሪክ የሚያስታውሰው ጅብዱ የፈፀሙ ጀግና ናቸው።
“እሮብ ተለቅልቆ ሀሙስ ተበራየ
ዳግም ነጭ አይበቅልም የጨረቃን ያየ” የሚለው የጀግና ግጥም ልክ መሆኑ የሚገባህ የጀግናውን ታሪክ ከስሩ ስታውቅ ብቻ ነው።
ጃንሆይ ኃይለሥላሴ ወደ ሃገራችን ከመግባታቸው በፊት አዛዥ ከበደ ተሰማ እና ኮሎኔል ሳንድፎርድ ወደ ጎጃም የጦሩን ሁኔታ ለመገምገም ተልከው ነበር። በዚህ ጊዜ አካባቢውን ከጠላት እና ስጋት ነፃ አድርግው እነ አዛዥ ተሰማ ከበደን ከተቀበሉት ጀግሞች መካከል ፊታውራሪ ኃይለየሱስ ፍላቴን ጨምሪ ሌሎች የደጋ ዳሞት እና ደንበጫ ጀግኖች ይገኙበታል።
ጠላትን ቀጥተው ወደ መጣበት የሸኙት የደንበጫ ጀግኖች አፄው የመሬት ግብር በመጨመሩ እና ለቀረበው ቅሬታ ተገቢ ምላሽ ባለመኖሩ እንደገና ተቃውሟቸውን ጀመሩ። ተቃውሞው በደንበጫ ከተማ፣ በሰቀላ ማርያም አካባቢ እየበረታ በኼደ ጊዜ ተቃውሞውን ለማብረድ ሦስት አባላት ያሉት ኮሚሽን ተዋቅሮ ወደ ደንበጫ ቢላክም ነገሩ ፍሬ አላፈራም። ተቃውሞው በእነ ቀኛዝማች ተፈራ ደስታ፣አቶ ቢተው ጌታሁን፣ ደጃዝማች ቸኮል ንጉሴ እና ደጃዝማች ደምሳሽ ገላዬ አማካኝነት ተጧጧፈ። አንድ ቀን ከሰረገላ ማርያም አካባቢ ከ1500 በላይ የተቃውሞ ድምፆች ተነሱ።
በከተማው የሚሰማው ተቃውሞ በግጥም የታጀበ ነበር።ተቃውሞን ጨምሮ ሌሎች ሁነቶችን በግጥም አዋዝቶ ማቅረብ በጎጃም ምድር የተለመደ ነው። በጊዜውም እንዱህ ተብሎ ነበር።
“በኩታ ነጠላዬን አልብሼ ብሰደው
ተመልሶ መጣ ርስቴን ሊወስደው።” ይኼ ግጥም ለጃንሆይ ኃይለሥላሴ የተገጠመ ነው። ” ኩታ ነጠላዬን አልብሼ ብሰደው” የሚለው ንጉስ ከስዴት ሲመለሱ የነበረውን አቀባበል ለማሳዬት ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የደርግ መንግሰት ጃንሆይን ገለበጦ መንበሩን ተቆጣጠረ፡፡የደርግ መንግስትም ቢሆን በጎ አቀባበል አልተደረገለትም። በተለይ ለአገልግሎት አቅርቦት (ለምሳሌ ትምህርት፣ ህክምና) አሰጣጥ አመችነት ሲባል በሰፈራ ስም ሰዎችን ከነበሩበት ቅዬ እና ርስት የሚያስለቅቅ በመሆኑ ደንበጫዎች አልወደዱትም ነበር።
“ጢና አዳም ነበረ ለኔስ መድሃኒቴ
እባክህ መልሰኝ ከፈረሰው ቤቴ።” ሲሉ በተለመደ ቅኔያቸው ተቃውመዋል። ይኼ ግጥም የዋዛ አይደለም ባሻዬ! ሰዎች ከለመዱት ቅዬ፣ ካደጉበት አረዳ፣ ከኖሩበት ሰፈር በምስረታ ስም መነሳታቸውን ያልወደዱት ደንበጫዎች “አታፈናቅሉን እንጅ የጤናውን ነገር እኛ እናውቅበታለን” ሲሉ መንግስትን የተቃወሙበት ነው።
እስኪ የከተማዋን አሁናዊ ሁኔታ እንመልከት፡፡ ከተማዋ ባህርዛፍ የተነበበች ናቸው። አሁን አሁን ውብ ህንፃዎች እየተገነቡ ነው። ከተማዋ በቂ መንገድ ባለመኖሩ መኪናዎች እና የፈረስ ጋሪዎች ተጋፍተው ነው የሚኼዱት። ቀን ኑሯቸውን ለማሸነፍ ከወዲያ ወዲህ ሲል በሚውሉ ሰዎች ተሞልታ የምትውለው ከተማ ማታ ጭር ትላለች። ማታ ማታ አየሯ ቀዝቃዛ ግን ለጤና ምቹ ነው። ሆቴሎች፣ ቡና ቤቶች፣ ሻይ ቤቶች ተባብረው የማታውን የከተማ ድባብ አሳምረውታል። ከተማዋ በወንዞች የታጠረች መሆኗ ግርማ ሞገሷን ጨምሮታል። የተምጫ፣ ብር፣ የጨረቃ እና ሌሎችም ወንዞች ደንበጫን ከብበው በየፊናቸው የሚፈሱ ቢሆኑን የጉላ ወንዝ ለከተማው እጅግ የቀረበ ነው። የጉላ ወንዝ ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ የተፈጥሮ ፀጋውን ለህዝቦቿ በመስጠት እንደ ጥሩ ባል ይንጎባለላል።
የከተማዋን ጥንታዊነት ሊመሰክር በከተማዋ ውስጥ በእርጅና ላይ የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት አለ:: ትምህርት ቤቱ የደንበጫ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን የተመሰረተው በ1936 ዓ. ም ነው፡፡ ለብዙ ታላላቅ ሰዎች መነሻ የነበረው ይኼ ትምህርት ቤት በአሁኑ ሰዓት “አርጅቻለሁና አድሱኝ” ሲል ለጆቹን እየተጣራ ይገኛል፡፡በከተማ ውስጥ የተመሰረተው የደንበጫ ወርዳ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ከ2002 ዓም ጀምሮ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ለኢትዮጵያ እየሰጠ ይገኛል።
ከተማው ውስጥ ወዳለው የገበያ ቦታ የዘለቀ ሰው የቆዳ ስሪት የሆኑ አገሬው አሁንም የሚጠቀምባቸው ቁሶች በገፍ ይገኛሉ።ለአብነትም ለመኝታነት እና ትራስነት የሚያገለግሉ እንደ ዠንዲ፣ ላምነት፣ አጎዛ፣ የጠፍር አልጋ፣ ነት፣ መጠገጊያ እና መክዳ ይገኛሉ።ባሻዬ! መቼስ ይኼ የዘመኑ ወጣት ነባር እና ባህላዊ ቁሶች መዘንጋቱ የሚታወቅ ነው። መጠጊያ ማለት በአጭሩ ትራስ ማለት ነው። መከዳ ምንድን ነው ካልኸኝ “መከዳ ማለት ጎምላላው የጎጃም አባወራ ከስራ ወደ ቤቱ ሲመለስ ከምንጣፍ (ዠንዲ) ላይ ወገቡን ደገፍ የሚያደርግለት ከመጠጊያ በመጠን ከፍ ያለ ባህላዊ ቁስ ነው” እልሃለሁ። ዠንዲ እና ላምነት የሚለያዩት ላያቸው ላይ ባለው ፀጉር ብቻ ነው። ባለፂም እና ፂም አልባ ወንድ አድርጋችሁ ውሰዱት። ሁለቱም ከላሞ ወይም ከበሬ ቆዳ ተሰርቶ ለመኝታነት የሚያገለግል ባህላዊ ቁስ ሲሆን ላምነት ፀጉሩ ሳይገረፍ ( ሳይወገድ) የሚሰራ መሆኑ ነው።
ምን ይኼ ብቻ! የአገሬ ገበሬ ለፍቶ ሰፊውን ህዝብ ሲመግብ ለእርሻ ስራ የሚጠቀምባቸው እንደ ምራን እና መርገጫ የመሳሰሉ ባህላዊ ቁሶች ይገኛሉ። የደንበጫ ሰው ሐይማኖተኛ ነው። አዘውትሮ ቤተ ክርስቲያን ይስማል። ለዚህም የመፅሐፍ ቅዱስ እና ሌሎች የፆሎት መፅሐፍትንን ሸክፎ የሚይዝበት ከቆዳ የተሰራ “ማህደር” የተሰኘ ቁስ በሰፊው ይገኛል። ከቆለምሸሽ እስከ ወስከንቢያ፣ከመርፌቁልፍ እስከ ወረንጦ አሁንም ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸውን የምታረጋግጠው ደንበጫ ከተማን ካዬሃት ብቻ ነው።ሌላው በገበያው የሚገኘው ከሸክላ የተሰሩ የመገልገያ እቃዎች ናቸው። ከነዚህም ውስጥ እንደ ጋን፣ ማድጋ፣ገንቦ ማሰሮ ፣ቶፋ፣ ሽንክላ እና ሌሎችም ይገኘሉ።እነዚህ የጥበበኛው ባላገር የእጅ ስራዎች በዘመኑ ቴክኖሎጅ ቢታገዙ ምንኛ መልካም ነበር።
የሆድ ህመም ፈውስ የሆነው አረቂዋ በዬሻይ ቤቱ ብቻ ሳይሆን በየሱቁም ይሸጣል። ደንበጫን አልፎ የሚኼድ ሁሉ አረቄ ሳይሸምት አይኼድም። በደንበጫ ከተማ አረቄ እጅግ የሚወደድ እና የሚዘወተር ባህላዊ መጠጥ ነው። አረቄ በባህላዊ ወይም በዘመናዊ መንገድ( በፋብሪካ) ሊዘጋጅ ይችላል። በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጀው አረቄ ከሦስት በበለጡ ባህላዊ እቃዎች በቤት ውስጥ ነው የሚዘጋጀው። የደንበጫ እናቶች በዋናነት መድፊያ፣ ማድጋ እና ዋዲያት የተባሉ ባህላዊ የሆነ እቃዎችን ተጠቅመው፣ እጅግ አድካሚ በሆነ መንገድ ነው አረቄን የሚያወጡት። መንግስት በቴክኖሊጅ የተደገፈ ስልጠና ሰጥቶ የእናቶችን ልፋት ቢቀንስ ሸጋ ነገር ነው።
ይኽች ጥንታዊ ከተማ የተሟላ መሰረተ ልማት የላትም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ልጆቿ ለህክናም ወደ አጎራባች ወረዳዎች ሲኳትኑ ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እንኳን ያገኘችው በዚህ ዓመት ነው:: በመሆኑም ታሪካዊነቷን እና ዕድሜዋን በሚመጥን ልክ የመልማት ጥያቄዋ ይመለስ ዘንድ እንጠይቃለን!!
የፎቶ መግለጫ
ከላይ በ1936 ዓ/ም የተመሰረተው ዕድሜ ጠገብ የደንበጫ ትምህርት ቤት፣ በዚህ ዓመት የተመሠረተው የደንበጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ በ1771 ዓ/ም የተመሰረተው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን፣ በ2002 ዓ/ምን የተቋቋመው የደንበጫ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ፣ በደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ስም የተሰየመው የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ፣ የጀግናው አርበኛ ኃይለየሱስ ፍላቴ ሐውልት እና ከተማውን በከፊል የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ታትመዋል።
Filed in: Amharic