>
5:26 pm - Saturday September 15, 7427

የቋንቋ ፖለቲካ እና መዘዙ...!  (ሞገስ ዘውዱ)

የቋንቋ ፖለቲካ እና መዘዙ…! 

ሞገስ ዘውዱ

 

ቋንቋ፣ እንደ ሁኔታው ፖለቲካዊ ፣ እኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ አለው። ያልሰለጠነ ማህበረሰብ ( primitive society) ውስጥ ቋንቋ በዋናነት የማንነት መገለጫ ብቻ( identity marker) ይሆናል። የብሄረ-መንግስት ግንባታ ባላጠናቀቁት አገራት(ኢትዮጵያን ልብ ይሏል) ደግሞ ከፖለቲካው ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ይኖረዋል። በአደጉት አገራት ደግሞ የቋንቋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ይጎላል። ሰው ለኑሮውና ለጥቅሙ ሲል ቋንቋ ይማራል፣ ቋንቋውም በዚያው ልክ ያድጋል። እንደዚያም ሆኖ የቋንቋ ፖሊሲ በአመዛኙ ሁሉንም የቋንቋ ፋይዳዎች ባጠመረ መልኩ ( comprehensive language policy) ይቀረፃል። ቋንቋ ከትምህርት ስርዓት ጋር ሲገናኝ ደግሞ ተጨማሪ ከግንዛቤ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ( pedagogical issues)።

ቋንቋ እና ማንነት ሲጋቡ ወትሮም ችግር ሲሆን በዚህ ላይ ልጓም ከሌለው የብሄርተኝነት ፈረስ ጋር ሲጋቡ ውጤቱ ቀውስ እና የማህበረሰብ ግጭት ነው። በተለይ ህብረ-ባህላዊ ( የቋንቋ ብዛህነት ያለበት) ማህበረሰብ ውስጥ የቋንቋ ጉዳይ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያዝ፣ እውቀትና ማስተዋል የሚጠይቅ፣ የህዝብ ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስፈልገው ነው።

በኢትዮጵያ ( አዲስ አበባ) ምን እየሆነ ነው ያለው? የትኛው ቋንቋ ይሰጣል? መቼ ይሰጣል? በምን መልኩ ይሰጣል? ለምን አላማ ይሰጣል? ህዝቡስ ምን አለ? ለምን አሁን አስፈለገ? ሂደቱስ ምን መሆን ነበረበት? ለምንስ ተቋውሞ ገጠመው? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች መልስ ያስፈልጋቸዋል።

በመሰረቱ የኦሮምኛ ቋንቋ የስራ ቋንቋ እንዲሆን የረዥም ጊዜ ጥያቄ እና ያደረ ጉዳይ ነው። አላማውም ቋንቋው በብዙ ሰዎች ስለሚነገር በብሔረ-መንግስት ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እንዲኖረው ታስቦ ነው። ግን ይሄ ብቻ ነው? ኦሮምኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንዲሆን ተፈልጎ ነው? ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አሳስቧቸው? ማህበራዊ ትስስር ጨንቋቸው? አይደለም።  ኢትዮጵያ ውስጥ ቋንቋ የሚታየው፣ በተለይ በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ እንደ ማህበራዊ ምህንድስና ( social engineering tool) ነው።  ኦሮምኛ እና ሌሎች ቋንቋዎች የኢትዮጵያ ቋንቋ እንዲሆኑ ምን መደረግ እንዳለበት( መውጫ መንገድ ላይ) ከታች እንመለስበታለን።

አዲስ አበባ ላይ ሰሞኑን የምናየው( አሁን ጎልቶ ወጣ እንጂ ገዳዩ አመታት አስቆጥሯል) ነገር በበርካታ  ምክንያቶች ስህተት ነው። ከነዚህ ውስጥ ከህጋዊነት፣ ተጠባዊ ውጤት እና አፈፃፀም አንፃር ሲታይ አደገኛ አካሄድ ነው።

፩: ህጋዊነት:-

(ሀ) ሲጀመር የኦሮሚያ የትምህርት ፖሊሲም ሆነ ህጎች አዲስ አበባ ላይ በህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ምንም ዓይነት ተፈፃሚነት የሌለው ከመሆኑም በላይ constitutional usurpation ነው። አዲስ አበባ የራሱ ትምህርት ፖሊሲ አለው፣ በቂ የተማረ ሰውም አላት። ህፅን ልጅ እንኳን የማይናገረውን “የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ፖሊሲ ቋንቋ በሚሰጥበት መዝሙር እንዲዘመር  እና ባንዲራ እንዲሰቀል ስለሚያስገድድ ነው” የሚለውን ቀሽም ንግግር ትልቅ ህዝብና ከተማ ከሚያስተዳድር ከንቲባ መስማት እራሱ ያሳፍራል። እንደዚያ ከሆነማ የኦሮሚያ ህግ ስለሚያስገድድ ጀርመን አገር ባንዲራ እንዲሰቀል፣ መዝሙር እንዲዘመርልኝ ብሎ ሰልፍ መውጣት እና መልሱን ማየት ነው!

(ለ) የአዲስ አበባ ካቢኔ( አዳነች አቤቤን ጨምሮ) የተመረጠው እና ተጠያቂነቱ ለአዲስ አበባ ህዝብ እንጂ ለኦሮሚያ ክልል አይደለም። የሚያስተዳድሩትን ህዝብ ቃልኪዳን ሽረው መልሶ ማሰቃየት ሞራለ-ቢስነት ነው።

(ሐ) ባለው ህገ-መንግስት መሰረት አዲስ አበባ የከተማ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ መቀመጫ እንጂ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ አይደለችም። ከፌዴራል ህገመንግስት ጋር የሚጋጭ ማንኛውም ህግ፣ የኦሮሚያ ህገ-መንግስትን ጨምሮ፣ ተፈፃሚነት አይኖረውም።

(መ) ሁሉም ህፃናት በተቻለ መጠን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብት አላቸው። ይሄ ማለት ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ህፅናት። ስለዚህ፣ በህዝብ ትምህርት ቤት ላይ አብዛኛው ተማሪዎች በሚናገሩት ቋንቋ ይሰጣል፣ ቀሪው ደግሞ በተጫማሪ ቋንቋ መልክ( optional languages) ይሰጣል። እንዴት መሰጠት አለበት የሚለውም በጥናት፣ የህዝብ ተሳትፎ እና የሀገር ሀብት አንፃር የሚታይ ይሆናል።

(ሠ) ህገ-መንግስቱ ሳይሻሻል ሌላ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች(ኦሮምኛን ጨምሮ) የስራ ቋንቋ መሆን አይችሉም። እያወራን ያለነው ስለ ህጋዊ ስርዓት ከሆነ!

 ፪: ተጠባዊ ውጤት:-

አሁን ያለው አካሄድ ቋንቋ እና ተስፋፊ ብሔርተኝነትን በጉልበት ማጋባት( naked imperialism) እንጂ ቋንቋን የማበልፀግ አካሄድ አይደለም። እኔ እራሴ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ እና የባህሉ ባለቤት ነኝ። ለማንም ሰው ቢሆን ብዙ ቋንቋ ማወቅ ይጠቅማል። እሱ የሚሆነው ግን ቋንቋን የአንድ ብሔር የግል ንብረት አድርጎ እና እንደ አገር ግንባታ ህልም እርሾ እየተጠቀሙ አይደለም። ኦሮምኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንዲሆን መስራት ከሁሉም ይቀድማል። የኔ ብቻ የሆነውን ቋንቋ ተማርልኝ አይባልም፣ ነውር ነው። Afaan Oromoo( የኦሮሞ ቋንቋ) ብለህ ሰይመህ፣ ዋና የማንነት መገለጫ አድርገህ፣ አላማውንም በግልፅ ቋንቋ እየተናገርክ ሰው እንዴት በቅንነት ይቀበልህ?

ለመሆኑ የት አለም ላይ ነው የቋንቋ ትምህርት ሲሰጥ ተማሪዎች የብሄርተኝነት እና ተንኳሽ መዝሙር ዘምረው ትምህርት የሚጀምሩት? አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ሲውዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ኬንያ፣ ሱዳን? ቋንቋ ለመማር፣ ለምሳሌ Qubee, sagalee, jecha, keewwatta, kkf ለማለት “የ100 አመት እድፍ ማራገፍ እና የበለፀገች እናት አገር ኦሮሚያን መገንባት” ምን አገናኛቸው? እድፍ የሌለበት እና ከኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ ውጪ ሌላ አገር የሌለው ሰው ስለዚህ መዝሙር ምን ይመለከተዋል? ኧረ እንዲያውም ለኦሮሞ ልጆችስ ቢሆን እንዲህ ዓይነት ተንኳሽ፣ አስለቃሽ እና የእዬዬ መዝሙር በዘላቂነት ምን ይጠቅማቸዋል?

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ የቋንቋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈይዳው ተቀብሮ የብሄርተነት ግንባታ መሳሪያ ብቻ ሆኗል። እንደዚያ ሲሆን ደግሞ እንኳን ከሌላ ብሔር ተወላጅ የሆነ ይቅርና የኦሮሞ ልጅ ሆኖ የስግብግብነት ፖለቲካውን የማይጋራ እራሱ አይሰማችሁም!

፫: የአፈጻጸም ጉዳይ:-

ሁሉም ነገር ተገቢ እና ትክክለኛ ሆኖ እንኳን የተሳሳተ አፈፃፀም ድግሱን ያበላሸዋል። ከፍትፍቱ ፊቱ እንደሚባለው! ሰው፣ ጤነኛ ሰው፣ ለዚያውም ተጨቁኛለሁ ብሎ ሰርክ የሚያለቃቅስ ስብስብ፣ የሌላውን መብት ደፍጥጦ በገገማው የራሴን ፍላጎት ካላስፈፀምኩ እንዴት ይላል? ለዚያው በ 21ኛው ክፍለ ዘመን? ስለ እራስህ መብት ስታስብ የሌላው ተመሳሳይ መብት እንዴት ትዝ አይልህም? እሺ ሌላው ቢቀር የህዝብ ፍላጎት ዳሰሳ( baseline survey) ቀድመህ ለምን አትሰራም? የከተማውን ህዝብ ነዋሪ የስነልቦና ውቅር ማወቅ ለምን ተሳነህ? አዲስ አበባ በተፈጥሮዋ ህብረባህላዊ እና metropolitan የሆነ ማህበራዊ ስሪት እና መስተጋብር ያላት ናት። አካሄዱ ይሄንን እንዳያናጋ መጠንቀቅ ለምን አልተፈለገም? ምናልባት የለየለት ድ*ቁ*ና ይሆን?

ሌላው ቢቀር የእድፉን ጉዳይ እዚያው ኦሮሚያ ላይ አራግፋችሁ እና ባንዲራውን ትታችሁ መጀመሪያ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የቋንቋ አሰጣጥ( progressive and pragmatic approach) መከተል ለምን አልተቻለም?

እንኳን ቋንቋን የሚያህል ከስነቦና ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ይቅርና ምግብ እንኳን በጉልበት ማስበላት አይቻልም። ደግሞ የአፄ በጉልበቱ ዘመን አልፏል፣ በህግ ስርዓት ብቻ ስትሉ አልነበር!? የአንዱን ብሄር ቋንቋ ብቻ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

ምን መደረግ አለበት( ነበረበት)?

➡ኦሮምኛን የኢትዮጵያ ቋንቋ ማድረግ። ይሄ እንዲሆን ደግሞ ብሄርተኝነት እና ቋንቋን ማፋታት ይጠይቃል። ቢያንስ አብዛኛው ሰው ወዶት እንዲማር ሁኔታዎች ማመቻቸት( good incentives) ያስፈልጋል። ከሁሉም በፊት በኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መንገድ ህዝብን የበለጠ ማስተሳሰር፣ ቀጥሎ ቋንቋውን በተለያየ መልኩ ወደ ቢሮክራሲ ማስጠጋት፣ በመገናኛ ብዙሀን ማሰራጨት፣ በንግድ ስርዓት ውስጥ ማስገባት፣ ወዘተ።

ቀጥሎ “ሳይቸግር ፊደል ብድር” የሆነውን በማስቀረት የሳባን ፊደል አሻሽሎ መጠቀም። መቼም ለኦሮሞ ህዝብ ከRoman Empire የአቢሲንያው ይቀርበዋል። ባጭሩ ፊደሉን ኢትዮጵያዊ አድርጎ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በቀላሉ እንዲደርስ ማድረግ። የኢትዮጵያ የሆነውን ሁሉ እየተፀየፍክ የኔን ተማሩልኝ አይባልም!

➡ብሔራዊ የትምህርት ስርዓት ላይ ማሻሻያ አድርጎ ተማሪዎች ቢያንስ 2 የአገር ውስጥ ቋንቋ፣ 2 የዓለም አቀፍ ቋንቋ እና አቅም ከፈቀደ በHigh School ወይም ዩኒቨርሲቲ ደረጃ አንድ የአካባቢ ቋንቋ( such as Swahili or Somali) እንዲማሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት። ይሄን ለማድረግም ከማህበረሰቡ ግብዐት መሰብሰብ!

➡ሀሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ማድረግ። ጥድፊያውን ትቶ፣ በተለይ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት አስቸጋሪ ሁኔታን ከግንዛቤ በማስገባት፣ ትላልቅ የቤት ስራዎችን ለህዝባዊ ውይይት እና ዉሳኔ መተው። ዛሬ በጉልበት ቢሞከርም መሰረቱ አሸዋ ላይ ስለሆነ ነገ ወዲያ መፍረሱ አይቀርምና ከቅዥት በፊት ውይይት ይቅደም።

➡አስፈላጊ የህገ-መንግስት ማሻሻያ ማድረግ። ለኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ ተብሎ ሳይሆን የህገ-መንግስት ማሻሻያ ለረዥም ጊዜ ሲንከባለል የቆየና አንደኛው የችግራችን መፍቻ ቁልፍ ነው።

➡በመጨረሻም፣ ለተፈፀሙት ስህተቶች ህዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ ለቀጣይ ጉዞ መዘጋጀት ነው።

ከዚህ ውጪ በጉልባት የሚፈጠር የማንነት ንቅለ-ተከላ( social engineering) አይኖርም። ይሄው ነው!

Filed in: Amharic