ቴዎድሮስ ካሳሁንን በፍቅር እስከ መቃብር ውሰጥ
ፍሬድሪክ ኒቼ “ሙዚቃ የሌለበት ሐይወት ሥህተት ነው” ሲለን ሔንሪች ሄይን ደግም “ቃላት ካቆሙበት ሚዚቃ ይጀምራል” ይለናል። ሁለቱም የሙዚቃን አስፈላጊነት በተለያየ መንገድ ነገሩን። ለእኔ ደግሞ ሙዚቃ ከህመም ፈዋሽ መድሃኒት ነው። እንደ ቴዎድሮስ ካሳሁን አይነቶች ሲዘፍኑት ደግሞ ሙዚቃ ከምንም፣ ከማንም በላይ ይሆናል። የሥነ ፅሑፍ አድባር የሆኑት ሃዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብርን ፅፈው አስደምመውን ሳያበቁ የሙዚቃው ንጉሥ ቴዎድሮስ ካሳሁን ” ጎጃም ኑራ ማሬ” ሲል ደስታችንን እጥፍ አድርጎታል። ዘፈኑ ለሕዝብ ጆሮ ከበቃ የሰነበተ ቢሆን ዛሬም እንደ አዲስ አዳምጠው ይዣለሁ።
ባሻዬ! እስኪ ሰምቼ የተሰማኝ ላጋራህ።
የፀበል ዳር እንኳይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል
ተሸፍና ዋርካ ክልሏት የዛፍ ጠል።
ሰብለወንጌል (የጎጃምን ሴት ወክላ) በፀበል ዳር እንኳይ ተወክላለች።እንኳይ በበረሃ አካባቢ የሚበቅል ፍሬ ነው። እረኛ ሆነን ፈልገን እንመገበው ነበር። ጣዕሙ ለትንግርት ነው። ቴዎድሮስ የፀበል ዳር እንኳይ ሲል ማንም የማይነካት ለማለት ነው። የለመነ፣ የተማፀነ፣ ደጅ የጠና ሁሉ የማይዘግናት የጎጃም ሴት ፀበል ዳር ባለ እንኳይ ተወክላለች።ጉሩም ነው።
የት ነበር ያረኩት ቀፎዬን ስል ኖሬ፣
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኑራ ማሬ።
በዛብህ የሰብለወንጌል ፍቅር ሲበረታበት ፍለጋ ወደ ጎጃም ነጎደ። “ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኑራ ማሬ” የሚለው ስንኝ ሁለት ነገር ይነግረናል። የመጀመሪያው ጎጃም የማር አገር በመሆኑ ንቦች ሁሉ መንገዳቸው ወደ ጎጃም ነው የሚለውን ሲሆን ሁለተኛው በዛብህ አበባ ለመቅሰም ወደ ጎጃም የሚኼዱ ንቦችን ሲመለከት ፍቅረኛው ( ሰብለወንጌል ) ጎጃም ውስጥ እንደሆነች ተረዳ። “ጎጃም ኑራ ማሬ” በሚለው ሐረግ ውስጥ በዛብህ “ማሬ” የሚላት ሰብለወንጌልን ነው።አንድም ጣፋጭ ሁለትም መድሃኒት ናት ለማለት ተፈልጎ ነው።
ብራናዬ አንች የልጅነት ጓዴ፣
ተረሳሽ ወይ የእሳት ዙሪያው ተረት ባንዴ።
በዚህ ግጥም ውስጥ በዛብህ ሰብለወንጌልን ያስተምር በነበረበት ወቅት የነበረውን ሳቅ እና ጨዋታ ወደኋላ ተጉዞ ያስታውሳል። ትዝታዬን ረሳሽ ወይ ሲል በፍቅር ይጠይቃል። ለነገሩ ግን ትዝታ ምኑ ይረሳል?
ፍቅር የበዛበት ዘልቆ ከማንኩሳ
መንናለች ቢሉኝ ቢጫ ልብስ ለብሳ
ሸዋ ከሩፋኤል ስጠብቃት ኖሬ
ንቤ ገዳም ገብታ ጎጃም ኑራ ማሬ
ቴዲ ቅኔ ያውቃል ሳይሆን ራሱ ቅኔ ነው። “ፍቅር የበዛበት” የሚለው በሰብለወንጌል ፍቅር ክንፍ ያለውን የማንኩሳውን በዛብህን ነው። በዛብህ ትመጣለች ብሎ በጉጉት ሲጠብቃት የነበረችው ሰብለወንጌል “የውሻ ሽታ” ብትሆንበት በፍለጋ ምድሩን አሰሰው። ማሬ ሲል የሚጠራትን ሰብለን በመፈለግ ሂደት በሽፍታዎች ተደብድቦ ከአንድ ሴት ተጠግቶ በአንድ በኩል ቁስሉን በሌላ በኩል የሰብለን የፍቅር ርሃብ ሲያዳምጥ ሰብለ የምልኩስና ልብስ ለብሳ አገኛት። በሳቅ እና በሰቀቀን መሐል እንዳለ ነፍሱ አለፈች። ልብ ይሰብራል። የልብን መሻት ማጣት ህመም ምን ያኽል ይሆን? ፈልጎ በማጣት ውስጥ ያለው ቅጣት ምን ይኾን?
ያሳደገኝ ደብር የሥለት ልጅ ሆኜ
ካሕን እንዴት ይፍታኝ ያንች እስረኞ ሆኜ።
በዛብህ የሥለት ልጅ ነው።የበዛብህ እናት ለቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግል ሰጥታዋለች ። ይኼንን አፍርሶ ነው ከሰብለወንጌል ጋር በፍቅር የወደቀው። በዛብህ “ካሕን እንዴት ይፍታኝ ያንች እስረኛ ሆኘ” በሚለው ስንኝ ውስጥ ሰራሁት ለሚለው የፈጣሪ ሕግ መተላለፍ “ማንኛው ካሕን ይፈታኝ ይሆን (ከፈጣሪ ያስታርቀኝ)?” ሲል አጥብቆ ይጠይቃል። በሌላ በኩል ከፍቅርሽ እስር ቤት እንዴት ልውጣ ማለቱ ነው? ለነገሩ ግን የፍቅር እስር ቤትን ሰብሮ መውጫው ቁልፉ ምንድን ነው?
በጊዜ ተደፋ የቀለሙ ቀንዴ
የኔ ፊደል ማወቅ ካንች አዳነኝ እንዴ?
ለካ ሰው አይድንም በደገመው መፅሐፍ
እንደሰም አቅልጦ ፍቅር ካ’ረገው ጧፍ
በዛብህ ፊደል መቁጠሬ፣ ቅኔ መማሬ፣ መፅሐፍ ማንበቤ ማሬ ሲል የሚያቆላምጣትን( ሰብለን) የግሌ ለማድረግ ካላስቻለኝ ምን ሊጠቅም እያለ መማሩን ይረግማል። ቴዎድሮስ የፍቅርን ኃያልነት ሲገልፅ በፍቅር የሰከረን ድግምት አያድነውም ይለናል። እውነት ነው። በሌላ በኩል በዛብህ የቅኔ ትምህርቱን ዳር ሳያደር (ሳይጨርስ) በሰብለ ፍቅር ተነድፎ መቅረቱን ሲገልፅ “በጊዜ ተደፋ የቀለሙ ቀንዴ” ይላል።
ወንጌል መነኮሱ በልጅነታቸው
ማር እስከጧፍ ሆኖ ዓለም ቢነዳቸው።
ቴዲ “ወንጌል መነኮሱ በልጅነታቸው” ሲል በአንቱታ የሚያቀብጣት የቀድሞ ፍቅረኛውን ሰብለወንጌልን ነው።በጎጃም ባህል መሰረት መነኩሴ አንቱ እንጅ አንተ ወይም አንቺ አይባልም።በሁለተኛው ስንኝ ላይ”ማር እስከጧፍ ሆኖ ዓለም ቢነዳቸው”ሲል ሰብለወንጌልን ለምንኩስና ያበቃቸውን ምክንያት ይነግረናል።ሰብለወንጌል ከበዛብህ መጥፋት በኋላ ዓለምን ንቃለች። በዚህም ምርጫዋ መገደም ሆነ።
አንቺ የፍቅር ፅጌ ውድነሽ በጣሙን፣
መምጣቴ ነው በቃ እኔ አቃተኝ አሁን።
እጅግ ልብ በሚሰብር አኳኋን በዛብህ ተስፋ ቆርጧል። ሟች እናቱን ( ውድነሽ በጣሙን) አልቻልሁም ጥሪኝና ልምጣ ሲል ይማፀናል። ለነገሩ በዛብህ በዙሪያው ሰው የለም። አባቱም እናቱም የሉም። ሰብለወንጌልን የማግኘት ዕድሉ በዘመኑ የፊውዳል ሥርዓት የመደብ ልዩነት ምክንያት የተመናመነ መሆኑን ሲረዳ ነው ይኼንን ማለቱ።
ዲማ ጊዮርጊስ ወይ ማንኩሳ
ያች ወንጌል ብጫ(ቢጫ) ለብሳ
ከ’ንግዲህማ ቆብ አስጥዬ
እንዳልወስዳት አባብዬ
ሰብልዬ ሆና እማሆዬ
ባሻዬ! ቴዲ ልዩ ክስተት ነው። ቢጫ ለብሳ የመነኮሰችውን ሰብለወንጌልን (ያች ወንጌል ይላታል) ቆብ አስጥሎ ሊያስወጣት ቢያብም እማሆይ መሆኗን በተረዳ ጊዜ ተስፋው እንደ ጠዋት ጤዛ ሲረግፍ ይታያል። ለዚህም “እንዳልወስዳት ቆብ አስጥዬ፥ ሰብልዬ ናት እማሆዬ” ሲል በሁለት ልብ ይቆማል። ዓለም በቃኝ ብሎ የገደመን ሰው ቆብ አስጥሎ ( ከምንኩስና ሕይወት አስወጥቶ) ለራስ የማድረግ ምኞት ፍቅር ምንኛ ኃያል መሆኑን ያሳያል። በመጨረሻም ቴዲ የመፅሐፉን ደራሲ ሃዲስ አለማየሁ እና የመፅሐፉን ተራኪ ወጋዬሁ ንጋቱን እንዲህ ሲል የሥራው (የሙዚቃው) መታሰቢያ መሆናቸውን ይገልፃል።
አዲስአለም ሆነ ባንችልም ስል ወግአየሁ
እድሌ ሆነና ባጣሽ ተሰቃየሁ።
“አዲስዓለም” ማለቱ ሃዲስ አለማየሁን ሲሆን “ወግአየሁ” ማለቱ ወጋዬሁ ንጋቱን ማውሳቱ ነው። በአሁኑ ሰዓት ደራሲውም ተራኪውም በሕይወት የሉም። ሥራቸው ግን ሕያው ነው።
በወጋችን መሐል በዘፈኑ ውስጥ የሰብለወንጌልን ሚና ይዛ የምትተውነው የቴዲ ሚስት (አመለሰት ሙጨ) ናት።በጠፍር (የቆዳ ገመድ) ታስራ መታዬቷ ድሮ ሰብለወንጌልን ከበዛህ ለመነጠል አባቷ ያስሯት የነበረውን ለመተዘት ነው።
ባሻዬ! ሙዚቃ ስማ። ሙዚቃ የበሽታዎች ሁሉ ፍቱን መድሃኒት ነው። ሙዚቃ ስትሰማ ግን ምረጥ። ለጊዜው የቴዲን ” ጎጃም ኑራ ማሬ” ጋብዠሃለሁ።