>
5:13 pm - Wednesday April 19, 1911

ከአገራዊው ዋና ጉዳይ ማናጠቢያ (ከይኄይስ እውነቱ)

ከአገራዊው ዋና ጉዳይ ማናጠቢያ

ከይኄይስ እውነቱ

ላለፈው አንድ ወር ጊዜ የሰዉ ሁሉ ትኩረት ካ(ግ)ታር (Qatar) በተካሄደው የ2022 (እ.አ.አ.) የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ላይ ነበር፡፡ ወያኔ ሕወሓት እና ወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ እንደዚህ ዓይነቱን ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ እንደማናቸውም የትኩረት አግጣጫ ማስቀየሪያ ኹነት ሲጠቀሙበት ኖረዋል፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ለነገሩ እንደዚህ ዓይነቱ ኹነት ኖረም/አልኖረም ጭራቃዊው አገዛዝ የጭራቅ ተግባሩን ያቋረጠበት ጊዜ የለም፡፡ ምናልባት ግርግሩ ጥፋቱን እጥፍ ድርብ አድርጎ ለመፈጸም ምክንያትና ሽፋን ከሚሆንለት በቀር፡፡ በሌላ በኩል መቋጫ በጠፋለት የአገር ጉዳይና የኑሮ ውድነት ናላው ለዞረው ማኅበረሰብ ጊዜያዊ እፎይታና ማረሳሻ የፈጠረለት ኹነት ሆኖ አልፎአል፡፡ ሰላማዊውን የእግር ኳስ ፍልሚያ ማየቱ በራሱ ክፋት የለውም፡፡ ጨዋታው ተረኞቹ ለግል ዓላማቸው በተቆጣጠሩት አገራዊ ቴሌቪዥን መተላለፉ ዜጋው በ4 ዓመት አንድ ጊዜ የሚመጣው ዓለም አቀፍ ጨዋታ ታዳሚ እንዲሆን በማሰብ አለመሆኑ ግን ዕለት ዕለት የዜጎችን ሕይወት እምነታቸውንና ማንነታቸውን መሠረት አድርጎ በጅምላ በመጨፍጨፍ ከሚያሳየው ጭራቅነት የበለጠ ምስክር አያሻንም፡፡ ስለሆነም በራሱ በሕዝቡ ገንዘብ ጨዋታው በ‹ብሔራዊው ቴሌቪዥን› እንዲተላለፍ የገንዘብ ድጋፍ (ስፖንሰር) አድርገናል ብለው የተጮኸላቸው መንግሥታዊ ተቋማት (የግል ከሆኑት ሪል ስቴትና ሲሚንቶ ፋብሪካ በስተቀር) አሰልቺ የማስታወቂያ ግርግር ለብዙዎች ግራ የሚያጋባ ሆኖ አልፏል፡፡ 

ከዚህ ቀደም እንደገለጽሁት ላለፉት ሠላሳ ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያና ሕዝቧ መሆን ያለበት ብሔራዊ ቴሌቪዠንና ራዲዮ ባጠቃላይ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃኖች የውሸትና ቅጥፈት መሣሪያ፣ ንጹሐንን በሐሰት መክሰሻና መውቀሻ፣ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ማሠራጫ፣ ባጭሩ አገርን ማጥፊያ በመሆናቸው ምክንያት በቤቴና በገዛ ንብረቴ ቦታ አልነበራቸውም፡፡ አሁንም የላቸውም፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ዓለም አቀፍ ክንውን የቤተሰብን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል የኳስ ጨዋታውን ለመከታተል መክፈቱ የግድ ነበር፡፡ ታዲያ ባለፉት ሠላሳ ቀናት ቤተሰብ ኳስ ጨዋታው በሚካሄድበት ዕለት ሁሉ ሲተቹ እሰማ ነበር፡፡ የትችቱም መሠረት ጨዋታው ወደ ሕዝቡ እንዲደርስ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት ተቋማት ባመዛኙ የመንግሥት/የሕዝብ ናቸው፡፡ (እኔ በተለዋዋጭነት ተጠቀምሁባቸው እንጂ እውነታው በወንጀለኞቹ ሥርዓት የ‹መንግሥት› የሚለው ሕዝብን አይመለከትም)፡፡ የግሎቹ አጋጣሚውን ራሳቸውንና ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቀሙበት ይታወቃል፡፡ ተገቢም ነው፡፡ ያም ሆኖ ድንቊርና ይሁን ሆን ተብሎ በተወሰኑ ደቂቃ ልዩነቶች የጨዋታውን ሂደት ለመከታተል እስኪያስቸግር ድረስ አንዳንዴም ግብ በሚቆጠርበት ጊዜ የቴሌቪዥኑን መስኮት እስኪሸፍን ድረስ በሁለት ማዕዝናት የሚያጋድሙት የድርጅቶቹ ማስታወቂያ ምነው መተላለፉ በቀረ የሚያሰኝ እንደሆነ ከቤተሰቤ ጀምሮ በርካታ ተመልካቾች ሲያማርሩ ስሰማ አንገብጋቢ ጉዳይ ባይሆንም እንኳን ለታሪክ ተመዝግቦ ማለፍ ይኖርበታል በሚል ይህንን ማስታወሻ ለመጻፍ ተገድጄአለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የ‹መንግሥትም› ሆኑ የግል የሚባሉት ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃኖች በነፃነት የሚንቧቸሩበትና ሁሉም ተንታኝ የሆነበት መስክ ‹ስፖርቱ› ብቻ ይመስለኛል፡፡ እሱም ቢሆን አልፎ አልፎ የጐሣ ፖለቲካው ሰለባ ሆኖ ተመልካቾች እንዲሁም ተጫዋቾች ርስ በርስ የተናረቱበት ጊዜ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ይህ ዓይነት ክስተት ሲፈጠር ዘገባው ወደ ‹መደበኛው› (ሐሰት መረጃ) ይለወጥና ‹ነፃነቱም› ይገደባል፡፡ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ በሚባል ሁናቴ ያለች አገር ውስጥ የወንጀል ሥርዓቶቹ እንደ ኳስ ያሉ መዝናኛዎችን (ከቱርክ ያስገቡት ተንቀሳቃሽ ፊልምን ያስታውሷል) ወጣቱን ለማደንዘዝ እንደ ‹ማደንዘዣ ዕፅ› እየተጠቀሙበት መሆኑ በእጅጉ ያስገርማል፡፡ በመሆኑም የወንጀል ሥርዓቶቹ ሰለባ የሆነው ወጣት ቀን ከሌት ስለ አውሮፓ አገሮች እግር ኳስ ጨዋታ ሲጨነቅ/ሲጠበብ፣ ‹ዐዋቂና ተንታኝ›፣ ‹ለውጭ ቡድኖች አሠልጣኞች መካሪ› ሲሆን አልፎ ተርፎም ሲቧቀስ አይገርምም? ሁላችንም አንገርምም? 

በነገራችን ላይ የካ(ግ)ታር (Qatar) ጉዳይ ከተነሣ እግረ መንገዴን ማንሣት የምፈልገው ሜዲያውና ሰዉ ሁሉ ከራሱ ዐንቅቶ  ‹ኳታር› (“Quatar”) የሚል ስም ፈጥሮ የሌለ አገር ስም ሲጠራ ሰንብቷል፡፡ በርግጥ የአገርም ሆነ የሰው ስም አጠራር ማዛባቱ የኛ አገር ብቻ ችግር አይደለም፡፡ የኛ በጣም ራቀብኝና ነው የገረመኝ፡፡ ያልተጻፈ ማንበብ ያህል፡፡ ቀደምት ሊቃውንት አባቶቻችን በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊውም የባዕደ አገር ስምም ይሁን የሰው ስም በኢትዮጵያዊ አጠራር ሲሰይሙ ምክንያት ነበራቸው፡፡ የአሁኑ ግን ያለዕውቀት በዘፈቀደ የሚደረግ ነው፡፡ ውድድሩን ያካሄደው አገር የእገሌ አገር ሰዎች እንዲሁ ይሉኛል፤ ገሚሱ ደግሞ እንዲህ ይሉኛል በሚል ደጋግሞ መረጃ (https://youtu.be/utP3PbWHZrU) አስተላልፎ እያለ፣ የእኛዎቹ ‹መገናኛ ብዙኃን› ተብዬዎች ራሳቸው ስተው ብዙውን ተመልካች አስተውታል፡፡ ይህንን ስህተት በውሸትና በቅጥፈት መረጃ ስታስቡት ምን ያህል ሕዝቡን እንዳበላሹት መገመት አይከብድም፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ዜና ወይም መረጃ የሚያስተላልፉ ‹ባለሙያዎች› ጠይቀው/አጣርተው ማቅረብ ከሙያው የሚጠበቅ ዝቅተኛ መሥፈርት አይደለም? የእኛዎቹ መገናኛ ብዙኃን በተለይም የመንግሥትና መንግሥት አከል (Party/Government Affiliated) የሆኑት በዋናነት የእውነትና ሐቅ ጦመኞች በመሆናቸው  እንዲህ ዓይነቱ ‹ቀለል› ያለ ስሕተት ብዙም ላያሳስብ ይችል ይሆናል፡፡

ለማንኛው የእግር ኳሱ ኹነት ለወንጀል ሥርዓቱ አጀንዳ ማስቀየርያና ማደናገሪያ፤ ለሕዝቡ ደግሞ ዕለት ተዕለት ከሚታየውና ከሚሰማው አገራዊ ሰቆቃ ጊዜያዊ ማረሳሻ ሆኖ አልፏል፡፡

Filed in: Amharic