>

የአፍሪካው ቀንድ፣የመጪው ግዜ አለም አቀፍ የፖለቲካ መራኮቻ (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

የአፍሪካው ቀንድ፣የመጪው ግዜ አለም አቀፍ የፖለቲካ መራኮቻ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

Tilahungesses@gmail.com

ሁላችንም እንደምንገነዘበው፣ከአለም አቀፍ የመገናና አውታር እንደሚሰማው አለም የአንድ ጉልበተኛ ሀገር መድረክ መሆኗ እያከተመ ይመስላል፡፡ ባህላዊው የዲፕሎማሲ መስመር እየተዘጋ መጥቷል፡፡ አለም በምእራቡ አለም የዲፕሎማሲ ጫና ስር ብቻ መወደቋ እያከተመለት ነው፡፡ በአለም የፖለቲካ መድረክ ላይ ተገዳዳሪ የሆኑ ሀይላትም ብቅ እያሉ ነው፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች የተገኙና ጉልበት ያላቸው ሀይሎች በፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ እና መገናኛ ብዙሃን አውዶች ላይ ጫና እየፈጠሩ የሚገኙበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ በአጭሩ የቆየው የዲፕሎማቲክ መስመር እና እርዮት በአዲስ መልክ፣ በአዲስ መንገድ እየተከለሰ ይገኛል፡፡

በጉልበተኞችና በበለጸጉ ሀገራት መሃከል ያለው ከባድ ፉክክር የተፈጥሮ ሀብትን ለመቀራመት ሲሉ ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ስትራቴጂክ ወዳጅ ለማፍራትና የጂኦፖለቲካል ጥቅም የሚያስገኙ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ሲሉ የሚያደረጉት ፍልሚያ እና የረቀቀ ሴራ ሌላው የፉክክር አውድማ ሆኖ ይታያል ፡፡ (ነው ) በ20ኛው ክፍለ ዘመን አለም አቀፍ ሁኔታዎች በየግዜው የመቀያየራቸው ሁኔታ የሚያስገርም ላይሆን ይችላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ተግዳሮቶችና እድሎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከቀዝቃዛው ጦርነት ክስተት በተለየ መልኩ ዛሬ በአለም ላይ ላይ ፖለቲካዊና ርእዮታዊ ተጽእኖ እጅጉን ሰፊ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በደቡብ የአለም ክፍል በተለይም በአፍሪካ ምድር አንድ ጉዳይ ዛሬም ተጽእኖ አሳዳሪ ነው፡፡ ይህም አፍሪካ ዛሬም ዋነኛ ተቀባይ አህጉር መሆኗ ነው፡፡ አፍሪካ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የእርዳታ ጥገኛ አህጉር ናት፡፡ አፍሪካ በሰብዓዊና ቴክኒካል እርዳታ አኳያ የሌሎች ጥገኛ ናት፡፡ ለሰብዓዊ ቀውሶችና ቴክኒካል ድጋፍ በአውሮፓ በሚገኙ ሀገራትና ሌሎች ሀገራት ጥገኛ ናት፡፡ ሰለሆነም አንድ ሀብታም ሀገር በአፍሪካ ምድር በሚገኙ እና ቁጥራቸው ቀላል ግምት በማይሰጣቸው ሀገራት በቀላሉ የጦር ሰፈር ያቋቁማል፡፡ ከሃብታሙ ሀገር የሚጠበቀው ወረት መክፈልና እርዳታ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ አፍሪካ ከተጽኖ መውጣት የተሳናት አህጉር ናት፡፡

የአፍሪካው ቀንድን እንደ ጥሩ አብነት መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ይህ የአፍሪካ ክፍል የተወሳሰቡ የወታደራዊ ጦር ሰፈሮች ያሉበት ስፍራ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ የአፍሪካ ክፍል ዲጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ሱዳን በአለም ጸጥታ ጉዳይ ላይ ዋና ተዋናይ እየሆኑ ይገኛል፡፡ በተጠቀሱት ሀገራት በአለም ቱጃር ሀገራት የሚመሩ የጦር ሰፈሮች ተቋቁመዋል፡፡ በተለይም ዲጂቡቲ ከተለያዩ የአለም ክፍል የመጡ ሀገራት የጦር ሰፈራቸውን በማቋቋም በአካባቢው እየፈነጩ፣ አዛዥ ናዛዥ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል የተባበረችው አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የመካከለኛው ምስራቅና ገልፍ፣ ኤሽያ አንዳንድ ሀገራት በዲ. ጂቡቲ የጦር ሰፈራቸውን ከቆሙ አመታት ነጎዱ፡፡ ከታወቁት ሀገራት ውስጥ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ስፓኝ እና የተባበሩት አሜሪካ፣ ቱርክ ይጠቀሳሉ፡፡ ሜልቪን ( Melvin ) የተባለ የፖለቲካ ሰው በጥናቱ እንደረሰበት ከሆነ የተባበሩት አረብ ኤሜሪተስ፣ ግብጽ፣ እስራኤል፣ ሩሲያ፣ ሳኡዲአረቢያ፣ቱርክ በአካባቢው ከሚራኮቱ ሀገራት ውሰጥ የሚጠቀሱ ሲሆኑ ቃታር እና ቱርክ የሞቃዲሾን ማእከላዊ መንግስት የሚረዱ ናቸው፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የሁለቱም ሀገራት ተፎካካሪና ተቃዋሚ  የሆኑት ሳኡዲና የተባበሩት አረብ ኤሜሪተስ ሶማሌ ላንድና ፑንትላንድ ተብለው የሚጠሩትንና ከሶማሌ ለመገንጠል ፍላጎት ካላቸው የአካባቢ መንግስታት ይረዳሉ፡፡ በነገራችን ላይ በዲጂቡት የጦር ሰፈር የመሰረቱት የተባበረችው አሜሪካ፣ቻይና፣ጃፓንና የአውሮፓ ሀገራት ወደ ግጭት ስለማምራታቸው የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሁሉም እርስበርስ ፉክክር ውስጥ እንደወደቁ ግልጽ ነው፡፡ ሁሉም ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የቆሙ እንጂ ለአፍሪካው ቀንድ የሚደማ ልብ የሌላቸው ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ የአፍሪካው ቀንድ፡-

  • ለአመታት በቆየ ወታዳራዊ ግጭት ውስጥ የተዘፈቀ ነው፣
  • ቁጥሩ ቀላል የማይባል የአካባቢው ህዝብ ከቀዬው የተፈናቀለበት፣
  • የርበርስ ጦርነት የበዛበት፣
  • አስከፊ የምግብ እጥረት ያለበት፣
  • የባህር ላይ ወንብድና የተስፋፋበት የአለም ክፍል ነው፡፡ (እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1970 እስከ 1990 ዎቹ መጨረሻ  የባህር ላይ ወንብድና አስከፊ ነበር፡፡ )

በዛሬው ዘመን አካባቢው ወደ መፈረካከስ ያዘነበለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም በርካታ አለም አቀፍ የጦር ሰፈሮች በመቋቋማቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የአካባቢው ፖለቲካዊ ሁኔታ እጅጉን ተቀይሯል፡፡ ለአብነት ያህል የቀድሞዋ ኢትዮጵያ አሁን የለችም፡፡ ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሀይል ለመሆን እድሉ አላት፡፡ በተለያዩ የሶማሊያ ሀይሎች መሃከል፣ በደቡብ ሱዳን የተጀመረው የሰላም ሂደት፣ በኤርትራነ ኢትዮጵያ መሃከል የተደረገው የሰላም ስምምነት በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ሊያመጣ ያስችላል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ አዲሶቹ የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ሱዳን መሪዎች በመስቀለኛ መንገድ ላይ መገኘታቸው፣ በኢትዮጵያ እያገነገነ ያለው የውስጥ ትግል በአካባቢው ያለውን የሰላም ተስፋ የሚያሟጥጥ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር በኢትዮጵያ ምድር ከሚንቀሳቀሱ የተገንጣይ ሀይሎች ጀርባ ያሉ የውጭ ሀይሎች በአካባቢው ያለውን የሰላም ሁኔታ ከድጡ ወደማጡ ይወስዱታል፡፡ በሌላ አነጋገር በኢትዮጵያ ይህ በእንዲህ እንዳለ  የአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ህዝብ ምኞትና ፍላጎት በተጠቀሱት ሀገራት የዲፕሎማሲና ወታደራዊ መስፋፋት ምክንያት እየመከነ ይገኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የውጭ ወታደራዊ ሀይል በአካባቢው መስፋፋት የሀገራቱን ሉአላዊነት ጭምር የሚጻረር ሲሆን፣ እንደ ኢጋድ እና አፍሪካ ህብረት የመሳሰሉ የአካባቢና አህጉራዊ ድርጅቶች ላይ ያላቸውም ተጽእኖ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ዋናውና መሰረታዊ ጥያቄው ግን እነኚህ ወታደራዊ ቤዝ ያቋቋሙ ሀገራት ለምን ያህል ግዜያት በአካባቢው እንደሚቆዩ ካለመታወቁ ባሻግር ፣ የአካባቢውና አህጉራ ድርጅቶች ሚና ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡

እጅግ አነጋጋሪው ነገር በአፍሪካ ህብረት አንቀጽ 13 መሰረት የአፍሪካ ህብረት በአምስቱም የአፍሪካ ክፍሎች ቋሚ የወታደራዊ ሀይል ማቋቋም የሚችል ቢሆንም፣ በአፍሪካው ቀንድ የአለም ጉልበተኛ ሀገራት ሁሉ ተሰባስበው የጦር ሰፈር ሲያቋቁሙ ትንፍሽ አላለም፡፡

በአካባቢው ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የሚችል ሌላ ሃይልም ማስፈር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በሌላ አነጋገር እነኚሁኑ ተፎካካሪ ሀገራት ተክቶ የሚሰራ አፍሪካዊ ሀይል አሁን ድረስ አልተገኘም፡፡ አካባቢው የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የጦር ሰፈር ያቋቋሙ ሀገራት መራኮቻ ሆኗል፡፡ በአካባቢው የሰዎች ደህንነት እንዲጠበቅ ፣ ህዝቡ በእድገት ጎዳና እንዲራመድ ከተፈለገ ግን አፍሪካዊ ሰላም አስከባሪ ግድ ይላል፡፡

በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ነሃሴ 27 2019 የተባበረችው አሜሪካና ፈረንሳይ ወታደራዊ ኤክስፐርቶች ጉብኝት አድረገው ካበቁ በኋላ ባደረጉት ጥናት እንደተረጋገጠው ለጸጥታ ጥበቃ በሚል በአፍሪካ ከ34 በላይ ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች ይገኛሉ፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ከ7000 በላይ ወታደሮቿን በአፍሪካ ያሰፈረች ሲሆን ፈረንሳይ ትከተላታለች፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ዋነኛ የጦር ሰፈር ማእከል የሆነችው ዲጂቡቲ ስትሆን ከአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ በመያዝ ከ300 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በየአመቱ ትሰበስባለች፡፡ በነገራችን ላይ ወታደራዊ የጦር ሰፈር የሚገነቡ ሀገራት ዳጎስ ያለ ገቢ ስለሚያስገቡ ሀገራት እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ እየቆጠሩ የመምጣታቸው ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ እያደገ የመጣው የጦር ሰፈር እና የባህር ወደብ መስፋፋት ለሀገራቱ ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆንም ፣ ግልጽነት የጎደለውና የጦር ሰፈር ላቋቋሙት ሀገራት ጥቅም ብቻ ከሆነ መዘዙ ብዙ ነው፡፡

የአፍሪካው ቀንድ፣ ኢጋድና የአፍሪካ ህብረት  በአፍሪካ አፈር ላይ በአካበቢው ታላቅ የጦር ሰፈር ከመሰረቱት አፍሪካዊ ካልሆኑ ሀገራት ምን ይማራሉ ? እስቲ በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል በአፍሪካ ምድር የተቋቋመ የጦር ሰፈር መጠናትና መተንተን ያለበት ከአፍሪካ ኢኮኖሚያዊና ጸጥታ ወይም ደህንነት ጥቅም አኳያ ከመሆኑ ባሻግር የጦር ሰፈር ያቋቋሙ ሀገራት አላማ መጠናት አለበት፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው እውነታ ባሻግር የአፍሪካ ሀገራት የአከባቢ ህብረት በመፍጠር የባህር በራቸውን በትብብር በማስከበር የኢኮኖሚ ጥንካሪያቸውን ማጎልበት ይገባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ በአለም ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን አፍሪካውያን የህብረት ፍልስፍና ቢከተሉ መልካም ነው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ አሊያ የአለም ጉልበተኞች መጫወቻና መራኮቻ መሆናችን አይቀሬ መራር እውነት ነው፡፡ በተለይም የቀይ ባህር አካባቢ በአለም የተፈጥሮ ሀብት ጥማተኞች አይን ውስጥ የወደቀ ስትራቴጂክ ስፍራ በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ የመሰሉ ትልልቅ ሀገራት የውስጥ ቅራኔአቸውን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት አንድነታቸውንና ትብብራቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ በሰለጠነ መንገድ መገላገል ይኖርባታል፡፡ የአካባቢው ባለወረቶችም  በሀገራቸው ላይ መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ መበረታታት አለባቸው፡፡

በመጨረሻም የአፍሪካ ወኪሎች ባለ መሰልቸት ህብረታቸውን ማጠንከር ይገባቸዋል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ በተለይም የቀይ ባህርን ማስተዳደር፣ የቀይ ባህርን ጸጥታ ማስጠበቅ የሌሎች አፍሪካዊ ያልሆኑ ባእድ ሀይሎች አይን ካረፈበት ወዲህ ፣ እነኚሁ የጂኦ ፖለቲካ ሃይሎች ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ሲሉ የሚያደርጉት ሴራ እየባሰበት በመምጣቱ፣ የጎሳ ፖለቲካ በሚፈጥረው ልዩነት የተነሳ የሚቀሰቀሱ ግጭቶች በመበርከታቸው ምክንያት የአፍሪካው ቀንድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዝብር ወጣቶች እና ንጹሃን ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ሰላም፡፡

  

Filed in: Amharic