>

መንፈሳዊ መቀንጨር፤ መንፈሳዊነት + ካድሬነት...! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መንፈሳዊ መቀንጨር፤ መንፈሳዊነት + ካድሬነት…!

ያሬድ ሀይለማርያም


ስለ ግለሰብ ባልጽፍ ደስ ይለኛል። በሃሳቦችና በተቋማት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ናቸው አገራዊ ፋዬዳም ሆነ ትምህርት የሚገኝባቸው። ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች የተቋም ያህል ይገዝፉና በበጎም ይሁን በመጥፎ ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ይሆናሉ። በጎ እሳቢያቸው የብዙዎችን ህይወት የማለምለምና አገርን የመጥቀም አቅም ያለውን ያህል ጭንጋፍ አስተሳሰባቸው ደግሞ የዛኑ ያህል ትውልድ የማጉበጥ፣ አገርን የመጉዳት እና የመጥፎ እሳቤ ተምሳሌት የመሆን አቅሙም የዛኑ ያህል ይሆናል።

በዚህ ትዝብቴ ማተኮር የፈለኩት የመንፈሳዊ ሰዎች ወይም በጏይማኖት ጥላ ስር መልካም ዝናን ያተረፉ፣ ብዙ ተከታይ ያፈሩ፣ እውቅናን ያተረፉና በሹመትም የከበሩ ሰዎች የአንድን አገር ፖለቲካ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለማረቅ አቅም ይፈጥርላቸዋል። ለዚህ ብዙም እርቀን ሳንሄድ ቄስ ዴዝሞን ቱቱን ማሰብ ይቻላል። ሌሎችም ከሳቸውም ደረጃ የማይስተካከሉ ቢሆንም ቡዙ የፖለቲካውን ጫና ተገዳድረው እስከ መጨረሻው ለእውነት የቆሙ ሰዎችን ለእማኝ መጥቀስ ይቻላል። የፖለቲካ መንፈስ በሞራል እሴቶች የተገራ አይደለም። እንደ ፖለቲከኛው የአስተሳሰብ ብቃት እና እንደቆመበት ጫፍ ይለያያል።  የሃይማኖት መንፈስ ግን ልጓም አለው። የተገራና ልኬትም ያለው ነው። መነሻና መድረሻው የሚታወቅ፣ ሰዎች በውስጡ እየገቡ የሚፈተኑበት፣ ያልቻሉ የሚወድቁበት፣ የቻሉ የሚጸኑበት ነው። ከሰው ሰው ወይም ከቦታ ቦታ አይለያይም።

ትልቁ ጥያቄ ሁለቱ የፖለቲካና የሃይማኖት መንፈሶች ተጣምደው በአንድ ሰው ላይ ሲገጣጠሙ ያ ሰው እንዴት ያስተናግዳቸዋል የሚለው ነው።  ለዚህ ጽሑፌ ዋና ምክንያት ወደሆነኝ ጉዳይ ላምራ።

ከድቁና ወደ ፖለቲካው መንደር የመጡት፣ በመንፈሳዊ ህይወት ማዕረግም ምዋዕለ ዘጥበባት የተባሉት፣ ቤተክርስቲያን ያፈራቸቻው፣ በመንፈሳዊ ህይወታቸው በሰፊው የሚታወቁት ዲያቆን ዳንኤል አራት ኪሎ ቤተመንግስት ከከተሙ ወዲህ፤ በተለይም ላለፉት ሁለት አመታት አንደበታቸው እሳት ሲተፋ፣ ብዕራቸው ጥላቻን፣ ጸብን፣ እልቂትን እና የርስ በርስ ግጭትን ሲያራግቡ ባይ ጊዜ የተበላሸው ፖለቲካችን መንፈሳዊ ህይወትን የማንበርከክ አቅሙን እሳቸው ላይ አጉልቶ ማሳየቱን ነው የታዘብኩት።

እርግጥ ነው ሥልጣንና መንፈሳዊነት ብዙም አብረው የሚሄዱ ነገሮች አይደሉም። ለመንፈሳዊነት የተረታ የፖለቲካ ስልጣን ብዙም አላውቅም። መንፈሳዊነት ለስልጣንና ለፖለቲካ ሲረታ ማየት የተለመደ ክስተት ነው። እሳቸው ከድቁና ወደ ካድሬነት በመምጣት የመጀመሪያው አይደሉም። ግን በዚህ ደረጃ ይከሽፋሉ ብዬ አልገመትኩም።  ምክንያቱም ሲያስተምሩ፣ ሲጽፉበት እና ስያገለግሉት የኖሩት የቤተክርስቲያን የሰላምና የፍቅር ቋንቋ፣ እሴትና የሞራል ልዕልና እንዲህ ቁልቁል እንዳይወርዱ ድጋፍ ይሆናቸዋል የሚል እምነት ነበረኝ። እንዴት በቤተክርስቲያን ውስጥ ያደገ፣ በቤተክርስቲያን እሴት ታንጾ ለመንፈሳዊ ማዕረግ የበቃ፣ ሰላምና ፍቅርን ይሰብክ የነበረ ሰው ከሰላም ይልቅ ጦርነትን፣ ከእርቅ ይልቅ በቀልን፣ ከእውነት ይልቅ መድሎና ሀሰተኛነትን ምርጫው ያደርጋል። የኤርትራ ጦር ኢትዬጵያ አልገባም ከሚለው አይን ያወጣ የአደባባይ የሀሰት ስብከት አንስቶ እንደገብስ እሸው እያሉ ያራገቡት የእርስበርስ ጦርነት ዛሬ በእርቅ፣ በሰላም፣ በድርድር ሲፈታ ሲያዩ ዲያቆን ፖለቲከኛ ዳንኤል ምን አሉ ይሆን እያልኩ ሳስብ ከዚህ በታች ያለውንና ሌሎች በትዊተር ያጋሯቸውን መልዕክቶች ሳይ ድቁና ወይም መንፈሳዊነት ከፖለቲካ ጋር ጋብቻ ሲፈጥሩ የመንፈስ መቀንጨርን እንደሚያስከትል በሳቸው ላይ አየሁ። በአንድ መድረክ እንዴት ከወያኔ ጋር እርቅ ይውረድ ይባላል ብለው ሰላም ሰባኪዎችን ሲፎትቱም አይቻለሁ።

መቼም ክፉ ጊዜ ክፉ ነው ብዙ ያስተዛዝባል። ገለባና ፍሬውንም ያስለያል። እኔ ዛሬ ስለ ዲያቆን ዳንኤል እንዳወራ ያስገደደኝ የቤተመንግስት ቆይታቸውን ያራዘመላቸው መርጫ በተካሄደ ጊዜ አንድ ኢሳት ውስጥ የሚሰራ ወዳጄ ደውሎ እባክህ ዲያቆን ዳንኤል ለምርጫ እየተዘጋጁ ነው እና በመቶዎች ለሚቆጠሩ የምርጫ ታዛቢዎቻቸው ስለምርጫ ታዛቢነት ስልጠና እንድትሰጥላቸው ፈልገን ነበር አለኝ። እኔም ለሌላ ስራ ከአገር ለመውጣት ሁለት ስለቀረኝ ጊዜ እንደሌለኝ እና ከሁለት ቀን በኋላ ከአገር እንደምወጣ ገለጽኩለት። ወዳጄም ስልኩን ከዘጋ በኋላ ቆይቶ መልሶ በመደወል ከአገር እንደምትወጣ ስለነገርኳቸው የሥልጠናውን ቀን አንተ ባለህበት እንዲሆን አርገውታል አለኝ። እኔም ስምምነቴን ገልጬ ማታ በምበርበት ቀን ጠዋት ወደ ሥልጠናው ቦታ አመራሁ። እንደውም ሥልጠናው ቦታ በሰዓቱ ለመድረስ ስጣደፍ የምነዳት መኪና ከአንድ ሲንከወከው ከመጣ ቲኪና ገር ተጋጨች። እኔ ግን ከግጭቱ ይልቅ አዳራሽ ውስጥ የሚጠብቁኝ ሰዎች ጉዳይ ስለነበር ያሳሰበኝ የምነዳትን መኪና ባለቤት ጠርቼ እሱ የግጭቱን ጉዳይ እንዲከታተል አድርጌ ሥልጠናው ወደሚሰጥበት ላምበረት አካባቢ ወዳለው አራራት ሆቴል አመራሁ።

እጅግ ሰፊ አዳራሽ አፍንጫው ድረስ በዳቆን ዳንኤል ታዛቢዎች ተሞልቶ ደረስኩ። ይሄን ሁሉ ያተትኩት በዛ መድረክ ላይ ለሠልጣኞቹ ደጋግሜ የተናገርኩት አንድ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው። የተናገርኩትም ይህን ነበር፤ የምርጫ ሂደት የዲሞክራሲ ሥርአት ማዋለጃ ነው። በዚህ አይነት ሂደት ውስጥ መሳተፍ አገርን ዲሞክራሲ ጸንሳ እንድትወልድ በሚደረግ ሂደት ውስት ለውጤቱ ማማር ዋና ተሳታፊ መሆን ነው። ስለዚህ ምርጫውን ስትታዘቡ ለዲያቆን ዳንኤል ብላቸው ሳይሆን ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ለማዋለድ ስትሉ አድርጉት። ያኔ የእናንተ ዋና ግብ የሳቸው ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ መካሄዱ ላይ ይሆናል። በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሸነፍም እንደማሸነፍ ነው። የሚል ነበር።

እውነት ለመናገር የዲያቆን ዳንኤልን ወደ ፖለቲካ መምጣት በጥሩ መንፈስ ከተቀበሉት ሰዎች አንዱ ነኝ። ምክንያቴም በተለምዶ እሳት በሚተፋው ፖለቲካችን ውስጥ የመንፈሳዊ ሰዎች እሳቱን በማርገብ፣ የእርቅ፣ የሰላም፣ የመረጋጋት መንፈስን ወደ ፖለቲከኞች የማጋባት አቅም ይኖረው ይሆናል ከሚል እምነት ነበር። በተቃራኒው ከፖለቲከኞቹ ብሶ ዋና እሳት ተፊ፣ ዋና ጸብ አባባሽ፣ ወና የጦርነት አታሞ ጎሳሚ ይሆናል ብሎ ማን ያስባል።

ለማንኛውም ለሙአለ ዘጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ልቦናቸውን መልሶ፣ ከቀልባቸው አድርጎ በመንፈሳዊ ስልጣናቸው ልክ መንፈሳዊ ልዕልና አልብሶ ለአገር የሚበጅ፣ እርቅ የሚያወርድ፣ ሰላም የማያጸና መንፈስ ያላብሳቸው ዘንድ የልብ ምኞቴ ነው።

ዲያቆኑ በትዊተር ከሚረጯቸው መርዞች እና ጸብ አባባሽ ጽሑፎች አንዱን ከዚህ በላይ  አጋርቻለሁ።

Filed in: Amharic