አርቲስት መላኩ አሻግሬ “የኢትዮጵያ ቴአትር ቀማሪ ” – (1925 – 1985 ዓ.ም)
ታሪክን ወደኋላ
መላኩ አሻግሬ ከአባቱ ከአቶ አሻግሬ ወርቅነህና ከእናቱ ከወ/ሮ ወርቅነሽ ይዘኸዋል በ1925 ዓ.ም አዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ ተወለደ፣ የወላጆቹ የትውልድ ሥፍራ ወደ ሆነው ጅሩ አውራጃ ተወስዶ ዋቢ ስላሴ ከተባለ ቦታ ከ1 እስከ 7 ዓመት ዕድሜው አደገ፤ የአባቱ በሕይወት መለየትን ተከትሎ እናቱ ወደ አዲስ አበባ በድጋሚ ስለመጡ ቀጨኔ መድኃኒዓለም የቄስ ት/ቤት ገባ፡፡ ትምህርቱን እስከ ዜማ ዘልቆ በዚያው በቀጨኔ መድኃኒዓለም፣ በአራዳ ጊዮርጊስ፣ በዩሐንስና በማርቆስ ቤተ ክርስቲያናት ድምጹ እጅግ የተዋጣና ያማረለት ዲያቆን ሆኖ አገልግሏል፡፡
የዘመናዊ የቀለም ትምህርቱንም በቅድስት ሥላሴ ት/ቤት፣ በተፈሪ መኮንና ሐረር በሚገኘው አሊያንስ ፍራንሴ ት/ቤት ለመከታተል የራሱን ጥረት ያደረገና በቤተሰብ ችግር ምክንያት በ1942 ዓ.ም ትምህርቱን አቋርጦ በማዘጋጃ ቴአትር ቤት (የአሁኑ አዲስ አበባ የባህልና ቴአትር አዳራሽ) ሥራ መሥራት ጀመረ፡፡ በዘማሪነት፣ በሥነ ስቅለት ውስጥ ከተሳተፈ በኋላ ድራማው ከመድረክ ሲወርድ መላኩ በዘፋኝነትና በከበሮ መቺነት በማዘጋጃ ቴአትር ቤት አገለገለ፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ በሀገር ፍቅር ቴአትር ንቁ መሪ በነበረው ማቴዎስ በቀለ በተደረሱ ድራማዎች በተዋናይነት እንዲሁም በዘፋኝነት ሠራ፡፡
የአዲስ አበባው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቅርንጫፍ ወደ ሐረርጌ ሲዛወር መላኩም ከማቴዎስ ጋር አብሮ ሄደ፡፡ ከ6 ወር ቆይታ በኋላ ማቴዎስ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ “አንድነት ቴአትር ማኅበር”ን ሲመሠርት መላኩም በማኅበሩ ተቀጠረ፡፡ የቴአትር ቡድኑ ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጉዞ በነበረበት ወቅት በቡድኑ አለመግባባት በመፈጠሩ፣ መላኩ ከሥራው ተሰናብቶ ጅማ በመቅረት በከተማው ማዘጋጃ ቤት የርስት ክፍል በፀሐፊነት ተቀጠረ፡፡ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር የተመለሰው ብዙም ሳይቆይ ነው፡፡
በወቅቱ የቅጥር ሁኔታው በተዋናይነት ሳይሆን በሀገር ፍቅር ማኅበር ይታተም ለነበረው “የኢትዮጵያ ድምፅ” በጋዜጠኝነትና በአስተዳደር ነክ ሥራዎች ነበር፡፡ ከሚያዚያ 1946 እስከ የካቲት 1949 ዓ.ም ሰራና በስንብት መሥሪያ ቤቱን ለቅቆ በክብር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን በሲቪልነት ተቀጠረ፡፡
የሙዚቃ ቡድኑ “ወታደርና ጊዜው” የተባለ ጋዜጣ የማውጣት፣ ቴአትርና ሙዚቃ የማቅረብ ኃላፊነት ስላለው ከሀገር ፍቅር ያካበተውን ልምድ በመጠቀም መልካም እንቅስቃሴን አሳይቶ “ሴት አረዳችኝ” እና “ሰይጣን ለወዳጅ ቅርብ ነው” የተሰኙ ተውኔቶችን ደርሶ ለሠራዊቱ አባላት አሳየና ምንም ክፍያ ስለሌለው ያለጦሩ ፈቃድ በቀድሞው የማዘጋጃ አዳራሽ ውስጥ ለሕዝብ በማቅረቡም ተዋንያኑ ታሠሩ፣ መላኩም ተሰውሮ በዚያው ከክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ተለያየ፡፡ በመቀጠል የራሱን ተዋንያን አሰልጥኖ፣ የአቅርቦት ወጪ በመበደር ድራማውን ወደ ጅማ ወሰደው፡፡ ጅማ ላይ ከመግቢያ ዋጋ የተሰበሰበውን ገንዘብ ያዡው ይዞ በመሰወሩ መላኩና ተዋንያኑ የመመለሻ ገንዘብ አጥተው ትሬንታ ኳትሮ ለምነው አዲስ አበባ ደረሱ፡፡
እንደተመለሱ ነፍሰ ጡር ባለቤቱ ወ/ሮ ትፍስሀት አያሌው በመላኩ ላይ በደረሰው ኪሳራ ምክንያት ለችግር በመዳረጓ ትዳራቸው ሳንካ ገጠመው፡፡ በኋላ ሽማግሌ ከመሀል ገብቶ መላኩ ዳግመኛ በቴአትር ሥራ ዕዳ እንዳያመጣ ቃል ገብቶ ታረቁ፡፡
መላኩ ለመድረክ ጥበብ የተፈጠረ በመሆኑ የቴአትር ጥበብ በሀገራችን እጅግም ባልተስፋፋበትና በኅብረተሰቡ ክፍል ባልታወቀበት ዘመን የተገኘ ከያኒ ነው፡፡ የቴአትሩን ታላቅነትና ጥበቡን ለመላው የሀገራችን ሕዝብ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው የቅርብ ጊዜ ትውስታው ይናገራል፡፡ በሕይወት ዘመኑ የጥበብ ዝንባሌ ያላቸውን ወገኖች በማሰባሰብ በሙያው አሰልጥኖና አስተምሮ በ “ቴዎድሮስ የቴአትር ክበብ” ድርጅት ሥራ አደራጅቶ በርካታ ተውኔቶችን ጽፎ፣ ራሱ አዘጋጅቶ እየተወነና እያስተወነ ከመሃል እስከዳር ሀገር በመኪና፣ በባቡርና በአውሮፕላን፣ በጋማ ከብትና በእግር ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይል ለጥበብ ባለው ከበሬታ ደክሟል፡፡ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ መቃረቢያ ድረስ በተለያዩ ቦታዎች ትምህርት ሰጪና አንቂ ቴአትሮችን ለከተማና ለገጠሬ ወገኖች በማቅረብ የጥበቡን ብርሃን በስፋት አብርቶ ቴአትር ዛሬ ለደረሰበት ዕድገት ችግኙን ተክሎ ያለፈ ፋና ወጊ እንደነበር ቀሪ ሥራዎቹ ይመሰክራሉ፡፡
መላኩ ከ1950 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ዋና ጽሕፈት ቤትና በተለያዩ ት/ቤቶች በመምህርነት ያገለግል በነበረበት ወቅት ከባለቤቱ እየተደበቀ ተውኔት አላቋርጥ አለ፡፡ በ1954 ዓ.ም ተስፋዬ ገሠሠ የጻፈውን “ክህደት የኑሮ መቅሰፍት” የተሰኘውን ተውኔቱን “ዓለም ጊዜና ገንዘብ” በሚል ርዕስ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር አቀረቡ፡፡ ድራማውም አንዴ ታይቶ ስለታገደ መላኩ ዳግመኛ ከዕዳ ላይ ወደቀ፡፡ ወ/ሮ ትፍስህት የገባላትን ቃል ስላፈረሰ የመጀመሪያ ልጃቸውን ይዛ ከመላኩ ተለየች፡፡ ይህ ትዳር በመፍረሱም መላኩ ለመድረክ ያልበቃውን “አርብ ጥላኝ ሄደች” የሚል ተውኔት ጻፈ፡፡ አቶ ከበደ ሚካኤልም የደረሰበትን ሁኔታ ለንጉሠ ነገሥቱ በማስረዳት ንጉሡ ለመላኩ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ብር ለግሰው ከዕዳ ሊላቀቅ ችሏል፡፡
መላኩ የዲሲፒሊን ኮሚቴ ፀሐፊ ሆኖ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር እየሠራ በቴአትር አቀናባሪው በሪቻርድ ጠያቂነት በ1952 ዓ.ም ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ተዛወረ፤ ብዙም ሳይቆይ እንደገና ወደ ትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ተመልሶ በሥነ ጥበብ ዋና ዳይሬክሲዮን የድራማ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ተመደበ፡፡ በ1956 ዓ.ም ደግሞ ወደ ቀለመወርቅ ት/ቤት በቴአትርና በመዝሙር አስተማሪነት ተዛወረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ወደ ገፈርሳ ት/ቤት ተቀየረ፡፡ ከቦታ ቦታ እንዲዘዋወር የተደረገው እንደ ዲሲፒሊን እርምጃ ተቆጥሮ ነው፡፡ መላኩ ከማስተማር ይልቅ ድራማ በመጻፍና በመድረኩ ላይ እያተኮረ ተዋንያን ተማሪዎችን ናዝሬት፣ አሰላ፣ እና የመሳሰሉት ከተማዎች ይዞ በመሄዱ ከትምህርት ሚኒስቴር በተለይም ከረዳት ሚኒስትሩ በየጊዜው ጥብቅ ማስጠንቀቂያዎች ደርሰውታል፡፡
መላኩ አሻግሬ ወጣቶችን በማሰባሰብ የአተዋወን ዘዴን ካስተማራቸው በኋላ ተውኔቱ ወደ ተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች እየተዘዋወረ እንዲታይ ማድረጉ ጥንካሬውን አጉልቶ ያሳየ ተግባሩ ነው፡፡ ሌሎችም በመከተል ኤሌክትሪክ በሌለበት ፋኖስና ሻማን በመጠቀም፤ አዳራሽ የሌለበት ቦታ በድንኳን የሜዳ ትርኢቱን ያቀርብ ነበር፡፡ በድራማ ብዙ ገንዘብ ያሰባሰበ ቢሆንም ለጋስ በመሆኑና የቸገረውን በመርዳት ስለሚታወቅ ያኖረው ቅሪት አልነበረም፡፡ በበጎ አድራጊነቱም ለቀይ መስቀል 11,670 ብር ከገቢው መስጠቱ ይነገራል፡፡
በ1968 ዓ.ም ሐምሌ 1 ቀን በብሔራዊ ቴአትር ተቀጠረ፤ በ1981 ዓ.ም ጡረታ ወጣ፡፡ በዚህን ወቅት ከሁለተኛ ሚስቱ ከወ/ሮ አልማዝ ጋር ተለያይቶ ሦስተኛ ሚስቱን ወ/ሮ ደብሪቱን አገባ፡፡ “አንድ ጡት”ን ጽፎ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ለሕዝብ አቅርቦና የገንዘብ አጠቃቀሙንና አያያዙን አሻሽሎ መኪና ሊገዛና ቤት ሊሰራ ችሏል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል መላኩ ልጆቹንና ቴአትሮቹን ቅርሶቹ አድርጎ ያለፈና ለ10 ዓመታት የተዘነጋ ከያኒ ነው የሚሉም አሉ፡፡ አሟሟቱን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ቢሆንም ወደ ደቡብ በሄደበት ወቅት ለወባ መከላከያ የዋጠው ኪኒን ጉበቱ ላይ አርፎ በዚያ ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ በሕክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ ሕይወቱ ሰኔ 1 ቀን 1985 ዓ.ም ሊያልፍ ችሏል፡፡
መላኩ አሻግሬ የሚታወቀው በደራሲነት፣ ተዋናይነት፣ ቴአትር አዘጋጅነትና በዳንኪረኛነት (ሽብሻቦ) ነው፡፡ 26 የሚደርሱ አጫጭርና የሙሉ ጊዜ ተውኔቶችን ጽፎ እየተወነም አዘጋጅቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።
1. ክህደት
2. የኑሮ መቅሰፍት
3. ማጣትና ማግኘት
4. ዓለም ጊዜና ገንዘብ
5. ሽፍንፍን (1959) ቁጥር 1 እና 2
6. አዬ ሰው (1962)
7. ማሪኝ (1960)
8. የለሁም ብለው ጉድ ፈላ (1969)
9. ምን ዐይነት መሬት ናት? (1972)
10. አንድ ጡት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ ከአጫጭር ተውኔቶችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ደግሞ ይቅርታሽን፣ ግንድ አልብስ፣ ጤና ይስጥልኝ፣ ሱሚ ነው ይገኙበታል፡፡
መላኩ አሻግሬን ትልቅና አንቱ ከአሰኙት ቴአትሮች ውስጥ “ዓለም፣ ጊዜና ገንዘብ” ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ፍልስፍናና ሳቅ ጫሪ እንዲሁም ወቅታዊ በሆነ መልኩ የተጻፈ ቴአትር ቢሆንም በተከታታይ ለመድረክ ቀርቦ ለሕዝብ ሊታይለት አልቻለም፡፡ ይሁንና እድሜው ለሥራ ከደረሰበት ወቅት አንስቶ እስከ ዕለተ ሞቱ በቴአትር ዓለም ውስጥ ኖሯል፡፡
በተወነባቸው ቴአትሮች በአመዛኙ የማሳቅ ችሎታና ብቃቱ እጅግ የተዋጣና ያማረ ነበረ፡፡ በሞት እስከተለየበት ሰኔ 1 ቀን 1985 ዓ.ም እንደ እነ ማቴዎስ በቀለና ሌሎችም የሚደነቁ አንጋፋ የቴአትር መምህሩን አርአያነት የተከተለና በርካታ ተዋንያንን ያፈራ ከመሆኑም ሌላ ለኢትዮጵያ የቴአትር ዕድገት ፋና ወጊ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ተዋናይ፣ ደራሲ፣ አዘጋጅ ለሚሆኑ ወጣቶች የተውኔት ሀሁ አስቆጥሮ ለመድረክ ያበቃ፤ ቴአትርና ሙዚቃን በክፍለ ሀገራት በመዘዋወር ቄጤማ ጉዝጉዞ፣ መድረክ ገንብቶ፣ ጥበብን ለሕዝብ ያዳረሰ ድንቅ የሥነ ጥበብ ፈርጥ ነበር፤ መላኩ አሻግሬ፡፡