>

ዶ/ር ደረጀ ለሀገሪቱ ችግር መፍትሔ እንደማምጣት ሌላ ከፋፋይ አጀንዳ ይዞ መጥቷል...! (ጌታሁን ሄራሞ (ኢ/ር))

ዶ/ር ደረጀ ለሀገሪቱ ችግር መፍትሔ እንደማምጣት ሌላ ከፋፋይ አጀንዳ ይዞ መጥቷል…!

ጌታሁን ሄራሞ (ኢ/ር)


ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ ከርዕዮቱ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ጋር ያደረገውን ቃለመጠይቅ ተከታትዬ ነበር። በምልልሱ ዙሪያ የተፈጠሩብኝን አንዳንድ ጥያቄዎችን በውስጥ ሳጥን ለዶ/ር ደረጀ ለማቅረብ ያደረኩት ሙከራ ስላልተሳካ ወደ ገፄ መምጣት ግድ ሆኖብኛል።

በቃለ መጠይቁ ዶ/ሩ በቀደምት ቃለ መጠይቆች የነበረው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆኑን ይፋ አድርጎልናል፤ ሆኖም አመርቂ እንደሆነ የተነገረን የታዳሚዎቹ ግብረ መልስ ለዶ/ሩ ፈተና ሳይደቅንበት አልቀረም፤ ከቴዲ ጋር በነበረው ቆይታ የመሰለውን አልፎ አልፎም ከአንድ የዩኒቨርስቲ መምህር የማይጠበቁ ቃላትን ብቻ ሳይሆን ሐሳቦችንም እንዳሻው ሲሰነዝር ተዝበነዋል። በእኔ በኩል ትዝብቴን እንደሚከተለው ላቅርብ፦

1. ዶ/ር ደረጀ ረዘም ላለ ጊዜ ከማህበራዊ ሚዲያዎች ከጠፋ በኋላ ለሀገሪቱ ችግር መፍትሔ እንደማምጣት ሌላ ከፋፋይ አጀንዳ ይዞ መጥቷል፤ ኢትዮጵያውያንን ልክ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ሲያደርግ እንደነበረው በሁለት ጎራ ከፍሎአቸዋል፤ የመጀመሪያው ምድብ የኢትዮጵያን መሠረት እንደጣሉ የተናገረላቸው ሰሜናዊያኑ ማለትም የትግሬና የአማራ ብሔሮች ሲሆኑ በሁለተኛው ምድብ ያሉ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን “በደብዳቤ የተቀበሉ” ሌሎቹ ብሔሮች ናቸው። ቀደም ሲል ቴዲ ባለፈው የሀገረ መንግስት ታሪክ ሰሜኖቹ ደቡቦቹን ድምጥማጣቸውን ማጥፋት እየቻሉ ነገር ግን በምህረት እንዳለፏቸው ሲተነትን ነበር፤ ዶ/ር ደረጀ ደግሞ በተራው “አንተ እንዳልከው” እያለ ለቴዎድሮስ ዕብሪት ዕውቅናን ሰጥቷል። ሌላው የዶ/ር ደረጀ የክፍፍል አጀንዳ ኢትዮጵያዊያንን ነባርና መጤ/Late comers/ በማለት የመደበው ነው። በክልል ደረጃ ብዙ ደም እያፋሰሰ ያለውን የነባር/መጤ ትርክትን ወደ ሀገር ደረጃ አመንድጎታል። ፅንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞች የሚነገሩትን እየተከተሉ ፅንፈኛና ዛሬ ለሀገር አንድነት እምብዛም የማይፈይደውን ተመሳሳይ መንገድ መከተል ጥቅሙ አልታየኝም። ታሪክ የራሱ የሆነ እውነት ቢኖረውም የኋላውን ታሪክ ሌሎችን…ቁጫጭ፣ እኛ በፃፍነው በደብዳቤ ማንነታቸውን የተጎናፀፉ…እያሉ ለማኮሰስና ለማሸማቀቅ መጠቀም ከፅንፈኛ ብሔርተኞች ስህተት ጎራ የሚመደብ ጥፋት ነው። በአጭሩ የትንታኔውን ድምፀት(Tone) አልወደድኩትም።

2. ዶ/ር ደረጀ ብሔርተኝነትን አጥብቆ ሲጠላ ተመልክተናዋል፤ በግልባጩ ግን ራሱ ብሔርተኛ ስለመሆኑ ገና የተረዳ አይመስልም። አንድም ቴዲም ሆነ ዶ/ር ደረጀ ከሚናገሩት ሐቲት የሰሜኑን መሠረት የያዘ በአንዳንዶቹም “አቢሲኒያዊ” እየተባለ የሚጠራ ብሔርተኝነት አራማጆች ናቸው። ሁለቱም ኢትዮጵያ  በሚመጥናት የምርጫ እንጂነርንግና ደሞክራሲያዊው ሞዴል ሕብረ ብሔራዊነት ባማከለ መልኩ ሳይሆን በዚህ አቢሲኒያዊ ብሔርተኝነት እንድትመራ ጥሪ እያቀረቡ ነው፤ ስለዚህም የትግራይና የአማራ ብሔሮች የእርስ በእርስ ሽኩቻ አቁመው ወትሮም የነርሱ የነበረውን የፖለቲካ ሥልጣን እንዲረከቡ ድምፃቸውን እያሰሙ እንደሆነ መገንዘብ ያን ያህል አይከብድም። ዶ/ር ደረጀ ከዚህም በዘለለ ራሱን “አዲሳቤ” በሚለው ጎራ መመደቡ “Regional nationalist” ስለመሆኑም ጥቆማ ይሰጠናል። ብሔርተኝነትን እየጠሉ ብሔርተኛ ሆኖ መገኘት ምን ይባላል?

3. ሌላው የዶ/ር ደረጀ ሕፀፅ “ብሔርተኝነትን” በጅምላ ጭራቅ አድርጎ መሳሉ ነው። ይህ ከዘመኑ የፖለቲካ አውድ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። ባይሆን ብሔርተኝነትን “Moral Ethnicity” እና “Political Tribalism” በሚል ካምፕ ከፍሎ ማብራሪያውን ቢሰጥ ይሻል ነበር። ለምሣሌ ዶ/ር ደረጀ  የኢትዮጵያን ፀረ ቅኝ አገዛዝ እስከወዲያኛው እየደገፈ ብሔርተኝነትን በጅምላ መቃወሙም በራሱ የሚደገፍ አይደለም። ከጭቆና ለሚያለቅቅ ትግልና አርበኝነት ብሔርተኝነት እንደ “Power house” ሆኖ እንደሚያገለግል የዘነጋው ይመስላል።

4. ዶ/ር ደረጃ ስለ አማራ ብሔር ህላዌ ያነሳውም ሐሳብ አያሌ ጥያቄዎችን የሚጭር ነው። ለመሆኑ የአንድን ሕዝብ ስብስብ የብሔር ማንነት የሚወስነው ማነው? ፕሮፈሰር መስፍን? ዶ/ር ደረጀ? መንግስት? ወይስ የብሔር ምደባ መስፈርቶች? ወይስ ሕዝቡ ራሱ ማንነቱን ይወስናል? ከ1983 ወዲህ ኢሕአዴግ ከላይ ወደ ታች በሆነ መልኩ የዜጎችን የብሔር ማንነት Primordial በሆኑ Objective መስፈርቶች በመመደቡ እስከ ዛሬ እየተቃወምን ነው፤ ይህን የመንግስት ሚናን ግለሰቦች ተረክበው የብሔር ምደባውን አሁንም Objective በሆነ መልኩ ለመመደብ መሞከራቸው ገራሚ ነው። አሁን ባለንበት ዘመን የብሔር ማንነት ምደባ ከላይ ወደ ታች በመንግስት ወይም በግለሰቦች የሚወሰን ሳይሆን በየወቅቱ ተለዋዋጭ ሊሆን በሚችል ማህበራዊ ስሪትና Subjective መስፈርቶችም ጭምርም ይወሰናል። ዜጎች እስካመኑበት የጋራ ማንነት እንዳላቸው በሚገልፁ መስፈርቶች ዙሪያ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሔር አባል ነን የማለት ሙሉ መብት አላቸው። ጊዜና ሁኔታው አይፈቅድም እንጂ ሐሳቡን አያሌ ምሣሌዎችን እየጠቃቀሱ ማስረዳት ይቻላል፤ ለምሣሌ ያህልም ኮሶቮ ውስጥ የሚኖሩ የአልባኒያ ብሔር አባላት በአንድ ወቅት “እኛ በብሔር አልባኒያውያን ሳንሆን ግብፃውያን ነን” ብለው ለመንግስት ጥያቄን አቀረቡ። ይህን ማለታቸውን ከብሔር ንድፈ አንፃር ትንታኔ አኳያ በብዙ አቅጣጫ ማጤን ይቻላል፤ እናም የራሳቸውን ምክንያትና የዘር ሐረግ መዝዘው “ነን” ካሉ “አይደለችሁም” የሚል ማነው? ዛሬስ በኢትዮጵያ ውስጥ በፊት በአንድ ብሔር ሥር እንደነበሩ የሚነገርላቸው ነገዶች “እኛም ብሔር ነን” እያሉ ዕውቅናን እየጠየቁ አይደል? የብሔር ማንነት በማህበራዊ ስሪትና Subjective በሆኑ Situational መስፈርቶች ላይም የተመሠረተ ነው ስንል በምክንያት ነው።

ሌላው አስቂኙ ነገር ዶ/ር ደረጀ የአማራ ብሔር የሚባል ምደባ አለመኖሩን ለማሳየት የተጠቀመው የ”Regional identity” ማብራሪያ ነው። ለምሣሌ ጎንደሬው ጎጃሜውን እንዲህና እንደዚያ ስለሚለው የአማራ ማንነት ብሎ ነገር የለም ይለናል። ታዲያ ይህ በጂዖግራፊ የተማከለ Regional identity ሽኩቻ በኦሮሚያና በትግራይስ ቢሆን የለም? የወለጋው ኦሮሞ የባሌውን የአድዋው ትግሬ የእንደርታውን እንደዚህና እንደዚያ ብሎ ስለጠራው የኦሮሞም ሆነ የትግሬ ብሔር ማንነት የለም ብሎ መደምደም ይቻላል?

 5. ዶ/ር ደረጀ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአማራ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጡን በተመለከተ ሽንጡን ገትሮ ሲራገመው ታዝበነዋል። በተቃራኒው ደግሞ “እኔ በእግዜር የማምን ማርክሲስት ነኝ” በማለት ይናገራል። ማርክሲስቶች ግን የብሔርተኝነትን ውጤት(Effect) ብቻ አያጠኑም፣ ምንጩንም(Cause) ያጠናሉ። ለዚህም የአማራ ብሔርተኝነትን ማቆጥቆጥን በተመለከተ የአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ዲፓርትመንት ሌክቸረር የሆኑት አማኑኤል ተስፋዬ በአዲስ ስታንዳርድ ላይ “The Birth of Amhara Nationalism: Causes, Aspirations, and Potential Impacts” በሚል ርዕስ የፃፉትን ዶ/ር ደረጀ እንዲያነበው ምክሬን እለግሳለሁ። ሌክቸረሩ ለአማራ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ ወደ ስድስት ሰበቦችን አስቀምጠው ትንታኔ ሰጥተዋል። በሁለተኛ ምክንያታቸውም በድህረ ኢሕአዴግ በአማራው ብሔር ላይ የደረሰው ጥቃት፣ መፈናቃልና ግድያ ለአማራ ብሔር ማቆጥቆጥ ሰበብ ስለመሆኑ አንስተዋል። ማርክሲስቶችም ጭቆናን (Oppression) ለብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ ግንባር ቀደሙ ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ። ሰበቡን ትቶ ውጤቱ ላይ ብቻ ማብራሪያ መስጠት ዘለቂ መፍትሔን አያመጣም። አማራው በደረሰበት ግፍ ድምፃቸውን ያሰሙትን የአዲሱ ትውልድ አባላትን(አቶ አማኑኤልም ጠቅሰዋል) ዶ/ር ደረጀ “Demonize” ለማድረግ የሄደበት ርቀት ትክክል መስሎ አልታየኝም።

6. በመጨረሻም ዶ/ር ደረጀ ቃለ መጠይቁን በሚያምንበት የእምነት ተቋም ጥቅሶች መጠቅጠቁንም አልወደድኩለትም። ይህን ማድረጉ ምናልባት ስሜታዊ አድርጎኝ እኔንም ደስ ሊያሰኘኝ በተገባ ነበር። ነገር ግን ርዕሰ ጉዳዩ የሁሉም ነው፤ ኢትዮጵያም የሁላችንም ነች። በጋራ ጉዳይ መነሳት ያላባቸው የጋራ እሴቶች ናቸው። ፖለቲካዊ ትንተኔዎችን ለከትየለሽ በሆነ መልኩ  በምንከተለው ቤተ እምነት መስፈርቶችና ጥቅሶች ማስደገፍ በሌላው ቤተ እምነት ተከታዮች ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ ይከታል። ይህን ለዶ/ሩ ማሳሰብ አልነበረኝም…ግልፅና ማንም በቀላሉ የሚረዳው እውነት በመሆኑ!

ሰናይ ሰኞ

Filed in: Amharic