>

ፈተናው ይፈተን! (በጌጥዬ ያለው)

ፈተናው ይፈተን! 

በጌጥዬ ያለው


የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እያለን ልዩ ትዝታን ሰጥተውኝ ካለፉ አስተማሪዎቼ መካከል ጋሽ ጓዱ ተስፋ ግንባር ቀደሙ ነው። ጋሼ የጅኦግራፊ አስተማሪያችን ነበር። ደርባባ፣ ቧልት የሌለበት፣ ምክርና ተግሳፅ የሚያዘወትር፣ ተማሪዎቸን የሚያቀርብና ከክፍል ውጭም እንደየ መረዳት ችሎታችን በወሬ ውስጥም ጭምር ሳይንስ የሚያስተምር ባለሙያ ነበር። ታዲያ ዛሬም ድረስ በአዕምሮየ ተቀርፆ ያለው ልፋቱ ብቻ ይደለም፤ ውጤቱም ጭምር እንጂ። የማጠናከሪያ ትምህርት ከመደበኛው ክፍለ ጊዜ ያልተናነሰ እያስተማረ ሁላችንንም የክፍሉን ተማሪዎች ጎበዞች አድርጎን ነበር። ጎበዝ፣ ሰነፍ እና መካከለኛ የሚለውን ድንበር ሁሉ ለማጥፋት ተቃርቦ ነበር። ዛሬ ላይ ሳስበው ምናለበት ጋሼ ከእኛ በፊት የወዲያኞቹ አለቆቹን አስተምሯቸው በነበር እላለሁ። የልጅነት ትዝታየን የቀሰቀሰው ሰሞነኛው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት በነሲብ ማሽቆልቆል ነው። 

በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የተፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ይፋ ተደርጓል። ሆኖም ሁሉም ተማሪዎች ለማለት በሚጠጋ ደረጃ ከግማሽ ያነሰ ውጤት አስመዝግበዋል። እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በኢትዮጵያ አቀፍ ደረጃ ከተፈተኑት 896, 520 ተማሪዎች መካከል ግማሽና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡት 29, 909 ተማሪዎች ብቻ ናቸው። ይህም በመቶኛ ሲሰላ 96.7 ከመቶ ያህሉ ከግማሽ ያነሰ ውጤት አስመዝግበዋል ማለት ነው። 96.7 ለ100 ቅርብ ነውና፤ በሒሳብ የአቅራብ ስሌት መሰረት ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያዳዳ ደረጃ ተማሪዎች አነስተኛ ውጤት አስመዝግበዋል። ይህ እንዴት ሆነ? በተማሪዎች ድክመት ወይስ በአገዛዙ መበሽቀጥ?

በእጅጉ እንግዳ ክስተት ነው። በመሆኑም ፈተናው ከአገዛዙ ንክኪ በፀዳ ሂደት በገለልተኛ አካል በአስቸኳይ መመርመር ይኖርበታል። ከተማሪዎች ይልቅ የትምህርት ስርዓቱ  ድክመት የገዘፈ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው። ምክንያቱም፦ 
1. ክስተቱ በኢትዮጵያ የትምሕርት ታሪክ ውስጥ እንግዳ ነው። 2. ፈተናውም ሆነ ትምህርቱ ኢትዮጵያ በተረጋጋችበት ጊዜ የተሰጠ አይደለም። ትምህርት ቤቶችና አካባቢዎቻቸው የተረበሹበት ጊዜ ነው። 3. ከ70 ሺህ በላይ የአማራ ተማሪዎች አገዛዙን በመቃወም ያለመፈተን አድማ ያደረጉበት ጊዜም ነው። 4. ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ ከፍተኛውን ቁጥር የሚያስመዘግቡት (በተማሪዎች አገላለፅ የሰቃይነት ሚናን የሚጫዎቱት) ጥቂት ተማሪዎች የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ቢሆኑም፤ በአማካኝ ከግማሽ በላይ የሚያስመዘግቡት ግን የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው። በዘንድሮው ውጤት ግን ይህ ልምድ የተገላቢጦሽ ሆኗል። ከተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መካከል 6.8 ከመቶው ከግማሽ በላይ ሲያስመዘግቡ፤ ከማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች መካከል ግን 1.3 ከመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው ከግማሽ በላይ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉት። 

ከላይ በተጠቀሱት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ምክንያቶችም ጭምር በዚህ ውጤት ውስጥ ከተማሪዎች ይልቅ የትምህርት ስርዓቱን የሚመራው አገዛዝ ድክመት ጎልቶ ይታያል። የክፍሉ ተማሪዎች በአመዛኙ ወደ ቀጣዩ የትምህርት ደረጃ ለማለፍ ብቁ ካልሆኑ ወይም ብቃታቸው በተሳሰተ ሚዛን ተለክቶ በስህተት ደካማ ከመሰሉ ማፈር ያለባቸው አስተማሪዎችና ፈታኞች እንጂ ተማሪዎች አይደሉም። 
ይህ ውጤት ተማሪዎች በትክክል የተመዘኑበት ነው ብሎ ለማመን አያስችልም፤ ቅቡልነት ይጎድለዋል። የሞራል ተጠያቂነትም ጭምር አለበት። ለዚህም ነው በገለልተኛ አካል ፈተናው ይፈተን የምለው። 
ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ዩኒቨርሲቲ ገብተው የአንደኛ ዓመት ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ፣ ከጋማሽ በታች ያስመዘገቡት ደግሞ በከፊል ማለትም የተሻለ ውጤት ያላቸው በዩኒቨርሲዎች የመቀበል አቅም ልክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ለአንድ ዓመት ያህል ተምረው በድጋሜ እንዲፈተኑ አገዛዙ ያቀረበው ሃሳብ መፍትሔ ሰጭ አይደለም።  ምክንያቱም፦
ሀ. በትክክል ያልተመዘኑ ተማሪዎችን ጊዜ ያለአግባብ የሚያባክን ነው። 
ለ. የሕፃናት ተማሪዎችን ስነ ልቦና የሚጎዳ ነው። 
ሐ. እነኝህ ተማሪዎች በድጋሜ የሚማሩትም ሆነ የሚፈተኑን በዚያው የትምህርት ስርዓት በመሆኑ ጉዳዩ ከውርንጫ ድካምነት የዘለለ አይሆንም። 
በድምሩ ይህ የመፍትሔ ሃሳብ ሳይሆን ኢ-ፍትሐዊነት የተሞላበት የግጭት ቢጋር ነው ማለት ይቻላል። ለተፈተኑት ብቻ ሳይሆን ያለመፈተን አድማ ላደረጉትም ቢሆን መፍትሔ አይደለም። 

በፈረንጆቹ 2018 የትምህርት ዘመን በጀርመን ተከስቶ የነበረው የተማሪዎች አመፅ ከሰሞኑ የእኛ ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ ነው። በጀርመን አንድ ግዛት ውስጥ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ማለትም ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ከቀረቡ ፈተናዎች መካከል ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ በተለየ አነስተኛ ውጤት አስመዝግበዋል። በዚህም በአስተዳድሩ እና በተማሪዎች መካከል ተነስቶ የነበረው ውዝግብና የተማሪዎች አመፅ የሚታወስ ነው። 
በድምሩ ፈተናው በገለልተኛ አካል ተመርምሮ የተማሪዎችን ስነ ልቦና እና ጥቅም ያስቀደመ፣ ከፖለቲካዊ በቀል የነጣ የመፍትሄ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ያለመፈተን አድማ ያደረጉ የአማራ ተማሪዎችን ጥያቄዎች በጥሞና ማዳመጥና አዎንታዊ ምላሽ መስጠት፤ ብሎም በአስቸኳይ ተፈትነው ወደ ቀጣዩ የትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበትን ዕድል መፍጠር አስገዳጅና ተገቢ ነው። ይህ ካልሆነ ግን አገዛዙ ትምህርት ቤቶችን ወደ አመፅ አደባባይነት፣ ወደ ጦር ቀጣናነት እየለወጣቸው መሆኑን ሊረዳ ይገባል። ተማሪዎች ደብተርና ብዕር እንዲጥሉ በግፋት፤ ኮለሌ ድንጋይ እና ክላሽ እንዲያነሱ መጋበዝ ነው!

Filed in: Amharic