>

"ሳውል፣ ሳውል [መንግሥት ሆይ፥] የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብኻል፤"

“ሳውል፣ ሳውል [መንግሥት ሆይ፥] የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብኻል፤”

የታሪክ አዙሪት . . .!!


በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


በ1571 ዓ.ም ገደማ በልዑል ፋሲለደስ እና በቦረን ኦሮሞ ሠራዊት መካከል ጎጃም ውስጥ በተደረገ ጦርነት ቦረኖች አሸንፈው የንጉሡ ልጅ ሕጻኑ ሱስንዮስ ተማርከው በኦሮሞ ባህል ውስጥ በጉዲፍቻነት በቤተሰባዊ ፍቅርና እንክብካቤ አደጉ።

ዐፄ ሱስንዮስ ሲጎለምሱ ከመጫ እና ቱለማ የተሰባሰበ ጦራቸውን አስከትለው ደብረ ሊባኖስ ገዳም በሄዱ ጊዜ አቀባበል ያደረጉላቸው የገዳሙ መምህር “ሊቀ ደብር” አባ አብርሃም ነበሩ። “መነኮሳቱ አባት ለልጁ ያለውን ፍቅር በመሰለ መውደድ በክብር ተቀበሏቸው፤” ተብሎ ተጽፏል።

በዘመናቸው የተጻፈው ዜና መዋዕል እንደሚነግረን  [ምዕራፍ 22፥25 ላይ ተጽፎ እንደሚነበበው] ዐፄ ሱስንዮስ መልከ መልካም እና ሸርጋዳ የነበሩ ሲሆን ከቦረን ተነስተው በአምቦ እና ጉደር አካባቢ ከሚገኙ የቱለማ የኦሮሞ ጎሳ አባላት በ400 ቄሮዎች ታጅበው በመምጣት ሀገር ለመምራት በቅተው ነበር። (400 ቄሮ ብሎ የጻፈው በዘመኑ የነበረው ፖርቱጋላዊው ተጓዥና ጸሐፌ ትእዛዝ አማኑኤል አልአሜዳ ነው።)

ዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕላቸው እንደሚተርከው ለንግሥና የበቁት በጦራቸው ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በተለይ የሸዋ፣ ጎጃም እና የጉራጌ ሕዝቦችን ጨምሮ 42 ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ጎሳዎች የተባበረ ድጋፍ አድርገውላቸው ስለነበር ነው።

በኋላ ላይ ግን ንጉሥ ሱስንዮስ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለማግኘት ከፖርቱጋሎች ጋር ለነበራቸው ቀረቤታ አድልተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለሁለት ለመክፈል በመነሳታቸው ምክንያት ብዙ አመጽና ግርግር በሀገሪቱ ተነስቶ በተለይ ጎንደር ላይ ከ8000 በላይ ገበሬ “በሀገሬ እና በሃይማኖቴ አትምጡብኝ” ብሎ ሰማዕትነት ተቀብሏል።

ንጉሡ ፍጻሜያቸው እንደ ጅማሬያቸው አላማረላቸውም። የማይነካውን ነካክተው እንኳንስ ተጨማሪ ድጋፍ ሊያገኙ ቀድሞ የነበራቸውን ያንን ሁሉ የሕዝብ ድጋፍ ገደል ከትተው በመጨረሻ ዘመናቸው ሥልጣናቸውን ለልጃቸው  ፋሲለደስ አስረክበው አልፈዋል። [“ፋሲል ይንገሥ፤ ተዋሕዶ ይመለስ!” የሚለውን የዛን ዘመኑን ታሪካዊ ዐዋጅ ያስታውሷል።]

“ታሪክ ራሱን ይደግማል፤” እንዲሉ ይህ ከ400 ዓመታት በፊት በሀገራችን የሆነው አሳዛኝ ታሪክ አሁን በዘመናችን በዘውጌ ብሔርተኞችና በመንግሥት ግልፅ ጣልቃ ገብነት አማካኝነት ጥንታዊቷን፣ ሐዋርያዊቷንና ኩላዊቷን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈልና ለመለያየት በግልጽና በስውር እየተሄደበትን ያለውን ታሪካዊ ስሕተት የሚያስታውሰን የታሪካችን አዙሪት ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የቤተክርስቲያን ላይ እጃቸውን ላነሱ ሁሉ ይህን መለኮታዊና ዘላለማዊ የኾነውን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እናስታውሳቸው ዘንድ እንወዳለን፤

“እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለኹ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።”
(የማቴዎስ ወንጌል ፲፮፤፲፰) 

“ሳውል፣ ሳውል የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብኻል፤”
(የሐዋርያት ሥራ ፱፤፭)

[ማስታወሻ፤ የዐፄ ሱሰንዮስ ዜና መዋዕል አስቀድሞ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን በ1888 በሊዝቦን (ፖርቱጋል) በአማኑኤል አልአሜዳ ወደ  ፖርቱጋልኛ ተተርጉሟል። የመጀመሪያው ቅጂም በዚያው በሊዝበን ቤተመጻሕፍት ይገኛል።]

Filed in: Amharic