የአፍሪካ ታላላቅ አባቶች፣ ህልማቸው ጨንግፎ ይሆን ?
ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )
ፓን አፍሪካኒዝም ፣ የታላላቅ አባቶቻችን ህልም
አፍሪካ አሁን ያለችበት ምስል የተጠበቀ አልነበረም፡፡ የቀደሙ የአፍሪካ አባቶቻችን ህልም የነበረው የቅኝ ገዢዎችን ፊትአውራሪነት ማስቀረት ነበር፡፡ ቅኝ ገዢነት እንዲከስም ህልምና ፍላጎት ነበራቸው፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መጋቢት 1957 የአለም ትኩረት የነበረው በጋና እና በታዋቂው ብሔርተኛ ኑክሩህማ ላይ እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ክዋሚ ከሰሃራ በታች ከሚገኙት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ያካሄዱ መሪ ነበሩ፡፡ የክዋሚን የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግልን ተከትሎ በርካታ ሀገራት የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል መጀመራቸው የሚታወስ ነው፡፡ በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ጨለማዋ አህጉር ተብላ ትጠራ የነበረው አፍሪካ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን የሚያወሱ ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮቻቸው አፍሪካ ከቅኝ ገዢዎች የግፍ አገዛዝ እንድትወጣ ፋና ወጊም ነበሩ ፡፡ ንክሩህማ ፡፡
ንክሩህማ የእኛ ነጻ መውጣት (መላው አፍሪካ ነጻ ሳትወጣ )የእኛ ብቻ ነጻ መውጣት ትርጉም የለውም የሚል ዘመን አይሽሬ ንግግር ነበራቸው፡፡ ንክሩህማ ሁሉም ( አርባ አራቱም የአፍሪካ ሀገራት ) ከቅኝ ገዢዎች ነጻ መውጣት አለባቸው ብቻ ማለታቸው አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አፍሪካ ከችጋር፣ እርሃብ፣ በሽታ እና ድንቁርና ነጻ መውጣት አለባቸው ማለታቸው ነበር፡፡
ክዋሜ አፍሪካ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንድትወጣ፣አንድነቷ እንዲጠበቅ፣በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መዳፍ ስር እንዳትወድቅ፣ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነጻ መውጣት እንዳለባት፣ ወዘተ ወዘተ ጠንካራ ርእዮት ዓለም ነበራቸው፡፡ ከመጽሐፋቸው የተወሰደው የሚከተለው አረፍተ ነገር ጠንካራ አመለካከትና ህልም እንዳላቸው ማሳያ ነው፡፡
‹‹ በሌላ አካል ከመገዛት ይልቅ እራስን መምራት ወይም አለ አግባብ ራስን መግዛት የተሻለ ነው፡፡ በአፍሪካ ባህላዊ ማህበረሰብ ላይ የተመሰረተው አፍሪካዊነት ሰብዓዊነት ነው፡፡ ››
ከላይ የተጠቀሰው ቁም ነገር እንዳለ ሆኖ አጼ ሀይለስላሴ ቢሆኑ የዚሁ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አንዱ እንደነበሩ የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 1958 በአፍሪካ መልካም እንቅስቃሴ በነበረበት ግዜና በአክራው የአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ የትውልድን መንፈስ የሚያድስ ንግግር አሰምተውም ነበር፡፡
አለም ዛሬ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ምን እንደሚፈልጉ የተረዳበት ግዜ ላይ የምንገኝ ይመስለኛል፡፡ ይህም ማለት ሰላም፣ ነጻነት፣ የሰው ልጆች ብልጽግና እውን ሊሆን የሚቻለው መንፈሳዊ ጥንካሬ ያላቸው አፍሪካውያን ሲነሱ ወይም ሲበቅሉ ብቻ ነው፡፡
የአጼ ሀይለስላሴና ክዋሚ ንክሩሃማን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ታላላቅ መሪዎች ባደረጉት ታላቅ ጥረት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ግንቦት 1963 የ32 ነጻ ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ላይ በመሰብሰብ የአፍሪካን የመጀመሪያውን አህጉራዊ ተቋም ( የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በማባል ይታወቅ የነበረውን ማለቴ ነው) በማቋቋማቸው ታሪክ ስፍራውን የሚነሳቸው አይመስለኝም፡፡ በዚህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያው የአፍሪካ አገሮች የመሪዎች ስብሰባ ላይ በታሪክ ምን ግዜም የሚታወስ ንግግር አሰምተው ነበር፡፡ እንደሚከተለው እጠቅሰዋለሁ፡፡
‹‹ ዛሬ ላይ ቆመን ነገን የምንመለከተው በእርጋታ፣ በእራስ መተማመንና በጉብዝና ( አሸናፊነት ) መሰረት ላይ ቆመን ነው፡፡ አፍሪካ ነጻ መሆን ወይም አንደነቷ መጠበቅ አለበት፡፡ በአፍሪካውያን መሃከል ልዩነቶች እንዳሉ ይገባናል፡፡ ሆኖም ግን እጅግ በጣም ተስፋ በቆረጠ አህጉር ውስጥ አንድነት ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለን እናስባለን፡፡ የባህል፣ሃይማኖት፣ ጎሳ ወይም ዘር፣ ልማድ ልዩነቶች ለአንድነታችን በፍጹም እንቅፋት ሊሆኑን አይቻላቸውም፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን አንድነት ጥንካሬ ነው፡፡ (. History teaches us that unity is strength. )
በአፍሪካ የነጻነት ትግል ውስጥ አንጸባራቂ ኮከብ የሆኑት የታንዛኒያው አባት ጁሊዬስ ኒሬሬ ካደረጉት ንግግር ደግሞ የሚከተለው ይጠቀሳል፡፡
የአፍሪካ ትንሳኤ ለሌሎች ታላቅ ደስታ ነው፡፡ ስለሆነም እኛ አፍሪካዊ መሆናችን ይሰማናል፡፡ አንድ ህዝብ መሆናችንን እናውቃለን፡፡ ስለሆነም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1964 የግብጹን ዲክላሬሽን ተከትሎ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በቀላሉ ለመቀራመት ሲሉ ያሰመሩት ሰው ሰራሽ ድንበር ሳይሆን አፍሪካውያን አንድ ጥንታዊ ድንበር ያላቸው ነበሩ፡፡ የአፍሪካውያን ታላላቅ መሪዎች ህልም የነበረው የአፍሪካን አንድነት ማስከበር እና ማጽናት ነበር፡፡ ስለሆነም አፍሪካን ባልካናይዝ የማድረግን የቅኝ ገዢዎችን ሴራ እውን እንዳይሆን አፍሪካውያን ማክሸፍ አለባቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የቅኝ ገዢዎች ሴራ አልከሸፈም፡፡ በአፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች በድንበር መስመር አለመግባባት የተነሳ ጦርነቶች ተከፍተው የሰው ህይወት ጭዳ ሆኗል፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያና ሶማሊያ መሃከል በግዛት ይገባኛል ሰበብ ጦርነት ተከፍቶ ከሁለቱም ሀገራት ወገን በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ተሰደዋል፣ታስረዋል፣ ንብረት ወድመዋል፡፡
ንክሩሁማ ቅኝ ገዢዎችን እንደተቃወመው ሁሉ የአፍሪካን መከፋፈል አይደግፍም ነበር፡፡ ወይም አፍሪካን ተከፋፍላ ማየት አይፈልግም ነበር፡፡ ለእርሱና ለብዙዎቻችን አፍሪካውያን ባልካናይዜሽና ( ከፋፍለህ ግዛ ) ቅኝ አገዛዝ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽዎች ናቸው፡፡ አፍሪካ በእውነት መሰረት ላይ ሆና ነጻ ከወጣች ሁለቱንም መንትዮች መቋቋም ይቻላታል፡፡ አፍሪካን ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ ለማውጣት የሚደረገው መራር ትግል ከባልካናይዜሽን ( ከፋፍለህ ግዛ) ግፍ ለመገላገል ከሚደረገው ትግል ጋር መተጋገዝ ይኖርበታል፡፡
አፍሪካን አንድ ለማድረግ ታላቁ የንክሩሃማ ታላቅ ሃሳብና ራእይ በሌሎች የአፍሪካ ፓንአፍሪካኒስት ጽንሰ ሃሳብ አራማጆች አፍሪካውያን ተቀባይነት ነበረው፡፡ ለአብነት ያህል የጊኒው ፕሬዜዴንት ሴኩቱሬ ይጠቀሳሉ፡፡
በድህነት ለመኖር የመረጥን ነን፡፡ እኛ ወደ ባርነት እየሄድን ነው፡፡ ጊኒ ትንሽ ሀገር ናት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ፍርሃታችንን አስወግደን ነጻነታችንን ለመጎናጸፍ መነሳት አለብን፡፡ ማንም ሰው የሌሎች አፍሪካውያን ብቸኛ የነጻነት ታጋይ እኔ ብቻ ነኝ ማለቱ ስህተት ነው፡፡ አፍሪካውያን ሁላችንም በህብረት ነጻነታችንን ማስጠበቅ አለበን፡፡ እያንዳንዱ አፍሪካዊ ስለ አፍሪካ ብልጽግናና ሉአላዊነት በተመለከተ ሃሳቡን መስንዘር መብት አለው፡፡ ( ፕሬዜዴንት ሴኩቱሬ )
ሌላው በግዜው የታወቁት አፍሪካዊ መሪ የነበሩት የሴኒጋሉ ፕሬዜዴንት ባለቅኔውና ጸሃፊው ሊኦፖልድ ሴንጎር (Leopold Senghor ) ነበሩ፡፡ እኚህ ታላቅ ሰው ጥልቀት በርካታ ጽሁፎቻቸው ለአፍሪካ አንድነት ጽኑ አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻግር ሊኦፖልድ ለአፍሪካ ባህል መጠበቅና መጎምራት የኔግሮ (Negritude) ጽንሰ ሃሳብም እንዲበለጽግ በብዙ የደከሙ መሪ ነበሩ፡፡
ኔግሪቲዩድ (Negritude ) ማለት የጥቁርን ህዝብ የተወሳሰብ የስልጣኔ፣ ባህል፣ምጣኔ ሀብት፣ማህበራዊ ዋጋ ያለው ሲሆን የሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሃሳብን የያዘ ነው፡፡
ከላይ በስም የተጠቀሱት የአፍሪካ መሪዎች ሁሉ የአፍሪካ ሰብዓዊና የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል፣ የሳይንስ ፣ቴክኖሎጂ እና ኢንዱስትሪዎችን በማበልጸግ፣ንግድ እና ገበያን በማስፋፋት የተባበረችወ አፍሪካን ለመመስረት አቅድና ዝግጅት እንደነበራቸው የአሁኑ ትውልድ ሊገነዘበው ይገባል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ማንኛውም ሰው ሊገነዘበው የሚቻለው ቁምነገር ቢኖር እውነተኛ አንድነት በአፍሪካ እንዳይሰፍን በርካታ ደንቃራዎች እንደነበሩት ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት በተለይም በአፍሪካ ፖለቲካዊ አንድነት እውን ለማድረግ በብርቱ አዳጋች ነበር፡፡ እውነትም አይመስልም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን ለመክላት፣ መረጋጋት ለማስፈን፣ ባልካናይዜሽንን ( የከፋፍለህ ግዛ ስርዓትን ) ለማምከን፣ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ምዝበራ ለማክሸፍ፣ ሙሰኝነትን ለመዋጋት የአፍሪካ አንድነት መጠበቅ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡
የፓንአፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብ የተወለደው የጋራን ችግር እና የፍሪካን የጋራ ግንዛቤ ከመረዳት የመነጨ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በግዜው የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን መጎናጸፍ አለባቸው፣ እንዲሁም የአፍሪካወያንን ክብር ለማስጠበቅ የሚል ህልም የነበራቸው ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ ጀማሪዎቸና አራማጆች ነበሩ፡፡ ይህን መንፈስ ተከትሎ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1960 እና 1970 አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ ወጥተው ነበር፡፡
ሆኖም ግን ይሁንና አንዳንድ አፍሪካውያን ጽዮናዊነትን እንደ አንድ ፖለቲካዊ አንደነት መመልከታቸው ሃሳባዊነት ነበር፡፡ ስለሆነም የፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካውያን ወጣቶች ህልምና ተስፋ ነው፡፡
የ 1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ሌጋሲዎች ( እ.ኤ.አ. )
የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት የሚያነጋ እንቅስቃሴ የተጀመረው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ የተደረገውን የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተከትሎ እንደነበር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ያስተምረናል፡፡ እርግጥ ነው ይገባኛል፡፡ ያንዬ በሀገር ፍቅር የነደዱ ፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና የብዙ ሺህ አመታት ታሪክ ይደግፉና ያስተምሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊ የዩነቨርስቲ መምህራና ተማሪዎች ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያ ተማሪዎችን የዲሞክራሲ ጥያቄ ተገን በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ውስጥ ሰርገው የገቡ የገንጣይ ሀይሎችና የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ለኢትዮጵያ አንድነት መናጋት ስጋትና እንቅፋት መሆን የጀመሩት ያንዬ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና የምእራባውያን የስለላ ድርጅት ተደግፈው የኢትዮጵያን ህልውና የተፈታተኑትና አደጋ ላይ መጣል የጀመሩት ያንዬ ነበር፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ የኢትዮጵያን መጥፎ እድል ሰንመረምር ይህ የጎሳ ፖለቲካ በተከታታይ ትውልድ ተቀናይነት ማግኘቱ ሲታሰብ ህሊናን ያደማል፡፡ ቀሪው አለምና መላው አፍሪካ ወደ ታሪክ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ አሽቀንጥረው የወረወሩትን የጎሳ ፖለቲካ ዛሬም ድረስ የሀገሪቱ የፖለቲካ ስልጣንን የተቆጣጠሩት አካላት መመሪያቸው መሆኑ በእውነቱ አንገትን ያስደፋል፣ ህሊናን ያደማል፡፡ በተለይም የቀድሞዋ ሶቬዬት ህብረት ከፈራረሰች በኋላና የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሚያን ተከትሎ የጎሳ ፖለቲካ መሪዎች የሐገሪቱ የፖለቲካ አቅጣጫ አዛዥ ናዛዥ መሆናቸውን የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የጎሳ ፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ካለፈው ውድቀታቸው መማር ባለመፈለጋቸው ምክንያት የተነሳ ዛሬም ሀገሪቱን እንጦርጦስ እየወሰዳት ያለውን የጎሳ ፖለቲካ ያለምንም ይሉኝታ እያራመዱ የሚገኙበት አስደንጋጭ ግዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ስታሊናዊ መንፈስ ያለውን ህገመንግስት ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ህዝብ መቀበሉን በአደባባይ እንዲናገር ነጻነቱ አልተሰጠውም፡፡ በብዙ ምሁራን የጋናውን አይነት ዘመናዊና ዲሞክራሲያዊ ህገመንግስት በኢትዮጵያ ገቢራዊ እንዲሆን በብዙ ቢደከምም ወይም አይናቸው ደም እስኪመስል፣ እጃቸው እስኪዝል ቢጽፉም ዛሬም ሃሳበቸው ተቀባይነት አላገኘም፡፡
ያንዬ የነበረው ትውልድ የማርክሲስት ሌኒንስት አቀንቃኝ የነበረ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ብዙዎቹ የማርክስን መጽሀፍ በቅጡ ያነበቡት አልነበሩም፡፡ ብዙዎቹ ሳያነቡ የማርክስ አፍቃሪ ነበሩ፡፡ አንዳንዶች ያነበቡትም ቢሆኑ ማርክስን የተረዱት አልመስልህ አለኝ፡፡ እውነትን ለመፈለግ ያደረጉት መንገድ ምክንያታዊ አልነበረም፡፡ እውነተኛ ምርምር ለማድረግ የሞከሩ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ አብዝሃው ወጣት መሬት ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ለመረዳት አልቻለም ነበር፡፡ ( ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ )
በነገራችን ላይ እንደ ወያኔ የመሰሉ የተገንጣይ ሀይሎች የተማሪው ትግል ውጤቶች እንደሆኑ በርካታ የፖለቲካ ተጠባቢዎች በጥናታቸው የደረሱበት ጉዳይ ነው፡፡ ወያኔዎችም ሆኑ ሌሎች የጎሳ ፖለቲከኞች የኢትዮጵያን የረዥም ዘመን ታሪክ የሚቀበሉ አይደሉም፡፡ ከአለም የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ እጅጉን የራቁ ናቸው፡፡ ወጣቱን ትውልድ እርዮት አልባ በማድረግ ሆኖም ግን መፈክር በማሸከም አላማቸውን ያራመዱም ናቸው፡፡ ካለፈው ውድቀታቸው እና የክሽፈት ታሪካቸው ለመማር ፍጹም ዝግጁ አይደሉም፡፡ እዚች ላይ እንደ ኦነግና ህውሃት የመሳሰሉ የተገንጣይ ሀይሎች ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ሁነኛ ድጋፍ መስጠታቸውን ለማወቅ የሚፈልግ አሁን ያለው ትውልድ ( ሁሉንም በደምሳሳው ሳይሆን ለመጠየቅ መንፈሳዊ ወኔ የታጠቁትን ማለቴ ነው፡፡ ) ይህንን መራር እውነት የሚያወሱ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክን እንዲመረምር ሳስታውስ በታላቅ አክብሮት ይሆናል፡፡ በእውነቱ ለመናገር ወያኔም ሆነ አጋሮቹ ‹‹ የራስን እድል በራስ መወሰን ›› የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ የሚተረጉሙት አዲስ ሀገርን መፍጠር ማለት እንደሆነ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ጽንሰ ሃሳብ በደቡብ አፍሪካዊት ገቢራዊ ከነበረው የባንቱስታናይዜሽን፣ አፓርታይድ ስርዓት ሁሉ ኋላቀር ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ መጨረሻው አፋጀሽኝ ነው፡፡ ዛሬ የሚደረገው ትግል ኢትዮጵያን ከተሳሳተ፣ከማያነብ፣ እና ሙሰኛ ከሆነ የፖለቲካ ኤሊት ለማዳን የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጎሳ ፖለቲከኞች ፍቅርና ጠብ ምክንያት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ አልተቻላቸውም፡፡ የተገንጣይ ሀይሎች በተፋቀሩና በተጣሉ ግዜ ኢትዮጵያ ለምን ትጎዳለች ብሎ መጠየቅ ቡራ ከረዩ ያስብል ይሆን ? ዛሬ አይንና ናጫ ቢሆኑም፣ ወያኔ ከሻቢያ ጋር ፍቅር በነበረበት ግዜ ይህቺ ጥንታዊ ታሪካዊት ሀገር የባህር በር (ወደብ ) የምታገኝበትን ጥሩ እድል ያመከነ እኩይ የፖለቲካ ቡድን ነው፡፡
አፍሪካ፣ የወጣቶች ችግር
‹‹ ወጣቱን ትውልድ በቀላሉ ማሳመን ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በፍጥነት ተስፋ ስለሚያደርግ ነው ››( አሪስቶትል )
“ Youth is easily deceived because it is quick to hope.” Aristotle
አሪስቶተል የራሱ እውነት አለው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች በተስፋ የተሞሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አሁን መሬት ላይ እውን በሆነው የፖለቲካ አውድ ምክንያት ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ ደምተዋል፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፖለቲከኞችን ማመን ተስኗቸዋል፡፡ የፖለቲካ ኤሊቶች የሀገሪቱን ቁልፍ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ተስኗቸዋል ብለውም ያምናሉ፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በብዙበ የአፍሪካ ሀገራት ተስፋ በጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ተተክቷል፡፡
ትልቁ የአፍሪካ ችግር ፣ማህበራዊ ድረገጽን አለአግባብ መጠቀም ነው
የአፍሪካ ብልጽግና፣ እድገት እና በቴክኖሎጂ መግፋት የሚታየው በኢንተርኔት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የማህበራዊ ግንኙነቶች መንገዶች በሆኑት ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ትዊተር፣ ወዘተ የህብረተሰቡ መገናኛ ከሆኑ ሰነበቱ፡፡ የህብረተሰቡ ዋነኛ የዜና ምንጮች ማህበራዊ ድረገጽ እየሆነ ይገኛል፡፡ የቴሌቪዥን ተጠቃሚዎች አፍሪካውያን ቁጥር እየቀነሰ ይገኛል፡፡ ከአንዳንድ የጥናት ውጤቶች ላይ ለመመልከት እንደቻልኩት 60 ፐርሰንቱ አፍሪካዊ የመጀመሪያ የመረጃ ምንጩ ማህበራዊ ድረገጽ ሲሆን፣ 25 ፐርሰንቱ ከቴሌቪዥን፣6 ፐርሰንቱ ደግሞ ጋዜጦች የመጀመሪያ የዜና ምንጮቻቸው ናቸው፡፡
በእርግጥ ማህበራዊ ድረገጽ በትምህርት፣ ንግድ እና በሌሎች በርካታ የትምህርት ዘርፎች አኳያ ያላቸው አበርክቶ ወደር የለውም፡፡ በአጠቃላይ ተማሪዎች የማህበራዊ ድረገጽ የሚጠቀሙት ወዲያውኑ ያገኙትን መረጃ ለማሰራጨት፣ ችግሮቻቸውን ለመከለስና መፍትሄ ለመፈለግ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አብዛኞቹ የአፍሪካ ወጣቶች፣ በተለይም ለኢትዮጵያ ወጣቶች ዋነኛው የዜና ምንጭ የማህበራዊ ድረገጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ፈጣን፣ በቀላሉ በእጅ የሚያዝ ( ሞባይል ስልክን በኪሳችን ይዘን ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ መንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ ) እና አዝናኝ ስለሆነ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ጋዜጦችና መጽሀፍትን የማንበብ ፍላጎታቸው እየከሰመ ይገኛል፡፡ አብዛኞቹ ወጣቶች በኢንተርኔት የሚሰሙ ( የሚለጠፉ) ዜናዎች ሁሉ እውነት ናቸው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ወይም የሀሰት ዜናዎችን ካዩ በኋላ ትክክል ስላለመሆናቸው የሚያስተጋቡ ወጣቶች ቁጥር እጅጉን ትንሽ ነው፡፡ ብዙዎች ለሀሰት ዜናዎች ወይም መረጃዎች በቀላሉ የሚማረኩ ናቸው፡፡ እነርሱ ማመን የሚፈልጉት ለማመን የሚፈልጉትን ጉዳዮች ብቻ ነው፡፡ ለአብነት ያህል አንድ ኢትዮጵያዊ ለሀገር መድህን የሚሆን ሃሳብ በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ቢለጥፍ ጽሁፉን ስራዬ ብሎ የሚያነበው ወጣት ቁጥሩ አነስተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰበር ዜና በሚል የሀሰት ዜና የሚያራግቡ፣ የምእራባውያን ባህልን የሚያስተዋውቁት ቁጥሩ ቀላል የማይባል ወጣቶች ይከተሏቸዋል፡፡
የሀሰት ዜና (“Fake news ) ማለት ሆን ተብሎ፣ ታቅዶ፣ ታስቦበት የሰውን መንፈስ ለማነሳሳት እና አለ አግባብ ለመጠቀም ሲባል የሀሰት ዜና ማሰራጨት ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የማህበረሰብን ግጭት ለማቀጣጠል ወይም ግጭቶችን ለመፍጠር ሲባል የሀሰት ዜናዎች ሁነኛ ሚና እንዳላቸው ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ አንዳንድ የጥናት ውጤቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ በአሜሪካን ሀገር የማህበራዊ ድረገጽ አንባቢዎች አኳያ የሚሰራጩ የሀሰት ዜናዎች፣ በአሜሪካን ህብረተሰብ መሃከል እምነት እንዳይኖር ሁነኛውን ሚና እየተጫወቱ ስለመሆኑ አመላካቾች ናቸው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በአሜሪካን ምድር እምነት ማጣትን ብቻ ኋላቀርነትን ከማስፈኑ ባሻግር፣ እረብሻን የሚያባብስ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ በአሜሪካን ማህበረሰብ መሃከል የነበረውን የማህበራዊ ህይወት ትስስር ( the fabric of American life ) በነገራችን ላይ ከአንዳንድ የጥናት ውጤቶች ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው የሐሰት ዜና የሚፈበረከው በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ እነኚህም፡-
- የሀሰት ዜናዎች ግጭቶች እንዲቀጣጠሉ ያደርጋሉ፡፡ ህብረተሰቡ እርሰበርሱ እንዳይተማመን ያደርጋሉ፡፡ ዴሞክራሲ እንዳይሰፍን ደንቃራ ይፈጥራሉ፡፡
- ማህበረሰቡ በሁነኛ ጉዳዮች ላይ እንዳያተኩር ያደርጋሉ፡፡ የሰውን አይምሮ እንዳይረጋጋ እና መፍትሔ የሌላቸውን ችግሮች እንዲቀፈቀፍ ያደርጋሉ፡፡
በነገራችን ላይ ማህበራዊ ሚዲያ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት እድገት ሁነኛውን የሚቻወት ሲሆን፣ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ አክራሪነትና ብሔርተኝነት ለመስበክ የሚውል መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ማህበራዊ ሜዲያ አሸባሪዎችን በቀላሉ ለመመልመል፣ ለማሰልጠን፣ለማደራጀት፣ በጣም እሩቅ ቦታ የሚገኙ ተከታዮቻቸውን ለመመልመል እና ለመመዝገብ አመቺው ፕላት ፎርም እንደሆነ እንደ ሻለቃ ዳዊት የመሰሉ የፖለቲካ ተጠባቢዎች በጥናት ወረቀቶቻው ላይ አስፍረውት ይገኛል፡፡ በዛሬው ዘመን አል-ሸባብ፣ ቦኮሃራም፣አይስል፣ እና ሌሎች በአፍሪካ የሚገኙ አሸባሪዎች እንደ ትዊተር (Twitter,) ፣ማህበራዊድረገጽ (Facebook ) ፣ዩቲዩብ (YouTube ) የመገናኛ ፕላትፎርሞችን ተጠቅመው መልእክቶቻቸውን ይልካሉ፡፡ ተከታዮቻቸውን እንደሚቀሰቅሱ ይነገራል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ደጋፊዎቻቸውን በአባልነት እንዲመዘግቡ ይቀሰቅሳሉ፡፡
በኢትዮጵያ የሀሰተኛ ዜናዎች ስርጭት ብዙዎችን ያሳሰበ አይመስልም፡፡ ብዙዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉ ይመስላል፡፡ አይተው እንዳላዩ ሆነዋል ማለትም የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ድንቁርና ወይንስ ስልጣኔ ? ስልጣኔ አይመስለኝም፡፡ ከሆነም ድንቁርና ነው፡፡ አብዝሃው ወጣቱ ትውልድ እውነትን ሲፈልግ አይታይም፡፡ ለምን ይሆን የሀሰት ዜናዎች ሲሰራጩ ምክንያታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ቁጥራቸው ያነሰው ? በነገራችን ላይ የሀሰት ዜናዎች ከእውነት ጋር የተጣሉ ስለሆነ የሚጠቅሙት አገዛዞችን ወይም ግፍ ፈጻሚዎችን፣ አሊያም የእነርሱ ጋሻ ጃግሬዎቻቸውን ነው፡፡ ሁሉም የሆነው ማህበራዊ ሚዲያን በቀላሉ መጠቀም ስለሚቻል ነው፡፡
እኛ የትነው ያለነው ?
ብዙውን ግዜ የህለመኞቹ ሃሳብ እሩቅ ህልም ይመስላል፡፡ በአፍሪካ በርካታ ጉዳዮች በጥሩ ሁሌታ እየሄዱ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል አማካኝ የአፍሪካዊ እድሜ ጣሪያ 50 አመት ነው፡፡ የጎልማሶች ትምህርት እድገት እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ምንም እንኳን ይሁንና አንዳንድ መሻሻሎች ቢታዩም፣ አፍሪካ ዛሬም በአለም ላይ ከፍተኛ የህጻናት ሞት ቁጥር ከፍተኛ የሆነባት አህጉር ናት፡፡
በአንዳንድ መንገዶች ሌላው አለም ወደፊት እየገሰገሰ አፍሪካ ዛሬም የኋልዮሽ እየተንፏቀቀች ነው፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹና 1960ዎቹ ላይ አፍሪካ በምግብ ራሷን የቻለች ፣ ወደ ውጭው አለም የምግብ እህሎችን በመላክ የምትታወቅ አህጉር እንዳልነበረች፣ አፍሪካ ዛሬ ዋነኛ የምግብ ሸማች እንደሆነች ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በጥናት ወረቀታቸው ላይ አስፍረውት ይገኛል፡፡
በቀን አንድ ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ የሚያገኙ ሰዎች የሚኖሩበት ( እንደ ኑሮ ከተቆጠረ ማለቴ ነው) ከሰሃራ በታች ያለው የአፍሪካ ክፍል በአለም ላይ በድህነትና ችጋር የመጀመሪያው እረድፍ ላይ የተቀመጠ ነው፡፡ እንደ የአፍሪካ የምጣኔ ሀብት ጠበብት የጥናት ውጤት ከሆነ ዛሬ በአፍሪካ ያለው የነፍስወከፍ ገቢ አፍሪካ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1970 አፍሪካውያን ያገኙት ከነበረው የነፍስወከፍ ገቢ ያነሰ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ከ700 ሚሊዮን አፍሪካውያን ግማሹ ህዝቧ በቀን ከ1የአሜሪካን ዶላር ያነሰ ገቢ ያገኛል፡፡ ከሰሃራ በታች የሚገኘው የአፍሪካው ክፍል በዓለም ላይ ካሉ አካባቢዎች ሁሉ ከፍተኛው የድሆች ቁጥር የሚገኝበት የዓለም ክፍል ነው፡፡ ( 50 ፐርሰንቱ የዓለም ደሃዎች ቁጥር በዚሁ የአለም ክፍል ይገባል፡፡ ) እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1981 እና 2002 በአፍሪካ ድህነት ሁለት እጥፍ አድጓል፡፡ በአጭሩ ከሃያ አመት በፊት ከነበረው የኑሮ ደረጃ አሽቆልቁሎ እንጦርጦስ ወርዷል፡፡
አብዛኞቹ የዓለም ምዝብር ህዝቦች የሚኖሩት ከሰሃራ በታች በሚገኘው የአፍሪካ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ በአፍሪካው የአፍሪካ ክፍል በችጋር ውስጥ የሚሰቃየው ወደ 41 ፐርሰንት ግድም ይጠጋል፡፡ በአለም ላይ ከሚገኙት የድሃ ደሃ 28 ሀገራት መሃከል 27ቱ የሚገኙት በዚሁ ጨለማው የአለም ክፍል ውሰጥ ነው ተብሎ ቢጻፍ የሚቆጣ ይኖር ይሆን ካለም እውነት መራር ብትሆነም ከመጋት ውጭ አማራጭ የለውም፡፡
በሌላው የአፍሪካ ክፍል የሚታየው መራር እውነት በኢትዮጵያ የሚታይ ነው፡፡አብዛኛው ወጣት ትውልድ ተጠቃሚ ሳይሆን ተጠቂ እየሆነ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በርስበርስ ጦርነት፣ለከቱን ባጣ ድህነት፣ፍርሃት፣በሀገር ውስጥ መፈናቀል፣ስደትና ምን ክፉ እጣ እንደሚገጥማት ባለማወቋ የተነሳ ፍዳዋን የምትቆጥር አሳዛኝ ሀገር ናት፡፡ በነገራችን የወደፊቷ ኢትዮጵያ በወጣቱ እጅ ላይ ናት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ወጣቱ ትውልድ የሥራ እድል ካላገኘ፣ እድል እና ትኩረት ካልተሰጣቸውተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ አሪስጦጥል እንዳለው ‹‹ ወጣቶች በፍጥነት ተስፋ ያደርጋሉ፣ ሆኖም ግን ይሁንና በሁሉም ነገሮች በተለይም በመንግስት ላይ ተስፋ ከቆረጡ የወደፊት ተስፋቸው ይጨልማል ፡፡ የአሪስቶትል ጥቅስን ለማስታወስ ‹‹ ወጣቱ በፍጥነት ነው ተስፋ የሚያደርገው፣ በፍጥነትም ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ተስፋ ከቆረጠ፣የወደፊት ተስፋው ከተነነ፣ የሚገጥማቸው መጥፎ እድል ነው፡፡ ይህ ወጣቶችን ወደ መጥፎ ውሳኔ ይወስዳቸዋል፡፡ ለስደት ይዳረጋሉ፡፡ የውጭ ሀገር ምእራባውያን ጥገኛ እና አሽከር ለመሆን ይሽቀዳደማሉ፡፡ በዘር ተከፋፍለው ይፋጃሉ፡፡ አፍሪካዊ ወጣቶች ኢትዮጵያውያንንም ይጨምራል፣ ተስፋ በመቁረጣቸው የተነሳ ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ ባህር አቋርጠው አስቸጋሪና አደገኛ ጉዞን ይመርጣሉ፡፡ ወጣቶች ስደትን ይመርጣሉ፡፡ ወደ ሀገራቸው ፊታቸውን ለማዞር በፍጹም አይፈልጉም፡፡ ለአብነት ያህል በአንዲት ናይጄሪያዊት ሴት ላይ የደረሰውን ክፉ ገጠመኝ እዚች ላይ መጥቀሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንዲት ናይጄሪያዊት ውቅያኖስ አቋርጣ ወደ ጣሊያን ለመጓዝ የተጫነችባት ጀልባ ድንገት ብልሽት ባጋጠማት ቅስፈት ወደ ሀገሬ ናይጄሪያ አልመለስም በዋናም ቢሆን አቋርጬ ወደ ጣሊያን እሄዳለው በማለት ነበር ለነብስ አድን ሰራተኞች የነገረቻቸው፡፡
ይህ የወጣቶች የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ ( እንደ ዘይቤ ከተቆጠረ ማለቴ ነው፡፡) የሰብዓዊ ስሜታቸው እየተሟጠጠ ነው፡፡ ብዙዎችየሰውን ሀብት ለመንጠቅ ( ለመዝረፍ ) ሲሉ ለወንጀል ድርጊትም ይጋለጣሉ፡፡ ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች የወንጀለኞች መሳሪያ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ እንደ እነ ሻለቃ ዳዊት የመሰሉ አፍሪካዊ ምሁራን በጥናታቸው ላይ እና በአካል እንደደረሱበት እንደደረሱበት ከሆነ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት የግጭቶች መስፋፋትና አለመረጋጋት ዋነኛ ምክንያት ወጣቶች ስራ እጥ በመሆናቸው እንደሆነ ደርሰውበታል፡፡ ወጣቶች የስራ እድል ከተነፈጉ ያላቸው የመጀመሪያው እድል የአማጺ ሀይሎች አባል መሆን ነው፡፡ በማናቸውም የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በሚካሄዱ ግጭቶች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ግንባር ቀደም ተፋላሚዎች ናቸው፡፡
ተደጋግሞ እንደሚነገረው መጪው ትውልድ አፍሪካን የሚያድን ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አብዛኛው ከሰሃራ በታች የሚገኘው ወጣት ከመቼውም ግዜ በላይ በድህነት የሚማቅቅ ነው፡፡ ከአራት ወጣቶች መሃከል ሶስቱ ወጣቶች በቀን የሚያገኙት የገቢ መጠን ከ 2 የአሜሪካን ዶላር ከማነሱ ባሻግር እውቀትም የላቸውም፡፡ ከሰሃራ በታች ከሚገኙት የአፍሪካ አጠቃላይ የወጣት ቁጥር 23 ውስጥ ፐርሰንት የሚደርሰው ማንበብና መጻፍ አይችሉም፡፡
የአፍሪካ ወጣቶች ውድ የአፍሪካ ሀብቶች ቢሆኑም ብዙዎቹ እውቀት እና ጥሩ እድል የላቸውም፡፡ ወጣቶች የሚወክሉት አደጋን እንጂ ጥሩ እድልን አይደለም፡፡ ስለሆነም የአፍሪካ ወጣቶች በፖሊሲ ጥናት ውይይት ላይ በመካፈል አፍሪካ ለገጠማት ችግር ሁነኛ መፍትሔ መሻት አለባቸው፡፡
‹‹ Passion rebuilds the world for the youth. It makes all things alive and significant.” Ralph Waldo Emerson.
በነገራችን ላይ አፍሪካን ለማሳደግና ለማበልጸግ የአንበሳውን ድርሻ መጫወት የሚችለው ወጣቱ ነው፡፡ የማናቸውም ሀገር ትልቁ ሀብትም ቢሆን ወጣቱ ነው ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ተስፋ እና እውቀት የታጠቀ ወጣት አፍሪካን መቀየር ይቻለዋል፡፡ ለዚህ እውን መሆን ግን መንግስታት ከፍተኛ ወጪ በትምህርት ላይ ማፍሰስ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ጥራት ያለው ትምህርት ለወጣቱ ማድረስ ይጠበቃል፡፡ ወጣቱ የመቻቻል ባህል፣ እንዲያዳብር፣ ሰላማዊ ህይወት እንዲላመድ በብርቱ መሰራት ይጠበቃል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ ዋና ዳይሪክተር ዶክተር ባባቱንዴ ኦስቶሚሂን .( Dr. Babatunde Osotimehin,) ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ‹‹ በአንድ ሀገር ወይም አህጉር ውስጥ ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሩ ውስጥ 40 ፐርሰንቱ ወጣቱ በሆነበት፣ እንዲሁም 65 ፐርሰንት የሚሞላው ደግሞ እድሜው ከ 35 ዓመት በታች ከሆነ 65 ፐርሰንት የሚጠጋው የአህጉሪቱ ሀብት በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ መመደብ አለበት፡፡ ››
በአሁኑ ግዜ ዘለቄታዊ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ እድገት እውን እንዲሆን የአህጉሪቱ ወጣቶች በወደፊቱ የአህጉሪቱ መጻኢ እቅድ ላይ መሳተፍ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአህጉሪቱ ሰርክ አዲስ ለሚቀፈቀፉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ( ለአብነት የሃይል ምንጭ እጥረት፣ኋላቀርነት..ወዘተ ወዘተ ) ለመክላት ወይም ለመቋቋም አዲስ ሃሳብ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና መሰረት ነው፡፡ ወጣቶችን ማግለል ለአህጉሪቱ ከባድ ችግር የሚፈጥር ነው፡፡ ይህ የሀዝብ አካል ( ክፍል) የአፍሪካን ገጽታ መሸፈን የሚችል ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ አፍሪካ ለሚገጥማት ተግዳሮቶች ሃላፊነት ወስዶ ሰራሄ መፍትሔ መሻት ግዴታው ነው፡፡ ምክንያቱም አህጉሪቱ ለሚገጥማት ችግሮች አንዱና ዋነኛው ሃላፊነት የወጣቱ በመሆኑ ነው፡፡ ወጣቱ የእኛ ዋና እና እጅግ አስፈላጊ ሀብትም ነው፡፡ ስለሆነም የወጣቱን ሀይል ትርጉም ባለው የልማት መንገድ በመጠቀም የአፍሪካን ልማት ማፈጠን እጅን ጠቃሚ ነው፡፡
ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ እንደ ጎርጎሮሲያ አቆጣጠር 1993 ፓን አፍሪካንስትና ደራሲ ከሆነው ጋናዊ ጓደኛቸው ሚሰትር ኦሲ ጂ. ኮፊ (Osei G. Kofi, ) ጋር አንድ ላይ በመሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ (The project was titled “Africa: The Next Generation – Alliance of the African Youth ) በሚል ርእስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደጠቀሱት የወጣቱን ህይወት ለመለወጥ ‹‹ እጅግ ከባድ ስራዎች መከናወኑን፣ ብዙ ለውጦች ለማምጣት መሞከሩን ከገለጹ በኋላ የሙሉ ግዜ ፕሮፌሽናል ስራዎችን በማለመካሄዱ የታቀደው ሰናይ አላማን ለማሳካት አልታደልንም፡፡ ስለሆነም የማህበራዊ ፍትህ ለማስፈን፣ ተተኪ መልካም አመራር ለመፍጠር፣ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎን ለማዳበር ወጣቶችን ማብቃት አማራጭ የለውም ብለዋል፡፡
በነገራችን ላይ ወጣቶች የገጠማቸውን ችግር በትክክል ለመግለጽ፣ ለማወቅ እጅጉን አዳች ሲሆን፣ ሁነኛ መፍትሔም ለማግኘት እንዲሁ ጥልቀት ያለው አካዳሚክ ምርምር የሚፈልግ ነው፡፡ የወጣቱ ችግር በካድሬ ልፈፋ፣ በጥቅም በመደለል፣ ደጋፊ አድርጎ ብር ማስታቀፍ መፍትሔ አያመጣም፡፡ የሚበጀው ሳይንሳዊ ምርምር አድርጎ ሳይንሳዊ መፍትሔ መስጠቱ ነው፡፡ የተቸገሩ ወጣቶችን ወደ መልካም ህይወት ማምጣቱ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በሰከነ መንፈስ ከተኬደ፣ ፍትህና ነጻነት ከሰፈነ የወደፊቱን ሀገር ተረካቢ ወጣት ህይወት መታደግ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲ የሰፈነበት ፣ ነጻነት የተከበረበት፣ ታማኝ የሀገር መሪ ያለባት አፍሪካ ለወጣቶቿ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ለማበጀት ቀና መድረክ ትሆናለች ብዬ አስባለሁ፡፡ በቅርቡ ዴሞክራያዊ ምርጫ በማካሄድ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ተምሳሌት የሆኑት ኬኒያውያን ጎረቤቶቻችን የወጣቶቻውን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ጥርጊያ መንገድ እየሰሩ ስለመሆኑ መገመት ይቻላል፡፡
ለወጣቶች አንድ ምክር ቢጤ አለችኝ፡፡ ወጣቶች በአጭበርባሪዎች፣ሞራለቢሶች፣ጨካኞች፣ ስግብግቦች፣ውሸታሞች፣አምባገነኖች መመራትና መታለል የለባቸውም፡፡ ወጣቶች የአይምሮ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ሀይላቸውን ተጠቅመው ህይወታቸውን ማሻሻል አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች የወጣቶችን ፍርሃት፣ የደህንነት ስጋት፣ ረዳት አልባት፣ የዋህነትን በመጠቀም ለራሳቸው ጠባብና ሰይጣናዊ አላማ የሚጠቀሙባቸው ስለሆ
የሰው ደህንነት ( Human Security )
አፍሪካ በብዙ ችግሮች የተተበተበች ናት፡፡ ለአብነት ያህል ዋነኛው ችግሯ የጸጥታ ችግሯ ይጠቀሳል፡፡ አፍሪካ ለህዝቧ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ተስኗታል፡፡ በጣም የሚጠቀሰው ህዝቧ ምሉሄ በኩልሄ የሆነ ነጻነትና ፍትህም አልተጎናጸፈም፡፡ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ አሸባሪዎችና ወንጀለኞችም ወንጀል ለመፈጸም የሚያስችላቸው ምቹ ለም መሬት ናቸው ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡
በተደራጁ የወንጀለኛ ቡድኖች ተቀነባብረው የሚፈጠሩ ችግሮች ወይም ጉዳቶች በአካባቢ እና አለም አቀፍ ሰላም፣መረጋጋት፣ የምጣኔ ሀብት እድገት ፣ በሰላም አብሮ ተከባብሮ የመኖር መንፈስ ላይ፣ በመንግስት እና የህግ የበላይነት ላይ ውድቀትን ያስከትላል፡፡ የመንግስት አስተዳደር እና የህግ የበላይነት፣ ጉቦ፣ የወደቁ ተቋማት፣ የተዳከመ ማህበረሰብ፣ችጋር፣ የአግድሞሽ እና የጎንዮሽ ዕኩልነት አለመኖር፣( horizontal and vertical inequality ) የድንበር ይገባኛል ግጭት፣አክራሪነት፣ ወዘተ ወዘተ በአንድ ሀገር ላይ የእርስበርስ ጦርነት እንዲከፈት፣ ወንብድና እንዲስፋፋ ሁነኛ ምክንያት ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ለወደፊቱ ተስፋ የሚሰጡ ቁምነገሮች እየከሰሙ በመምጣታቸው የተነሳ ወጣቶች የአሸባሪዎችና ጦረኞች ሲሳይ እየሆኑ ስለመምጣታቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራ እጣፈንታ ያሳዝናል፡፡ በአብዛኛው በሰሜን፣ምእራብ፣ በመሃከለኛውና በአፍሪካው ቀንድ፣ ሞዛምቢክ የግጭት ቀጠናዎች መብዛታቸው የአፍሪካን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ መግባባት፣ ፍቅርና ሰላም፣እንዲሁም አንድነት ቅንጦት እየሆኑ ነው፡፡
በነገራችን ላይ በአፍሪካ የሚገኙ አማጺ ሀይሎችና የሽር ቡድኖች ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ወጣቶች አባላቶቻቸው እንደሆኑ በብዙ የጥናት ወረቀቶች ላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ለምንድን ነው ይህ የሆነው ? የሁሉም መጥፎ ነገሮች እውን መሆን መሰረታዊ ምክንያቱ ድህነት ወይም ችጋር ነው፡፡ አፍሪካ በአለም ላይ ግንባር ቀደሟ በችጋር የምትታወቅ አህጉር ናት፡፡ በድህነት የሚማቅቁ ወጣቶች ደግሞ በቀላሉ የወንጀለኞች ቡድን አባል ከመሆናቸው ባሻግር፣ የአደንዛዥ እጽ ተጠቂ የመሆናቸው እድል የሰፋ ነው፡፡ ስለሆነም የአፍሪካ መንግስታት የወጣቱን የኑሮ ደረጃ የማሻሻል ግዴታቸውን እንዲወጡ ሳስታውስ በታለቅ አክብሮት ይሆናል፡፡ እሰናበታለሁ፡፡
እንደ መውጫ
የእነ ክዋሚ ንክሩህማ ሀገር የነበረችው ጋና፣ ሴዳር ሴንጎር ሀገር የሆነችው ሴኒጋል፣ ሙዋሊሙ ጁሊዬስ ኔሬሬ ሀገር የሆነችው ታንዛኒያ፣ የታላቁ የአፍሪካ ልጅ ሀገር የሆነችው የደቡባዊት አፍሪካዊት ሪፐብሊክ፣ የጆሞ ኬኒያታ ሀገር የሆነችው ኬኒያ፣ ናሚቢያ፣ ቦትስዋና፣ ሲሼልስ ወዘተ ወዘተ በሀገሮቻቸው ላይ የዴሞክራሲ አዝመራ ዘርተው ፍሬውን እየሰበሰቡ የሚገኙበት ግዜ ላይ ደርሰናል፡፡ በጎሳ ፖለቲካ አስከፊ ፍጅት አስተናግደው የነበሩት ሩዋንዳና ቡርንዲን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ የጎሳ ፖለቲካን ወደ የታሪክ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ አሽቀንጠርው የጣሉት ሲሆን፣ የእነ አጼ ሀይለስላሴ፣ ክቡር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ፣ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፣ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ፣ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ፣ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ኮሎኔል አብዲስ አጋ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፣ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ሳይንቲስት ጌታቸው ቦለዲያ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ( የስባቱም ነብሳቸው በሰላም ትረፍ ) ወዘተ ወዘተ ሀገር የሆነችው ታሪካዊት ኢትዮጵያ ግን ካለፉት 30 አመታት ወዲህ የጎሳ ፖለቲካን የሙጥኝ ብላ መያዟ ሲታሰብ እድላችንን አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ በነገራችን ላይ ከላይ በስም የጠቀስኳቸው ሀገራት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ መልኩ የዲሞክራሲን ባህል እየተላመዱ ቢመጡም በብዙ የአፍሪካ ሀጋራት ያለው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ ተስፋ ሰጪ አይደለም፡፡ እንዲሁም የቀደሙት የአፍሪካ ታላላቅ መሪዎች ህልምና ፍላጎት የነበረው የአፍሪካን አንድነት ማጠንከር እንቅስቃሴ ግን እየከሰመ ስለመሆኑ የአሁኑ አፍሪካዊ ትውልድ ማወቅ እና መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ቁጭ ብሎ የማይሆን ህልም ከማለም የቀደሙት አባቶቹን ጥያቄ እና መልስን ማሰላሰል፣ የአይምሮ ሀይሉን
ገቢራዊ በማድረግም የመፍትሔ ሃሳብ ማንሸራሸር የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ይሆናል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ጉዳይ እጅጉን አሳሳቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አፋጀሽኝ ከሆነው የጎሳ ፖለቲካ በሰለጠነ መንገድ ፣ በውይይት፣ በመነጋገር ተራማጅ የሆነ የፖለቲካ ዘይቤ ለማራመድ መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ አለባቸው የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች በርካታ ናቸው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ባለፉት ሰላሳ አመታት ተሞክሮ የከሸፈ እንደሆነም በብዙ የጥናት ወረቀቶች ላይ ተጽፎም ይገኛል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የሚገኙ በርካታ ምሁራን የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ይበጃታል ብለው ይከራከራሉ፡፡ ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ምድር የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሽን የፈሉት ፡፡ በእኔ በኩል እንደ ቀድሞው ሁሉ በግድ በጠመንጃ ሀይል የኢትዮጵያን አንድነት ማስከበር ይቻላል የምል ተላላ ሰው አይደለሁም፡፡ ለኢትዮጵያም የወደፊት እጣ ፈንታ መልካም መሆን የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና ይበጃል ከሚሉት ኢትዮጵያውን መሃከል አይደለሁም፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በአዲስ የፖለቲካ ፍልስፍና አንድነቷ ሊጠበቅ ይችል ይሆን የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡ ይሀውም የኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰውነት ክብር ሊጠበቅ የሚቻለው በሁለቱም ወገን ያሉትን የተራራቀ የፖለቲካ አስተምህሮ ( የጎሳ ፖለቲካ አይበጀንም የሚሉ የፖለቲካ ሀይሎችና የጎሳ ፖለቲካ ለዚች ሀገር የፖለቲካ ችግር ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለው የተነሱትን ) የሚያቀራርብ ወደ መሃል የሚያመጣ የፖለቲካ አስተምህሮ በምሁራን መዘጋጀት ያለበት ይመስለኛል፡፡
የቀድሞው አንጋፋ የአፍሪካ መሪዎች ( ክዋሚ ንክሩህማ፣ አጼ ሐይለስላሴ፣ ሴዳር ሲንጎር፣ መሀመድ ቢንብልቢ፣ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ሙዋሊሙ፣ ጆሞ ኬንያታ ወዘተ ወዘተ ) ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት በአንድነት ለማቆም ሲነሱ እኛ እንዴት ኢትዮጵያን በአንድነት ማቆም ይሳነናል እስቲ በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት፡፡
መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም.
ማስታወሻ የዚህ ጽሁፍ ሁሉም መረጃዎች (“ What a Life” from which ) ከተሰኘው የሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ መጽሀፍ የተወሰደ ነው