>

ዳኛቸው ወርቁ ሊያጡት የማይገባ የእውቀት ሎሌ...! (ከደራሲ እንዳለጌታ ከበደ)

ዳኛቸው ወርቁ ሊያጡት የማይገባ የእውቀት ሎሌ…!

ከደራሲ እንዳለጌታ ከበደ

“–ለሁለተኛ ኅትመትም ታሰበ፤ ግና የጋሽ ዳኛቸው አለቅጥ መናደድ ያሳሰባቸው አንዳንድ የድርጅቱ አርታኢያን፤ ቀጥለን ደግሞ በተራው የአምሳሉን ስም ዝቅ አናድርገው ሳይሉ፣ ሁለቱን ስም በመጀመሪያ ረድፍ ላይ አሰፈሯቸው፤ ትይዩ! እና መጽሐፉ ወጣ።–”

ጋሽ ዳኛቸው የእንግዳ ባህርይ ጌታ ነው። በቀላሉ ተግባቢ አይደለም፤ በ”አደፍርስ” ልቦለዱ ነው የሚታወቀው፤ አደፍርስ የመጽሐፉ አቢይ ገጸ ባህርይ ነው፤ ልክ እንደ ደራሲው ´የተለየ´ ዓይነት ሰው ነው፤ ዳኛቸው የአደፍርስን የመሰለ  ባህርይ አለው ማለት ግን አይደለም፤አደፍርስ ከበብ ሲያደርጉት የሚወድ፣ ከፍተኛ የሆነ የመደመጥ ጽኑ ፍላጎት ያደረበት ዓይነት ሰው ነው።

ማወቁን ስለማሳወቅ እንጂ የበታቾቹ እንዲገባቸው የሚፈልግ ዓይነት አይደለም። አደፍርስ በዚህ ዘመን ቢኖር ለሞዴል አርሶ አደሮች ስለ ቦናባርቲዝም ሊናገር፣ ለመነኮሳት ደግሞ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት ሊደሰኩር ይችላል። ዳኛቸው ግን ክበቡኝ፣ አድምጡኝ አይልም፤ የከበቡትንና የሚያደምጡትን ሰዎች ግን በጥርጣሬ ሊያይ ይችላል (እናውቀዋለን የሚሉ እንደሚናገሩት)፣ የሆነ ሰው ሆን ብሎ በሆነ ቦታ ተንኮል እያሴረበት ያለ ይመስለዋል። ከጥቂት ደራስያን በቀር ከብዙዎች ጋር የሚግባባ አይደለም። በራሱ ላይ የዘጋ ነው – ከሕዝብ ጉባዔ ተነጥሎ ለብቻው ሱባዔ የገባ!

ያዩት እና ያወቁት ስለ እሱ የሆነ የማይረሳ ነገር ይኖራቸዋል። ከሆነ ሰው ወይም ከሆነ ቡድን ሲላተም ያጋጥማቸዋል። የሆነ ነገር ሲደፈርስ ይታያቸዋል፤ ይህንን እንግዳ ባህርይ ተቋቁመው፣ የጓደኝነት ድንበር ሳይጥሱ ከልብ የቀረቡት ደግሞ “… ሊያጡት የማይገባ የዕውቀት ሎሌ። ለወዳጅነት የተከፈተ ልብ ያለው!” ይሉታል፤ እርግጥ ነው ዳኛቸው ለሀቅ ሽንጡን ገትሮ ስለሚከራከር ከውሸት ጋር ማኅበር ከሚጠጡ፣ ጽዋ ከሚያነሱና ብርጭቆ ከሚያጋጩ ጋር ሕብረት አልነበረውም፤ እርግጥ ነው ቀጠሮ ሰጥቶ በቀጠሮው ቦታና ሰዓት የቀጠረው ባለጉዳይ በተባባሉት ሰዓትና ቦታ ካልተከሰተ አምስት ደቂቃ ሳይታገስ ወደ ጉዳዩ ይሄዳል። እርግጥ ነው አንድ ወዳጁ በሌላው ላይ ሴራ ሲጠነስስ ካየ ወይም እየጠነሰሰ ነው ብሎ ከጠረጠረ ተራራ በሚያክል ኩርፊያ ያስተናግደው ይሆናል…

በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ጸሐፍት ተሰባስበው የአቦ ጠበል ይጠጡ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩ ብዙዎቹ ተራማጅ ደራስያን ከሚታደሙበት ከዚያ ጉባዔ እራሱን የነጠለው ዳኛቸው ነበር። “ዳኛቸው አይመጣም ነበር…”ይላል ጋሽ ሰለሞን ደሬሳ፤ ስለባህርይውና ስለነበራቸው ቅርበት ሲናገር።

“ተጎትቶ ካልሆነ ከሰው አይቀርብም ነበር፤ ከእኔ ጋር ግን ውጪም ወዳጆች ነበርን። “ልጅነት” ታትማ ስትወጣ በመጠኑ ቁጣ ወረደባት። የኢትዮጵያን የግጥም አወራረድ አበላሸ፤ ከፈረንጅ ያመጣው ነው ምናምን ይባል ነበር። የማስታውሰው የምስጋና ጽሁፍ ያገኘሁት ከዳኛቸው ወርቁ ብቻ ነው። የደረሰኝ የምስጋና ጽሁፍ የቄስ ጽሕፈት ይመስል ነበርና የእሱ መሆኑን ያወቅሁት በኋላ ስንቀራረብ ነው። አልፈረመበትም ነበር። እንደ አጋጣሚ ደግሞ አደፍርስን አግኝቼ ሳነብ፣ ማነው ልጅነትን የጻፈው ብሎ ሲፈልግ ነው የተገናኘነው። በጣም በጣም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ቦታ ከማደንቃቸው ጸሐፊዎች ዳኛቸው አንዱ ነው። በሁሉም ሳይሆን በ”አደፍርስ” እና በ”Thirteeneth sun” በማለት ስለነበረው ባህርይና ችሎታ ይናገራል።

ወንጀል ነክ ልቦለድ ደራሲው ይልማ ሃብተየስ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፤ እርስ በርስ የወደዷቸውን ስራዎች አይወዷቸውም። “ልጅነት”ም “አደፍርስ”ም ውሃ የማይቋጥሩ ናቸው፤ በእሳቸው እይታ ሲሰፈሩ።

“እነዚህ ሰዎች (ዳኛቸው ወርቁና ሰለሞን ደሬሳ) አጭበርባሪዎች ናቸው። ለኢትዮጵያ  ስነ-ጽሁፍ ምንም የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የለም። እንዴት የማይገባ ነገር ይጻፋል? ምን ትርጉም አለው? የዳኛቸው ወርቁን “አደፍርስ” ብዙ ሰዎች እንደ ትልቅ መጽሐፍ ነው የሚወስዱት። ግን አስረዱ፤ ምንድነው ትርጉሙ ሲሏቸው የሚናገር የለም። አንዳንድ ጭንቅላታቸው ብዙም የፈረስ ጉልበት የማይመዝን ሰዎች “አደፍርስ”ን  አንብቤ በጣም በጣም አደነቅሁ ይላሉ። ምኑ ላይ ነው ያደነቅህ ሲባል፣ መልስ የለም። ምንድን ነው የሚያደርጉት፣ ዩኒቨርስቲ አካባቢ የተደነቀ ስለሆነ እኔም ያን ባደንቅ እንደ ትልቅ ሰው እቆጠራለሁ በሚል ለመኮፈስ፣ ያላነበቡትን ያልተረዱትን ትልቅ ነው ይላሉ። እሱ መጽሐፍ አብዘርድ ነው፤ ተራ መጽሐፍ የማይነበብበት ሀገር ላይ ምንድነው ጥቅሙ? ውጭ ጀምስ ጆይስ ዩሊሰስ የሚባል መጽሐፍ ጽፏል። ያ ስታይል ነው፤ ያ ስታይል በአውሮፓና በአሜሪካ እንኳን ተቀባይነት የለውም። በጣም ጥቂት የተማርን ነን የሚሉ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው አንብበን ተረዳን የሚሉት። ሌላው ተራ ህዝብ አያነበውም፣ ሊገባውም አይችልም፣ “አደፍርስ”ም “ልጅነት”ም ይኸው ናቸው።

“ዳኛቸው ወርቁን አውቀዋለሁ፤ ዝግ ሰው ነው፤ የመጀመሪያ መጽሐፌን የተየበችው ታናሽ እህቱ ነች። ታናሽ እህቱ ደግሞ የጓደኛየ ሚስት ናት። በዚህ ምክንያት እሷ ቤት ስሄድ ይመጣልና አገኘዋለሁ። ከባሏም ሆነ ከእሷ ጋር አይግባቡም፤ ትንሽ ለየት ያለ ሰው ነው።” ብሏል ጋሽ ይልማ – በአንድ ወቅት።

… ጋሽ ዳኛቸው ለክብሩ ተጨናቂ ነው። በአንድ ወቅት ከአምሳሉ አክሊሉ (ዶ/ር) ጋር ሆነው አንድ መጽሐፍ አዘጋጁ። “የአማርኛ ፈሊጣዊ አነጋገሮች” የሚል። መጽሐፉ እንዲታተም ግፊት ያደረገው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ነው። ኩራዝ የመጽሐፉ ረቂቅ እንደተጠናቀቀ ግራ የሆነበት ጥያቄ፣ የማናቸው ስም ነው ከላይ መስፈር ያለበት? የሚል ነበር። እና  አንድ መፍትሄ ተገኘ፤ በአማርኛ ፊደል ቅደም ተከተል የማን ስም ነው መጀመሪያ ሊቀመጥ የሚገባው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት። ይኼ አካሄድ ውጭ ሀገርም ይሰራበታል። ስለዚህ የሁለቱን ሰዎች ስም የመጀመሪያዎቹ ፊደላት ይዘው ክትትል ሲያደርጉ አምሳሉ (ዶ/ር) ቀደመ፤ ዳኛቸው ተከተለ። መጽሐፉ ወጣ፡፡

ጋሽ ዳኛቸው መጽሐፉን ባየ  ጊዜ ተናደደ። “ከፊል የሆነውን ስራ የሰራሁት እኔ በየትኛው መስፈርት ሰፍራችሁ ከብዶ ቢታያችሁ ነው፤ ስሙን ከስሜ በላይ የሰቀላችሁት?” አለ።

መስፈሪያቸውን ነገሩት፤ አልተቀበላቸውም።

የሆነው ሆኖ መጽሐፉ ተሰራጭቶና ተሸጦ አለቀ።

ለሁለተኛ ኅትመትም ታሰበ፤ ግና የጋሽ ዳኛቸው አለቅጥ መናደድ ያሳሰባቸው አንዳንድ የድርጅቱ አርታኢያን፤ ቀጥለን ደግሞ በተራው የአምሳሉን ስም ዝቅ አናድርገው ሳይሉ፣ ሁለቱን ስም በመጀመሪያ ረድፍ ላይ አሰፈሯቸው፤ ትይዩ! እና መጽሐፉ ወጣ።

የጋሽ ዳኛቸው ፊት እና ልብ ግን አልተፈታም፤ ከድርጅቱ ሰራተኞች አንዱ የሆኑት ጋሽ አስፋው ዳምጤ አገኙት፤ “መጽሐፉ በጣም እየተሸጠ ነው፤ አንተ ግን ብንጠብቅህም አትመጣም፤ ብርህን ፈርመህ ውሰድ እንጂ!” አሉት።

“ሁለተኛ ደጃችሁ አልደርስም!”

“ምነው?”

“ያደረጋችሁትንማ ታውቁታላችሁ…”

“ብዙ ሺህ ብር´ኮ ነው ያለህ!”

“እንዴትም ቢሆን ግድ የለኝም፤ ነፍሴ ተቀይማችኋለች”

Filed in: Amharic