አዎ! ላለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ‹‹መንግሥት የላትም››
ከይኄይስ እውነቱ
ኢትዮጵያ አገራችን ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ሥጋ በለበሱ አጋንንት እየተፈጸመ ስላለውና ስለቀጠለው ግፍና ሰቈቃ፣ ይህን ግዙፉንና የማናያቸውን ረቂቅ ዓለማት ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ እግዚአብሔር አምላክ አለ ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዕለት ተዕለት ጥያቄውና አልፈታ ያለው እንቆቅልሽ፣ እንደ ወርቅ ጥና ሁሉ በእጁ የተያዘ÷ ሁሉን ማድረግ የሚችል÷ የሚሳነው የሌለ÷ ጊዜና ቦታ የማይወስነው÷ በሱ ዘንድ አንዳችም የተሠወረ የሌለ÷ ፊት አይቶ የማያዳለ እውነተኛ ፈራጅ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት ዝም ብሎ ይመለከታል? የሚል ነው፡፡
የምድራዊውን አሠራር በቅጡ የማያውቅ መዋቲና ደካማ ፍጡር ሰማያዊውን ረቂቅ አምላክና አሠራሩን እንዴት መመርመር ይችላል? ልቡና ያመላለሰውን ኵላሊትን ያጤሰውን የሚያውቅና የሚመረምር አምላክ ይህን በሕፃናት፣ በእናቶች፣ በደካማ አረጋውያን ወገኖቻችን ላይ የሚፈጸመውን ግፍና በደል ባጠቃላይ ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ቋያ በቅሎባት የተፈታች ምድር ለማድረግ የሚተጉትን እኩያን ዓይን፣ ጆሮና አእምሮን የፈጠረ አምላክ የማያይ÷ የማይሰማና የማያውቅ ይመስለናል? ታዲያ ለምን? ደጋግመን እንደምንናገረው በእግዚአብሔር የማዳንና ትድግና ሥራ ውስጥ ከአእምሮውና ከሕሊናው ያልተፋታ የሰው ልጅ የራሱ ድርሻ አለው፡፡ እኛ ደግሞ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ተካከልን በድለናል፡፡ አብዛኛው አያገባኝም ብሎ ተራው እስኪደርስ እየተጠባበቀ ይመስላል፡፡ ያገባኛል ብሎ ትንሽ የሚወራጨውም የሚመራውና የሚያደራጀው አጥቶ የዕውር ድንብር ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ጠላቱን በቅጡም የለየ አይመስልም፡፡ ዛሬ የትኛው የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ነው ወገናችንን በቅንነትና በትህትና የምንስተናገደው? ከኃላፊው እስከ ተራው ሠራተኛ አብዛኛው በንቅዘት የተጨማለቀ አይደለም? በሽያጭ ካልሆነ ትክክለኛ መረጃስ የሚሰጥ አለ? አልቅሶ፣ አማርሮና ተበሳጭቶ የማይመለስ ሰው እናገኛለን ወይ? የትኛው ነጋዴ ነው የወገኔን ደም አልመጥም፣ መጠነኛ ትርፍ ይበቃኛል ብሎ እግዚአብሔርን ፈርቶ ሰውን አክብሮ የሚሠራ? የድርሻችንን በጽኑ ልቡናና በቊርጥ ሕሊና ለመወጣት ከመጣር ይልቅ ጐሣውን ማን ይቊጠርልን? ‹ክልሌ› ነው አትድረስብኝን ማን ይዘምርልን? ከዚህ የባሰ አታምጣን ማን ይተርትልን? ‹እሱ› ያመጣብንን ፍዳ ምን ማድረግ ይቻላል የሚለውን እንቶ ፈንቶ ማን ይዘባርቅልን? እኔ ጋር እስካልመጣ ድረስ ምን አገባኝ የሚለውን የግዴለሽነት ሕይወትን ማን ይኑርልን? ባንድ አገር ውስጥ ‹15መንግሥታት›፣ ‹15 ሰንደቅ ዓላማዎች› እና ‹80 ብሔራዊ መዝሙሮች› ካልሆነ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ማን ይደንቊርልን?
ዳኝነትና መልካም አስተዳደር በጠፋበት ፍትሕ በተቀበረበት የተገፋውን ማን ይታደገው? ደሀ ልመናውን በ‹ሀብታሞች› ተቀምቶ ጦሙን በሚያድርበት፤ አድርባይነት የሕዝብም የአገርም ገዳይ ነቀርሳ በሆነበት፤ ሐሰት÷ ቅጥፈት÷ ንቅዘት ባጠቃላይ ነውር ሁሉ ክብር በሆነበት፤ የወንጀል ሥርዓቱ ያበቀላቸው ‹አረሞች› ንጹሐን ዜጎችን የሚያርዱ አረመኔዎችን ለመደገፍ በሚሰለፉበት፤ የእግዚአብሔር እንደራሴ አዕይንተ እግዚአብሔር የተባሉ በእረኝነት የተሰየሙ የሃይማኖት መሪዎች መንጋውን በትነው ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብለው ዝምታን በመሩጡበትና ገሚሱም ቤተ መንግሥት ውስጥ ካሉ ‹ሠራዊተ ዲያቢሎስ› ጋር ባበሩበት፤ ‹ትዳራቸውን› ጭምር ከሚሰጡ ምእመናን በሚገኝ ከብት ራሳቸውንና ዘመዶቻቸውን በቅምጥል እያኖሩ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የተባሉና ባደራ የተረከቧቸው ምእመናን ‹በተኩላዎች ሲበሉ› የማይጮኹ÷ የማያጽናኑ÷ በጸሎተ ፍትሐት የማይሸኙ÷ ክብር ያለው ቀብር እንዲያገኙ የማያደርጉ÷ በየጫካው በየምድረ በዳው ከተበተኑበትና ከተቅበዘበዙበት ሰብስበው አለኝታ መከታ በማይሆኑባት ኢትዮጵያ ከእግዚአብሔር ምን እንጠብቅ? ባለቤቱ አእምሮውን ነፃነቱን ሰጥቶ ምርጫና ውሳኔውን ለኛ ትቶልናል፡፡
ጎበዝ! ድንቊርናና ዕብደታችን እኮ ለከት የለውም፤ የ27ቱን አቆይተን የትናንት የ5ቱ ዓመት ጥፋት ዝርዝር ዕፅዋት ብርእ፣ አብርሕት ቀለም፣ ምድር ብራና ቢሆኑ ተጽፎ የሚያልቅ አይደለም፡፡ አንዳንዶች በስንፍናና ሳይገባቸው ‹አባቶችን› አትናገሩ፡፡ ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ አገርንና ሃይማኖትን የሚያጠፋ አረመኔ ሲሠለጥን ‹መንጋውን› እንዲጠብቁ የተሾሙት ምእመኑን አስተባብረው አገርንና ሃይማኖትን ካልታደጉ ‹አባቶች ወይም እረኞች› ብሎ መጥራት ይቻላል ወይ? ቤተክርስቲያን/ሕንፃ እግዚአብሔር ማለት በዋናነት ማኅበረ ምእመናን ናቸው፡፡ ምእመናኑ በዓላውያን ሲጨፈጨፉ ዝም ብለው የሚመለከቱ ‹ጳጳሳት› እንዴት ‹መንፈሳዊ አባቶች› ሊሆኑ ይችላሉ? እስከ መቼ ነው ቤተክህነቱ እንደ መከኑት ‹የፖለቲካ ማኅበራት› በማውገዝና መግለጫ በማውጣት የሚወሰነው? አሁን እየደረሰ ካለው ጥፋት የበለጠ ምን ዓይነት ጥፋት እስኪፈጸም ነው እየተጠበቀ ያለው? ምእመኑ የሚላስ የሚቀመስ ሳይኖረው ሃይማኖቱን ቤተክርስቲያኑን አስቀድሞ፣ ‹መንፈሳዊ አባቶቹን› አክብሮ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ፣ በግፍ ተገድሎ አስከሬኑን የሚያሳርፍበት ኩርማን መሬት ሲነፈገው አለሁልህ የማይለው ‹አባት› እንዴት መንፈሳዊ አባት ተብሎ ሊጠራ ይችላል? ባለፉት 32 ዓመታት ቤተክህነቱ (በውስጥም በውጭም ያለው) በንቅዘተ በጐሣ አስተሳሰብ የተበላሸ መሆኑን ምእመኑ በሚገባ ያውቃል፡፡ ‹አባቶች› ለተባሉት ከአጥቢያ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ላሉት አክብሮትና ታዛዥነቱን የቀጠለው አገርና ሃይማኖት ለማጥፋት ዐቅደው የሚሠሩ አረመኔዎች በቤተመንግሥቱ መሠልጠናቸውን ስለሚያውቅና የቤተክህነቱን ጉዳይ በጊዜው ጊዜ እንመለስበታለን ብሎ እንጂ ዘንግቶት አይደለም፡፡
በርእሴ እንደገለጽሁት ኢትዮጵያ ‹መንግሥት› የላትም በተለይም ኢትዮጵያዊ መንግሥት፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያዊ ያልሆነ መንግሥት አላት እያልሁ አይደለም፡፡ የዓፄ ምንይልክን ቤተመንግሥት በጉልበት የተቆጣጠሩ የተራ ወሮበሎችና ዱርዬዎች ስብስብ ግን አሉ፡፡ ከወያኔ ትግሬ በውርስ የተቀበሉትን የጐሣ አገዛዝ አስቀጥለው ንጹሐን ዜጎችን በጭካኔ የሚጨፈጭፉና ቀን ከሌት በሙሉ ኃይላቸው አገርን እያወደሙ የሚገኙ፣ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ጥላቻ ናላቸው የዞረ ሠራዊተ አጋንንት በማን አለብኝነት እየፈነጩባት ያለች አገር ሆናለች፡፡ ወንድ ከዋለበት የማይውሉ እንደ ፍልፈል እየተሽሎከሎኩ ሕፃናትን፣ ሴቶችንና ደካማ አረጋውያንን በማረድ የተጠመዱ ፈሪ ሽብርተኞች የሚተራመሱባት አገር ሆናለች፡፡ መንግሥት የሚባለው ኅብረተሰብ የፈጠረው ተቋም የትኛውም ቅርፅ ወይም ስያሜ ይኑረው፣ በሕዝብ የተመረጠ ይሁን/አይሁን ሁለንተናዊ ተቀባይነት ያለው የጋራ መገለጫ ወይም ዓላማ አለው፡፡ እነዚህም የዜጎችን የበዓለ ሀገሩን ደኅነትና ሰላም መጠበቅ እና የአገርን ሉዐላዊነትና ዳር ድንበር ማስከበር ናቸው፡፡ እነዚህን መደበኛና ተቀባይነት ያላቸውን ተግባራት የሚፈጽም ተቋም የሌለው አገር መንግሥት አለው ለማለት አይቻልም፡፡ እኛ ደግሞ እንደዚህ ከሆንን ውለን አድረናል፡፡
ሰሞኑን አንድ የአክሲዮን ማኅበር ስብሰባ ላይ አንድ ወዳጄን ወክዬ ተገኝቼ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ባገራችን የሚንቀሳቀሱ የአክሲዮን ማኅበራት ነባርም ሆኑ አዲስ ሀብታሞችን የሚያበለጽጉ ኩባንያዎች መሆናቸው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በሙያዊ ምልከታ ራሱን ችሎ የሚጻፍበት ርእሰ ጉዳይ ነው፡፡ የጐሣው አገዛዝ አሻሽዬዋለሁ ብሎ ያወጣው የንግድ ሕጉም የሀብታሞችን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑ የሕግ ዕውቀት የሌለውም መድበሉን አንብቦ የሚረዳው ነው፡፡ ብዙዎች ያላቸውን ሥጋት በተለያዩ መድረኮች በጽሑፍ ጭምር ገልጸው አገዛዙ ደናቊርት የሠለጠኑበት በመሆኑ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ምልዐተ ጉባኤ ስለመሟላቱ ከሚደረግ የድምፅ ቆጠራ ጀምሮ የኩባንያውን ህልውና የሚነኩ ዐበይት አጀንዳዎች የሚወሰኑት እነዚህ ተጽእኖ ፈጣሪ በተባሉ ባለአክሲዮኖች ነው፡፡ ሕጉ ጠቅላላ ጉባኤው የአክሲዮን ማኅበራት የበላይ አካል እንደሆነ ቢያስቀምጥም በተግባር የዲሬክተሮች ቦርድና ተጽእኖ ፈጣሪ የተባሉት ባለአክሲዮኖች የጉባኤውን ሥልጣን ነጥቀውታል፡፡ አነስተኛ ድርሻ ያላቸውን ባለአክሲዮኖች ጥበቃን በሚመለከት በሕጉ የገባው ድንጋጌ ፋይዳው አንድ ነገር ተብሏል ከሚለው የዘለለ አይደለም፡፡ ስብሰባው ላይ የሚደረገው ሁሉ ጽሑፈ ተውኔቱ (ስክሪፕቱ) አስቀድሞ የተዘጋጀና እየተተወነ መሆኑን የተረዳሁት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ 1ኛ/ አንድ ከጎኔ የተቀመጠ ተጽእኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮን መሆኑን የነገረኝ ሰው ለቦርድ ዲሬክተር አስመራጭነት ኮሚቴ አባል እንዲሆን በቦርዱ አባላት የተጠየቀና በስብሰባው ዕለት እንደሚጠቆም (ግለሰቡ መጠቆም ብቻ ሳይሆን ተመርጧል) ሲነግረኝ እና 2ኛ/ ባለአክሲዮኖች ርስ በርሳችን የማንተዋወቅ ሰዎች ሆነን ሳለን (አስቀድሞ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የባለአክሲዮኖችን መጠነኛ ፕሮፋይል ሳናውቅ) እንዴት አድርገን መጠቆምና መምረጥ እንችላለን ብሎ ላነሣው ጥያቄ ከቦርዱ ሰብሳቢ የተሰጠው መልስ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ስለሆነ መምረጥ ግዴታችን ነው በሚል ለባለአክሲዮኖች ከሚጠቆሙት 10 እጩዎች መካከል ባያውቋቸውም 5ቱን እንዲመርጡ አስቀድሞ በተዘጋጀና ለባለአክሲዮኖች በታደለ የመምረጫ ወረቀት ላይ የማታውቋቸውን ሰዎች ምረጡ ሲባል ነው፡፡ በእኔ በኩል ውክልና የሰጠኝ ወዳጄን አቋም ስለማውቅ (ለውጥ ባያመጣም) ማንንም ሳልመርጥ፣ ማንሣት ለምፈልጋቸውም ጥያቄዎች ጊዜ የለንም በሚል ዕድል ሳይሰጠኝ ስብሰባውን ታዝቤ ወጥቼአለሁ፡፡ ወገኖቼ! ከሁሉ የገረመኝ የዲሬክተሮች ቦርዱና ተጽእኖ ፈጣሪ የተባሉት ባለአክሲዮኖች ድርጊት ሳይሆን አዳራሹን የሞላው ባለአክሲዮን ባለማወቅ፣ በቸልተኝነትና አንዳንዱም ምርጫ ሲካሄድ (ከወንጀለኞቹ የወታደራዊው አገዛዝ አሁን እስካሉት የጐሣ አገዛዞች ካድሬዎች ባገኘው ልምድ መሠረት) በዝምድናና በጥቅም ግንኙነት ባለ ትስስር ጠቋሚዎች መሆናቸው ነው፡፡ አብዛኛው ባለአክሲዮኖቹ ኩባንያዎቹ ካተረፉ የሚያገኘውን የትርፍ ድርሻ ከመውሰድ ባለፈ በኩባንያዎቹ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ፍላጎቱም ዕውቀቱም የለውም፡፡ እንደ አገር አናሳዝንም?
ከፍ ብዬ እግረ መንገድ ያነሣሁላችሁ ገጠመኝ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ ሆኖ አይደለም፡፡ ባንድ በኩል እንደ ማኅበረሰብ ኢንቨስት ባደረግነው ገንዘብ እንኳን ግዴለሽ መሆናችንን፣ የመብታችንን ጉዳይ ለሌሎች አሳልፈን መስጠታችንን እና በላያችን እንዲረማመዱብን መፍቀዳችን፤ በሌላ በኩል በስብሰባው ወቅት ከጎኔ ተቀምጦ የነበረው ባለአክሲዮን ኩባንያውን የሚመሩት ኃላፊዎች ሆን ብለውም ሆነ ባለማወቅ ከሕግ ተቃራኒ ድርጊት ሲፈጽሙ፣ የአብዛኛውን አለማወቅ ሲጠቀሙበት ይህ በፍጹም ትክክል አይደለም ንግድም ቢሆን ሥነ ምግባር አለው፡፡ በማለት ላስረዳው ስሞክር የተናገረኝ ቃል አስደንግጦኝ ነው፡፡ አንተ ትልቁን ሥዕል ስለማታይ ነው፡፡ ለትልቁ ሥዕል ሲባል ሕግም ሥነምግባርም ቢጣስ ችግር የለውም፡፡ ዐቢይን ብዙ ሰው ያልተረዳው ለትልቁ ሥዕል (አገርን በኢኮኖሚ ለማሳደግ) ሲል ነው የሰው መሞትና መፈናቀል ግድ የሆነው፡፡ አንዳንዶች ግን ዜጎች ተጨፈጨፉ እያሉ ይንጫጫሉ አለኝ፡፡ ለካስ ሳላውቀው ከበሽተኛና ሰነፍ ሰው ጋር ነው ስነጋገር የቆየሁት በማለት መልስም መስጠት ሳያስፈልገኝ ቦታ ቀይሬ ለመቀመጥ ተገደድሁ፡፡ ለካስ ሕዝብ እየጨረሰ አገር እያፈረሰ ያለውን ጭራቅ የሚያመልኩ ቁርጥራጭ ጭራቆች በየቦታው ናኝተዋል፡፡ ሕፃናትን፣ እናቶችንና አረጋውያንን ማረድ፣ ሕዝብን ከቤት ንብረቱ ማፈናቀል፣ ተሠርታ ያደረች አገርን ማፍረስ ለኦነግ/ኦሕዴዳውያን ትልቁ ሥዕል መሆኑን ስንቱ ኢትዮጵያዊ ይሆን የሚያውቀው?