>
5:21 pm - Sunday July 21, 3907

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ማን ናቸዉ? (ደብረ ኤልያስ የጥበብ ማዕከል)

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ማን ናቸዉ?

-ደብረ ኤልያስ የጥበብ ማዕከል 


ጎጃም በሃገራችን ዉስጥ ታላላቅ ስራዎችን የሰሩ የሊቃዉንት መፍለቂያ ምድር ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻዉም፡፡

#በጎጃም ምድር በደብረ ኤልያስ ወረዳ ተወልደዉ በደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስትያን ተምረዉ ለሃገራቸዉ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያ ታላላቅ ስራዎች የሰሩትን ሁለተኛዉ የኢትዮጵያ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ (1902-1968) እናስተዋዉቃችሁ

ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በቀድሞዉ ጎጃም ክፍለ ሃገር በአሁኑ በምስራቅ ጎጃም ዞን  በደብረ ኤልያስ ወረዳ ሚያዚያ 16 ቀን 1902 ዓ/ም  ከአባታቸው ከአቶ ወልደማርያም ውቤና  ከእናታቸው  ከወ/ሮ ዘርትሁን  አደላሁ ተወለዱ ፡፡

ቤተሰቦቻቸው መጀመሪያ ያወጡላቸው መጠሪ ስም “መልዕክቱ” ነበር ፡፡ መልዕክቱ እድሚያቸው ለትምህርት ሲደርስ በተወለዱበት ቤተ-ክርስቲያን ንባብ ከመርጌታ ረዳኸኝ፣ ዜማ ከግራ ጌታ ሳህሉ ቅኔና የመጽሀፍ ትርጓሜ ከእውቁ መምህር ገብረ ስላሴ ተምረው ቅኔ ተቀኘተው በቅኔ መምህርነት ተመርቀዋል፡፡

በ1920 ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመጽሐፍት ሀዲሳትን፣ የፍትሀ ነገስትን ትርጓሜና የአቡሻክርን ትምህርተ ሚስጥራት ከመምህር ሐዲስ ተክሌ፣ በኋላ ንቡረ እድ ተክለሃይማኖት፣ በመጨረሻም ብፁእ አቡነ ዮሐንስ ይባሉ ከነበሩት ታለቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ጠንቅቀው ተምረዉ ለመምህርነት በቅተዋል፡፡

አባ መልዕክቱም በፈንታቸው ጉባኤ ዘርግተው በማስተማር አያሌ ሙህራንን አፍተዋል ፡፡ በ1930 ዓ/ም በ27 ዓመታቸው መንፈሳዊውን ጎዳና በመምረጥ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ማዕረገ ምንኩስና ተቀብለዋል ፡፡

በ1934 ዓ/ም ቀዳማዊ ኃይል ስላሴ ከሃያ አብያተ ቤተ ክስርስቲያናት  ሊቃውንት ተመርጠው በዚያን ጊዜ ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት/አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ/ ቅጽር ግቢ ዘመናዊ ትምህርት በተለይም እንግሊዘኛ ቋንቋ እንዲማሩ ከተደረጉት መካከል ትምህርቱን ፋጻሜ ላይ ካደረሱት አንዱ አባ መልዕክቱ ነበሩ፡፡

የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በ1935 ዓ/ም መንፈሳዊና ስጋዊውን  ትምህርት አጣምሮ በሚሰጥ መልኩ ሲቀየስ፣ በትምህርት ሚኒስተር ስር ሆኖ በእሳቸው የበላይ አስተዳዳሪነት እንዲመራ ተደረገ፡፡ በዚያው ዓመት የመካነ ስላሴ ገዳምንም እንዲያስተዳድሩ በመምህርነት ማዕረግ ተሾሙ፡፡  በ1938 ዓ/ም ገዳሙ “መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ” ተብሎ በግርማዊ ጃንሆይ ሲስየም አስተዳዳሪው ፣ “ሊቀ ስለጣናት” እንዲባሉ ስለተፈቀደ ሊቀ ስልጣናት መልዕክቱ ተብለው ከንጉስ ነገስቱ የራስ ወርቅና ካባ ላንቃ ሽልማት አግኝተዋል፡፡

በኢትዬጵያና በእስክንድሪያ ቤተ ክርስቲያናት መካከል ለኢትዬጵያዊያን የጵጵስና ማዕረግ እንዲሰጥ ስምምነት ሲደርስ ሚያዚያ 19 ቀን 1938 ዓ/ም በአዲስ አበባ በተደረገው ምርጫ ከአምስት እጩዎች መካከል አንዲ ሊቀ ስልጣናት መልዕክቱ ነበሩ ፡፡ ነገር ግን በእስክንድሪያ ቤት ክርስቲያን በተፈጠረው ችግር ምክንያት ለሁለት ዓመት ሹመቱ  ዘግቶ ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ/ም በእስክንድሪያው ፓትሪያሪክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ብፁዕ አብነ ቴዎፍሎስ ተብለው የሐረርጌ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡

በ1942 ዓ/ም በቅዱስ ሲኖዶስና በብፁዕ አቡነ ባስልዬስ መልካም ፈቃድ የሊቀ ጳጳሱ እንደራሴ ሆኑ ፡፡ በዚህ በያዙት ጵጵስና እንደራሴነት ላይ በ1943 ዓ/ም ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ባስለዬስ በኢትጵያ የብፁዕ ወቅድሱ አቡነ ዮሳብ ወኪል እንዲሆኑ ተደረገ፡፡የኢትዬጵያ ቤተ ክርስቲያን በ1951 ዓ/ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ከፍተኛዉን የፓትርያሪክነት መብት ካገኘች በኋላም ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በያዙት ሀገር ስብከት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ተሰጣቸዉ፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ፣ለተወሰነ ወራት ተጠባባቂ ፓትርያሪክ በመሆን ከቆዩ በኋላ መጋቢት 29 ቀን 1963 ዓ/ም በተደረገዉ ምርጫ ቀዳሚ ሆነዉ ተመረጡ፡፡በዓለ ሲመታቸዉ ግንቦት 1 ቀን 1963 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስትያን ንጉሰ ነገስቱ፣ሊቃነ ጳጳሳት፣ካህናት፣የዉጭ ሃገር አብያተ ክርስትያናት መሪዎች ተወካዮች ፣ዲፕሎማቶች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በደማቅ ታሪካዊ ስነ ስርዓት ተከብሯል፡፡ይህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከራሷ ተወላጆች ፓትርያሪክ መርጣ በራሷ ምድር በራሷ ሊቃነ ጳጳሳት ስትሾም ነበር፡፡ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ መንግስት ከስልጣናቸዉ ወርደዉ እንዲታሰሩ እስከተደረገበት እስከ የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ/ም ድረስ በፓትርያሪክነት ስልጣን ላይ ቆይተዋል፡፡

አቡነ ቴዎፍሎስ ከ1935 እስከ 1968 ዓ/ም ባሉት 33 ዓመታት ከላይ በተጠቀሱት የስልጣን ደረጃዎች በቆዩበት ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ታሪክ ዉስጥ እንደ እንቁ ሲያበሩ የሚኖሩ ታላላቅ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ከመምህር እስከ ፓትርያሪክነት የፈጸሟቸን ዓበይት ተግባራት ሙሉ በሙሉ በዝርዝር ማቅረብ ከቶዉንም የማይሞከር ነዉ፣ነገር ግን ለዝክረ ነገር ያህል የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስንና የመምህር ኪዳነ ማርያም ጌታሁን መጽሃፍቶችን መሰረት በማድረግ፣ጥቂቶችን እንሆ በረከት እንላለን፡-

አቡነ ቴዎፍሎስ በመምህርነታቸዉ የቤተ ክርስትያን የቅዳሴ መጻሕፋት ከግዕዝ ወደ አማረኛ ተርጉመዋል፡፡የዳዊትን ትርጉም አርመዉና አስተካክለዉ ለህትመተ ብርሃን አብቅተዋል፡፡በትምህርቱ ዘርፍ አያሌ የቤተ ክርስትያን ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል፡፡የመንፈሳዊ ኮሌጅ ከተቋቋመ ወዲህ ፣የኮሌጁ አስተዳዳሪ በመሆን ለቤተ ክርስትያኗ የዘመናዊ ዕዉቀት በር ከፋች የሆኑ ምሁራንን አፍርተዋል፡፡ከዚህ በተጨማሪ አያሌ መንፈሳዊ ወጣቶችን ወደ ዉጭ አገር ለመንፈሳዊ ትምህርት በመላክ ለቤተክርስትያኗም ሆነ ለሃገራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ምሁራንንና ተመራማሪዎችን አስገኝተዋል፡፡በሃረርጌ ጠቅላይ ግዛት ዘመናዊ፣የመነኮሳት ፣ቀሳዉስትና ዲያቆናት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶችን ከፍተዋል፡፡ከነዚህም በሀረር ከተማና በቁልቢ ገዳም የከፈቱትን ለናሙና መጥቀስ ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ከልጆቿ መካከል አበዉ መነኮሳትን መርጦ ጳጳሳትን ለመሾም እንድትችል ለረዥም ጊዜ ከእስክንድርያ ቤተ ክርስትያን ጋር በተደረገ ዉይይት ቅዱስነታቸዉ ታሪክ የሚያስታዉሰዉ ሚና ተጫዉተዋል፡፡የኢትዮጵያን መልዕክተኞች በመምራትና ዉይይቱ ፍሬያማ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡

የብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ሐዋርያዊ ተልዕኮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በመንቀሳቀስ በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በማጥመቅና አብያተ ክርስትያናትን በመመስረት ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ይልቁንም በአሜሪካ፣በትሪንዳድ፣በቶቤጎ፣በብሪትሽ ፣ጊያናና በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያናት እንዲሰሩና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት በመላዉ ዓለም እንዲሰራጭ ያልተቆጠበ ሃዋርያዊ ጥረት አድርገዋል፡፡

አርቆ አሳቢ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስትያን የመንግስት ጥገኛ ሆና የምታገኘዉ መተዳደሪያ ዘላቂነት የሌለዉ መሆኑን አስቀድመዉ በመገንዘባቸዉ ራሷን ችላ በራሷ ገቢ የምትተዳደርበትን የሰበካ ጉባኤ አደራጅተዉ በቃለ አዋዲ እንዲመራ አድርገዋል፡፡ይህን ስልት ቀድመዉ ባይቀይሱ ኖሮ የቤተ ክርስትያን ንብረት፣እርስትና ህንጻ በተወረሰ ጊዜ የቤተክርስትያን እጣ ፈንታ ጨርሶ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ከዉጭ አብያተ ክርስትያናት ጋር የነበራትን ግንኙነት በማደስና በማጠናከር ፣እንዲሁም አዳዲስ ግንኙነቶችን እንድትመሠርት በማድረግ የፈጸሙት ተግባር ወደር የለሽ ነበር፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የዓለም አብያተ ክርስትያናት ጉባኤ መስራች አባል እንድትሆን ያደረጉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1940 ዓ/ም በአምስተርዳም ፣ሆላንድ በተካሄደዉ መስራች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ መልዕክተኞች መርተዉ ተሳታፊ በመሆናቸዉ ነበር፡፡ከዚህ በኋላ ይህ ጉባኤ ባካሄዳቸዉ ተከታታይ ጉባኤዎች የኢትዮጵያን ልዑካን በመምራት ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡በወቅቱም በነበራቸዉ ንቁ ተሳትፎ የዚህ ጉባኤ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነዉ በመመረጥ የሃገር መኩሪያነታቸዉን አስመስክረዋል፡፡

አቡነ ቴዎፍሎስ ከመላዉ አፍሪካ አብያተ ክርስትያናት ሶስት ፕሬዜዳንቶች መካከል አንዱ በመሆን ለሁለት ጊዜ በተከታታይ በተደረገዉ የፕሬዘዳንቶች ምርጫ ተመርጠዉ ለእስር እስከተዳረጉበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል፡፡

በ1961 ዓ/ም በአቢጃን፣አይቮሪኮስት የተካሄደዉን የዓለም አብያተ ክርስትያናት ጉባኤ በፕሬዘዳንትነት የመሩት አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ፡፡በ1963 ዓ/ም የዓለም አብያተ ክርስትያን ማህበር ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመጋበዝ የጉባኤዉ ተካፋዮች የኢትዮጵያን ቤተክርስትያንና ታሪክ ጥንታዊነትን በይበልጥ እንዲገነዘቡ አድርገዋል፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መሪነት በሃይማኖቱ መስክ ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች በተገቢዉ ሁኔታ ተጠብቀዉ ለቀጣይ ትዉልድ እንዲተላለፍ ያልተቃጠበ ጥረት አድርገዋል፡፡ለዚህም ስኬታማነት የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መምሪያ በመንበረ ፓትርያሪኩ ስር እንዲቋቋም ከማድረጋቸዉም በላይ ቅርሶች በዘመናዊ ዘዴ እንዲጠበቁ በ1962 ዓ/ም በአሜሪካ ከሚገኘዉ የብሄራዊ የሰብአዊ ጥናቶች መረጃ ድርጅት የገንዘብና የመሳሪያ ዕርዳታ በመጠየቅ በየገዳማቱና በየአድባራቱ የሚገኙት የብራና መጽሀፍትና የኪነጥበብ ዉጤቶች በማይክሮ ፊልም እንዲቀረጹ አድርገዋል፡፡በልማት መስክም ካከናወኗቸዉ ታላላቅ ተግባራት አንዱና ዋናዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የልማት ኮሚሽን ማቋቋማቸዉ ነበር፡፡በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በመንፈሳዊ ተልዕኮ ብቻ ሳትወሰን በተቻላት አቅም በልማት መስክም ከመንግስት ጎን ተሰልፋ ረሃብን፣ድርቅን፣ድንቁርናን እና በሽታን የምትዋጋበት መንገድ ቀይሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የልማት ኮሚሽን በታህሳስ 26 ቀን 1964 ዓ/ም ጀምሮ በመንበረ ፓትርያሪኩ ወገኖቻችንን ለረሀብና ለሞት አደጋ በተጋለጡበት ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አቅም የሚፈቅደዉን የገንዘብ እርዳታ እንድታደርግ አድርገዋል፡፡በዚህም ሳይወሰኑ በሰዋሰዉ ብርሃን ቅዱስ ጳዉሎስ ትምህርት ቤት ቅጽር ግቢ አንድ የህጻናት ማሳደጊያ ድርጅት እንዲቋቋም በማድረግ በረሃቡ እናትና አባታቸዉ የሞቱባቸዉ 50 ታዳጊ ህጻናት ከወሎ መጥተዉ በድርጅቱ እንዲረዱ አድርገዋል፡፡በዚህ መልክ የጀመሩት የምግባረ ሰናይ ድርጅት ዛሬ ቤተክርስትያኗ አጠናክራ በሰፊዉ ለምታካሂደዉ መሰል ተግባራት መሰረት ሁኗል፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በሃገር ዉስጥና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ላከናወኑት ፈርጀ ብዙ ታላላቅ ተግባራቸዉ በግንቦት 28 ቀን 1965 ዓ/ም አሜሪካን አገር የሚገኘዉ የቦስተን ዩኒቨርስቲ ለቅዱስነታቸዉ የቴኦሎጅ የክብር ዶክተርነት ዲግሪ ሰጥተዋቸዋል፡፡

አቡነ ቴዎፍሎስ የትዉልድ ስፋራቸዉን ከሀገር ጉዳይ የሚያስቀድሙ አባት አለመሆናቸዉን ማንም የሚመሰክረዉ ሀቅ ቢሆንም የደብረ ኤልያስን ዉለታ ግን አረሱም ነበር፡፡ለዚህም ምንም እንኳ እንደ ቃላቸዉ ባይተገበርም በግል ገንዘባቸዉና ከባንክ ተበድረዉ ከብሄራዊ ስታዲየም ጀርባ ያስገነቡትን ቤት አስመልክተዉ በጽሁፍ ካሰፈሩት የኑዛዜ ቃላቸዉ መረዳት ይቻላል፡፡በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ ፓትርያሪክ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ባሳተሙት መጽሀፍት ዉስጥ የሰፈረዉ የኑዛዜ ቃላቸዉ ቤቱን ለገነተ ኤልያስና ለጎፋ ገብርኤል እንዳወረሱ በሚከተለዉ መልኩ ያብራራል፡፡

“በአዲስ አበባ ከተማ በብሄራዊ ስታዲየም በስተጀርባ በቁጥር——-ካርታ የተነሳዉን ቦታዮንና በላዩ ላይ የሰራሁትን ፎቅ ቤት ከነ መኪና መቆሚያ ቤቱ በስጋ ብቻ ሳይሆን በጥምቀትም ከሥላሴ ለተወለድኩበትና ከሰፊዉ የመንፈሳዊ ትምህርት ገበታ በመጀመሪያ የተሳተፉኩበት በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ለሚገኘዉ ለደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስትያን የህይወቴን ዘመን ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲዉል ለመረጠኝ አምላክ መመስገኛ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ምዕመናን መጠቀሚያ ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ በጎፋ ሰፈር በግል ገንዘቤ በገዛሁት ቦታ ላይ ላቋቋምኩት ለመካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ርስት አድርጌ በዚህ ጽሁፍ ሰጥቻለሁ፡፡”

በመጨረሻ ይህን መሰል እጅግ ከፍተኛና ፍሬያማ የሆነ አገልግሎት በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያበረከቱ አባት ከየካቲት 9 ቀን 1968 ዓ/ም እስከ ሐምሌ 7 ቀን 1971 ድረስ በእስር ቤት ብርቱ ስቃይና መከራ ሲቀበሉ ከቆዩ በኋላ በግፍ ተገድለዉ ሰማዕት ሆነዉ አልፈዋል፡፡

Filed in: Amharic