>

ብልጽግና ማለት ራሱ ገርፎ ራሱ የሚያለቅስ እኩይ ፓርቲ ነው...! (አሳዬ ደርቤ)

ብልጽግና ማለት ራሱ ገርፎ ራሱ የሚያለቅስ እኩይ ፓርቲ ነው…!

አሳዬ ደርቤ


ከብልጽግና አስከፊ ባሕሪያት አንዱ የሆነ አገራዊ ክሕደት ወይንም ጥፋት መፈጸም ሲያስብ ድርጊቴን ያከሽፉብኛል የሚላቸውን ንቁ ዜጎች እስር ቤት ማስገባት የሚወድ መሆኑ ነው። እራሱ በፈጸመው (በሚፈጽመው) ጥፋት ሌሎችን መቅጣት የሚያስደስተው ፓርቲ መሆኑ ነው።

ለምሳሌ ያህል “ከህውሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መደራደርና አዲስ የኃይል አሰላለፍ ማዋቀር ያማረው ቀን ይሄንን ቁማሩን የምንቃወም ወገኖችን አፍሶ ከእስር ቤት ካስገባን በኋላ የመሠረተብን ክስ “ከህውሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመገናኘት የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ሞክራችኋል” የሚል ነበር።

ይሄን ብዬ ወደ ሰሞኑ አጀንዳ ስመጣ… “ከክልሌ ባንድራ ስር ቆመህ አንተን እያንኳሰሰ፣ እኔን የሚያወድሰውን ዝማሬ አነብንብ” የሚለው ትዕዛዝ “የኔን ኃይማኖት ተቀብለህ ፥ እኔ ለማመልከው አምላክ የማዜመውን ምስጋና አቅርብ” ከማለት አይተናነስም።

እንዲህ ያለው እብሪት ወለድ ትዕዛዝ ደግሞ በአጸፋ መልክ የእራሱን መዘዝ ይዞ መምጣቱ አይቀርም።

ብልጽግና ግን ሕዝብን ከመጠን በላይ የሚንቅ መናኛ ፓርቲ በመሆኑ አገሬው ጋር የሚያላትመውን አጀንዳ አንጠልጥሎ ወደ ታች ሲገሰግስ ተገፍትሮ መመለስ ወይንም ደግሞ መፈራረስ ሊያጋጥመው እንደሚችል አይረዳም።

ይሄውም የአጸፋ እርምጃ ሲያጋጥመው “ሕዝቡ የተቃወመኝ ምን አይነት ጥፋት ብሠራ ነው?” ብሎ እራሱን ከመጠየቅ ይልቅ “ሕዝቡ የተንጫጫብኝ ማን ቀስቅሶት ነው?” በሚል ቁጣ የካቴና ደንበኞቹን እያፈላለገ ወደ እስር ቤት ማጓጓዝ ሙያው ነው።

የሰሞኑ የአፈና ዘመቻ ታዲያ ከእስካሁኑ ለየት የሚያደርገው ለእስር ቤቱ ደንበኞቹ ብቻ ሳይሆን ለፖሊሶች፣ ለአቃቢያኖች እና ለዳኞችም ጭምር የማይመጥን መሆኑ ነው።

ምክንያቱም ለጆሮ የሚዘገንን ወንጀል የተሸከመ እልፍ አእላፍ ተከሳሽ በወንበሯና በምድሯ ላይ አስቀምጣ በምትሰቃይ አገር ውስጥ “የክልል ባንድራና መዝሙር ወደ ፌደራል ለማሻገር ስሞክር መስከረምና ናትናኤል የተባሉ ተጠርጣሪዎች አክሽፈውብኛል” የሚል ክስ መጦመር አይነፋም።

(ፍትሕ ቢኖር ኖሮ  እንደውም፥  እንዲህ ያለውን ሕገወጥ ክስ ይዞ ከዳኛ ፊት የሚቀርብ ካድሬም ሆነ መርማሪ “ተጠርጣሪ” ተብሎ በቁጥጥር ስር መዋል ነበረበት። )

በመሆኑም የአገሪቷን ሕገ መንግሥት፣ የሕዝብን ፍላጎትና መብት መሠረት ባላደረገ መልኩ ባርነትን የሚቀበሉ ሕጻናት ፍለጋ ወደ ትምሕርት ቤት አምርቶ በፈጸመው ትርምስ በፍርድ ቤት ሊከሰስ የሚገባው የአዳነች አበቤ ካቢኔ በእነ መስከረም አበራና ናትናዔል ያለምዘውድ ላይ የመሠረተውን ክስ አቋርጦ ብልጽግና እጅ ላይ ካቴና የሚያስገባ የፍትሕ ቀን እስኪመጣ ድረስ ወደ ቀጣይ የጥፋት አጀንዳው እንዲሸጋገር እንመክራለን።

Filed in: Amharic