>

 ዳሞቴው ገጣሚ ሲዘከር  (ፀሐፊ- ጌታ በለጠ - ደብረ ማርቆስ፣ ጎጃም)

 ዳሞቴው ገጣሚ ሲዘከር

  ፀሐፊ- ጌታ በለጠ (ደብረ ማርቆስ፣ ጎጃም)


ዛሬ ጎጃም፣ዳሞት ዘልቄ አንድ የጥበብ ሰው ላወሳ ነው። ብዙ ጊዜ ከመድረክ ጀርባ ያሉ ሰዎችን ሰፊውህዝብ አያውቃቸውም።ከፊልም ደራሲዎች በላይ ተዋንያን ይደምቃሉ፥ከዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ይልቅ ዘፋኞች ይገዝፋሉ። ወደ ዳሞት የምወስዳችሁ ከብዙ ጥዑም ዜማዎች ጀርባ ሆኖ ጀሮአችን ወዷቸው ያደመጥናቸው ለእነ ይሁኔ በላይ፣ ፍቅራዲስ ነቃዓጥበብ፣ መሰረት በለጠ፣ ሶሎሞን ካሳ፣ አምሳል ምትኬ እና ሌሎችም አቀንቃኞች የዘፈን ግጥም በመስጠት ዘመናችንን በሙዚቃ ብሩህ ያደረገ ጎልማሳ ሥም ለማንሳት ነው።”ማነው?”የሚለውን አቆይተን የዘፈን ግጥሞቹን ቆንጠር እያደረግን እንመልከት።

ዳሞት ዘልቄ አንድ የጥበብ ሰው ላወሳ ነው። ብዙ ጊዜ ከመድረክ ጀርባ ያሉ ሰዎችን ሰፊውህዝብ አያውቃቸውም።ከፊልምደራሲዎች በላይ ተዋንያን ይደምቃሉ፥ከዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ይልቅ ዘፋኞች ይገዝፋሉ።ወደ ዳሞት የምወስዳችሁ ከብዙ ጥዑም ዜማዎች ጀርባ ሆኖ ጀሮአችን ወዷቸው ያደመጥናቸው ለእነ ይሁኔ በላይ፣ፍቅራዲስ ነቃዓጥበብ፣ መሰረት በለጠ፣ ሶሎሞን ካሳ፣አምሳል ምትኬ እና ሌሎችም አቀንቃኞች የዘፈን ግጥም በመስጠት ዘመናችንን በሙዚቃ ብሩህ ያደረገ ጎልማሳ ሥም ለማንሳት ነው።”ማነው?”የሚለውን አቆይተን የዘፈን ግጥሞቹን ቆንጠር እያደረግን እንመልከት።

የባህል አቀንቃኙ ይሁኔ በላይ “ውዴን ይዘሽው ነይ” ሲል ባሽሞነሞነው ዘፈን ውስጥ ያሉ ድንቅ ግጥሞችን ብዕር አንስቶ ያዋቀራቸው ይኽ ሥሙን በይደር ያቆየነው ዳሞቴ ነው።

ፀጉርሽን ነስንሰሽ አድርጊው ገመድ

አስረሽኝ ልቀመጥ ልሁንሽ ዘመድ።

ውበት አስሮ አስቀምጧችሁ ያውቃል? እንደ ጎጃም ማኛ የሚዘናፈል ፀጉር አይታችሁ “ፍዝዝ” ብላችሁ ታውቃላሽህ? ይኼን ዳሞቴ “አስረሽኝ ልቀመጥ” ያስባለው እንዲህ አይነት የራስ ላይ ውበት ነው። አዎ! የራስ ላይ ውበት-ፀጉር።

 

እስኪ ውደቂና ላንሳሽ ደጋግሜ፣

ተይው ይሁንብሽ ህመምሽ ህመሜ።

ሆዴ ያገሬ ልጅ ከጥርስ ወተት፣

አለብኝ እንግዳ የምሸኝበት።

እናትሽ ይውለዱ ቆንጆ ደጋግመው፣

‘ለኔ ቢጤ ይሁ ዕድል ቢገጥመው።

ከልብ የሆነ መውደድ እንዲህ ነው። እሷ ወድቃ አንተ ታነሳት ዘንድ ትመኛለህ። ለነገሩ ግን ሳትወድቅ መደገፍ አይቀልም? ሰው እንደ ልክፍቱ ነው። በጥርሷ ውበት የሚሸኘው እንግዳ ማነው? ልቡ ይሆናል። ላፈቀረ ሰው ልብ ሁሌም እንግዳ ነው። ለዚህም ነው ” ከጥርስሽ ወተት- አለብኝ እንግዳ የምሸኝበት” እያለ ራሱን የልቡ አስተናጋጅ ማድረጉ። የሚዳት ልጅ እናት ደጋግማ ትወልድ ዘንድ “እናትሽ ይውለዱ ቆንጆ ደጋግመው” ሲል ይማፀናል። ቆንጆ የሚያፈራ ማኀፀን ስለምን ይንጠፍ? ይውለዱ እንጅ!

 

በጎጃም ባህል መሰረት “ጥሎሽ መስጠት” የሚባል ሥርዓት አለ። ጥሎሹ ሙሽራይቱን ከማስጌጥ ተሻግሮ የሙሽራይቱ ቤተሰቦችን የሚያዳርስ ነው። ገጣሚው ” ለእናትሽ ለአባትሽ ሽህ ወጪት ሰፍሬ” ሲል ለወላጅ የሚሰጠውን ጥሎሽ ነው። ሙሽሩትስ ምን ይቀርባታል? ለእግሯ አምባር፣ ለአንገቷ የጠገራ መስቀል ሳይጥል ባል ስለመሆን ሊያስብ አይችልም።

ለእናትሽ ለአባትሽ ሽህ ወጩት ሰፍሬ፣

አስጎትጄ ባዝራ- ዝናር አሰግሬ፣

ለአንገትሽ ጠገራ፣ ለእግርሽ አምባር ጥዬ

ፎክሬ ወሰድሁሽ ሆ- ብዬ ሆነ- ብዬ።

በገና መደርደር የትላንትም ነው።ታቦተ ፀዮን ከእየሩሳሌም ስትወጣ በገና ተደርድሮላታል። ገጣሚው “እምዬ ሐና” ሲል የሚጠራት እናታችን የክብር ሞት ትሞት ዘንድ ልጅ በፈቀደ ጊዜ ዕዝራ በማሲንቆ፣ ዳዊት በበገና ከበው እያመሰገኗት ባለችበት ወቅት ነው ነፍስ ከሥጋዋ የተለየችው። ታዲያ መውደድህ ኃያል ሲሆን ዳዊት ያነሳውን በገና፣ ዕዝና የተሸከመውን ማሲንቆ አንስተህ ለእምዬ ሐና እንደተዜመው ማዜም ያምርሃል። ማሲንቆ ከበገና አንስቶ የሚወዷትን ጉብል ላፍታም አለመርሳት ፀጋ ነው። ትቂቶች ብቻ የሚችሉት ፀጋ።

ዕዝራ በማሲንቆ፣ ዳዊት በበገና፣

እንደዘመሩላት እንደ እምዬ ሐና፣

እኔም ላወድሳት ላንጎራጉርላት፣

መቸም ህመሜ ናት ለአፍታም አልረሳት።

ዳሞቴው ገጣሚ በዚህ አልተወሰነም። የመለዬትን መራራነት “መለዬት”በሚል የይሁኔ ዘፈን ውስጥ ነፍስ ዘርቶ እናገኘዋለን። 

ከወዲያ ተራራ ማነው የሚጣራ

መለዬት እንዳይሆን ያ ስመ መራራ። 

ሲል የመለዬት መራራነት በማንሳት ይጀምራል። መለዬት ይሉት ክፉ መንፈስ ከአንድ ተራራ ጫፍ ኾኖ ሲጣራ መስማትን የመሰለ ግም ነገር የለም።

ለዓይንና ለወዳጅ ትንሽ ይበቃዋል፣

እንዳትርቂኝ እቴ ሆዴን ይከፋዋል።

ሰው ነው መዳኒቴ አጀብ እወዳለሁ፣

መለዬትን ይዤ መኖር እፈራለሁ።

ግሩም ነው። ገጣሚው ሆደ ብቡ መሆኑን ከሥራዎቹ መረዳት ይቻላል። ብትለየው ሆዱ ይባባል። በሰዎች ሲታጀብ ልቡ ሃሴት ታደርጋለች። መለየትን እያሰበ መኖር ጭንቁ ነው። ለነገሩ መለዬት ሁልጊዜ ፈቅደህለት አይመጣም። ዱብዕዳ ነው።

ከዳመና ከብዶ ከመጣብኝ እኔ፣

እደበቀዋለሁ ይኼን አረመኔ።

እያለ እንደ ዳመና አግዝፎ የተመለከተውን የመለዬት ዕዳ ሲሸሸው እናያለን። ለዚህ ገጣሚ መለዬት ዕጣ አይደለም። በእህል- ውሃ የሚወሰንም አይደለም። ቁጣ ነው። ለዚህም “ጠበል ነው መፍትኄው” ሲል ይሰማል።

እጣ ነው እያሉ እህል ውሃ እያሉ፣

አየሁ ሲሸኛኙ ቻው ቻው ሲባባሉ፣

እኔስ አይበጀኝም እዚያው በጠበሉ።

የዓለምን ፍፃሜ ሊነግር ከሚጎሰም የነጋሪት ድምፅ በላይ መለየትን ይፈራዋል። ሞትን ይረግማል፥ መለዬትን ይኮንናል። 

ነጋሪት ቢጎሰም ስለዓለም ፍፃሜ፣

አንችን ማጣቴ ነው የሚያስፈራኝ እኔ።

ባይኖር ምን አለበት ሞት እና መለዬት፣

ከወደዱት ጋራ ቢዘልቁ ለሽዓመት።

ሽፍን ሽፍን አርጉኝ ከፊት ከኋላዬ፣

ይቅር ብቸኝነት አይወድም ገላዬ።

ይኼ ብርቱ ገጣሚ ይሁኔ በላይን “የዘገሊላ ዕለት-ነይልኝ በእኔ ሞት” ሲያስብለው መስማት ሌላ ድንቅ ነገር ነው። “የዘገሊላ ዕለት” በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ በስፋት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ወጣቶች የንግሡ አከባበር ላይ ያላቸውን ሁነት ያሳያል። በበዓሉ ሎሚ ወንድ ወጣቶች ወደ ጉብል ሴቶች የፍቅር ሎሚ ይወረውራሉ። ጉብሏ ሎሚውን አንስታ ከያዘች ፍቅሩን እንደተቀበለችው ይቆጠራል። ይኼ ባህል የሚፈላለጉ ወጣቶች በነፃ የሚገናኙበት መድረክ ነው። ለዚህም ገጣሚው ይኼንን ይላል።

ወርውሬ መታሁት ጥላሽን በእምቧይ፣

ደሞ ባንች በኔ ከልካይ አለ ወይ።

በወቅቱ ሴቶች በተለያዩ የባህል ልብሶች ለብሰው፣ በውድ ጌጣጌጦች ተውበው ወደ በዓሉ ይኼዳሉ። ያላገባች ሴት የምትለብሰው መቀነት አይነት፣ መቀነቱ፣ ለማስጌጫ የሚውሉት ( ማርዳ፣ ዛጎል እና አምባር) ልዩ ነው።ገጣሚው በሚከተለው መልኩ ውብ አድርጎ አቅርቦታል።

ወንዞ አይፈሬው ቀሚስ የተሸነሸነው፣

ትፍትፉ መቀነቱ ወገቧን የዞረው፣

ልቤን በጉንፏ አውሎ አሳደረው።

እንኳን ዛጎል ማርዳው አምባሩ መስቀሉ፣

ሽርብት አደሬ ማተብሽ ድንግሉ፣

አንችን ለማሳመር መች አነሰ ባሉ።

የባህል ዘፋኟ መሰረተ በለጠ የሥሟ መጠሪያ እስኪመስል ድርስ የታወቀ ” ጉም- ጉም”የሚል ዘፈን አላት።

በፍቅር ጉም ጉም፣

በመውደድ ጉም ጉም፣

እረ እንዴው ጉም ጉም፣

ጀመረው እንግዲህ ደግሞ ሊያልጎመጉም።

እያለች በውብ ድምጿ ያስደመመችን መሰረት በለጠ ይኼ ድንቅ ደራሲግጥሙን ባይሰጣት እንዴትስ ልንሰማው እንችል ነበር? እንዲህም ይለናል:-

ዓይኑ በኩል ያምራል ጥርሱ በውቅራት፣

እያማረጡ ነው ሸጋ – ሸጋ መብላት።

ፍቅር ብርታቱ ከእንቅልፍ ያፋታሃል። ሐሳብ ሁሉ አንድ ቦታ ይሰበሰባል፥ ፍቅር ላይ። ታዲያ ይኼንን ድንቅ ስሜት ገጣሚው እንዲህ አድርጎልሃል።

መች እንቅልፍ ይወስዳል ከነጋ ቢተኙ፣

እስከ ዶሮ ጩኸት በአሳብ ከዋለሉ።

ገናናዋ አምሳል ምትኬ “የሸበሉ” ስትል የምትቀብጥበት፣ በአርበኛው በላይ ዘለቀ አምሳያ ወንዶችን የምትመዝንበት ዘፈን ውስጥ ያሉ ውብ ግጥሞች የዚህ ዳሞቴ የአዕምሮ ሥራ ውጤቶች ናቸው። እስኪ ይፈተሹ።

የሸበሉ የሸበል በረንታው፣

ሸጋው በላይ አምሳያኽ አለወይ?

አባይ ገመገሙን ተሻገርኩት በእግሬ፣

ባገርህ በወንዝህ በስምህ ፎክሬ።

ምን ይሉት ጥያቄ ነው ወንዶችን ሁሉ በበላይ መመዘን? ሚዛኑስ እንዴት ይሙላ? ማንስ ተመዝኖ ነው የሚሞላው? የበላይ አምሳያ መሆን ሲባል እንዴት ነው? አምሳያነት ቀላል ነው እንዴ? የመስፈሪያ መስፈርቱስ ምንድን ነው? ልበ ሙሉነት? ላንት ባንድራ ታምኖ መሞት? የጦር ስልት ነዳፊነት? ደግነት ወይስ ሌላ? የበላይ አምሳያ መሆን እንዴት ይቻላል?

እንዳንተ የሚሆን የቸገረ ዕለት፣

አልወለደችም ወይ የጎጃም ዕናት።

ልሂደው ልሂደው አገሩን ልቃኘው፣

በፍኖተ ሰላም ምን አልባት ባገኘው።

ገጣሚው የጭንቅ ዕለት የሚደርስ፣ ዋይ ሲባል “ከተፍ” የሚል፣ ሀገር ስትረበሽ፣ ሰማይ ሲጠቁር፣ እናት ስታዝን፣ ልጆች አንገታቸውን ሲደፉ ሊደርስ የሚችል የበላይ አምሳያ የሆነ ወንድ (ወንድ በግብር እንጅ በፆታ ያላይደለ)ሰው ፍለጋ ላይ ነው። ፍኖተ ሰላምን አካልሎ መዞሩ እውነት የበላይ አምሳያ ፍለጋ ይሆን? ገጣሚው ማስደመሙን ቀጥሏል።

የሰዓት ምሳውን በአገልግል ቋጥሬ፣

ጠላውን በገንቦ በዋርማ ሰፍሬ፣

እንካ ቅመስ ብለው ከማሳው ሄድኩና፣

ጊዜው ይድረስ አለኝ ጀንበሩን አየና።

የጎጃም ሕዝብ ሐይማኖተኛ ነው። ገበሬው ጿሚ እና ፆሎተኛ ነው። አርሶ አደሮች የጀንበርን መጥለቅ የፆም ሰዓት መድረሱን መለኪያ አድርገው ይቆጥራሉ። ለዚህም ነው የአገልግል እንጀራውን እና የገንቦ ጠላውን ያለጀንበር መግባት አልቀምስም ማለቱ።

አሰትም አያውቁ ለእውነትም አይላሉ፣

እኒህ ጎጃሜዎች አምነው ይሞታሉ።

ከግጥሙ ውበት የተፃፈበት የጎጃም ዘዬ ይማርካል። ከላይ ያለው ስንኝ መጀመሪያ ላይ ” አሰት” የሚለው “ሀሰት” ለማለት ነው። ያባቶቻችን ዘዬ ልዩ ነው። የሁለተኛው ስንኝ ” እኒህ ጎጃሜዎች አምነው ይሞታሉ” የሚለው ቅኔ ነው። አምነው ይሞታሉ ማለቱ በአንድ በኩል ታማኝነትን ሲያሳይ በሌላ በኩል የሐይማኖት (እምነት) ፅኑነትን ያሳያል።

ባሻዬ! ገጣሚው ልዩ ነው ስልህ!። 

አሁን ደግሞ አምሳል ምትኬን “ፍቅር አበረረኝ” እያስባለ ጎጃምን ያዞራታል።

ውብ አረማመዱ ደርባባ አካላቱ፣

የግንባሩ ፀዳል የአይን አከፋፈቱ፣

ቁጥብ አንደበቱ ማር ልውስ ቃላቱ፣

ምን ጥርጥር አለው በጎጃሜነቱ።

ደግሶ ይጠራል ፍቅሩ ለብቻው ነው፣

ምን ጎሎበበት ጎጃም ጎተራው ሙሉ ነው

አንደበቱ ቁጥብ ያለ፣ ሲናገር ቃላቶቹ ማር የተቀቡ፣ ግንባሩ ፅዱ፣ ገምሻራ አረማመድ ያለው ሰው ካዬህ ጎጃሜ መሆኑን ታውቅ ዘንድ ገጣሚው ነግሮሃል። 

ቁርሴን ደጀን ልብላ ምሳ ደብረ ማርቆስ፣

ጅጋ አመሻሽቼ አዳር ቡሬ ልድረስ፣

ሎሚና ትርንጎ ይዞ ሚጠብቀኝ፣

አለኝ የልብ ወዳጅ ሁሌ የሚናፍቀኝ።

እያለ ከዓባይ ድንበር ደጀን እስከ ወለጋ ድንበር ቡሬ ያስቃኘናል። ከዓባይ እስከ ዓባይ ማለት ይኼ አይደል?

በሸበል በረንታ በእነማይ ደባይ፣

ያንዣብባል ልቤ በጎጃም ሰማይ።

በርሌ በርሌ ልክ እንደ ወፊት፣

ማረፊያው ባህርዳር ሆኖ አገኘሁት።

ያየሁት ደብረ ወርቅ ቢቸናና ሞጣ፣

እስከዘላለሙ ከልቤም አይወጣ።

ተመልከት ባሻዬ! የእናርጅ እናውጋ መዲና የሆነችውን ደብረ ወርቅ፣ እነማይ ወረዳን፣ ጥንት አውራጃ የነበሩ ሞጣና ቢቸናን አልፎ ታላቋ የአማራ መዲና ባህርዳር ሲያስጎበኘን። የዚህን የጥበብ ሰው ሥራዎች በዚህ መንደር ዘርዝሮ መጨረስ የሚቻል አልሆነም።በሁለት ስንኞች ልጨርስ።

ጉልማ ያልጎለምኩ ዘር ያልበተንኩ ሰው፣

የሆዴን ጥያቄ እንዴት ልመልሰው።

ይኼ ግጥም የተወሰደው ገጣሚው ለበእውቀቱ ሰውመሆን ከሰጠው “ጉስም-ጉስም” ከተሰኘው ዘፈን ነው። “የላብህን ብላ” የሚል አንድምታ አለው። ሰርቶ መብላትን የመሰለ ትልቅ ዕሴት ያበረታታል። የሆድን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው በሥራ ብቻ መሆኑን በማያሻማ መንገድ ነግሮናል።

ከእነዚ ሁሉ መልካም ሥራዎች ጀርባ የምናገኘው ገጣሚ የተወለደው በ1964 ዓ/ም ነው። ትውልዱም ጃቢጠህናን ወረዳ- ጎረፍ ቃውንቻ ቀበሌ ነው።የሚያሳዝነው ግን አሁን በሕይወት የለም። አዎ! አቤል መልካሙ በ2005 ዓ/ም ነበር ይኼን የምድር ድካም የተሰናበተው።

Filed in: Amharic