>

"የማይገመት ልብ ያለው፣ ጀግንነት፣ ብልሃት፣ አሸናፊነትንና ጽናትን የታደለ ኃያል ንጉሥ - እምዬ ምንይልክ...! "   (በታርቆ ክንዴ) 

“የማይገመት ልብ ያለው፣ ጀግንነት፣ ብልሃት፣ አሸናፊነትንና ጽናትን የታደለ ኃያል ንጉሥ – እምዬ ምንይልክ…! ”  

በታርቆ ክንዴ 


በጀግንነቱ የሚቀኑ ይጠሉታል፣ ሀገር የሚክዱ ባንዳዎች ይፈሩታል፣ በአንድነት የማያምኑ ይሸሹታል፣ ለሀገርና ለሠንደቅ ሲል መዋደቁን ረስተው፣  ለኢትዮጵያ ክብር፣ ለሠንደቁ ፍቅር የከፈለውን መስዋእትነት ዘንግተው ስሙን ሊያሳንሱ ይዳዳቸዋል። ምኒልክ ያዋጋውና የተዋጋ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊያን አለፍ ሲልም ለመላው የጥቁር ዘር ነው።

የምኒልክ ዘመዶች ትግሉን የሚረዱ፣ ሃሳቡን የሚወዱ፣ እርሱ በቀየሰው የአንድነት መንገድ የሚሄዱ ናቸው። የምኒልክ ጠላቶች ደግሞ ከፍ ያለውን ሀሳቡን በቅናት የሚያወርዱ፣ ማሸነፉንና ለአንድነት እና ለሉዓላዊነት መድከሙን የሚክዱ ባንዳዎች ናቸው። በዓድዋ ተራራ ላይ የተሸነፉት፣ በምኒልክ ብልሃትና ሃሳብ የተበለጡት ሁሉ ጀግንነቱን አምነው አይቀበሉም።

ኢትዮጵያዊነት በደሙ ያለ ሁሉ ምኒልክን አባቴ ይለዋል። እርሱ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ነውና። የነጭ ክንድ ከጀርባው የተነሳለት ጥቁር ሁሉ ይመካበታል። መመኪያ መከታ ነውና።

ምኒልክ በኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያዊነት የተዋደቀ ኃያል ንጉሥ ነው። ኢትዮጵያዊነትን የሚያምን ሁሉ ዓድዋን ሊክድ አይችልም። ለምን ካሉ ዓድዋ በደምና በአጥንት ማሕተም የታተመ እውነት ስለሆነ። ምኒልክ ደግሞ የዚህ እውነት መሪ ነው።

ጀግንነቱን ዓለም መስክሮለታል፣ ስሙን ከፍ አድርጎ ጠርቶታል፣ ታሪክ በማይጠፋ ቀለም፣ በማያረጅ ብራና አስፍሮታል፡፡ ጠላት ሮጦለታል፣ በስሙ ተሸብሮለታል፣ ከእግሩ ሥር ወድቆ ይማሩኝ ንጉሥ ኾይ ብሎለታል፡፡ በጀግንነቱ በጠላቶቹ ልብ ላይ የነገሠ፣ በዝናው ዓለምን ያዳረሰ፣ የጠላቶቹን አንጀት የበጠሰ፣ የወዳጆቹን አንጀት ያራሰ ጀግና ነው እርሱ፡፡

የማይገመት ልብ ያለው፣ ጠላት የማይችለው፣ ጀግንነት፣ ብልሃት፣ አሸናፊነትና ጽናት የታደለው ኃያል ንጉሥ፡፡

ነጭ ባየለበት ዘመን በነጭ ላይ  የገነነ፣ የነጭን ኃያልነት የበጣጠሰ፣ የነጭን አብዮት ያፈራረሰ፣ የጥቁርን ክብር የመለሰ፣ ያለቀሱትን እንባቸውን ያበሰ፣ በጨለማ ውስጥ ለነበሩት የደረሰ፣ በድል ብቻ የገሰገሰ፣ በጨለማው ምድር ብርሃን ያበራ፣ ከተራራ የገዘፈ፣ ዘመናትን በክብር ያለፈ ታሪክ የሠራ፣ የጥቁር አባት፣ የነጻነት መሪ፣ የጨለማ ዘመን አሻጋሪ፣ የአሸናፊነትን ድል አብሳሪ ነው ኃያሉ ንጉሥ፡፡

በደል ያልተገኘባቸው የአፍሪካ ሀገራት በበደለኞች እጅ ወድቀው ነበር፡፡ ቀኝ ገዢዎች በእርስታቸው በተቀመጡት ደጋግ ሕዝቦች ላይ ተነስተው የግፍ ግፍ ይፈጽማሉ፡፡ ሰዎችን እንደ ሸቀጥ ይሸጣሉ፣ ይለውጣሉ፡፡ እያሰሩ አያሌ በደሎችን ይፈጽማሉ፡፡ ባለ እርስት የሆኑት ጥቁሮች በባዕዳን መከራው ጠንቶባቸዋል፡፡ በበደለኞች ተገፉ፣ ተዳፉ፡፡ አፍሪካን የመከራና የስቃይ ምድር አድርገው ኃያልነታቸውን ማስፋት ፈለጉ፡፡ ኃያል ያደርገናል ያሉትን ሁሉ በአፍሪካ ምድር ላይ ፈፀሙ፡፡ ብዙዎችን ያለ በደላቸው በቀያቸውና በእርስታቸው በግፍ ገደሉ፡፡

አፍሪካን የደም ምድር አደረጓት፣ ብርሃኗን ነጥቀው በጨለማ ውስጥ እንድትኖር ፈረዱባት፣ ማንነቷን ወስደው የማይመስላትን ማንነት ልበሽ አሏት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ጨለማ ያልደረሰባት፣  የባዕድ ማንነት ያልነካካት፣ ጨለማ የማይደፍራት፣ ብርሃን የከበባት፣ ጀግና ልጆች ያሏት፣ ደፋር ኩሩ ንጉሥ የነገሠባት ምድር ነበረች፡፡ በጨለማው መካከል ብርሃን ያበራች፣ በጠላት ያልተደፈረች፣ በደምና በአጥንት የተጠበቀች፣ ጀግና ልጆችን የወለደች ወልዳም ያሳደገች ምድረ ቀደምት ሀገር ናት፡፡

ጠላቶች እንደሌሎቹ ሁሉ ሊያጠፏት፣ ክብሯንና ማንነቷን ሊነጥቋት ወደ እርሷ ወሰንም ዘለቁ፡፡  እነዚያ የሮም መሪዎች ነጻ የሆነችው ሀገር ነጻነቷን ሊነጥቋት ቋመጡ፡፡ በሌሎች ሀገራት ድል ለምደዋልና በኢትዮጵያ ሰማይ ሥርም በድል እንደሚንበሸበሹ ተማምነዋል፡፡ ዳሩ ኢትዮጵያ ከሁሉም ትለያለች፣ ለአሸናፊነት የተፈጠረች እንጂ መሸነፍ በፍጹም አይነካካትም፡፡

በጦር ወግቶ ማሸነፍ ለእርሷ ብቻ የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ በየዘመናቱ የተነሱትን ጠላቶቿን እየወጋች ድባቅ እየመታች ኖራለችና ማንም ቢነሳ አትበገርም፡፡ የጠላትን ፉከራና ድንፋታ አስቀድማ ሰምታ ነበር፡፡ ንጉሡ ምኒልክም የሀገሬው ሕዝብ ለዘመቻ እንዲነሳ በማርያም ምሎ አዋጅ አስነገረ፡፡ እንኳን በአዋጅ ተጠርቶ እንዲያውም ለሀገሩ መዝመት የሚወደው የሀገሬው ሰው የንጉሡን ቃል ከያለበት ሰምቶ ተንቀሳቀሰ፡፡

የሮም ሠራዊት በአፍሪካ ምድር የምታበራዋን ብኛዋን መብራት አጥፍቶ፣ አፍሪካን በድቅድቅ ጨለማ ሲያስውጣት ለማዬት የጓጉ የኢጣልያ ወዳጆች የድሉን ዜና ለማስማት ቸኮሉ፡፡

ድል ፈጽማ ከኢጣልያ ሠራዊት እንደማትርቅ ተማምነዋል፡፡ ጥያቄው ድሉ የሚበሰረው መቼ ነው የሚለው ነው፡፡ አይደርስ የለም ያ ቀን ደረሰ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሳይደርሱባቸው አይደርሱም እንጂ ከደረሱባቸው አመላለሱን ያውቁበታል፡፡

አውግስቶስ ቄሳር በሮም ነግሦ በነበረበት በዚያ ዘመን ሮም ቁጥራቸው የበዙ የዓለም ሀገራትን አስገብራ ነበር፡፡ ይህም ንጉሥ ተከብራ እንጂ ተደፍራ የማታውቀውን ሀገር ኢትዮጵያን ለመውረር አይሎስ ጋሎስ በሚባል የጦር አበጋዙ የሚመራ ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ምድር ላከ፡፡ ያም ዘመን ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ በ29 ዓ.ዓ እንደበር ይነገራል፡፡ በዚያ ዘመን ኃያል የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጽሞ ለጠላት የሚቀመስ አልነበረም፡፡ የአይሎስ ጋሎስ  ሠራዊትም ከንጉሡ በታዘዘው መሠረት የኢትዮጵያን ወሰን ለመድፈር ጦርነት ከፈተ፡፡  ኢትዮጵያውያን ጀግኖች  ሀገር ሊወር የመጣውን ጠላት ነዲድ እሳት ሆነው ጠበቁት፣ እንደ አመጣጡ እየለበለቡ አቃጠሉት፡፡

አውግስቶስ ቄሳር ያሰበው ሳይሳካ ሠራዊቱን አስጨረሰ፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጦርና ጎራዴ የተረፈውን ሠራዊት ይዞ እንዲመለስ ለአይሎስ ጋሎስ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

ከኢትዮጵያውያን ጎራዴ የተረፈው ሠራዊትም ብዙዎችን በጎራዴ አስበልቶ፣ በሳንጃ አስወግቶ፣ በበረሃ ትቶ በሐዘን ወደሀገሩ ተመለሰ፡፡

በአውግስቶስ ቄሳር ዘመን የደረሰባቸውን ሽንፈት ያካክሱ ዘንድ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ54 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ሌላ ወራሪ ሠራዊት ላኩ፡፡ በዚያም ዘመን የነገሰው ኔሮ ነበር፡፡ እርሱም ኢትዮጵያን አስገብራታለሁ ሲል ፎክሮ ተነሳ፡፡ አማካሪዎቹ ኢትዮጵያውያንን ማስገበር ፈጽሞ እንደማይቻል አስቀድመው ነገሩት፡፡ እርሱ ግን አሻፈረኝ አለ፡፡ መጣም ተሸንፎ ተመለሰ፡፡

ከአባቶቻቸው የወረሱትን የዘር ሽንፈት ልጆቹ ሊደግሙ በዘመነ ምኒልክ ኢትዮጵያን ሊወሩ ገሰገሱ፡፡ ምኒልክም ሠራዊቱን አስከትሎ፣ ጀግኖቹን የጦር አበጋዞችን ይዞ፣ ከብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ጋር  ጠላት ወዳለበት ገሰገሰ፡፡ በዚያም ጠላትን ድባቅ መታው፡፡ ከዘር የመጣው የኢጣልያ ሽንፍትም በዓድዋ ከፍ ብሎ ተሰማ፡፡ ኢጣልያ አፈረች፣ ኮሰመነች፣ የአፍሪካን ብቸኛ ብርሃን ልታጠፋ ስትቋምጥ የራሷን ብርሃን አጠፋች፣ በዓለም ፊት ተዋረደች፣ ምኒልክ ኃያላን ነን በሚሉት ሁሉ ተፈራ፤ ተከበረ፡፡

በአንድ ጀንበር ዓድዋ ላይ የዓለም ታሪክ ተቀየረ፡፡ አፍሪካ መውጫ ብርሃኗን ከወደ ኢትዮጵያ አየች፡፡ በዚያ መንገድም ለመጓዝ ተነሳች፡፡

ታላቁ ንጉሥ በዓድዋ ተራራ ላይ ጠላትን እንዳልነበር አደረገ፡፡

የኢጣልያ ሠራዊት አብዛኛው በኢትዮጵያውያን ጎራዴ ተበልቶ ላይመለስ አሸለበ፡፡ የቀረው እጁን ሰጠ፡፡ ጥቂቱም ፈርጥጦ አመለጠ፡፡ ጀግና አስታወይና ብልህ ነውና ምኒልክ የኢጣልያ ምርኮኞች በሰላም እንዲኖሩ አደረገ፡፡

ኒኮላስ  ኒዎንቲቭን ጠቅሰው ጳውሎስ ኞኞ ሲጽፉ ʺ ንጉሡ ድል ማድረጋቸውን እንዳወቁ እጅ የሰጡትን ጣልያኖች ሠራዊታቸው እንዳይገድል አስጠነቀቁ፡፡ እንስራ ተሸክመው ለሠራዊቱ ውኃ ያቀብሉ የነበሩ የኢትዮጵያ ሴቶች ሁሉ ሸክማቸውን እያስቀመጡ ምርኮኞቹን በማገዝ ይረዱ ጀመር፡፡ አስክሬኖች በብዛት ተከምረዋል፡፡ በሜዳው ላይ በትንሹ ይወርድ የነበረው ደም ወደ ወንዝነት ተለውጧል” ብለዋል፡፡

ምኒልክ በጠላቶቹ ላይ አይጨክንም፡፡ መሸነፋቸውን አውቀው እጅ ከሰጡ ይንከባከባቸዋል እንጂ፡፡ ጀግና እጁን በሰው ክብር ላይ የሚዘረጋውን ይቀጣል እንጂ እጅ የሚነሳውን አይቀጣም ምኒልክም ጀግና ነውና ጠላት ስለሆኑ ብቻ ይገደሉ አላለም፡፡ ለምርኮኞች እንክብካቤ እንዲደረግ አዘዘ እንጂ፡፡

ʺበዚያ ጊዜ ምኒልክ አንድ መጠለያ አቋቁመው ስለነበር ልብስ፣ ምግብና ውኃ ይሰጣል፡፡ ለቁስለኞችም የሕክምና እርዳታ ይደረግ ነበር፡፡ የቆሰሉት ምርኮኞች የሚጓዙበት ተሰጥቷቸዋል” ሲሉ ጳውሎስ ግሊከንን ዋቢ አድርገው ጽፈዋል፡፡ ምኒልክ ጀግና ብቻ ሳይሆኑ ሩህሩህም ናቸው፤ ቆፍጣና እንጂ ጨካኝ አይደሉም፡፡

” እርር ቅጥል ቢሉም የእርሱ ጠላቶቹ፣

ምኒልክ ጀግና ነው እስከ ዘመዶቹ”

ጠላት ታሪኩን ለማጠልሸት፣ በማይጠፋ ቀለም የሰፈረው ስሙን ለማበላሸት ቢጥርም፣ ምኒልክ ግን ጀግና ነው፡፡ ምኒልክ ዛሬም ድረስ ያለ የሚመስል፣ መንፈሰ ጠንካራ ለልጅ ልጆቹ አሸናፊነትን ያወረሰ፣ ለተቸገሩት የደረሰ፣ የጠላትን ግንብ ያፈራረሰ ኃያል ንጉሥ ነው፡፡

ጠላቶች ስሙን ማሳነስ አይቻላቸውም፡፡ እርሱ ስሙ ለዘላለም ከፍ እንዲል አድርጎ በዓድዋ ተራራ አናት ላይ ሰቅሎታል፡፡ በኢትዮጵያ ምድርም በጸና ዓለት ላይ ተክሎታል፡፡ ጠላቶቹ ይንጫጫሉ፣ የምኒልክ ልጆች ይኮራሉ፡፡ ታሪኩን አክብረው ይከበራሉ፡፡ በአባታቸው የጥንካሬ መንፈስ ተነሳስተው ሌላ ታሪክ ይሠራሉ፡፡

Filed in: Amharic