>
5:30 pm - Saturday November 2, 6611

ዮሃንስ  ተማሪው በሕይወት ካለህ ይኸው ጣፋጩ ትዝታዬ ። (ደረጀ መላኩ)

ዮሃንስ  ተማሪው በሕይወት ካለህ ይኸው ጣፋጩ ትዝታዬ ። 

 

እንኳን ለ2015 ዓም አደረሰህ !

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

Tilahungesses@gmail.com

 

እንደ መግቢያ

 

በቅድሚያ በዓሉን ከቤተ ዘመድ ጋር በመልካም ላሳለፋችሁ ሁሉ የከርሞ ሰው እንድትሆኑም ከወዲሁ ደግ ደጉን እናስብ ።

ዝነኛው ድምፃዊ ታምራት ሞላ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1968 ዓ.ም. ያዜማት አንዲት መልካም ዜማ ነበረቺው ። 

አንዴ በጊዜዋ ተቀርፃለችና ዛሬም ቢታሰስ አለች ። አትጠፋም ። የበረታ ፈልጎ ያድምጣት!

ፍቅሬ በምን ቋንቋ በምን ቃል ላስረዳሽ በጣፋጩ ቅላፄ ካወረደው በኋላ የሚለውን ብሎ … አንቺን እንዳይከዳሽ ይላል ።

ክህደት ለሀገርም በግል ግንኙነታችን ሁሉ ሲበዛ ክፉ፣ አስነዋሪና አሳፋሪም ነው ። ከመቃብርም አያስቆም ።

ክህደት አንድም ፣ ሁለትም፣ ሦስትም ከዚያም በላይ ልትሆን ትችላለች ።

እንደቀድሞው ከነበረው የውስጣችን መፈክር ከሆነ ደግሞ

አገሩን  እና የልብ ጓደኛውን የከዳ … አይጣል ነው። ይቀፋል ። ያሳዝናልም፡፡

ትምህርት እስከ ሰባት

እንደምናስታውሰው የቀድሞ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርታችን ከእንግሊዝኛ ጀማሪ ቋንቋ እስከ ጊዜያቶች መሠረታዊ መረዳት በስተቀር በአማርኛችን እናነጋግረው ነበር ።

ሚኒስትሪን ፈተና አልፈን ወደ መለስተኛ ሁለትኛ ደረጃ ስንገባ ደግሞ ቢገባንም ባይገባንም ሂሣብ ፣ ሣይንስ ፣ ታሪክ ፣ ጂኦግራፊ ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ግብርና፣ብረትና እንጨት ሥራ ፣ ባልትና ለሴቶች በእንግሊዝኛ መፍጨት ጀመርነው ።

ወሮ ሶካሊንግሃም ሕንዳዊት የሣይንስ መምህራችን ነበሩ ። በቅጽል ስማቸው ኮምፒዩተር እና ማዘርኦፍ ባይሊጂ  ብለን እንጠራቸው የነበሩ ጎበዝ ህንዳዊ የሂሳብና የሳይንስ መምህራን ነበሩን፡፡ 

ሁሌም አለባበሳቸው ባሕላዊ ነበር። ( የሐገራቸውን የህንድ ባህላዊ አለባበስ ማለቴ ነው ፡፡ ) 

አንድ ቀን ትምህርቱ ግር ያለን መስሏቸው ህንዳዊው የሂሳብ መምህራችን እንዲህ አሉ ። 

I Know አማርኛ ብዙ ትንሽ ብቻ ። ቂቂቂ 

መቼ ግርታው በሰባትያ ት/ት ብቻ በቃና ዛሬም ግርር ብሎታል።

ተምረን ተምረን ይኸው አለን በቃ

ዕውቀትና ጊዜን ስንፈጅ በተርታ

ቀርተን ወደ ኋላ ሰባትያ ከረምን ፍፁም ሳንበረታ ። ያሳዝናል የእኛ ነገር ሁሌ እንደ ካሮት እድገታችን ቁልቁለት ነው፡፡

 ዮሃንስ ( ጆን) ጓደኛዬ

ዮሃንስ በቀድሞው አጠራር በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት የተወለደ እና የልብ ባልንጀራዬ ነበር፡፡ ዛሬ በህይወት ይኑር አይኑር ለማወቅ ባለመቻሌ፡፡ የታሪክ ፌዝ ሆነና እኔ እና ጆን የሁለት ሀገር ዜጎች ሆነናል፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ፣ እርሱ ደግሞ ኤርትራዊ፡፡ ጆን ኤርትራዊ ዜግነት ቢጎናጸፍም( እንደ ዜግነት ከተቆጠረ ማለቴ ነው፡፡ ) ነበረን ጣፋጭ ትዝታ ግን ዝንተ አለም አይረሳኝም፡፡ ለዚህም ነው የማይዘነጋውን ግንኙነታችን ለሃበሻ ገጽ መጽሔት አንባብያን ለማካፈል ህሊናዬ የኮረኮረኝ፡፡ እንደ ቁምነገር ከተቆጠረ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ

ከትናንት በስቲያ ( ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ) ዓመታዊ የተቋሙን ምርቃት ዕለት መፅሔት ካኖርኩበት ብፈልግ ብፈልግ አጣሁት ። 

እልህ ያዘኝና ያሉኝን የመፃሕፍት ማጎሪያ ገለባበጥኩት ። 

ወዲያ ወዲህ ባተራምሰው የአንጋፋውና በአገራችን የመጀመሪያው የፔዳጎጂካል ሳይንስ ማስተማሪያና ማሠልጠኛ፣ በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የጎልማሶች ትምህርት ኮሌጅ የነበረው በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የባህርዳር ፔዳጎጂካል ኮሌጅ የሐምሌ 1991  ምሩቃንን ዓመታዊ መፅሔትን ካኖርኩበት አጣሁት ። 

በእጄ እንደነበረ አብሮኝም ይዞር ነበር ። 

ምንአልባት ወዳጆቼ ሳላውቅ ወስደውት ይሆን ? 

ጠፋኝ ! 

ከነከነኝ !

ምንአልባት አንድ ወዳጄ የነበረች ጋር ይኖራል ብዬም አሰብኩ ። ለነገሩ ወረቀትና መዝገብ ጠባቂ ነበርኩ ። 

በዚህኛው ግን አልተሳካም ። የሚገርም ነው ።

የዛን ጊዜ የተቋሙ ዲን የነበሩት ጎበዝ የነበሩ የሂሳብ ትምህርት ተጠባቢ ( አራት ኪሎ ዩንቨርስቲ ተማሪ በነበሩበት ግዜ አልበርት ተብለው ይጠሩ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡) ለግሌ የፃፉት የየካቲት ወር 1991 ዓም ደብዳቤ ከዶሴዬ አለች ። 

ኮሌጅ ከመግባቴ በፊት የጤና ረዳት ሙያ ስለነበረኝ በተቋሙ  ክሊኒክ ውስጥ እሰራ ነበርኩኝና የኮሌጁ ዲን ሊያውቁኝ ችለዋል፡፡ 

ለተቋሙ ኅብረተሰብ ደህንነትና ጤና ነውና የሰራሁት በወር 60 ብር ደመወዝ ይከፈለኝ እንደነበር አስታውሳለሁ ። ያንዬ ይህ ብር ብዙ ቀዳዳዎችን ይሸፍንልኝ ነበር፡፡ 

በነገራችን ላይ ተቋሙ ዛሬ እራሱን ችሎ የባህርዳር ዩንቨርስቲ በመባል ይጠራል፡፡ ያንዬ ከ900 በላይ ተማሪዎችን ብቻ የመቀበል አቅም የነበረው ፔዳጎጂካል ሳይንስ ኮሌጅ ዛሬ የባህርዳር ዩንቨርስቲ የታላቁን አባይ ወንዝና የጣናን ሀይቅ ተጎራብቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም በመያዙ ህሊናን ደስ ያሰኛል፡፡ 

የባህርዳር ዩንቨርስቲ  ሀገር አቀፍ እና አለም አቀፍ የፓናል  ውይይት ለማካሄድ የሚያስችል ደረጃ ላይ በመድረሱ በቀድሞው ዘመን የባህርዳር ፔዳጎጂ ተማሪዎችን መንፈስ የሚያበረታታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፔዳጎጂ ጠንካራ ስፖርተኞችን ያፈራ ነበር፡፡ 

የረዥም ርቀት ሩጫ ( ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ እስከ አስከ ፔዳጎጂ ኮሌጀ ቅጥር ግቢ ) ድረስ ሰርክ አዲስ የሚሮጡ፣ አካል ብቃት የሚሰሩ አስተማሪዎችና ተማሪዎች ነበሩ፡፡ መረብ ኳስ፣ እግር ኳስና ሌሎች በርካታ የእስፖርት አይነቶችን የሚያዘወትሩ ጎበዝ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ ኮሌጁ የሰውነት ማጎልመሻ ዲፓርትመንት እንደነበረው ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡

አሁን በርካታ እስፖርተኞችን እንደሚያፈራ ተስፋ እናደርጋለን፡፡  

ዛሬ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተብሎ ይጠራል ። ይህ ዩንቨርስቲ  አለም አቀፍ እውቅና ያገኝ ይሆን ? ተስፋ አለኝ ።

ዮሃንስ የኤርትራ ክፍለ ሃገር ልጅ ነበርና  በቀድሞው አጠራር እዚሁ ፔዳጎጂ ግቢ ተገናኘን ። 

እርሱ አዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት፣ እኔ ደግሞ በቀድሞው ተፈሪ መኮንን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ካጠናቀቅን በኋላ ነበር በፔዳጎጂ ትምህርት ክፍል የተገናኘነው፡፡ እኔ ቀጥታ ከ12ኛ ክፍል አልነበረም ኮሌጅ ጆይን ያደረኩት፣ በመጀመሪያው በለስ ስላልቀናኝ በጤና ረዳትነት ሁለት አመት ካገለገልኩ በኋላ ነበር ኮሌጅ የገባሁት፡፡ ዮሃንስ ግን በቀጥታ የ12ኛ ክፍል እንዳለፈ ነበር ኮሌጅ የገባው፡፡ እኔ ኮሌጅ ለመግባት ከ12ኛ ክፍል በኋላ ሁለት ሶስት አመት ፈጅቶብኝ ነበር፡፡  

ለ፪ተኛ ደረጃ ት/ ቤቶች  መምህራን የሚሆኑ፣ በትምህርት ቢሮዎችና የትምህርት ሚንስትር ውስጥ የስርአተ ትምህርት ዝግጅት ኤክስፐርት፣ የትምህርት አስተዳደር፣ ሱፐር ቫይዘሮችና ዳይሪክተሮች ወዘተ ክፍል ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሁሉ ኮሌጁ ከተመሰረተ ዓ.ም ጀምሮ በተቋሙ ይማሩ ነበር ። 

በነገራችን ላይ በተለያዩ የትምህርት አይነቶች ዲፕሎማ ከጨበጡ በኋላ የዲግሪ ፕሮግራም ለመቀጠል  ለሁለተኛ ጊዜ የገቡ ነበሩ ። ፔዳጎጂ እርሻ ዴፓርትመንት የለውም ነበር ።

በነገራችን ላይ ይህ ኮሌጅ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር ይገኙ ከነበሩት ኮሌጆች መሃከል አንዱና ዋነኛው እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ 

ተማሪዎቹ ቁጥራቸው እስከ ስልሳ  ይደርሳል ።

በ1991  በአገሪቱ ያሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በመላው በሁሉም የስፖርት ዓይነቶችም ውድድር በተማሪዎቹ ያካሂዱ ነበር ። 

በተለያዩ አመታት ተቋሞቻቸውን ወክለው ከየርቀት የመጡትን ተማሪዎች ስድስት ኪሎ ቅጥር ግቢ በማረፊያና በምግብ አገልግሎት በመስጠት አስተናግዳለች ። 

የኛ ማረፍያ እንዲህ ወደ መነን ት/ ቤት ከሚያዋስነው አጥር ጥጉ ሥር

” ሳይቤሪያ ” ተብለው እንደ ነገሩ ከተቀለሱ የቆርቆሮ ግድግዳ ዓይነት የተሰሩ መኖሪያ ናቸው ። 

የስፖርት በዐሉም በልደት አዳራሽ ሲዘጋም የተለያዩ የኪነት ጓድ መድረክ ላይ ያቀረቡትና ” የተለያዩ ህብረ ዝማሪዎች ››የኅብረት መዝሙር ትዝ የማይለው ተሜ ይገኝ ይሆን ?

የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ቡድኖችስ በአብዛኛው የስፖርትና ጅምናስቲክ ትምህርት መምሪያ ሠልጣኞቹን ማሰማራቱ ይታወሰን ይሆን ? 

የኮተቤው ባለ ቼዙ ዝነኛስ ፓቼ ?

ስማቸው የተዘነጋኝ የ4ት ኪሎዎቹ የእጅ ኳስ መታሪዎቹ  ?

የዓለመያዎቹ  ምርጥ ተጨዋቾች ፣አጭሩ የቅርጫት ኳስ የማይስተው ወርዋሪስ ?

የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ   መሃል እግርኳስ የቀድሞው ቴዎድሮስ ቡድን ተጫዋች እና አብዶ ሰሪዎቹ ግርማ አለማየሁ፣ህሩይ  ?

የስድስት ኪሎውን የ፲ ሺ ሯጭ ?

በስድስት ኪሎ ዋና ግቢ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ስሜት፣ ህብረ ዝማሬ ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊ ፍቅር  የማያስታውስ ይኖር ይሆን ? እንደዛሬ ሳይሆን ያንዬ ዩንቨርስቲ ትንሹ ኢትዮጵያ ነበረ፡፡

ዮሃንስ ረዥምና ሰውነቱ ደልደል ያለ ሲራመድም አፈስ አፈስ እያለ የሚጓዝ ጠይም መልክ ያለው ባለ አፍሮ ስታይል ፀጉር ነበር ። 

ዮሃንስ የስፖርተኛ ሰውነት አለው ። 

እግር ኳስ የእጅና የመረብ ኳስም ይጫወታል ።

ዮሃንስና የእግር ኳስ ሜዳ ሲገናኙ ኳስ እያንከባለለ እንደ ፈረስ ይጋልብብታል ።

ለተቋሙ ከላይ ቢጫ ከታች አረንጓዴ ቀለም ቁምጣ ለብሰን እግር ኳስና ሌሎች በርካታ ስፖርቶችን ተሳተፍን ። ቼዝና ጠረጴዛ ቴኒስም አልቀረ ። 

የሚገርመው አብዛዎቹ ስፖርተኞቻችን ሁለትና ከዚያም በላይ ጨዋታ ተጫዋቾች ነበሩ ። 

ስንታየሁ ጊዜና ሢሣይ እግር ኳስ ቅርጫት ኳስ የእጅ ኳስ ፣ ግሩም ታምር አየሁ ቅርጫት ኳስ እጅ ኳስ ቴኒስና ቼዝ …

 

ዮሃንስ በዋና ተከላካይነት ( ተርሲኒ ) ይሰለፍ እንጂ ሜዳውን ይዞራል ። 

እኔ ደግሞ በተጠባባቂነት የግራ ተከላካይን መስመር ተሰልፌአለሁ ። ስፈለግ እገባለሁ ። ታለባለዚያ በተጠንቀቅ እዛው” ቤንች ” ላይ ነኝ ። 

የስፖርት መኮንናችን አቶ መኮንን ይባላል ። 

ድምፁ ጎርነን ብሎ በቀስታ የሚወጣ ዓይነት አለው ። በርካታ የሰውነት ማማሟቂያ ትዕዛዝ ብቀበልም ወደ ውስጥ ግን ከስድስት ኪሎ ቡድን ጋር ስንጫወት ብቻ ለቆኛል ። 

በተረፈ ቤንቹን አሙቄ ተመልሻለሁ ። 

ምን አልባት በቤንች በመቀመጥ ጊዜ የበዛላቸው ተጭዋቾች ሽልማት ቢኖር የመጀመሪያው ሳልሆን እቀራለሁ ?

ዮሃንስ ኃይለኛ ነው ። እርሱ ኳስ ከያዘ ሜዳው ይንቀጠቀጣል ። እኔማ ” ባቡር ” ነበር የምለው ። 

የ፫ ተኛው ክፍለ ጦር የ፲ ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ የሠራዊቱ ቡድን 10 ቁጥር ለብሶ የሚጫወተውና ሁላችን የዛን ጊዜ ውጫጮች በቅፅል ስሙ ” ባቡር ” የሚሉት ጎበዝ ተጫዋች ትዝ እያለኝ ።

አዎን ! ዮሃንስ እግር ኳስ ሜዳው ውስጥ ደከመኝ አይልም ። እስተመጨረሻው ይለፋልም ያለፋል ። 

በል ካለውም ትዕግሥት የለውም የወገን ቡድኑ ኳስ አያያዝ ካልጣመውም ተንደርድሮ ሄዶ ይነጥቅና ኳስ መሄድ ወዳለባት ያጎናታል ።

ዮሃንስ አማርኛው ጭምር ጠይም ናትና ሲናገር ፈገግ ያሰኛል ። ኳስ አስተካክለህ ወደ ወገን ቡድን ካላሻገርክ…….አሁን ይቺ አቅታህ ነው ? አንተ ዋ ! ዋ !…” መሬት ብላ ” ይልሃል ። ያው አፈር ብላ ማለቱ ነው ።

ዮሃንስ ጋር በክፍልም በሜዳም ስለምንገናኝ ቀረቤታ ቢጤም አለን ። ዮሃንስ በትምህርቱም ቢሆን ሰቃይ ከሚባሉት ተርታ የሚሰለፍ ሰው ነበር፡፡ ሲዝናናም በሰፊው ነበር፡፡ ከቤት ገንዘብ ሲላክለት ያገኘውን ተማሪ ያለስስት ይጋብዝ ነበር፡፡ ዮሃንስ ካገኘው የኮሌጁ ተማሪ ጋር በፍጥነት የመግባባት ክህሎት ነበረው፡፡ 

አንተ ” ደረጁ ” የሁልጊዜው ስሜን ሲጠራ ድምፁ ነው ። 

አንድ ቀን እንዲህ ሆነ ። እኔ ከተማ እወዳለሁ ። 

በተለይ ” ባህርዳር ” የሚባል ሆቴል አለ ። 

በረንዳው ደስ ይለኛል ። መስተንግዶውም ጭምር ። አንዳንዴ የሚያስተናግዱትም ኮረዶች ጭምር የባለቤቱ የደረሱ ልጃገረዶች ነበሩና …በዓይን ማየቱም…ምን ልታዘዝ ድምፅ መስማቱም …ወይ ጉድ እውነት ፍቅር ያስይዛል ።

በመልዕክት ሣጥን ቁጥር ….. ባህርዳር ፔዳጎጂ ከወላጅ አባቴ በሪኮማንዴ ደብዳቤ መሽሩፍ በየወሩ የተለመደ ነበርና  ፖስታ ቤት ማዘውተር የተለመደ ነበር፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ ተሜ የቻይና ሳይክል እየጋለበ ከፔዳ ወደ መሃል ከተማ ለተለያዩ ጉዳዮች መሄድም ያዘወትር ነበር፡፡

 

 

የአደራ ደብዳቤ ስለሆነ በቀጥታ ለተላከለት ሰው መስጠትና ቀሪ ወረቀት ላይ ፊርማ መኖር አለበት ።

ዮሃንስ  ከመንገድ ” ጂራሬ ” ስመታ ተገናኘን ። 

ዮሃንስ …አንተ ደረጁ እዚህ ትዞራለህ ” የሚሮጥ ደብዳቤ ” ይፈልግሃል አለኝ ። 

የሚሮጥ ደብዳቤ…አሁን ገባኝ ፡፡

” ሪኮማንዴ ” ” አስቸኳይ ወይም የአደራ ደብዳቤ” እንደሆነ ተረዳሁኝ ።

ለዮሃንስ …ዝናብ ሲወርድ…ማይ መጣ ውሃ መጣ ነው።

እነሆ ዮሃንስን ፎቶውን እንዳላሳያችሁ መፅሔቱ ጠፋብኝ ።

 

የዮሃንስና የሎሎች በርካታ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችም በዚሁ ተቋም ተምረዋል ። የሚገርማችሁ ከየዓመቱ ተማሪዎች ቁጥር እኒሁ ልጆች ድርሻቸው በመቶኛም ትርጉም አለው ። 

ፔዳጎጂ ትምህርት መማር ይወዳሉ። 

ተሳትፏቸው ላቅ ያለ ነው ። 

ግን ለምን ? የተቋሙን ስታትስቲኩን ይመልከቱት ።

አሥመሪና ! አሥመሪና !

ስገመዬ አሆሆ ! ስገመሄ ላሌ !

ናይ ከተማ ምፅዋ !

አያ በየነ ! ፀሐይቱ ባራኪ

አቆርዳት ትሠነይ…….በረከት

 

መስከረም ፩ ቀን 2015 ዓ.ም

Filed in: Amharic