>

ሊቁ አለማዬሁ ሞገስ ደርሶ (በጌታ በለጠ )

ሊቁ አለማዬሁ ሞገስ ደርሶ

በጌታ በለጠ (ደብረ ማርቆስ፣ ጎጃም)


እንሆ ሊቅ፡፡ ዛሬ የምናወሳው ከልጅነት ዘመናቸው ጀምረው ሲያነቡ እና ሲጽፉ ስለኖሩት ሊቅ ደራሲ እና መምህር አለማዬሁ ሞገስ ደርሶ ነው፡፡ አዎ፣ ከስር በፎቶግራፍ የሚታዩት ግለሰብ ሊቁ አለማዬሁ ሞገስ ናቸው፡፡ አለማዬሁ ሞገስ ትውልዳቸው ጎጃም፣ ሜጫ ነው፡፡ ሜጫ ከባህርዳር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ቦታ ናት፡፡ አባታቸው መሪጌታ ሞገስ ደርሶ እና እናታቸው ወይዘሮ ወርቅነሽ ደስታ ይባላሉ፡፡አለማዬሁ ሞገስ የተወለዱት በ1913 ዓ/ም ነው፡፡አለማዬሁ ገና በልነታቸው ከፊደል እስከ ጾመ ድጓ ደረስ በአባታቸው ቤት ተምረዋል፡፡አባታቸው መሪጌታ ደርሶ እውቅ የቅኔ ዘራፊ ናቸው። አለማየሁ ሞገስ “መልከዐ ኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ቅኔ ከአባታቸው የወረሱ መሆናቸውን እንዲኽ ሲሉ በግጥም ይገልጻሉ።

ሊቅ ሞገስ ደርሶ የሰራልኝ ቤት፣

ቅኔ ነው ልውረሰው በታላቅ ትጋት።

አለማዬሁ የቅኔ ትምህርታቸውን ያገኙት ጎጃም ምድር ብቻ አይደለም። ወደ ወሎም ዘልቀው ሸምተዋል። ወሎ ክፍለሀገር፣ ዞብል ከተባለ ቦታ በመኼድ ከመርጌታ ወልደሰንበት ቅኔ ቤት ቅኔ ተምረዋል፡፡ እዚያው ወሎ ውስጥ እየተዘዋወሩ ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ትርጉም ተማረዋል፡፡ ይኼንን በተመለከተ ደራሲው ” ሁሉም ሁሉን ይወቅ” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 12 ላይ በ1936 ዓ /ም ከብሉይ ተክሌ ዘንድ ብሉይ ኪዳን ያጠኑ እንደነበረ ገልጸዋል።

ታዲያ እኒኽ ሊቅ ቅኔን እንዲኽ አድርገው ይረዱታል፥ የተረዱትንም ያብራሩታል። 

“ቅኔ ግዕዝ ወልዶ አሳድጎ በሽምግልናው ለአማርኛ ያስተዋወቀው፣ በሰምና ወርቅ ተሸልሞ፣በኀብር አሸብርቆ፣ በመንገድ አጊጦ፣ የደቂቀ ግዕዝን አንጎል ለማርካት፣ በደስታቸው ላይ ደስታ ለመጨመር፣ የልቡና ተድላ፣ የህሊና ሐሴት፣ የአእምሮ ትፍሥሕት፣ የድካም መድኀኒት፣ የኀዘን ማስረሻ፣ የፍልስፍና ማጎልመሻ…ጤፍ ሥጋዊ ምግብ እንደሆነች እሱም አእምሮአዊ ምግብ ሆኖ ከልዑል እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠ ሀብት ነው።”

ቅኔዋን ፉት ካሉ በኋላ ከመርጌታ ይኸይስ የሥዕል ጥበብ ተምረዋል፡፡ የሥዕል መስሪያ ግብዓቶች አሥመራ ይገኛሉ የሚል ወሬ ሰምተው ከወሎ ወደአሥመራ በኼዱ ወቅት ለበርካታ ዓመታት ሲቀመጡ ትግሬኛ ቋንቋ ተማሩ፡፡ አጋጣሚዎችን ሁሉ ለመልካም ነገር መጠቀም ማለት ይኼ ነው። አላማዬሁ ብርቱ ናቸው። መኼድ አይሰለቻቸውም። በአንድ ወቅት ኢየሩሳሌም የሚገኘውን የጌታችን መቃብር ለመጎብኘት አሰቡ፣ መንገድ ጀመሩ። መንገድ ላይ ሱዳንን ይገዙ የነበሩ ቅኝ ገዥዎች አስረዋቸው ለአንድ ዐመት በቆዩበት ወቅት ዐረብኛ ቋንቋ ለመዱ፡፡ 

ከስደት መልስ በአዲስ አበባ ከተማ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው ሱዳን ላይ የተማሩትን አረብኛ እና ተጨማሪ ዕብራይስጥኛ ቋንቋ ተማሩ፡፡ደራሲው አዲስ አበባ የመጡት ከ1940 ዓ/ም በፊት ወይም በ1940 ዓ/ም እንደሆነ የሚያመለክተው በ1940 ዓ/ም ጃንሆይ በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት ጠርተው እንዳነጋግሯቸው” ሁሉም ሁሉን ይወቅ” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 12 ላይ ጽፈዋል።

በዘመናዊ ትምህርትም ገፍተው ስለነበረ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ቋንቋ እና ታሪክ ሁለት ድግሪ ይዘዋል፡፡ በጣሊን አገር በሥነ ጽሑፍ ሌላ ድግሪ ተቀብለዋል፡፡ አለማዬሁ ሞገስ ልዩ የቋንቋ ችሎታ እንዳላቸው የሚያሳዬው ግእዝ፣ትግሬኛ፣ኦሮሞኛ፣ አገውኛ፣አረብኛ፣ዕብራይስጥኛ፣ ግሪክኛ እና እንግሊዝኛ የሚናገሩ መሆናቸው ነው፡፡  ደራሲው “ሁሉም ሁሉን ይወቅ” ሲሉ በ187 ዓ/ም ባሳተሙት መጽሐፍ ገጽ 10 ላይ እንዲህ ይላሉ። “ዘመናዊ ትምህርት ከመከታተሌ በፊት የቅኔ መምህር ሆኜ መጻሕፍት ሐዲሳትን አጥንቼ ነበር። ከዚያም በኋላ የሐይማኖት ትምህርቴን ለማጣራት ዘጠኝ ቋንቋ ( ቋንቋዎች) አጥንቼ ነበር። አሁን ግን በእርጅናና ብቸኝነት ምክንያት ስለማልጠቀምባቸውም ከትቂቶቹ በስተቀር ወደሀገራቸው መመለስ ጀምረዋል።” 

አለማዬሁ ሞገስ አዲስ አበባ የዲፕሎማቶችና የነገሥታት ቤተሰቦች ብቻ ከሚማሩበት ሳንድፎርድ ትምህርት ቤት ያስተምሩ እንደነበረ መንገሻ ከበደ ተሰማ (የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ልጅ) በአንድ ቃለ መጠይቆ ሲያወሩ ሰምቻለሁ። ከዚያ በፊት የቅኔ መምህር በመሆን መጻሕፍት ሐዲሳትን አስተምረዋል። በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ተቀጥረው ለብዙ ጊዜ አስተምረዋል፡፡

የደራሲው ግጥሞች ግሩም ናቸው። የደራሲውን የግጥም ችሎታ ለማወቅ “መልከዐ ኢትዮጵያ” የተሰኘውን መጽሐፋቸው ማንበብ መልካም ነው።”መልከዐ ኢትዮጵያ” የተጻፈው የሀገራችንን ልምላሌ እና ሀብት፣ ቁንጅናና ውበት በቅኔ ለመግለጥ እንደሆነ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ሰፍሯል፡፡እቴጌ መነን አስፋው ለትምህርት መስፋፋት ያደረጉትን አስተዋጽኦ ደራሲው እንዲኽ ሲሉ በግጥም ይገልጹታል። በእርግጥ የግጥሙን ይዘት በሌላ መንገድ የተረዱትም አልጠፉ።

ስንፍና ብልግና የሴቶች ጋኔን፣

መጽሐፍ ብታሳያቸው እቴጌ መነን፣

ጥሏቸው በረረ በትቂት ዘመን። 

አለማዬሁ ሞገስ ዕድሜያቸውን ሙሉ ሲያነቡ እና ሲጽፉ ነው የኖሩት። በዘመናቸው ከደረሷቸው መጽሐፍት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

 1. አንድ እረኛ አንድ መንጋ (1989)
 2. ወይዘሮ አለሚቱ (1857)
 3. ሰምና ወርቅ አማርኛ እስኪ እንወቅ አንደኛ መጽሐፍ (1953)
 4. ሰምና ወርቅ አማርኛ እስኪ እንወቅ ሁለተኛ መጽሐፍ (1955)
 5. የአማርኛ ግጥምና ቅኔ ማስተማሪያ (1954)
 6. የድርሰት አብነት (1957)
 7. ሰዋሰወ ግእዝ ተሰነዐወ (1950)
 8. የአማርኛ ሐረግ (1967)
 9. መልክዐ ኢትዮጵያ 
 10. ሰርግና ልማድ (1956)
 11. የኢትዮጵያ ቅኔ
 12. ለምን አልሰለምሁም (1990)
 13. የግእዝ ቅኔ ዜማ ልክ (1967)
 14. ሁሉም ሁሉን ይወቅ (1987)

እኒህ ገናና ሊቅ በ1956 ዓ/ም ወይዘሮ አበበች ወልደ ትንሣኤ ከተባሉ ሴት ጋር በጋብቻ ተጣምረው ዘራቸውን ተክተው በ1992 ዓ/ም ከዚህ ዓለም ድካም ተሰናበቱ፡፡ 

Filed in: Amharic