>

እውቁ የታሪክ ዘካሪ ፀሐፊ ደራሲ አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ - /የኢትዮጵያ ታሪክ አባት/...! (ታሪክን ወደኋላ)

እውቁ የታሪክ ዘካሪ ፀሐፊ ደራሲ አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ – /የኢትዮጵያ ታሪክ አባት/…!

ታሪክን ወደኋላ


ተክለፃዲቅ መኩሪያ ብዙ የታሪክ መፅሀፍት ፅፈዋል ። የታሪክ ፀሐፊው  የኢትዮጵያን ሙሉ የሶስት ሺህ አመት ታሪክ በአጠቃላይ በአስራ አንድ መፅሀፍት ፣በስፋትና በዝርዝር የዳሰሱ ናቸው። ዳጎስ፣ ዳጎስ ያለ ቅፅ ያላቸው እነዚህ እልፍ መፅሀፍት ብዙ የተለፋባቸው እንደሆኑ ያስታውቃሉ። የተክለፃዲቅ መኩሪያን ሁሉንም መፅሀፍት አበጥሮ ያነበበ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ በዘመናት ርዝመትም ሆኖ በጂኦግራፊያዊ ስፋት የተሟላ መረጃ ይኖረዋል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

አስባችሁታል ግን? ተክለፃድቅ መኩሪያ ባይኖሩ ኖሮ የኢትዮጵያን ታሪክ የምናነበው በምን ቋንቋ እንደሆነ በውጪ አገራት ቋንቋ ሊያውም ካገኘነው…

ታዲያ ለታሪክ ረሃብተኞች የተክለፃዲቅ መፅሐፎች ቢበልጡብንም፣ የጳውሎስ ኞኞም ሶስት  የታሪክ መፅሀፍት ቋንቋውና አፃፃፉ ይማርከኛል።

ተክለፃዲቅ መኩሪያ መስከረም 1 ቀን 1906  ሸዋ በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በጊናገር ወረዳ፣ በአሳግርት ልዩ ስሙ አቆዳት በሚባል ስፍራ ተወለዱ። ወደ አዲስ አበባ መጥተው የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በአማርኛና በግዕዝ ካጠናቀቁ በኋላ በቀድሞ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት የፈረንሳይኛ ትምህርት ተምረዋል። ለኢጣሊያ የወረራ ዘመን ሶስት ዓመታት በግዞት በሶማሊያ ቆይተዋል። ከዚያም ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ አገዛዝ ነፃ እንደወጣች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በአስተዳደርና በዲፕሎማሲ መስክ አገልግለዋል።

አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ በኢትዮጵያ የንባብና የትምህርት ዓለም በስፋት የሚታወቁት ፅፈው ባዘጋጇቸው እጅግ ግዙፍ በሚባሉ መፃሕፍቶቻቸው ነው። በቀደመው ዘመን ላይ ለትምህርት ቤቶች የታሪክ መማሪያ በአምስት ቅፅ የታተሙት መፅሐፍቶቻቸው ነበር የሚያገለግሉት። የኢትዮጵያን ታሪክ ከማንም በበለጠ መልኩ የፃፉ ሰው ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ እርሳቸው የኢትዮጵያን ታሪክ ለባለታሪኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመፃፍ ይታወቃሉ። የእርሳቸው ዘመን ላይ የነበሩ የታሪክ ምሁራንም ሆኑ አሁን ያሉት ምሁራን በአብዛኛው የሚፅፉት በውጭ ሀገር ቋንቋ ነው። እርሳቸው ግን ለኢትዮጵያዊ ወገናቸው ውብ በሆነ የአፃፃፍ ስልታቸው ሲፅፉለት ነበር የኖሩት።

ከታሪክ ፀሐፊነታቸው በተጨማሪ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ብዙ አገልግለዋል። ከጣሊያን ወረራ በኋላ ከ1934 ዓ.ም እስከ 1935 ዓ.ም በመዝገብ ቤት ሹምነትና በሚኒስትር ፀሐፊነት ሰርተዋል። ከ1935-1966 ዓ.ም ደግሞ የምድር ባቡር ዋና ተቆጣጣሪ፣ በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዋና ፀሐፊ፣ የጡረታ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር፣ በረዳት ሚኒስትርነት ማዕረግ የብሔራዊ ቤተመዛግብት ወመዘክር ዋና ኃላፊ፣ በሚኒስትር ማዕረግ በእየሩሳሌም ቆንስል፣ በቤልግሬድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል። የአፄ ኃይለሥላሴ ስርዓት በኃይል ከተወገደ በኋላም በዘመነ ደርግ እስከ 1967 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የትምህርትና የባሕል ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸውን ታሪካቸው ያወሳል። ከዚያም በጡረታ ተገለሉ።

እኚሁ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ለንባብ ያበቋቸውን የኢትዮጵያን የታሪክ መፃሕፍት በአብዛኛው የፃፉት በመንግሥት ሥራ ላይ እያሉ የእረፍት ግዜያቸውን በመሰዋት ነው። ለሕትመት ከበቁላቸው አያሌ ሥራዎቻቸው መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

1. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣

2. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ልብነድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ፣

3. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ይኩኖ አምላክ እስከ አፄ ልብነድንግል፣

4. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱም ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ፣

5. የኢትዮጵያ ታሪክና ኑቢያ፣

6. ከጣኦት አምልኮ ወደ ክርስትና፣

7. ጥንታዊት ኢትዮጵያና ግብፅ

8. የሰው ጠባይና አብሮ የመኖር ዘዴ፣

9. የግራኝ አሕመድ ወረራ

10. አፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት

11. አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት፣

እና ሌሎችም ያልታተሙ አያሌ ስራዎች አሏቸው።

እነዚህ ከላይ የሰፈሩት የታሪክ መፃሕፍት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ታላላቆቹ ቅርሶች እንደ አክሱም፣ ላሊበላና ጎንደር የሚታዩ እንደሆነ ፀሐፊያን ይናገራሉ። አሁን ያሉ ወጣት ፀሐፊያን የታሪክ መፃህፍት እያሉ የሚያሳትሟቸው ስራዎቻቸው በአብዛኛው ከአቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ስራዎች የተገለበጡ ናቸው። የተኮረጁ ናቸው። የተሰረቁ ናቸው። ለአንዳንዶቹ ደግሞ የመነሻ ሃሳብ የሚሰጡ ናቸው። ተክለፃዲቅ መኩሪያ በኢትዮጵያ የታሪክ ፅሁፍ ውስጥ ዘላለማዊ ብርሃን ረጭተው ያለፉ ብርቅዬ ደራሲ ነበሩ። ለኢትዮጵያዊ ወገናቸው

ውብ በሆነ የአፃፃፍ ስልታቸው ሲፅፉለት ኖረው ሐምሌ 16 ቀን 1992 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ሀገርን ከነድንበሩ፣ ታሪክን ከነባህሉ፣ ቋንቋን ከነፊደሉ ላቆዩልን፣ለጀግኖች እናትና አባቶቻችን ክብር ይሁን።ትናንትን በመልካም በቅንነት የሚያስብ ሁሉ የአባቶቻችንን ስራና ገድል ይዘክራል ያከብራል።

•ታሪክን ወደኋላ

©️ ታሪካችንን ዕንወቅ

Filed in: Amharic