>

ድሮም የመንደር ውል ፊርማው ሳይደርቅ ይፈርሳል....! (ግዛው ለገሠ)

ድሮም የመንደር ውል ፊርማው ሳይደርቅ ይፈርሳል….!

› የሰሞኑ “የትግራይ” ጉራማይሌ መግለጫዎች

(በግዛው ለገሠ)


ትናንት የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን ከናይሮቢ ሲመለሱና የአበባ ጉንጉን በሚጠልቅላቸው ሰዓት፣ “ከትግራይ መንግሥት” የተፃፈ የስምምነቱን አካሄድ “የሚቃወም” መግለጫ ይፋ ሆኗል። እስካሁን እየሆነ ያለውን እንመልከት፦

– ኖቬምበር 2

እኛንም ዓለምንም ያስደመመ ስምምነት ተፈረመ፥ በመላው ኢትዮጵያ አንድ መከላከያ ሠራዊት ብቻ እንዳለና እንደሚኖር፣ “የህወሓት ታጣቂ ኃይል” ከባድ እና ቀላል ትጥቁን እንደሚፈታ፣ የሰብዓዊ እርዳታ በአስቸኳይና በአግባቡ ያለክልከላ እንዲዳረስ፣ መከላከያ እንደሚገባና የፌደራል መንግሥት ተቋማት ሥራቸውን እንደሚጀምሩ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል አዲስ ምርጫ እስከሚካሄድ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ተስማምተው ፈረሙ።

– ኖቬምበር 3፣ 4፣ 5፣ . . .

ከውጭም ከውስጥም ስምምነቱ ላይ ተቃውሞዎች ይሰሙ ጀመር። በተለይ የትግራይ አክቲቪስቶች እና ደጋፊዎች ከሁሉም በላይ የሻዕቢያ ጦር እና ሌሎች ኃይሎች በክልሉ እስካሉ ድረስ በምን ዋስትና ነው ስለትጥቅ መፍታት የምትስማሙት፣ ስምምነቱ የትግራይን ሕዝብ አደጋ ላይ የሚጥል ነው እያሉ ተቃውሟቸውን አሰሙ። በተጨማሪም ስምምነቱ ላይ “የሕወሓት ታጣቂ” እየተባለ የተጠቀሰው ልክ አይደለም፣ ህወሓት ታጣቂ ኃይል የለውም፣ ቲ.ዲ.ኤፍ እና ህወሓት ለየቅል ናቸው፣ ተደራዳሪዎቹ ህወሓትን ሳይሆን የትግራይ መንግሥትን ወክለው ነው የተገኙት፣ . . . ሌሎችም ትችቶች ይደመጡ ጀመር።

ይሄ ነጥብ፣ ማለትም የህወሓት አባል ያልሆኑ ግለሰቦችን ያካተተው የትግራይ ልዑክ ህወሓትን አይወክልም የሚለው ነጥብ፣ በአስሩ ቀናት ድርድር ላይም ተነስቶ ይሆናል። የኢትዮጵያ መንግሥትም እውቅና ሰጥቶ ሊደራደረው የፈቀደው ቀድሞውኑ እንደኃይል በሽብርተኝነት የሰየመውን ህወሓትን ስለመሆኑ በማስረገጡም ሊሆን ይችላል ስምምነቱ በሁለቱ መካከል እንዲሆን ተደርጎ የተፈረመው። ሆኖም ይህ ጉዳይ በመሠረታዊ ድንጋጌዎች እና በስምምነቱ ጠቅላላ ግብ ላይ ስምምነት እስካለ ድረስ ስምምነቱን አደጋ ላይ የሚጥል አይሆንም ነበር፣ በቀጣይ ሂደቶችም፣ በአተገባበርም ሊስተካከል የሚችል (የተስተካከለ) ነው። (የትጥቅ አፈታት ጉዳይም ጉልህ ማስተካከያ ሲደረግበት ቀጥሎ እንመለከታለን።)

– ኖቬምበር 12 (#1)

በዋናው ስምምነት መሠረት የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ ኮማንደሮች በናይሮቢ ለአምስት ቀናት መክረው የስምምነቱን አተገባበር የሚያፀና ሌላ ስምምነት ፈረሙ። የፊርማ ሥርዓቱ (እና ጋዜጣዊ መግለጫው) ከጠዋቱ አምስት ሰዓት ተቀጥሮ፣ ከምሽቱ አስራሁለት ሰዓት ገደማ ተካሄደ። ለሰዓታት የዘገየው መግለጫ በዋናነት ትጥቅ መፍታትን በተመለከተ አንድ ጉልህ የስምምነት ነጥብ አካትቷል፤ ይኸውም የትግራይ ታጣቂ ኃይል የከባድ መሣሪያ ትጥቅ መፍታት ተግባራዊ የሚሆነው የውጭ ኃይሎች (በስም ባይጠቀስም የሻዕቢያ ጦር) እና ከመከላከያ ውጪ የሆኑ የሀገር ውስጥ ኃይሎች ከትግራይ ክልል በሚወጡ ጊዜ (ጎን ለጎን) ነው የሚል ነው። ይህ እነ ጌታቸው ረዳ ላይ ለነበረው ተቃውሞ እና ጫና መልስ የሚሰጥ ነበር፤ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከባድ ውሳኔ ይመስለኛል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ የኮማንደሮቹ ስምምነት አሁንም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረገ መሆኑን በርዕሱ ቢገልፅም፣ በውስጥ ክፍሉ የትግራይ ታጣቂ ኃይል የሚሉ ቃላትን ያካተተ ሲሆን፣ በትግራይ በኩል ፈራሚ የነበረው ጀነራል ታደሰ ወረደ “የትግራይ ታጣቂ ኃይል ኮማንደር” በሚል ተጠቅሷል።

– ኖቬምበር 12 (#2)

የኮማንደሮቹ ስምምነት ፊርማ ሥርዓት ለሰዓታት ቢዘገይም፣ ልክ በሚካሄድበት ምናልባትም በተመሳሳይ ሰዓት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ አወጣ። በዋናነት የቀድሞዎቹን ተቃውሞች፣ ማለትም ህወሓትን የወከለ ተደራዳሪ የለም፣ ስምምነቱ ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር እንደተደረገ ተደርጎ ይስተካከል፣ እንዲሁም የህወሓት ታጣቂ የሚባል ነገር የለም የሚል ነው። ሆኖም በእለቱ በዚያው ሰዓት የተፈረመው የኮማንደሮቹ ስምምነት እነዚህን ተቃውሞዎች በአብዛኛው ለመመለስ የጣረ ብቻ ሳይሆን፣ በዋናው ስምምነት ትጥቅ ለመፍታት በግልፅ ያልተቀመጠን ቅድመሁኔታ (የሌሎች ኃይሎች ከትግራይ መውጣትን) ያካተተ ነበር።

– ኖቬምበር 13 (ትናንት)

ሌላ መግለጫ ወጣ። ይሄኛው ከህወሓት ወይም ከማዕከላዊ ኮሚቴው ሳይሆን፣ “ከትግራይ መንግሥት” የተሰጠ ነው። ከአንድ ቀን በፊት በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ የተጠቀሱትን ነጥቦች አሁንም አስረግጦ ያካተተ ሲሆን፣ በተጨማሪ አዲስ ጥያቄ ጨምሮ የመጣ ነው።

ይህ አዲሱ ጥያቄ እንዲሁ በአካሄድ እና በአተገባበር የሚስተካከል አይደለም፤ የወናው ስምምነት መሠረታዊ (substantive) ድንጋጌ ማሻሻያን የሚጠይቅ ነው። የዋናው ስምምነት አንቀጽ 10 (1)፣ ህወሓት የሽብርተኝነት ስያሜው በፓርላማ ከተነሳ በአንድ ሳምንት ውስጥ እና በምርጫ ቦርድ አማካኝነት በትግራይ የክልል እና የፌደራል ፓርላማ ምርጫዎች እስከሚካሄዱ ድረስ ሁሉን አካታች የሆነ ክልላዊ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚመሠረትበት ሁናቴ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ይደነግጋል። ይህም ማለት “የትግራይ መንግሥት” መፍረስ ወይም አለመኖር ገና ድሮ (ኖቬምበር 2 ላይ) በስምምነት በፊርማ ፀድቋል፣ የትናንቱ “ከትግራይ መንግሥት” የተባለው መግለጫ ግን እንዲህ ብሏል (ቃል በቃል ላይሆን ይችላል) ፦

« . . . በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ የትግራይ መንግሥት ሊፈርስ ወይም ሊቀየር የሚችለው በትግራይ ሕዝብ እንጂ “ግጭትን ለማቆም” ተብሎ በሚፈረም የስምምነት ሰነድ ሊሆን ስለማይገባው፣ ይህ ነጥብ ከስምምነት ሰነዱ ሊወጣ/ሊሰረዝ ይገባል።»

ይህ ነገሩን ከባድ ያደርገዋል። ነገር ግን ከሁሉም የበፊቶቹ ተቃውሞዎች በተለየ፣ ይህ ጥያቄ ለትግራይ ሕዝብ በመቆርቆር የቀረበ ነው ብሎ ለማመን ይከብዳል፤ ምክንያቱም አሁን የትግራይ መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ሥልጣኑ ቀጠለ፣ አልቀጠለ ለትግራይ ሕዝብ ቀዳሚ ጉዳዩ ነው ብዬ አላስብም።

ይልቁንም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚቋቋምበት ሁኔታ ስምምነት ላይ የሚደረሰው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በሚደረግ የፖለቲካ ውይይት ብቻ መሆኑን የትግራይ ልጆች ሊቃወሙ ይገባ ነበር። ሌሎች የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጀመሪያ በምርጫው ሚና እንዳይኖራቸው ተገፉ፣ ቀጥሎም በጦርነቱ ሂደት እና የትግራይ ሕዝብ ጉዳት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት፣ ለትግራይ ሕዝብ ሲሉ የህወሓትን መንገድ በመደገፋቸው ከፖለቲካው ደበዘዙ እንጂ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱም ፖለቲካ ላይ ሚናቸው ሊቀጥል ይገባል። አካታችነቱ ይህንን ያሰመረ ሊሆን እንደሚገባ የትግራይ ልጆች ሊከራከሩ ይገባል እንጂ ለህወሓት የፖለቲካ ሥልጣን ሊጨነቁ አይችሉም።

ይህ የመንደር ውል አይደለም! በዋናው ስምምነት አንቀጽ 15 አማካኝነት የሁለቱንም ተፈራራሚዎች ይሁንታ መሠረት ባደረገ መልኩ ማሻሻያ መድረግ የሚቻል ሲሆን፣ ይህም በፅሁፍ የቀረበና በሁለቱም ወገኖች በፊርማ የፀደቀ ሊሆን ይገባል። ይህም ዳግም ድርድር የሚጠይቅና የስምምነቱን አፈፃፀም የሚያሰናክል፣ ወደኋላ የሚጎትት ነው። ለአስር ቀና ሲደራደሩ ቆይተው ተስማምተው የፈረሙ ሰዎች፣ አሁን ዘግይተው ይህን ጉዳይ ማንሳታቸው ከመነሻው በቀና ልቦና መፈራረማቸውን እንድንጠራጠር ያደርገናል።

Filed in: Amharic