>
5:26 pm - Wednesday September 15, 1683

እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፥ይጠቅማሉ...! (በእውቀቱ ስዩም)

እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፥ይጠቅማሉ…!

(በእውቀቱ ስዩም)


የሰው ልጅ የመጀመርያ ስራው ማደን እና ፍራፍሬ መልቀም ነበር፤   መሮጥ ማባረር መውጣት መውረድ፤ ካንዱ ስፍራ ወደ አንዱ ስፍራ መፍለስ  ተግባሩ ነበር፤ የሰው ተክለሰውነት ለእንቅስቃሴ እንዲመች ተደርጎ የተዋቀረ ነው፤

 

ከለታት አንድ ቀን  የአደም ዘር ፥ ተቧድኖ ከማደን ተቧድኖ  ወደ ማረስ ተሸጋገረ፤ እንቅስቃሴው ውስን ሆነ፤ ያም ሆኖ ሰው እጁን እግሩን ከማሰራት አልታቀበም፤  አያቶቻችን እንዴት እንደኖሩ እናስብ! ሴቶች ከመንደራቸው ወዲያ ማዶ እሚገኝ ገበያ ሸቀጣቸውን አዝለው ረጅም መንገድ በሌጣ እግራቸው  ይጓዙ ነበር፤  ወታደር ከወረይሉ እስከ አምባላጌ ድረስ በእግሩ ይወዘወዛል፤  የቆሎ ተማሪ አንድ አኮፋዳውን በቁራሽ ለመሙላት  ሁለት ሶስት መንደር በእግሩ ያካልላል፤

 

የኛን ኑሮ ደግሞ አስቡት!  የምንኖረው በስልጣኔ ውስጥ ነው፤ ስልጣኔ ሰውን ከተንቀሳቃሽነት አውጥቶ ተቀማጭ አድርጎታል፤ ቢሮዋችን ውስጥ በኮምፒውተራችን ፊትለፊት ለረጅም ጊዜ እንጎለታለን፤ ታክሲ  ውስጥ እንቀመጣለን፤ ምግብ ቤት እና ካፌ  ውስጥ አስተናጋጁ እስኪገላምጠን ዘለግ አርገን  እንቀመጣለን፤  ሰውነታችን ሊንቀሳቀስ  እንጂ ሊዘፈዘፍ ስላልተፈጠረ፥ ቀስ በቀስ፥ ባእድ  አካል   እና ባእድ ስሜት ይጎትታል፤ ባጭሩ፤  ጮማና ድብርት ያፍነናል፤

 

“ ገፋ ገፋ አድርገህ ውጣው አቀበቱን

ልብ ያሰበው ነገር  አይገኝ እለቱን “ ይላል ይርጋ ዱባለ፤ የቀደሙ ሰዎችን የልብ እና የአካል ጥንካሬ የሚያሳይ ዘፈን ነው፤ የዘመናዩ ትውልድ የኑሮ ዘይቤ ደግሞ በሚከተለው የሙሉቀን  መለሰ ዘፈን ተንጸባርቋል፤

“ ሄድኩኝ ሄድኩኝና ቀረሁ ከዳገቱ

ሬሳሽን አንሽ በሏት ያችን ከንቱ “

በጥንቱ ህይወት ውስጥ ሰዎች ወደ ጂም አይሄዱም ፤ የእለት ተእለት ውሏቸው  ጂም ነበር፤ አሁን ረጅም መንገድ እንሄድ ብንል መንገዱ አይመችም፤ ጸሀይ  እንደ ድሮው ልዝብ አይደለችም፤ በማይመች መንገድ በወበቅ ስር ጉዞ መንሸራሸር ሳይሆን  እንደ ቃየን መቅበዝብዝ ነው፤

በመዲናችን ሰዎች በሙዚቃ የታጀበ የአካል እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ማህበር አለ፤ Ethio dance and fitness   ይባላል፤ ከየአቅጣጫው ተጠራርተህ  በተለያዩ ብሄረሰቦች ዘፈኖች በህብረት ትወዛወዛለህ፤ ባንዴ ኪነት እና ስፖርትን ትቀዳጃለህ፤ ባንዴ ድብርትን እና ትርፍ ጮማን ታራግፋለህ፤

እኔ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ  እምላወስ እንጂ እምንቀሳቀስ አልነበርሁም፤ የአክሱም ሀውልት ከኔ የተሻለ ይንቀሳቀሳል፤  በውዝዋዜ የደረጃ ምደባ፥  በካሳ ተሰማ እና በካስማሰ መካከል የነበርሁ ሰው ነኝ ፤ በዚህ ማህበር ከታቀፍኩ በሁዋላ ግን  ወይዘሮ ደስታ ገብሬን አስንቃለሁ🙂

 

እስካሁን ያለው ምስክርነት ሲሆን ፥ ከዚህ በሁዋላ ያለው በነጻ የቀረበ  ማስታወቂያ ነው፤

ኢትዮ ዳንስ ፊትነስ በመጭው ጥቅምት ሀያ ሰባት በወዳጅነት ፓርክ እልል ያለ የውዝዋዜ ኮንሰርት  አሰናድቷል፤  እርስዎ ተሳታፊ እንጂ ተመልካች አይደሉም፤ የመግቢያ ትኬት  ለአዋቂዎች አራት መቶ ብር ፤ ለልጆች ሶስት መቶ ብር መሆኑን ካዘጋጆች ሰምቻለሁ፤ ወዝውዞ አደሩ ያሸንፋል! እንቅስቃሴዎች ሁሉ፤ ይጠቅማሉ::

Filed in: Amharic