>

የዘንድሮ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ወረቀት  ስርቆት ለመከላከል በአገዛዙ የተላለፈው ውሳኔ አንድምታ (ከይኄይስ እውነቱ)

የዘንድሮ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ወረቀት 

ስርቆት ለመከላከል በአገዛዙ የተላለፈው ውሳኔ አንድምታ

ከይኄይስ እውነቱ

 

በሕይወት ልምድና በትምህርት የለዘበ የሽማግሌና ዐዋቂዎች መካር የሌለው አገር ለጥፋት ቅርብ ነው፡፡ 

በአዲስ አበባና በየክፍለ ሃገሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ትምህርት ‹ያጠናቀቁ› ተማሪዎች የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱት እንደ ቅደም ተከተላቸው በአ.አ. ዩኒቨርስቲና በየክፍላተ ሀገራቱ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች መሆኑን አገዛዙ አስታውቋል፡፡ የተሰጠውም ምክንያት በየጊዜው እየተሠረቀ የሚወጣውንና ተማሪዎች ጋር የሚደርሰውን የፈተናው ወረቀት ለማስቀረት እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ለዚህም ፈተናው ከሚሰጥባቸው ቀናት ቀደም ብሎ (ከመጪው ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ) ተማሪዎች በየዩኒቨርስቲው ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል የሚል ነው፡፡

ይህን የፖለቲካ ውሳኔ ስላስተላለፈው አገዛዙም ሆነ ተቀብለው ተግባራዊ ስላደረጉት የየዩኒቨርስቲው ሴኔቶች ጥቂት ቃላት ከመናገሬ በፊት፣ ይህን ነውረኛ ተግባር (የፈተና ወረቀት ስርቆትን) የጀመረው የአሁኑ አገዛዝ የግብር አባት የነበረው ወያኔ/ሕወሐት መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሁለቱ የወንጀል ሥርዓቶች ልዩነት የኋለኛው ነውሩን እጥፍ ድርብ አድርጎ መፈጸሙ ነው፡፡ አገዛዙ በሚከተለው ትውልድ ገዳይ የትምህርት ፖሊሲ ምክንያት ስለተፈጠረው የተበላሸ የትምህርት ሥርዓት እና በትምህርት አስተዳደር ተቋማት ውስጥ በዘረኝነት ስለመደባቸው ነውረኞች ሳይጨነቅና ለማስተካከልም ፍላጎት ሳይኖረው የፈተና ወረቀት ስርቆትን ለመከላከል በማሰብ ፈተናው እስኪጠናቀቅ ተማሪዎቹ በየዩኒቨርስቲው እንዲቆዩ አድርጌ (አግቼ) እቆጣጠራለሁ ማለቱ ታላቅ ፌዝ ነው፡፡

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ስርቆት በይፋ ባደባባይ የተነገረው የወያኔ አገዛዝ ሊወድቅ ሲቃረብ በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በሚባለው ተቋም ይሠሩ የነበሩ የአሁኑ አገዛዝ ወኪሎች ለጀዋር መሐመድ ልከውለት የፈተናው ወረቀት በእጄ ገብቷል ብሎ ያለምንም ኀፍረት እንደ ጀብዱ በተናገረ ጊዜ ነው፡፡ ለመሆኑ የአገዛዙም ሆነ የአካዳሚ ሴኔቶቹ ውሳኔ አንድምታ እንዴት ይታያል?

1ኛ/ ከአገዛዙ ዓላማ በመነሣት ጉዳዩን በሚገባ ለመረመረው ሰው የፈተናው ወረቀት ስርቆት በአ.አ. ተፈጽሞ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም በጥላቻ የሚመለከቱትን የአ.አ. ሕዝብ የሚጠቅሙበት ምንም ምክንያት የላቸውምና፡፡ የፈተናው ወረቀት በቅድሚያ በየክፍለ ሃገሩ እንዲደርስ ቀደም ብሎ ይላካል፡፡ በተለይም ኦሮሚያ በሚባለውና ተረኞቹ እናስተዳድረዋለን በሚሉት ግዛት ሲደርስ የአካባቢውን ተማሪዎች የጠቀሙ መስሎአቸው በተከታታይነት የፈጸሙት ተግባር ነው፡፡ በአ.አ. ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የፈተናው ወረቀት የሚሠራጨው ፈተናው በሚሰጥበት ዕለት ነው፡፡ ሆኖም የፈተናው ወረቀት በየክፍላተ ሀገሩ ከተላከና ስርቆቱ ከተፈጸመ በኋላ አ.አ. የሚገባበት ዕድል አይኖርም ማለት አይቻልም፡፡ 

2ኛ/ ዛሬ ማዕከላዊው አገዛዝ ክፍላተ ሀገራቱን መቆጣጠር በተሳነውና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ የአገዛዙ ኃላፊዎች ‹የክልል አስተዳደር የለም፤ ማንም አያዘንም› እያሉ ባደባባይ በሚናገሩበት ወቅት (በቅርቡ የሙዝ ዋጋን መወደድ አስመልክቶ ደቡብ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ወረዳ ኃላፊ አገዛዙ ለራሱ ዓላማ በተቆጣጠረው ‹ኢቲቪ› የሰጠውን ቃለ መጠይቅ ያስታውሷል) የፈተናው ወረቀትን አውጥተው በፉክክር በአካባቢያቸው ለሚገኙ ተማሪዎች ማሠራጨታቸው የሚገርም አይሆንም፡፡

3ኛ/ በአ.አ. ዩኒቨርስቲም ሆነ በየክፍላተ ሀገራቱ የሚገኙ ‹ዩኒቨርስቲዎች› ያሉ ‹አካዳሚ ሴኔቶች/ቦርዶች› ተወካዮች ባመዛኙ አገዛዙ የመደባቸው ታማኞች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ አሁን የተደረሰበት ውሳኔ በየሴኔቶቹ ውይይት የተደረገበት ስለመሆኑ ባይታወቅም (ቢደረግበትና የተለየ ሃሳብ በድፍረት የሰነዘሩ ጥቂት ግለሰቦች ቢኖሩ እንኳን የሚመጣ ለውጥ ስለማይኖር)፣ ውሳኔው የፖለቲካ መሆኑ ግን ጥርጥር የለውም፡፡

3.1/ እንኳን በየክፍላተ ሀገሩ ያሉ ‹ዩኒቨርስቲዎች› አ.አ. ዩኒቨርስቲን ለሚያውቅ ሰው የመኝታ ክፍሎቹም ሆኑ የመመገቢያ አዳራሾች ተፈታኝ ተማሪዎችን ለማስተናገድ በቂ አይደሉም፤ ከሁሉም በላይ የመጸዳጃ ቤቶቹን ይዞታ ለሚያውቅ (አብዛኞቹ የተበላሹ፣ የውኃ አቅርቦቱ አስተማማኝ ያልሆነ) ከብዛታቸው አንፃር ልጆቹን በበሽታ ሊጨርሷቸው አስበዋል የሚያሰኝ ነው፡፡ እውን በአ.አ. ዩኒቨርስቲ ድንኳን እስከመትከል ያደረሳቸው የፈተናው ስርቆት ጉዳይ አሳስቧቸው ነው?

3.2/ በዚህ አስተያየት በዋናነት ላተኩርበት ያሰብሁት አሳብ፣ እንኳን ለብሔራዊ ፈተና፣ ተማሪዎች ለማናቸውም ፈተና ሲቀመጡ የሚፈጠሩ የፍራቻና የመረበሽ ስሜቶች አሉ፡፡ ድንገት ከለመዱትና ከሚያውቁት የመማሪያ ቦታ አዲስ አካባቢ መሄዱ፣ በአንድ መኝታ ክፍል ውስጥ ከሚያውቋቸውም ሆኑ ከማያውቋቸው ተማሪዎች ጋር ባንድነት እንዲያድሩ ሲደረጉ የሚፈጥረውን ተጨማሪ ጫናና ጭንቀት ማሰብ የሚከብድ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ፈተና በሚወስዱበት ዕለት ወላጆች (ዐቅም ያላቸው/የሌላቸው) ለልጆቻቸው ምግብ ምን ያህል እንደሚጨነቁ እናውቃለን፡፡ ታዲያ (ፈተናው በሚሰጡበት ዕለታት ጥራት ያለው ምግብ ለማቅረብ ታስቦ ካልሆነ በቀር) ያልለመዱትንና በጥራት ጉድለቱ የማይታማውን የዩኒቨርስቲ ምግብ እንዲበሉ ማድረግ ሕማም ቢያስከትልባቸው ሌላ እንቅፋት አይሆንም ወይ? ይህ የሚያሳየው አገዛዙም ሆነ ‹አካዳሚክ ሴኔቶቹ› ለልጆቹ ደኅንነትና በተረጋጋ አእምሮ ለፈተናው ዝግጅ እንዲሆኑ ያሰቡ አለመሆኑን ነው፡፡ 

    እነዚህ ልጆች በተበላሸው የትምህርት ሥርዓትም ቢሆን 12 ዓመታት ደክመዋል፤ ወላጆችም ዐቅማቸው በሚፈቅደው መጠን የልጆቻቸውን ፍላጎት አስቀድመው ብዙ ኢንቨስት ማድረጋቸው ልጆችን የሚያሳድግ ሁሉ በሚገባ የሚረዳው ነው፡፡ አገዛዙና በሚመለከተው ተቋም ያስቀመጣቸው ሰብእናቸውን ያጎደፉ ግለሰቦች ምክንያት በተፈጠረ ችግር እነዚህ ልጆችና ቤተሰባቸው አላስፈላጊ ዋጋ የሚከፍሉበት ምክንያት በየትኛውም መመዘኛ ሲታይ ተቀባይነት የለውም፡፡

 3.3/ ዩኒቨርስቲዎቹ ለተወሰኑ ቀናት ለቅድመ ዝግጅትም ሆነ ፈተናው ለሚቆይባቸው ቀናት መዘጋታቸው በየዩኒቨርስቲው የሚገኙ ተማሪዎችን መርሐ ግብር ማቃወሱና መምህራንም ሆኑ የአስተዳደር ሠራተኞች ከሥራ ውጭ በመሆናቸው ውሱን በሆነው የአገር ሀብት የሚደርሰውን ጥፋትና ብክነት ለማስተዋል የፈለገ አካል ያለ አይመስልም፡፡ 

3.4/ ከሁሉም በላይ የፈተናዎቹን ወረቀቶች የሚያዘጋጀውና የሚያሠራጨውን አካል ወይም ግለሰብ ለመቆጣጠርና ስርቆቱን ለመከላከል/ለማስቀረት የተበጀ ሥርዓት እስከሌለ ድረስና ነውሩም አገዛዛዊ ድጋፍ ካለው (ድርጊቱ ባገዛዛዊ ይሁን የተጀመረ ነውና) ተማሪዎቹን ‹አግቶ› ፈተና መስጠቱ ስርቆቱንና ሥርጭቱን ያስቀረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡

3.5/ ባለፉት 2/3 ዓመታት ከነበረው ተሞክሮ በመነሣት የፈተናው ወረቀት ቢወጣም/ባይወጣም ተማሪዎች ውጤታቸውን ካወቁ በኋላ ምደባን በሚመለከት አገዛዙ ዓይን ያወጣ ሸፍጥ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ አ.አ. ዩኒቨርስቲ የመደባቸው ተማሪዎች ኦሮሚያ ከሚባለው አካባቢ የመጡና በጐሣ ማንነታቸው ተመርጠው የመጡት መሆናቸው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ የሚገርመው ከተጠቀሰው አካባቢ የሚመጡት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች አገዛዙ ለሚያራምደው ፖለቲካ ሲል በተረኝነት መንፈስ ስላበላሻቸውና ሳይገባቸውም ልዩ መብት እንዳላቸው ቆጥረው የተሳሳተ ግንዛቤ የያዙ በመሆናቸው ምክንያት፣ ፍላጎታቸው ሳይሠሩ ገንዘብ ማግኘት፣ ትምህርቱንም ባግባቡ ሳይከታተሉ በስርቆት ማለፍ፣ በመጨረሻም ሳይማሩ የመመረቂያ ‹ጋዋኑን› መልበስ የሚፈልጉ ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ ጠባይ አገዛዙ አ.አ. ዩኒቨርስቲ በዘረኛነት መንፈስ በመደባቸው ተማሪዎች በግልጽ የታየ ከመሆኑም በላይ በአገዛዙ የተረኛነት ችሮታ ያለ ችሎታና ብቃት የተመደቡት ተማሪዎች ትምህርቱን መቋቋም ሲያቅታቸው በየጊዜው ረብሻና አምባጓሮ መፍጠር፣ መምህራንን እና ሌሎች ተማሪዎችን ማስፈራራት የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ በዚህም አገዛዙ ለፖለቲካ ድጋፍ ሲል በዘረኛነት መንፈስ የመለመላቸው ወጣቶች በሚያሳዝን ሁናቴ በሚሠማሩበት ቦታ ዕውቀትና ችሎታ የሌላቸው፣ በሥነ ምግባር የዘቀጡና ላገር ሸክም ከመሆን አልፈው አገር የሚያፈርሱ መሆናቸው በመንግሥታዊ ተቋማት በገሃድ እየታየ ነው፡፡ 

አገዛዙ ለፖለቲካ ድጋፍ ሲል ይህንን የተበላሸ የትምህርት ሥርዓት፣ የፈተና ወረቀት ሥርቆቱንና በተማሪዎች ምደባ ረገድ በዜጎች መካከል አድልዎ ማድረጉን የሚቀጥል ከሆነ፣ አገራዊ ሀብት ማባከን ሳያስፈልገው ፈተናው ተሰርቆ ቢወጣም ምንም ቊጥጥር ማድረግ ሳያስፈልግ ማስመሰሉን ትቶ በጐሣ መሥፈርት የሚፈልጋቸውን ተማሪዎች ፈተናው ሲታረም አልፈዋል ብሎ ውጤት ቢሰጣቸው ይቀላል፡፡ የወንጀል አገዛዝ ሥርዓቱ እስካለ ድረስ ለስርቆቱና ለምደባው ጠያቂ ከሌለ ያሻቸውን ውጤት ለመስጠት ጠያቂ ከየት ይመጣል? ለሕዝብና አገር ደኅንነት ደንታ የሌለው የወንጀል ሥርዓቱ ራሱ ካልተወገደ በቀር፡፡

አገዛዙስ ተልእኮውና ዓላማው ነው፤ በአገራችን የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና አስተዳደር በሙሉ በፍራቻና በ‹እንጀራ› ሰበብ ይህንን ውሳኔ ተቀብለው ተግባራዊ ማድረጋቸው የውድቀታችንን ጥግ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ድርጊት ይመስለኛል፡፡ 

Filed in: Amharic