>

ኢንጂነር ታደለ ብጡል.... (ታሪክን ወደኋላ)

ልክ በዛሬዋ ዕለት  የሲቪል መሃንዲስ፣ የባንክ ባለሙያና ፀሐፊ የሆኑት ኢንጂነር ታደለ ብጡል  ምድራችንን ተቀላቀሉ…!

ታሪክን ወደኋላ


በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ የተሳተፉ ፣ ሁለገብ ባለሙያ እና ዘርፈ ብዙ ስራዎችን የሰሩ ፣ የሲቪል መሃንዲስ፣ የባንክ ባለሙያና ፀሐፊ የሆኑት ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት ከ 96 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተወለዱበት ዕለት ነበር።

ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት ታህሳስ 21 ቀን 1919 ዓ.ም አዲስ አበባ ተወለዱ፡፡ በአራት ዓመታቸው፣ አዲስ አበባ በሚገኘው ባለወልድ ቤተክርስቲያን ግቢ አብነት ትምህርታቸውን ጀምረውና ዳዊት ደግመው እንደጨረሱ የቃል ትምህርታቸውን ቀጥለው ከአቡነ ማቴዎስ የድቁና ማዕረግ ተቀበሉ፡፡ ጣሊያን ከአገራችን ከተባረረች በኋላ የባላባት ልጆች ትምህርት ቤት ገብተው ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታተሉ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መግቢያ ከወሰዱት 60 ተማሪዎች መሐከል ፈተናውን ካለፉት 17 ልጆች ጋር ታደለ ብጡል ክብረት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመስከረም ወር 1935 ዓ.ም ትምህርት ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያው አንድ ዓመት የክለሳ ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ፣ መደበኛው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት መስጠት ተጀመረ፡፡

በ 4ኛው ዓመት በ 1940 ዓ.ም ተፈትነው አለፉ፡፡ ወዲያውኑ በኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ተቀጥረው እስከ 1948 ዓ.ም ድረስ ሲሰሩ ቆዩ፡፡ በዚሁ ዓመት ወደ አሜሪካ ሄደው በ1953 ዓ.ም በስተረክቸራል ዴዛይን የመጀመሪያ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ዲግሪ ተቀበሉ፡፡ ከዚያ ወደ ስዊድን ሀገር ሄደው በጆንማትሰን ኩባንያ ተቀጥረው የቬኔግሬን የሪሰርች ማዕከል ግንባታ ላይ መሥራት ጀመሩ፡፡ በዚህ መሀከል የ 1953 ዓ.ም የእነጀነራል መንግሥቱ ንዋይ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ ያደረጉትን ጥረት፣ ስዊድን አገር አምባሳደር ከነበሩት ወዳጃቸው አቶ ተፈሪ ሻረው እና ከቅርብ ጓደኛቸው ኢንጂነር አሰፋ ብርሃነ ሥላሴ ጋር ሆነው መፈንቀለ መንግሥቱን ደገፉ፡፡ ሆኖም የመንግሥት ግልበጣ ሙከራው ስለከሸፈ ሁሉም ፓስፖርታቸውን ከመነጠቃቸው ለስደት ተዳረጉ፡፡

በዚህ ምክንያት የጆን ማትሰን ኩባንያ ባለቤት የሆነው ሰው፣ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የመስራት ፍላጎት ስለበረው፣ ኢንጂነር ታደለን ከሥራ አባረራቸው፡፡ በዚህ መሐል፣ ቀደም ሲል እዚህ አዲስ አበባ ገብቶ የግዮን ሆቴልን የመዋኛ ገንዳ የሰራው መሐንዲስ ጉስታቭሰን፣ ለምን እኛ ቢሮ አትሰራም ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ኢንጂነር ታደለ፤ ጉስታቭለን ከሚሰራበት ሀዩስ ኮንሱልት ቢሮ ተቀጥረው ሁለት ዓመት ከሰሩ በኋላ የራሳቸውን የሪል ስቴትና የግንባታ ድርጅት አቋቁመው ለግላቸው ይሰሩ ጀመር፡፡ በዚህም አሮጌ ቤቶችን እየገዙ አድሶ በማከራየት ሥራ ተሰማርተው በቂ ሀብት ለማግኘት በቁ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ በመከሰቱ የወሎ እና የትግራይ ሕዝብ በረሀብ እያለቀ መሆኑን ከዲያምቢልቢ ፊልም እንዳዩ የአገራቸውን ሕዝብ ለመርዳት ከስዊድን ሕዝብ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መድኀኒት፣ የሆስፒታል አልጋ፣ የኤክስሬይ መሣሪያ ስላገኙ የትራንስፖርቱን ወጪ ከራሳቸው ገንዘብ በመክፈል ቁሳቁሶቹን አምጥተው ለእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ለአቶ ሽመልስ አዱኛ ስላስረከቡ በደብዳቤ አመስግነዋቸዋል፡፡

ከዚያ ቀጥሎ ስድስት ጊዜ ከስዊድን እየተመላለሱ በመምጣት ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ከድኩማን ድርጅት፣ ለገበሬዎች ማህበርና ለዕድገት በህብረት ተማሪዎች፣ ለከፍተኛ 14፣ ቀበሌ 12 ነዋሪዎች 300 ሕፃናት የሚማሩበት ትምህርት ቤት ሰርተው በነፃ አስረክበዋል፡፡ እነዚህና ሌሎች በጎ ሥራዎቻቸው “በአቶ አክሊሉ አበሩ የተዘጋጀው የኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት የሕይወት ታሪክ አርዓያነት” በሚባለው መጽሐፍ የተገለፀ በመሆኑ መፅሐፉን ማንበብ ጥሩ ይሆናል፡፡

እኚህ ሰው የአክሱም ሐውልት ከጣሊያን አገር ተነቅሎ በጥንት ስፍራው ይቆም ዘንድ ከጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ከተደራደሩት ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ሀውልቱን የመመለስ የአዎንታ መልስ ከጣሊያን መንግሥት ከተገኘ በኋላ ሐውልቱን ለመንቀል ለመጓጓዝ እና በጥንት ስፍራው አክሱም ከተማ መልሶ ለመትከል በተደረገው ጥናት እና ምርምርም ኢንጂነር ታደለ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ለእነዚህ ከፍተኛ ተግባሮቻቸው የሚከተሉት ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል፤

1. የወርቅ ሜዳሊያ፣ ከኢፌዴሪ መንግሥት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

2. የወርቅ ካባ፣ ከክልል አንድ መስተዳድር ፕሬዚዳንት

3. ሐውልቱን ለማስመለስና መልሶ ለማቆም ባደረጉት ሀገራዊ ፍቅር ያለበት እንቅስቃሴ፣ የአክሱም ሕዝብ በመደሰቱ፣ የአክሱም ሐውልቶች ቅርፅና ሐረግ ያለበት ከእንጨት የተሰራ፣ ታጣፊ የፎቶግራፍ ማቀፊያ ሸልመዋቸዋል፡፡

በበጎ አድራጎት ሥራቸው ትምህርት ቤቶችን በመክፈታቸው እና ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት ላደረጉት ጥረት ከሌሎች ድርጅቶች የሚከተሉትን ሽልማቶች አግኝተዋል፡፡

1. የ2008 ዓ.ም የዓመቱ በጎ ሰው ድርጅት ሽልማት በቅርስና ባህል ዘርፍ፤

2. ከንባብ ለሕይወት ድርጅት የዕድሜ ዘመን ታላቅ የጥበብ ባለውለታ ዋንጫ፤

3. ከ2002 እስከ 2009 ዓ.ም የዲካ ትራቨል ኤንድ ሎጅስ አስጎብኝ ድርጅት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ለፈፀሟቸው ከፍተኛ ተግባራት ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡

እንዲሁም ለአዲስ አበባ ዴዛይን ትምህርት ቤት፣ ለያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እና ለኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ላደረጉላቸው ልዩ ልዩ ድጋፎች ሁሉም የሚከተሉትን ሽልማቶች ሰጥተዋቸዋል፡፡

1. ለአዲስ አበባ ዲዛይን ትምህርት ቤት፣ ከፊንላንድ ኤምባሲ ለምነው ባስገኙት 650 ሺህ ብር ባለ 2 ፎቅ ቤት በማሰራታቸው ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እጅ የተማሪዎች መመረቂያ የሆነ ውብ ሥዕል ተሸልመዋል፡፡

2. የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን እና የአዲስ አበባ ዲዛይን ትምህርት ቤት ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ከፍ እንዲል በኮሚቴ አባልነታቸው ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሁለቱ ትምህርት ቤቶች ስም በዲዛይን ትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በአርቲስት በቀለ መኮንን እጅ አንድ ውብ ሥዕል ተሸልመዋል፡፡

3. የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማኀበር የሕፃናት ትምህርት ቤትና የማኀበሩን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከፊንላንድ ኤምባሲ እና ከካናዳ ድርጅት ለምነው በአገኙት ገንዘብ ሙሉ እድሳት እንዲደረግ ላደረጉት አስተዋፅዖ ከማህበሩ ፕሬዚዳንትና ከፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኀበር ተሸልመዋል፡፡

ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት ደራሲም ናቸው፡፡ ከ15 በላይ የሚሆኑ መጽሀፍት በማዘጋጀት ለአንባቢ አበርክተዋል፡፡ በተጨማሪም በሰባ ስድስት ዓመታቸው የምልክት ቋንቋ በመማር የምልክት ቋንቋ መጽሀፍ ለመፃፍ ችለዋል፡፡ ከዚህ ሌላ “ኢትዮጵያ ጽናት” የሚል ፊልም ፕሮዱስ የሀገራቸውን ታሪክ ለምርምር በመሰነድ ታሪክ ሰርተው  ለህዝብ አበርክተዋል፡፡ ደራሲ እና ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት በስነጥበብ ፣ በታሪክና በቅርስ ጠባቂነት ፣ በንግግር አዋቂነት ፣ በበጎ አድራጊነት ስራቸው  እኛ ኢትዮጵያዊያን  ታታሪነትና ሀገርን መውደድ በተግባር ያሳዩን ትልቅ ሰው ተመልክተን እንደ እሳቸው መሆን ቢያቅተን የአቅማችን ለሀገራችንና ለወገኖቻችን ልናደርግ የተገባ ነው፡፡ መማራችን ፣ ሀብት መሰብሰባችን ለሀገራችን ለወገኖቻንን ካልሆነ………ለጥምቀት ያልሆነ…. እንደሚባለው፡፡ ከእሳቸው ግጥሞች አንዱ…

ጣቶችህን ዘርጋ ይበላለ ጣሉ

አጭርና ረጅም ሆነው ይታያሉ

ቀጫጭኖች ወፍራሞችም አሉ

ጨብጣቸውና እኩል ይሆናሉ፡፡

Filed in: Amharic