>
5:28 pm - Monday October 9, 0575

ጅልና ብሔረተኛ አትሁን፤ ዜጋ ሁን!! (በፍሬሕይወት ተሰማ)

ጅልና ብሔረተኛ አትሁን፤ ዜጋ ሁን!!

በፍሬሕይወት ተሰማ

(Don’t be an Idiot & Tribalist, be a Citizen ከሚለው መጽሐፍ የተተረጎመ)

አሁን ባለንበት በሰለጠነው ዘመን ወደ ሁለንተናዊ ዕድገት የምናደርገውን ጉዞ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደ አንድ ዜጋ ስለጅሎች እና ብሔረተኞች ውይይት መጀመር በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። ነገር ግን ወደድንም ጠላንም ዛሬ በዓለማችን ውስጥ እነዚህ አስተሳሰቦች  ህያው መሆናቸው አሳዛኝ እውነታ ነው፡፡ ከሁሉ የሚከፋው  ደግሞ  በጅልነትና  በብሔረተኝነት ምክንያት የሚመጣው መለያየትና መከራ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ሰዎች ለሰብአዊነት ታማኝነት ይልቅ ለብሔራቸው ወይም ለጐሰኝነት ፖለቲካ ያላቸው ታማኝነት የጐላ ነው፡፡ በዚህ አሳዛኝ ምክንያት ነው ይህን ጽሑፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው፡፡ በታሪክ ወደኋላ ስንመለስ የሰው ልጆችን ስነባሕርይ የሚያጠኑ ጥንታውያን ተመራማሪዎች በዚያን ጊዜ የነበረውን ሕዝብ ባሕርይ በሶስት ቡድን መድበዋል፡፡ ይህ  ሶስትዮሽ  መደብ  የተጠናው  የዴሞክራሲ አባት ተብለው  ከሚታመኑት ጥንታዊ  የግሪክ ተመራማሪዎች ነው፡፡ ግሪኮቹ ሶሶቱን መደቦች ጅሎች፣ ብሔረተኞችና ዜጐች ብለው ለይተዋቸዋል፡፡ 

  1. ጅሎች

ለዘመናዊ ስልጣኔ በተለያየ ሁኔታና ደረጃ  አስተዋጽኦ ያደረጉት ግሪኮች የመጀመሪያዎቹን ክፍሎች ጅሎች ብለው ጠርተዋቸዋል፡፡ ግሪኮቹ ጅሎች ብለው የለዩዋቸውን ክፍሎች በአስተሳሰብ ደካማ ያልሆኑ ነገር ግን ድብቆች፣ ግላዊነት የሚያጠቃቸው፣ ራስ ወዳድና ራሳቸውን ፍላጐት ብቻ ያማከሉ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ 

ጅሎቹ ሁል ጊዜ የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጐት የሚያሳድዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሕዝብ የሚጠቅም ፍልስፍና፣ የሙያ ክህሎትና እውቀት የላቸውም፡፡ ጅሎች ደግነትና በጐነት የሌላቸው ሲሆኑ ለሕብረተሰቡና ለአካባቢያቸው ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡  እነርሱን የሚያሳስባቸው የግል ጥቅማቸውና ፍላጐታቸው ብቻ ነው፡፡ ግሪኮቹ ገምጋሚዎች ጅሎችን መለስተኛ አረመኔዎች ናቸው ይሏቸዋል፡፡ 

ያኔ  በጥንታዊ  ግሪክ  ዘመን  እንደነበረው  ዛሬም  ተመሳሳይ  ባህርይ  ያላቸው  ጅሎች  በመካከላችን  ይገኛሉ፡፡  ጅሎች  የግል ጥቅማቸውን ማሳደድ፣ በአቋራጭ መክበርና ለሕግና ስርአት አለመገዛት ሁነኛ መገለጫ ባሕሪያቸው ነው፡፡ ባለሥልጣን ከሆኑ ለነርሱ የግል ጥቅምና ምቾት ይሁን እንጂ እጃቸው የደረሰበትን ገንዘብ ለሕዝቡ ልማት በሚል መመዝበር ሁነኛ መለያቸው ነው፡፡ 

የዘመናችን ጅሎች

የዘመናችን ጅሎች ሥልጣንና አቅም  ካገኙ  በፍጹም ለሰው  ልጆች  ጥቅም  የሚሆን  ሥራ  ሲሰሩ  አይታዩም፡፡  ይልቁንም ሥልጣናቸውን፣ የሕዝቡንና የመንግሥትን ገንዘብና  ንብረት  ለግል  ምቾትና  ጥቅማቸው ያውሉትና ለታይታ ግን የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የቆሙ ይመስል እድል ባገኙ ቁጥር ይህንኑ ይደሰኩራሉ፡፡ ራስ ወዳድነታቸው ስለሚያይል ሁሉንም ከጥቅማቸው አንጻር ብቻ ያያሉ፣ ያውላሉ፡፡ ማንኛውም እንቅስቃሴና ሥራቸው ከራስ ተኮርነት፣ ጥቅመኛነትና ገብጋባነት የሚነሳ ነው፡፡ 

በማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴአቸው ትንሽም ቢሆን ትልቅ ሥራ ሲሰሩ በቀጥታ ግብር ከመክፈል ይልቅ ለገቢ ባለሙያዎች ጉቦ በመስጠት ማለፍ መገለጫቸው ነው፡፡ ሁል ጊዜም ከሕጋዊ መንገድ ይልቅ ማጭበርበርን ከመምረጣቸው በላይ ይህ አካሄዳቸው ልክ  እንደሆነም ምክንያት ይደረድራሉ፡፡ የአገራቸውን ኤኮኖሚ ደም በመምጠጥ ሕዝቡ በችግር እንዲሰቃይ ከእነርሱ ቢጤዎች ጋር ይመሳጠራሉ፡፡ ዋናው አላማቸው ሕግን አጣመውና ተላልፈው  በኪራይ ሰብሳቢነት የግል ሀብታቸውን ማካበት ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን  በገንዘብ  በማማለል ሕግ እንዲጣስ ማድረግን እንደጥፋት ከመቁጠር ይልቅ ትክክለኛ አካሄድ  እንደሆነ  ሲሞግቱ ይታያሉ፡፡ 

ጥንታዊ ሮማውያን “ገንዘብ እንደውቅያኖስ ውሀ ነው፤ ብዙ በጠጣኸው ቁጥር ይበልጥ ይጠማሃል” የሚል አባባል አላቸው፡፡ ይህ አባባል በተለይ የዚህችን ደሀ አገር ገንዘብ የመዘበሩና ያስመዘበሩ፤ በተለያየ የመንግሥት ወይም የግል ስልጣን ያላቸው ተከታይና አጃቢ የበዛላቸው የዘመናችንን ጅሎች በትክክል ይገልጣቸዋል፡፡ ከትንሹ ጀምረው ካለምንም ሐፍረትና ይሉኝታ በድፍረትና ከአእምሮ በላይ በሆነ መጠን የሀገሪቱን ሀብት ዘርፈው፤ ግዙፍ ሀብት አካብተው ታላቅ ዝናና ብዙ አውደልዳይ አትርፈዋል፡፡ 

  1. ብሔረተኞች

እንደግሪኮቹ ጥናት  በሁለተኝነት  የለዩዋቸው ብሔረተኞችን  ነው፡፡ ይህ  ልየታ  በምንም መልኩ ከአንድ ማኀበረሰብ  የተገኙ ወይም በማንነታቸው የሚኮሩ ሕዝቦችን አይመለከትም፡፡ ከአንድ ጐሣና አካባቢ መወለድ ከዚያም አካባቢ መሆንን መግለጽ፣ መሳዩን መፈለግ  ተፈጥሮአዊ  ነው፡፡  የሚያኮራም  ነው፡፡  ነገር  ግን  ብሔረተኞች  ተብለው  በዚህ  ክፍል  የተጠቀሱት ጭፍን  ጐሰኛ  አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ነው፡፡ 

ግሪኮቹ እነዚህን ቡድኖች የገለጿቸው ሁሉንም ነገር ከራሳቸው  ብሔር አንጻር ብቻ  የሚመለከቱ  ናቸው  በሚል  ነው፡፡ ብሔረተኞች ዋነኛው ታማኝነታቸው ለብሔራቸው ብቻ  ነው፡፡ ሐይማኖታቸው ጐሰኝነት  ነው፡፡ በብሔራቸውና በጠባቧ  ሰፈራቸው የተወሰነ ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው፡፡

ግሪኮቹ እንዳሉት ብሔረተኞች ከነርሱ ብሔር በትንሹም ቢሆን ለየት ያለን ሰው  ይጠራጠራሉ፣ ይፈራሉ፡፡ ጐሰኞች ከጥርጣሬና  ፍርሃታቸው  የተነሳ  ከነርሱ  ብሔር  ወይም  ዘር  ውጪ  የሆነን  ሕብረተሰብ በማስፈራራት፣ በኃይልና በሁከት እንጂ በመቻቻልና አብሮ በመኖር አያምኑም፡፡

ግሪኮቹ ብሔረተኛና ጐሰኞቹን ጦረኞችና ጠበኞች ወይም ተዋጊዎች ብለው  ሰይመዋቸዋል፡፡ በውነትም ይህ ስያሜ እንደሚገባቸው የሚያስታውቀው ብሔረተኞች ሁሌም  ሰላም የማይወዱና ጠብና ጦርነት ለመጀመር ቅርብ መሆናቸው ነው፡፡ ብሔረተኞች ከፋፋይ፣ ከብሔራቸው ውጪ ለሆኑ ሰዎች ክብር የሌላቸው፣ እውቅና የማይሰጡና ቂመኞች ናቸው፡፡ ጐሳ ወይም ብሔር በሕብረተሰቡ ውስጥ የጋራ መኖሪያ፣ ቋንቋና ባሕል መጋራት ነው፡፡ የሥጋ ዝምድና፣ የሕብረተሰብ ወይም የፖለቲካ ግንኙነትም ለአንድ ብሔር ወይም ጐሳ ማንነት አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ 

ዘመናዊ ብሔረተኛነት

አሜሪካዊው ጸሐፊ ጆርጅ ኸርበርት ሚድ የአንድ አገር ሕዝብ በልዩነት ውስጥ ያለ  አንድነት  ያለው ነው ሲል ጽፏል፡፡ ከተለያየ የትውልድ አካባቢና ብሔር ብንመጣም በልዩነታችን  ውስጥ ውበትን እናያለን፡፡ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ውበት ለብሔረተኛው አይታይውም፡፡ ዘረኞች አእምሮአቸው ከዘራቸው በላይ እንዳያስቡና ምክንያትን በመሻር ጥላቻ አመክኖአዊ አስተሳስብ እንዳይኖራቸው  ያሳውራቸዋል፡፡

ብሔረተኞችና ዘረኞች አገራዊ ችግር ሲፈጠር ብሔራቸውን የሚወክል ጠባብ አቋም  በመያዝ ይታወቃሉ፡፡ የነርሱ ብሔር የሆነ ሰው ስልጣን ከያዘ በዙሪያው ይስለፉና አገሪቱ  በትክክለኛው ሰው እጅ ናት፤ ወደ እድገት ጐዳናም እየሄደች ነው ብለው ምክንያታዊ ያልሆነ ድጋፋቸውን ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን ከነርሱ ዘር ያልሆነ ሰው ስልጣን ከያዘ ወዲያውኑ አይናቸውን ጨፍነው መቃወም ይጀምራሉ፡፡ አገሪቱ አደጋ ላይ እንደወደቀች ያምናሉ፤ ለማሳመንም ክርክር ይገጥማሉ፡፡ ብሔረተኛ አስተሳሰብ ምክንያታዊ አስተሳሰብን አሽቀንጥሮ ይጥላል፡፡ ውጤቱ ደግሞ ጠብ፣ ክርክርና ስሜት ወደማይሰጥ ጦርነትና ዘር ማጥፋት የሚያመራ ነው፡፡

የተማሩት ዘረኞች በጐሰኝነት መጋረጃ ተከልለው የግል ዝና፣ ኃይልና ጥቅማቸውን ለማግኘት ይጠቀሙበታል፡፡ በፖለቲካዊ መልኩ የጐሳቸውን ዋና ጥቅም ለማስከበርና ሌላውን  በመደፍጠጥ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ ብሔሮች መገንጠልና በራሳቸው መተዳደር እንዳለባቸው በመደገፍ ይከራከራሉ፡፡ በኘሮፓጋንዳው የሂትለርን  ʻምንም ውሸት ቢሆን ደጋግመህ ከተናገርከው ሕዝቡ እውነት ነው ብሎ ያምናልʼ የሚለውን አካሄድ ይከተላሉ፡፡ የብሔረተኝነት አራማጆች ባሕርይ የውሸት ኘሮፓጋንዳን ካለማቋረጥ መንዛት  ነው፡፡ ይህ አካሄዳቸው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ሳይቀር አሳምነው  በሚያስደንቅ  ሁኔታ  ተከታዮቻቸው ማድረግ መቻላቸው ሲሆን ይህ አካሄድ ደግሞ እጅግ በጣም አደገኛ ነው፡፡ 

ብሔረተኞች ጸረ አንድነት የሆኑና ሰላምን  የማይፈልጉ፤ አብሮ ስለመኖርና ስለመቻቻል  የወጡ የአገሪቱን ሕጐች ማክበር እንደሌለባቸው የሚያምኑ  ናቸው፡፡ የሀሰት  ኘሮፓጋንዳን  በማሰራጨት፣  በመከፋፈልና  የጦር  ወሬን  በመንዛት  የእውቅና  ማማቸውን ያስጠብቃሉ፡፡  ብዙውን  ጊዜ  ምሁራን  ብሔረተኞች የተደበቀ እና ራስ ተኮር  ፍላጐታቸውን  በጐሳቸው  ስም ሲያራምዱ ይታያሉ፡፡ 

ሕዝቡ እድል አግኝቶ ፍላጐቱን መግለጽ ቢችል ከአገሩ  ሕዝብ ጋር ተለያይቶ፣  ተፈራርቶና  ተራርቆ መኖር ምርጫው ሊሆን እንደማይችልና እንወክልሃለን፣ ቆመንልሃል የሚሉት  ምሁራን ልጆቹ  ከሚያራምዱት  አካሄድ  ፍጹም ተቃራኒ አቋም እንደሚኖረው ግልጽ ነው፡፡

የአንድ አገር ሕዝብ አንድ የጋራ የእድገት ግብ ላይ ለመድረስ የእያንዳንዱን ብሔር አስተዋጸኦ ይፈልጋል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ብሔረተኞች ከዚህ አካሄድ በተቃራኒ በመቆም ለሕዝቡ ሰላማዊ ኑሮና እድገት ጠንቅ መሆናቸውን በራሳቸው ጊዜ አረጋግጠዋል፡፡ እርስ በርሱ  የተከፋፈለ  አገርና  ሕዝብ  ከመፍረስ  ሊድን  አይችልም፡፡  ካለጥርጥር  ከራሳቸው  ዘርና  ብሔር  ፍላጐት ውጪ የማያስቡ ብሔረተኞች እነርሱ የሕዝባቸውና የራሳቸው ጠላት ናቸው፡፡ 

  1. ዜጐች

እንደጥንታዊያኑ  ግሪኮች  ጥናት፤  በሕዝቡ  ውስጥ  የመጨረሻው  ቡድን  ዜጐች  ተብለው  የተጠኑት  ናቸው፡፡  ዜጐች  ትክክለኛና ፍጹም  መልካም  የሆኑ  የሕብረተሰብ  ክፍሎች  ናቸው፡፡  ከትርጉሙ  እንደምንረዳው  ዜግነት  ማለት  የአንድን  ሰው  የፖለቲካ  ሁኔታ የሚገልጽ አይደለም፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ ሕዝባዊ የሆነ ማንነትን የሚገልጽ ነው፡፡ 

ʻዜጋ ማነው?ʼ  ግሪኮቹ ዜጋን በእውቀት የታነጸ፣ በሕዝቡ ዘንድ የተከበረ መልካም ማንነት ያለው ነው ብለው ይገልጹታል፡፡ ዜጋ ራሱን  የጋራ ሀገር አባል  እንደሆነ  አድርጐ ያምናል፡፡ ዜጋ ስልጣኔ  የሚገባው፣ ለሕዝቡ  የጋራ ዕድገት የሚተጋና  የራሱንም አስተዋጽኦ የሚያደርግ  ነው፡፡  ዜጋ  በሕብረተሰቡ ውስጥ  ስላለው መብት  ግዴታና  ተግባራዊነት  ጥልቅ  የሆነ  ግንዛቤ  አለው፡፡  ነጻነትና መብትም ከኃላፊነት ጋር እንደሚመጡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ 

በዚህ ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ እኛ የቱጋ ነን?

እንግዲህ  አሁን  ከታሪክና  ዳራው  ወጥተን  ሃሣቡን  ወደራሳችን  እናምጣው፡፡ በዚህ  የግሪኮች  ገምገማ  ውስጥ  እኛ  የቱጋ እንገኛለን? የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው፡፡ እስቲ ከእነዚህ ሶስት ምድቦች ማረፊያችንን በማስተዋልና በጥንቃቄ እንገምግም፡፡ በሕብረተሰብ ውስጥ ያለንን ዋጋና ሚና ካላወቅን በሃገር ግንባታ ላይ ጠቃሚ የሆነ አስተዋጽኦ ማድረግ በፍጹም አንችልም፡፡ 

ራሳችንንና ገንዘባችንን ለሕዝብ ጥቅም ለሚውሉ ጉዳዮች መስጠት ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ይህ ግዴታ ሕግን ማክበር፣ ታክስ  መክፈልና  ሀገራችንን  ከውጭ  ከሚመጡ  ጠላቶች  መከላከልን ይጨምራል፡፡ ለመልካም ዜጋ የሌሎችን መብት፣ እምነትና አስተሳሰብ ማክበር በጣም ወሳኝ  ነው፡፡ ከሁሉ  የበለጠ  በመንግሥት የተደነገጉ  የዴሞክራሲ ሥርዓቶችን ማክበር  ለአንድ  ዜጋ  እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

በዘመናችን  ያለው  ገጽታ  ራስ  ወዳድ  በሆኑ ጅሎችና  አጋርነታቸው  የራሳቸው ብሔር ወይም  ጐሳ ብቻ  በሆነ ብሔረተኞች የተሞላ ነው፡፡ ነገር ግን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ለሕብረተሰብ የጋራ ጥቅም የሚጥሩ መልካም ዜጐች እንዳሉም መዘንጋት የለብንም፡፡ 

ታዲያ እኛ ከየትኛው ምድብ ውስጥ ነው የምንወድቀው?

ሀገር በጅሎችና በብሔተኞች ከተመራች አንድነት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና የሀገሪቱ የሕግ  የበላይነት በከባድ አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ እነዚህ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ብሔሮች መካከል ሕብረትና አንድነት በመፍጠር የሚያጋምዱ  ዋንኛ እሴቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ጠብንና አለመግባባትን መዝራት፣ እንዲሁም ʻከፋፍለህ ግዛውʼ የጅሎቹና ብሔረተኞቹ አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ 

ዜግነት ለጋራ መከባበርና ትብብር

የዓለማችን የፖለቲካና የኤኮኖሚ የጊዜው እውነታ እንደሚያሳየው አገሮች የመደጋገፍና የመቀባበል ስምምነቶችን በመፍጠር በአንድነት  ለትብብር  መቆም  እንዳለባቸው  ነው፡፡  ይህ ለሕዝቦች  ደህንነትንና  መረጋጋትን፣ አጠቃላይ ሰላምን ከፍ ሲልም ለሀገራት ፍጹም  የሆነ የእድገት ከፍታን ይፈጥራል፡፡ ጥቅምና ምቾት ለጥቂት ልሂቃንና ለተወሰኑ  ብሔረተኞች ሆኖ ሊቀጥል አይችልም፤ ይልቁንም በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖሩ ሁሉም ብሔርና ሕዝቦች መሆን ይገባዋል፡፡

የሚያሳዝነው ግን በማደግ ላይ ባሉ አገራት የሚገኙ ብሔረተኝነትን የሚያራምዱ ልሂቃን በድህነት የሚማቅቀው ብሔራቸው ከደሃዋ ሀገራቸው እንዲገነጠል መፈለግና ማነሳሳታቸው ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ዋና ዓላማ በዘራቸውና በጐሳቸው ስምና ሰበብ ገንዘብና ሥልጣን መያዝና መቀራመት ብቻ ነው፡፡ ይህ ራስ ወዳድና ብሔረተኛ አስተሳሰብ በአዳጊ አገራት ላይ ግራ መጋባትንና ሕገወጥነትን ያስፋፋል፡፡ ብሔረተኛ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ግለሰቦች በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከልክ ላለፈ ጉቦኝነት፣ መለያየትንና የበዛ ጥላቻን ያነሳሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ አካሄድ ለሀገር ሰላምና ለኤኮኖሚ እድገት ከፍተኛ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡

በሕዝቦች መካከል የሚያስፈልገው የጋራ መከባበር፣ ስልጣኔ እና መረዳዳት ነው፡፡ እያንዳንዱ ብሔር የራሱን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ባሕል፣ ቋንቋና ማንነት ማድነቅ፣ ማክበርና  መቀበል  ይኖርበታል፡፡ ይህ አድናቆት የሌሎችን  እሴትና ባሕል የሀገሪቱ መገለጫና ውበት እንደሆነ በጥልቅ ከመረዳትና ይህም እሴት ለሀገሪቱ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከማስተዋል የመነጨ መሆን ይገባዋል፡፡ 

ዜጋ መሆን ይገባናል

በየትኛው ዓለም ብንኖር ጥንታውያኑ ግሪኮች ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት 3ቱ ቡድኖች ከወዴት መመደብ እንዳለብን ከወዲሁ መወሰን የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፡፡ ባደጉ ወይም  በማደግ  ላይ ባሉ አገሮች ብንኖር ያለን አንድ አማራጭ ብቻ  እንደሆነ፤ ያም ለየሀገራችን መልካም  ዜጋ  መሆን  እንደሆነ  ግልጽ  ነው፡፡ አንዳንድ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች  በቋንቋና በብሔር ላይ  የተመሠረተ የፌደራል መንግሥት አወቃቀር ሥርዓት አላቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ከዚህ ሥርዓት ተላቀው ለሕዝባቸዉ ዴሞክራሲያዊነትና አንድነት እንዲበጅ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የዜግነት ፖለቲካ ማራመድ እንዲችሉ እንናፍቃለን፡፡

የአሜሪካ  14ኛው  ሕግ፤  ከየትም  ሀገር  መጥተው  በአሜሪካ  ውስጥ  የተወለዱ  ሰዎች  የአሜሪካ ዜግነትና እንደሚያገኙና የተወለዱበት የፌደራል መንግሥት ነዋሪ መሆን እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ ፌደራል መንግሥቶች በዜግነት ላይ ስልጣን የላቸውም፡፡ እነርሱ ጋር ቀዳሚው ዜግነት ነው፡፡ ይህ አወቃቀርና ሥርዓት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በብሔር ላይ የተዋቀረ ፌደራሊዝም በሚያራምዱ አገሮች ውስጥ አንድ ሰው ብሔሩ ባልሆነ አካባቢ ሲኖር የሌላውን ያህል መብት የለውም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች የክልሉ ተወላጅ ካልሆነ የመንግሥት ስልጣን መያዝም ሆነ ሕይወቱን ከሌሎች እኩል ለመምራት ችግር ያጋጥመዋል፡፡ በግልጽ የብሔር ማንነት ሰብአዊነትን ሲጨፈልቀው እናያለን፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የብሔረኝነት ዘውድ ወርዶ ሰዎች  በየትኛውም  ክልል  ቢኖሩ ሰብአዊነታቸውና  በመረጡት  ቦታ  የመኖር፣  ሥልጣን  የመያዝና  ሀብት  የማፍራት  መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል በሚል አስተሳሰብ ሥርዓቱ መገንባት አለበት፡፡  ዜግነት፣ ብዝሃነት፣ መቻቻል፣ መቀባበል፤ ለሕብረተሰብ በጋራ፣ በሰላምና በዴሞክራሲ መኖር ወሳኝ የሆነ እሴት ነው፡፡ 

በሕብረተሰብ  ውስጥ  ለተሻለና  ውጤታማ  የሕዝብ  እድገት  አማራጩ  ዜግነት  ነው፡፡  ዜግነት ሰዎች ማህበራዊ ፍትህን ለመገንባት የጋራ  ራእይን  የሚያራምዱበት፣  በሕብረተሰቡ የጋራ  አጀንዳ  ዙሪያ ሁሉን አቀፍ የሆነ መፍትሔ ለማምጣት የሚተጉበት ሥርዓት  ነው፡፡ ለሀገራችን ብሎም ለመላው ዓለም  የምንበጅ መልካም ዜጐች መሆን የእያንዳንዳችን  ምርጫ  እንደሚሆን እምነትና ተስፋ አለኝ፡፡ ሰው ነንና በተለያየ ሁኔታ በመካከላችን ልዩነት መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ችግሮችን ለመፍታት በፍጹም መሳሪያ ማንሳትን አማራጭ ማድረግ የለብንም፡፡ ይልቁንም ወደ ሰላምና ወደ ውይይት ማምራት ይኖርብናል፡፡ በማንኛውም አወቃቀር ሰዎችን በብሔራቸውና በዘራቸው ሳይሆን በሰብአዊነታቸው እንለያቸው፡፡ ከሁሉ በላይ አገራችን የምትፈልገውን ዜጋ ለመሆን እንትጋ፡፡

Filed in: Amharic