እናትና ልጅ የሁለት ስርአት ሰለባዎች…!
ሆህተብርሀን ጌቱ
እርጅና ቢጫጫናቸውም ጨዋታቸው ለዛ አለው። ከእርጅናው ይልቅ የልጃቸው ጉዳይ አሳስቧቸዋል። ውስጣቸው እንዳዘነ ከገፅታቸው ላይ ይነበባል። ለውጡ እንደ መጣ ሰሞን “ዶ/ር ዓቢይን በክፉ ሲያነሱብኝ ይከፋኝ” ነበር ይላሉ። “አሁን ምን አድርጓችሁ ነው በክፉስ የምታነሱት?” እያልኩ ከሰዎች ጋር እጣላ ነበር፣ በልጄ ሲመጣብኝ ግን ምን ነካው ደህና ሰው መስሎኝ እያልኩ የሚናገረውና የሚሰራው ሲጋጭብኝ ሰዎች በክፉ የሚያነሱት እውነት ኖራቸው ነበር እንዴ እያልኩ መጠራጠር ጀመርኩ። ብጠራጠርስ ይፈረድብኛል? በእኔ ልጅ የደረሰው በእናንተስ ላይ ቢደርስ ከእኔ የተለየ ሀሳብ ይኖራችኋል? እስኪ ፍረዱ!!
ልጄ ተመስገን እልኸኛ እንደሆነ አውቃለሁ። ከሌሎቹ ልጆቼም በእልኸኝነቱ ለየት ያለ ነው። የፈለገ ይሁን፣ ምንም ዓይነት ባሕርይ ይኑረው ግን አገሩንና ሕዝቡን አይዋሽም። ስለዚህ ባሕርዩ እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ። ምናልባት ከመንግሥት ጋርም ያጋጨው ይኸው አቋሙና እምነቱ ሊሆን ይችላል። ግን መንግሥት ሆደ-ሰፊ ሊሆን ይገባው ነበር ይላሉ ወ/ሮ ፋናዬ። ያገራችን መሪ ዶ/ር ዓቢይ “የኢትዮጵያ እናቶች ይጸልዩልኛል” እያሉ ሲናገሩ አዳምጫለሁ። እኔም ከኢትዮጵያ እናቶች አንዷ ነኝ። “አልዋሽህም ልጄ በወቅቱ እርሳቸውን ምንም አይንካቸው ብዬ እኔም ስጸልይላቸው ነበር። አሁን በጸሎቴ እንዳልቀጥል ልጄ በመታሰሩ ተከፋሁ። ከልጄ እርሳቸውን እንዳላስቀድም ተቸገርኩ። ይህን ችግር ደግሞ ልጅ ያላቸው እናቶች ሁሉ ያውቁታል። ጸሎቴን እንዳላቋርጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ታሳዝነኛለች እያሉ ለዛ ያለው ንግግራቸውን አወጉልኝ።
የጭውውቱ ባለቤት ወ/ሮ ፋናዬ እርዳቸው የጋዜጠኛ ተመስገን ወላጅ እናት ናቸው። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጀሙ ኮንዴሚኒዬም ይኖራሉ። በጭውውታችን መካከል አሰብ ያደርጉና መሬት መሬት እያዩ በዓይናቸው ዕንባ ሲሞላ ከገፅታቸው ላይ ይነበባል። ኃዘናቸውንና ትካዜያቸውን ዋጥ ያደርጉና ደግሞ በመካከሉ ቀልድ እየቀላቀሉ “ዛሬ በጾም ቀን የመጣኸው በሽሮ ተስተናግደህ ልትሄድ ነው” ብለው ቆንጆ የሽሮ ምሳ ተጋበዝኩ። ሽሮውም፣ ቡናውም ከእርሳቸው ለዛ ያለው ጨዋታ ጋር ተዳብሎ የተዋጣለት ነበር። በልጃቸው ምክንያት እርሳቸውንም ማወቅ በመቻሌ ደስ አለኝ። ብዙውን ጊዜ የእንግዳ አስተነጋገድ ባሕላችን ከሥጋ መስተንግዶ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የወ/ሮ ፋናዬን አባባል እረዳቸዋለሁ። እኔ ደግሞ ጥሎብኝ ይሁን አስተዳደጌ ሽሮ እወዳለሁ። እናም የሽሮውን መስተንግዶ ወደድኩላቸው። ልጃቸው ተፈቶላቸው አሁን ፅልመት የለበሰው ፊታቸው በደስታ ፈክቶ ማየት እንዴት ይናፍቃል መሰላችሁ? በዚያ ዕድሜያቸው የእናትዮዋ የሞራል ልዕልና ሲገርመኝ ልጃቸውን በቂሊንጦ እሥር ቤት ተገኝተን ስንጎበኘው ደግሞ ተሜን ድሮ ከምናውቅበት አይበገሬ አቋሙ ንቅቅንቅ አላለም። በነበረው ብረት አቋሙ እንደጸና ነው። አይበገሬው የፍትሕና የዴሞክራሲ ሐዋርያ!
አንድ ሰው ሲታሰር የሚጎዳው ታሳሪው ብቻ አይደለም። መላ ቤተሰቡ አብሮ ይታሰራል። የዓላማ ደጋፊው ሁሉ ይጨነቃል። ተመስገን “ወንጀል” ሰርቶ ከሆነ ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም። ሕግ ካለ እንደ ማንኛውም ሰው ከሕግ አያመልጥም። በሚሰራው የነፃ ፕሬስ ተግባር የሕግ አንቀጾችን የተላለፉ የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ማንኛችንም እርግጠኞች አይደለንም። አብዛኛዎቹ የፍትሕ መፅሔት ዕትሞች በእጃችን ይገኛሉ። የነፃ ፕሬስ መርህን የተከተሉ ርዕሰ-አንቀጾች፣ መጣጥፎች፣ ሐተታዎች ወዘተ… መረጃን ተንተርሰው ለንባብ ሲቀርቡ ተመልክተናል።
በእርግጥ መንግሥት የሚያይበት መነፅር ሊለያይ ይችላል። የፈለገ ይሁን ግን በዚች አገር የፍትሕና የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማምጣት እስከተፈለገ ድረስ ያለ ነፃ ፕሬስ መኖር አይታሰቤ ነው። “ፕሬስ አራተኛው መንግሥት ነው” እየተባለ የሚነገረው አባባል በተግባር ተተርጉሞ የምናየው ጋዜጠኞችን እንደ ጥጃ በማሰር- በመፍታትና በማሸማቀቅ ሳይሆን መንግሥትም፣ ጋዜጠኞችም ለሕግ ተገዥ ሆነው የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መገንባት ስንችል ብቻ መሆኑን አምኖ መቀበል ግድ ይላል። አልያ ስለ ፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ማውራቱ ከንቱ ነው። የማይጨበጥ ጉምና ሲነጋ ትርጉም- አልባ ቅዠትም ይሆናል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ትናንትም በወያኔ ዘመን የሚያምንበትን እውነት እየጻፈ እውነትን መዘገቡ እንደ ወንጀል ተቆጥሮበት በተደጋጋሚ ሲታሰር ሲፈታ መኖሩን እናውቃለን። የዛሬውም ሥርዓት በትሩን አሳርፎበታል። ስለ ለውጥ መኖር ሲወራ በእንደነ ተመስገን ዓይነት ሰዎች ላይ የሚደርሰውን አለ-አግባብ እሥር ስንመለከት ደግሞ ሁሉም ግራ ያጋባል። በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ቀጠሮ በ 10,000 ሺ ብር ዋስ እንዲፈታ ፍርድ ቤት ወስኖ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። ከዚያም በሌላ የተላለፈ ቀጠሮ በ መቶ ሺ ብር ዋስ እንዲፈታና ጉዳዩን ውጭ ሆኖ እንዲከታተል ፍርድ ቤት ወስኖለት ነበር። አሁንም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ በቂሊንጦ እሥር ቤት ሕይወቱን እየገፋ ይገኛል። ፍርድ ሰጭ አካላትና አስፈፃሚ አካላት በትዕዛዝ ሰጭነትና የአልቀበልም መንፈስ በእምቢተኝነት እስከ ተፋጠጡ ድረስ መንግሥታዊ ስርዓቱ ሕመምተኛ ስለ መሆኑ አመላካች ነው።
ቀጣዩ ቀጠሮም በመጭው ሀሙስ ጥቅምት 10 ቀን 2015 እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም የቀጠሮ ቀን ጋዜጠኛ ተመስገን ተፈቶ የምሥራች የምንሰባት ቀን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። ፍርድ ሰጭውና አስፈፃሚ አካላቱም ለሕግ የበላይነት ተገዥ ሆነው ሊሰጥ የሚችለው ብይን በተግባር የሚተረጎምበት አሠራር ይናፍቀናል። እውነትን መዘገብ ወንጀል አይደለም። በተለይ በተለይ ስሜን ዕዝን በውድቅት ሌሊት ከጨፈጨፈ ኃይል ጋር መንግሥት ለመደራደር ሽር-ጉድ እያለ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ስለ መከላከያ ጻፈ ተብሎ ጋዜጠኛውን መቀፍደድ ለሰሚው ሁሉ ግራ ያጋባል። ፍትሕና የዴሞክራሲ ሥርዓት በኢትዮጵያችን ይንገሥ! የሕግ የበላይነት ይስፈን! የሕግ ተጠያቁነት ለሁሉም! ፕሬስ የአንድ ሀገር ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ነውና የፍትሕ መፅሔት ማኔጅግ ዳይሬክተር የተመስገን ደሳለኝን ብዕር አስሮ ስለ ፍትሕ- ስለ ነፃ ፕሬስ ዲስኩር ማውራት ግራ ያጋባልና የታሰረ ብዕር ይፈታ!!
ጽሁፌን ሳልደመድም በተመስገን ዙሪያ አንድ እውነት መናገር የሚያስፈልገው ተሜ በሚያቀርባቸው በመረጃ የተሞሉ የኅያሴ ፅሁፎች መንግሥት ለእርምት እርምጃ ቢጠቀምባቸውና የጎበጠውን ለማቀናት ቢፈልግ ኖሮ፣ የሚታይበትን መንግሥታዊ ሕጸጽ እንደ መስተዋት ሆነው ስለሚያሳዩ የበለጠ ተጠቃሚው መንግሥት ይሆን ነበር። አልተገናኝቶም!