>

የታላቁ ንጉሥ መይሳው ካሳ ልደት ጥር 6 እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፤ ንጉስ ሆይ በመወለድዎ አገሬ አትርፋለች..

ሔቨን ዮሐንስ

የታላቁ ንጉሥ መይሳው ካሳ ልደት ጥር 6 እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፤ ንጉስ ሆይ በመወለድዎ አገሬ አትርፋለች…!

ሔቨን ዮሐንስ

መይሳው ካሳ ዘመነ መሳፍንት እንዲያከትም እንዲሁም ታላቅና ገናና አገር እንዲትሆን ሲታትር፤ ከዘመነ መሳፍንት ሸማምንቶች ጋር ጦር እየገጠመ፣ በእሳት ላይ እየተረማመደ፣ ሊገድሉት ሲያሳደዱት እየተዋጋ፣ በዱር በገድል እያደረ ህልሙን ለማሳካት ብዙ ውጣ ውረድን እና ረፍት አልባ ቀኖችን ለዓመታትን አሳልፋል። 

መይሳው ካሳ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ (አባ ታጠቅ) የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሥራች ፋናወጊ ነው። የኢትዮጵያ ባል የኢየሩሳሌም እጮኛ ባለ ራእይ ንጉሥ አጤ ቴዎድሮስ አገሩን ኢትዮጵያ ከገናና አገሮች አንዷ አድርገው እስራኤልን ደግሞ ከምርኮ ለማዳን ተስፋ ሰንቆ ሥራን ይሰራ ነበር፤ ለዚያም ነው የኢትዮጵያ ባል የኢየሩሳሌም እጮኛ የተባለው። አጤ ቴዎድሮስ ከመንገሡ በፊት መጠሪያ ስሙ ደጃዝማች ካሳ ኃያሉ ይባል ነበር። ከንግሥና በኃላ ያለውን አንቱ እያልኩ ልቀጥል።። 

ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ የግዛት ባላባቶችን በጦርነት አሸንፎ፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የነገሱት በደረስጌ ማርያም የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም ነው፡፡ 

ጦረኛው ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ ተገዳዳሪም አልነበራቸው ለጥንካሬያቸው ምንጭ እቴጌ ተዋበች እንደነበረች ይነገራል። እቴጌ ተዋበች ሚስት ብቻ ሳትሆን አማካሪም ታታሪ ሠራተኛም ጭምር ነበረች። ደጃች ካሳ ኃይሉ በ1845 ዓ.ም የጎጃሙን ባላባት ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴን ‹‹ጉራምባ›› ላይ እንዲሁም በጎንደር ቤተ-መንግሥት ንጉሥ አንጋሽና ሻሪ የነበሩትን ራስ አሊ (የወቅቱ ባላባቶች ሁሉ አለቃ)ን ‹‹#አይሻል›› ላይ ካሸነፉ በኋላ ንጉሥ መሆናቸው እንደማይቀር በህዝቡ ዘንድ እየታወቀ መጣ፡፡ 

ተገዳዳሪ ያልነበራቸው ካሳ ኃይሉ ለተረኛው ተጋጣሚ ለደጃች ውቤ መልክተኛ ላኩ። ደጃች ውቤም ለመንገስ ደፋ ቀና እያሉ ነበርና ማነው እንዲህ የሚቀብጠው ብለው “ማነህ አንተ” ሲሉ ለመልክተኛው መልስ ላኩበት። መይሳው ካሳም “ስሜን ሰሜን ላይ እነግርሃለሁ” ብለው መልስ ልከው ነበር። እንዳሉትም የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም የስሜንና የትግራይ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያምን ‹‹ቧሂት›› ላይ ድል ካደረጉ ከሁለት ቀናት በኋላ የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም፤ ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ሊነግሱባት አስጊጠው ባሰሯት ደረስጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ዕጨጌው በግራ፤ ጳጳሱ በቀኝ በኩል ተቀምጠው፣ መጽሐፈ ተክሊል እየተነበበ፣ በጳጳሱ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የታላቋ ኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኑ! 

ባለቤታቸው ወይዘሮ ተዋበች አሊ አብረው ቆርበው አክሊል ተደርጎላቸው የእቴጌነት ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በታሪካዊቷ ቦታ ደረስጌ ማርያም አዋጅ ወጥቶ ነጋሪት እየተጎሰመ ነው! ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ደጃዝማች ካሣ ስማቸው ‹ቴዎድሮስ› ተብሎ ንጉሠ ነገሥት ሆነዋልና ‹ደጃዝማች ካሣ› ብለህ የጠራህ ሁሉ ትቀጣለህ›› ተብሎ ተነገረ፡፡ አዲስቷ ኢትዮጵያ፣ አንድቷ ኢትዮጵያ በዚሁ በታላቋ ደራስጌ ማርያም አዋጅ ተነገረ። እንዲሁም ዘመነ መሳፍን 

አጤ ቴዎድ ከንግሥና በፊት ይሁን ከንግሥና በኃላ  ስለ አገራቸው ብዙ እጅግ ብዙ ህልሞች አልመው ደፋ ቀና ሲሉ እንግሊዞች እጅህን ስጥ አሏቸው። መይሳውም ህልሙን በልቡ ይዞ ዳገት ቁልቁለት ሲወጣና ሲወርድ #በጋፋት ኢንዱስትሪውን አሳልጦ ህልሙን ሊገላገል ሲል እጅህን ስጥ ሲባሉ እኔስ አገሬ እወድሻለሁ፤ ሞቼ አስከብርሻለሁ እንጂ እጅ ሰጥቼ አላዋርድሽም ሲሉ የሞት ጽዋን ተጎነጩ። መቅደላ ታላቁ ንጉስ ሲወድቅባት #ጋፋትም በዛን ዘመን የተወጠነ ኢንዱስትሪ ተቋረጠ። የመይሳው ህልም ቆመ። 

በነገራችን ላይ አጤ ቴዎድሮስ እጅ ሰጥተው አገርና ህዝባቸውን ላለማዋረድ ሲሉ ሽጉጥ ጠጥተው፤ ሞትንና ፍርሃትንም አሸንፈው ከማለፋችን በፊት ለእንግሊዙ ጀነራል ናፒየር መልክት ጽፈው ነበር። ይህ መልክት እጅግ ልብ ይነካል። የአጤ ቴዎድሮስ ደብዳቤ ከህግ እና ከሞራል አንግል ቢተነተን ለዛሬውም ትውልድ ይጠቅም ነበር። የሆነው ሆኖ ደብዳቤው እንዲህ ይላል:- 

“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ በሦስትነት በአንድነቱ በክርስቶስ ያመነው ካሳ መቼም ያገሬ ሰዎች በእግዚአብሔር ኃይል እኔ ካልወረድኩላችሁ ሽሽታችሁን አትተውም። ክርስቲያኑን ሁሉ ጉልበት አለኝ መስሎኝ ካረመኔ አገር አግብቼው ወንድ የሌላት ቆንጆ አለች፣ ወንድ የነበራት ቆንጆ ነበረች፣ ትላንትናም የሞተባት ትኖራለች ሽማግሌ ልጅ የሌለው ባልቴት ልጅ የሌላት፣ እኔ የምጦራቸው ብዙ በከተማየ አሉ። እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ፍቀዷቸው። ያረመኔ አገር ነውና ያገሬ ሰው ገብር ስርዓት ግባ ብየው ብለው እንቢ ብሎ ተጣላኝ። እናንተ ግን በስርዓት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ። እኔን ወደውኝ የተከተሉኝ ሰዎች አንድ እርሳስ ፈርተው ጥለውኝ ሸሹ፣ ልትቀጧቸው ከሮጡት ሰዎች ጋር አልነበርኩም፣ ጌታ ነኝ መስሎኝ ባልሰላ መድፍ ስታገል ውየ ነው። ያገሬ ሰው የፈረንጅ ሀይማኖት ይዟል እያለ አስሩን ምክንያት የሰጠኝ ነበር። እኔ ከከፋሁበት እግዚአብሔር መልካም ይስጠው። እንደወደደ ይሁን እግዚአብሔር ቢሰጠኝ ሁሉን ልገዛ ሀሳብ ነበረኝ። እግዚአብሔር ቢነሳኝ ልሞት ሀሳቤ ይህ ነበር። ከተወለድሁም እስከ አሁን ወንድ እጄን ጨብጦት አያውቅም ነበር፤ ሰዎች ሲሸሹኝ ተነስቼ ማረጋጋት ልማድ ነበረኝ፣ ጨለማ ከለከለኝ። እንደ እኔ አያድርጋችሷሁ። እንኳንስ የሀበሻ ጠላት የኢየሩሳሌም ዘምቼ ቱርኮችን አስለቅቃለሁ መስሎኝ ነበር። ወንድ ያቀፈ ወንድ ተመልሶ አይታቀፍም። ” 

“የአገሬ ሰው ገብር ስርዓት ግባ ብየ ብለው ተጣላኝ። እናንተ በሥርዓት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ።” የምትለው በተለይ ከህግና ከሞራል አንፃር ብዙ ትርጉም አላት። ዛሬም ድረስ የምታገለግል ይመስለኛል። ልብ አድርጉ መይሳው ያለው ህዝቤ ቢሰለጥንልኝ፣ አንድ ቢሆንልኝ እና በሥርዓት ገብሮልኝ ስለ አገሩ ቢያስብልኝ አታሸንፉኝም ነበር። አሁንም ያሸነፋችሁኝ እናንተ የሰለጠነ እና ታዛዥ አጋዥ ህዝብ ስላላችሁ ነው። ብሎ የፈለጉትን እሱን ይዞ የኢትዮጵያ ህዝብ አንገት ማስደፋት ነበርና ህልማቸው እውን እንዳይሆን ሞቶ ጠበቃቸው! ስለክብር መሞትን አሳያቸው! ለዛም ነው እንዲህ ሲሉ አገሬው ያለቀሱላቸው 

መቅደል አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ

የሴቱን አላውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ 

አጤ ቴዎድሮስ ያለ ዘመኑ የተፈጠረ ስልጡን እና ስልጣኔን ወዳድ ቴክኖሎጂ ናፋቂ ነበሩ። አጤ ቴዎድሮስ ቤተመንግስት ላስገንባ፣ ባስገነባሁት ቤት ታፍሬና ተከብሬ ዘና ብየ ልኑር አላሉም። አጤ ቴዎድሮስ የነገሥታት ቤት የነበረውን እና የማረከውን በእርሱ ፋንታ በነገሠበት ቤት ምቾት አገኝቶ መኖርን አልወደደም፤ ይልቁን ኢትዮጵያ አንድ አድርጎ መምራት፣ ኢትዮጵያን ገናና አገር ማድረግ፣ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ማስቻል እና ለሌሎች አገራት ኩራት እንዲትሆን ማስቻልን ነበር ትልቁ ህልማቸው። ህልማቸው በቶሎ እንዲሳካ ቅድሚያ ለቴክኖሎጂ ቦታ ሰጡ! ለዚያም ነው ከእንግሊዞች ጋር አታካራ የገቡት፤ ስለ ክብሩና ስለአገሩም ክብር የተሰውት።

በነገራችን ላይ በአለም ታሪክ የሌለ ትልቅ ሥራና ትምህርትም ከአጤ ቴዎድሮስ መማር እንችላለን። አንዱ መሪ መፍጠር ነው። ይህንን መይሳው እምየ ምንሊክን ቀርፀው አሳድገዋል። ከፍ ሲልም የበኩር ልጃቸውን ድረውላቸዋል። ለዛም ነው የአጤ ቴዎድሮስን ህልም እምየ ምኒልክ ያስፈፀሙት፤ ወደ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ሲያስገቡ የአገሬ ሰው ሰይጣናዊ ሥራ ይላቸው ነበር። እሳቸው ግን አይሰሙም ነበር ምክንያቱም የአሳደጋቸው ጥበብን ያስተማራቸው የመይሳው ካሳን ህልም ያውቁ ስለነበረ ነው። እምየ ምንሊክ ቴክኖሎጅ ብቻ ሳይሆን አገረ መንግስት ግንባታ ላይ በቀጥታ ያስቀጠሉት የመይሳውን ህልምና ጅማሮ ነበር። 

መዩ/መይሳው ካሳ (አጤ ቴዎድሮስ) እንኳንም ተወለዱልን፤ በመወለድዎ አገሬ አትርፋለች!

Filed in: Amharic