>

ተፈትኖ በወደቀ የዘውግ ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ አትፈወስም! (ዮሀንስ መኮንን)

ተፈትኖ በወደቀ የዘውግ ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ አትፈወስም!

ዮሀንስ መኮንን


ይህንን ጽሑፍ እንዳጋራ ያነሳሳኝ ሰሞንን የብልጽግና ሹማምንት በበደል ትርክት ተጠንስሶ ዘውጌ ማንነት ላይ የተንጠለጠለውን “የፌደራል ሥርዓት” ከችግራችን መውጪያ “መድኃኒት” አድርገው ሲሰብኩ በማየቴ ነው።

ፌደራሊዝም የሚለው ቃል ሥረወ ቃሉ የላቲኑ ፌደስ (Feodus) ሲሆን ትጓሜውም ‹‹ቃል ኪዳን›› ማለት ነው፡፡ (እንደ አላዛር እና ኦስተሮም ጥናት) የፌደራል ሥርዓት በዓለማችን ከተዋወቀ 230 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን በአሜሪካ በ1789፣ በስዊዘርላንድ በ1848፣ በካናዳ 1867፣ አውስትራሊያ ከ1901 ጀምሮ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ ካናዳዊው የፌደራሊዝም ተመራማሪ ዋትስ “Federalism, Federal Political Systems, and Federations” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት ‹‹በምሥራቅ የአውሮፓ ሀገሮች እና በሦስተኛው ዓለም ሀገሮች ፌደራሊዝም እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል›› ብለዋል (Watts1998)፡፡ ሽናይደር የተባሉ ሌላ አጥኚ በበኩላቸው የዩጎዝላቪያን እና የታላቋ ሶቪየት ኅብረት መፈረካካስ ምንጩ የተከተሉት የፌደራል ሥርዓት መሆኑን በጥናታቸው ሞግተዋል (Snyder 1999)፡፡

ሶቭየት ኅብረትና ዩጎዝላቪያ ውስጥ የነበረው ፌዴራሊዝም ከላይ ወደታች የተጫነ እንጂ የህዝቦች ቃልኪዳን ውጤት አልነበረም። ለዚህ ነው ሁለቱም ፈራርሰዉ ለብዙ ጥቃቅን ሉዓላዊ መንግሥታት መፈጠር ምክንያት የሆኑት።

በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ፌደራሊዝም ሥርዓት በሁለት መንገዶች ሊዋቀር ይችላል፡፡ (ጋሽ ኤፍሬም ማዴቦ ‹‹አብረን እንኑር››  እና ‹‹ሀገር እናድን›› ሲል ይፈታቸዋል) (Stephan 2001)

የመጀመሪያው አማራጭ ሉዓላዊ የሆኑ ሀገሮች በደኅንነት ወይንም በሌሎች ገፊ ምክንያቶች ወደ አንድ ስብስብ ለመምጣት (Coming Together) ሲወስኑ የሚፈጠር ሲሆን ሁለተኛው በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች መካከል የብሔር ወይንም የቡድኖች ፍላጎቶችን ለማቻቻል ሲባል የሚፈጠር  ነው፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አሠፋ ፍሰሐ “Federalism and the Accommodation of Diversity in Ethiopia: A Comparative Study’’  በሚል ርእስ ባሳተሙት ጥናት እንደሚጠቁሙት የአፍሪካ ፌደራሊዝም ቅኝ ግዛትን ተከትሎ አፍሪካውያንን ከፋፍሎ ለመግዛት የመጣ ሥርዓት ነው፡፡ ጋናዊው ክዋሜ ንኩሩማን የመሰሉ የነጻነት ታጋዮች ፌደራል ሥርዓትን አምርረው የተቃወሙት በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡

በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጡ የመረጡት የአስተዳደር ዘይቤ በቅኝ ገዢዎች የተጫነባቸውን በዘውግ ማንነት (በብሔር) ላይ የተዋቀረ ፌደራሊዝም አሽቀንጥው በመጣል አንድነታቸውን ለማጠንከር አሀዳዊ ሥርዓት ማስፈንን መርጠዋል፡፡ ዛሬም ድረስ በርካታ አፍሪካውያን “ፌደራሊዝም ጠባብ ብሔርተኝነትን ያስፋፋል” በማለት አምርረው ይቃወሙታል። (Kimenyi 1998)

ቅኝ ገዢዎች ለአፍሪካ ምንም ጥሩ ነገር ይዘው አልመጡም፡፡ ጥሩ ነገር ካመጡም ለነሱ በጣም ጠቅሟቸዋል ማለት ነው፡፡ ፌዴራሊዝምን የአፍሪካን ሕዝብ ከፋፍለው ለመግዛት ተጠቅመውበታል፡፡

በናይጄሪያ የፌደራል ሥርዓት ላይ ጥናት በማቅረብ የሚታወቁት J.Isawa Elaigwu “ፌደራሊዝም በአፍሪካ ግጭት ማርገቢያ ሳይሆን የግጭት መንስኤ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች በሕገመንግሥቶቻቸው የፖለቲካ ፓርቲን በብሔር ማደራጀትን ክልከላ እስከመጣል መድረሳቸው ነው፡፡ ይህም ሆኖ ሀገራችንን ኢትዮጵያ ጨምሮ 10 ያህል የአፍሪካ ሀገሮች የፌደራል ሥርዓትን ተከታይ ሲሆኑ የተቀሩት ከ40 በላይ ሀገራት አሀዳዊ ሥርዓት ተከታዮች ናቸው፡፡

የደርግ ሥርዓትን በማስወገድ መንበረ ሥልጣኑን የወረሰው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ የተከተለው ዘውግን (ብሔርን) መሠረት ያደረገው የፌደራል ሥርዓት አወቃቀር ምንም እንኳን “ለህዝቦች ሰላም እና አንድነት ያመጣል” ቢባልም በተግባር እንደታየው ባለፉት ሠላሳ ዓመታት የግጭት እና የቀውስ ምንጭ ሆኗል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው የፌዴራል ሥርዓት አንደኛ በህሕዝብ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በጉልበትና በኃይል የተጫነ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ ሁለተኛ መሠረቱ በየትም ያልታየ ብሔር እና ቋንቋ ብቻ ነው፣ ሦስተኛ የፌዴራል ክልሎቹ ሉዓላዊነት የተረጋገጠ አይደለም፡፡ አራተኛ- ከዲሞክራሲ ጋር የማይተዋወቅ ፌዴራሊዝም ነው።

በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ይተተበተበውን የዘውግ ፌዴራል ሥርዓት ነው እንግዲህ ሰሞኑን “ኢትዮጵያን ከግጭት የሚያወጣት ክትባት ነው” እያሉ የሚያንቆለጳጵሱት። ይህንን የፌደራል ሥርዓት ታቅፈን የግጭት እና የድህነት ምንጭ መሆኑ ሊገርመን አይገባም፡፡

Monahan እና Biyant የተባሉ አጥኚዎች በጥናታቸው እንደሚገልጡት በዓለማችን ከሚገኙ ከ89 ሕገ መንግሥታት መገንጠልን የሚፈቅዱት ሰባቱ (ኦስትሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ፣ ሲንጋፖር፣ ቅዱስ ክርሰቶፈርና ኔቪስ፣ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እና ቸኮዝሎቫኪያ) ብቻ ሲሆኑ ከሰባቱ ሁለቱ ሀገሮች (ሶቪየት እና ቸኮዝሎቫኪያ) ብትንትናቸው ወጥቷል።

ከላይ የጠቀስኩት የተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አሠፋ ፍሰሐ ጥናት ማጠቃለያ እደሚመሰክረው ኢትዮጵያ ውስጥ የተተከለው የጎሳ (የብሔር) ፌደራሊዝም በተግባር ተፈትኖ ወድቋል፡፡ (Asefa 2007) በህወሓት የተዘጋጀልን እና በሥራ ላይ ያለው የሀገራችን ሕገ መንግሥት ሀገሪቱን የዜጎች  ሳትሆን የዘውጌዎች (የብሔሮች) አክስዮን አድርጎ ቀርጿታል። በዚህ ስሌትም የሀገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የደኅንነት  ተቋማትን በጎሳ ለተደራጁ #አንደኛ_ደረጃ_ዜጎች በማስረከቡ በብሔር ከረጢት የማይመደቡ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር እና #ሁለተኛ_ዜጋ አድርጓቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራሊዝም ያስፈልጋል ተብሎ የሚታመነው ብዝኀነትን ያቀፈ ሀገራዊ አንድነት እንዲፈጠር፣ ለዘመናት የተጠየቀውን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ስለሚመልስ ኅዳጣንን (አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን) እንዳይበድል ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም መሠረቱን ያደረገው የልዩነት ምልክት በሆነው በብሔር ላይ በመሆኑ ያስወግዳል የተባለውን ዋናውን የሀገሪቱን ችግር አባባሰው እንጂ አልፈታውም፣ ሁሉንም ነገር ከብሔር ጋር አያያዞ ሀገራዊ አንድነትን አዳከመው እንጂ ጠንካራ አንድነት አላመጣም፣ ብዙኅኑ አናሳውን እንዲረግጥ መንገድ ከፈተ እንጂ ዲሞክራሲን አላመጣም፡፡

አሁን ባለው ሕገመንግሥት ማህቀፍ ውስጥ የኢትዮጵያን ችግሮች መፍታት በፍጹም አይቻልም፡፡ ይህንን የሀገርን ሉዓላዊነት ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦች ለሚባሉ ልዩነታቸውና አንድነታቸው በውል ለማይታወቅ ስብስቦች የሰጠውንና በተለይ ለብሔሮች ገደብ የለሽ መብት እንጂ መብታቸውን ከምንም ዓይነት ግዴታ ጋር የማይያያዘውን ሕገመንግሥት ይዘን እስካሁንም እንደ ሀገር መዝለቃችንም በራሱ አስገራሚ ነው።

ከላይ ከጠቃቀስኳቸው እና ሌሎች ጥናቶች በመነሳት ሀገራችን ኢትዮጵያ የተከተለችው ዘውግን (ብሔርን) መሠረቱ ያደረገው የፌደራል ሥርዓት አደረጃት ተፈትኖ የወደቀ እና በተጨባጭ የሚከተሉት ሀገራዊ ቀውሶች አስከትሏል እላለሁ፡፡

1) ዜጎች ከክልል ወደ ክልል በነጻነት እና በሰላም ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ ስለማያበረታታ ሀብት ፈጣሪዎችን በማብዛት ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ የምናደርገው ሀገራዊ ጥረት ከንቱ ልፋት አድርጎታል፡፡

2) ዕውቀት እና ሀብት ያላቸው የሀገሪቱ ዜጎች በመላዋ ሀገሪቱ ያለሰቀቀን ተንቀሳቅሰው ሥራ እንዳይፈጥሩ እና በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይሰፍን አድርጓል፡፡

3) በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት እንደታዘብነው የክልል ከተሞች ጎብኚዎች እና ሥራ ፈጣሪ ባለሀብቶች በማጣታቸው በከፍተኛ ፍጥነት እየተዳከሙ እና እየተፋዘዙ እንዲመጡ አድርጓቸዋል፡፡

4) በክልል ከተሞች ሀብት በመፍጠር እና ቀጣሪ በመሆን የሚታወቁ የሀገሪቱ ዜጎች ከክልሎቹ ባለሥልጣናት ትብብር እና ድጋፍ በማጣት አልፎ አልፎ በሚነሱ ብሔርን መሠረት ባደረጉ ግጭቶችም ሰለባ በመሆናቸው ሥራቸውን እየተዉ ወደ ማዕከል (አዲስ አበባ) ስለሚሰበሰቡ አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመላ ሀገሪቱ እየተዳከሙ ሄደዋል፡፡

5) ከግብር ከፋይ ዜጎች የተሰበሰቡ፣ በብድር እና በልመና የተገኙ የሀገሪቱ ውሱን ሀብቶች የፈሰሰባቸው የፌደራል ተቋማት በየውቅቱ የሚገነፍሉ ብሔር ተኮር ግጭቶች የጥቃት ዒላማ ስለሚሆኑ ለትውልድ የሚተርፍ ጥሪት ሳይሆን እዳ እና ኪሳራ ምክንያት ሆኗል፡፡

የመፍትሔ ሀሳች!

መፍትሔው የዝግጅት ሂደቱን በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ በመሻገር ላይ ባለው ሀገራዊ ምክክር ሁሉንም ባለድርሻዎች ያሳተፈ የሰከነ እና እውነተኛ ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ ሲሆን ምክክሩ የሚከተሉትን ውጤት ያስገኛል ብዬ ተሥፋ አደርጋለሁ፦

1) የችግሮቻን ምንጭ የሆነውን የዘውግ (የብሔር) ፌደራሊዝም በዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም መተካት፤

2) የሀገር ባለቤትነትን ሁላችንንም እኩል በሚያደርገን እና በሚያመሳስለን የጋራ እሴት በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ ማቆም፤

3) የሀገሪቱን የመንግሥት አወቃቀር የብሔሮችን ባህል፣ ቋንቋ እና ሌሎች የቡድን መብቶችን በሚያከብር ነገር ግን መሠረቱን ዜግነት ባደረገ ፍልስፍና መተካት !

4) የኢኮኖሚ መዋቅራችንን በሂደት ማኅበራዊ ፍትህ በሚያሰፍን (ለሁሉም ዜጎች እኩል እድል በሚሰጥ እና የተለየ ድጋፍ የሚያሻቸውን በማገዝ) ሥርዓት መተካት !

ሠላም !

Filed in: Amharic