ለኢትዮጵያ አየር መንገድ
የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደ ስሙ ዓለም አቀፋዊ ነውን?
ከይኄይስ እውነቱ
በርእሱ የተመለከተውን ትዝብት ለመጻፍ ያነሣሣኝ ከዓለም አቀፍ ጕዞ ወደ አገር ቤት የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን በመዳረሻዎች (ተርሚናሎቹ) የሚጠብቃቸው መስተንግዶ መንገደኞችን እጅግ የሚያሸማቅቅ፣ የሚያዋርድና የንቀት ጥግን የሚያሳይ ከመሆኑም አልፎ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን መንገደኞች ንብረታቸው ኹሉ ሥርዓት የለሽ በሆኑ አስተናጋጆች ከጥቅም ውጭ መሆኑን አስተውለናል፡፡ ይህ ትዝብት የበረራ ሠራተኞችን (አብራሪ ካፒቴኖችንና ረዳቶችን፣ የበረራ አስተናጋጆችን፣ በጠቅላላ የበረራ ቡድኑንና መስተንግዶውን) አይመለከትም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሔራዊ መለያችንና ዓርማችን ከምንላቸው አገራዊ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብሔራዊ ገፅታችን ምልክት፣ ብሔራዊ ወኪላችንና አምባሳደራችን ነው፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ኢትዮጵያን የሚጠሉ ወገኖች ካልሆኑ በቀር ልዩነት የሚኖር አይመስለኝም፡፡
የጐሣ ፖለቲካው ሰለባ ከሆኑ ተቋማት መካከልም አየር መንገዱ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ስለደረሰበት ሁለንተናዊ ችግር ብዙ ተብሏል፡፡ ወደዚህ መግባት የዚህ መልእክት ዓላማም አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ የጐሣ ሥርዓቱ ዓይነተኛ አሻራ በተለይ በመስተንግዶው ረገድ ጎልቶ የሚታይና ከፍ ብለን የጠቀስናቸውን ዘመናት ያስቆጠሩ እሤቶች የሚሸረሽር ብቻ ሳይሆን ለዘመናት የተገነባውን የአየር መንገዱን መልካም ስምና ዝና በእጅጉ የሚያጎድፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ጥያቄው በየተርሚናሎቹ በመስተንግዶ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች የጐሣ ተዋጽኦ ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ እስከሆነች/እስከሆነ ድረስ ከየትኛውም ጐሣ ትምጣ/ይምጣ ለሙያው/ሥራው ብቃት ካላት/ካለው የሚለው መሠረታዊ መመዘኛ የመሟላቱ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በወያኔ ሕወሓት ዘመን እንደታየው በቂ ሥልጠና ሳይሰጡ፣ የአእምሮ ውቅራቸውን ሳያስተካክሉ የኔ ወገን/ጐሣ ነው በሚል መሥፈርት ብቻ በተረኝነት ስሜት የሚደረገው ቅጥር አየር መንገዱን በእጅጉ ያስከፍለዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
1ኛ/ ዓለም አቀፍ መንገደኞች ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መዳረሻ ሲደርሱ፣ ቀጣይ ጉዞ ካላቸው መንገደኞች በስተቀር ኢትዮጵያውያን መንገደኞችም (locals) ሆኑ መዳረሻቸው ኢትዮጵያ የሆነ ሌሎች መንገደኞች የውስጥ ሥነ ሥርዓቱን አጠናቅቀውና ጓዛቸውን ይዘው ለመውጣት ከ2 እስከ 3 ሰዓት የሚጠብቁበት ምክንያት የመስተንግዶ ችግር እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ያውም ተጨማሪ አዲስ ተርሚናል ተሠርቶ፡፡ በቅድሚያ የአገር ውስጡን መንገደኛ ለይቶ ተራ ማስያዝና ማስተናገድ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ጉዞአቸውን ለማጠናቀቅና መዳረሻቸው ለመድረስ ሌላ አየር መንገዶችን የሚጠቀሙ መንገደኞችን (transit passengers) ደግሞ ለይቶ ማስተናገድ ይቻላል፡፡ ይሄ እየተቻለ ቤተሰብ ይዘው፣ ጓዝ ይዘው፣ በድካም በምሽት ገብተው 2/3 ሰዓት መሰለፍ በየትኛውም መመዘኛ ሲታይ ተቀባይነት የለውም፡፡ ይሄ ከአንድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የማይጠበቅና ደረጃው በእጅጉ የወረደ አገልግሎት (sub-standard service) ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሥር የሰደደ የአመለካከት (mindset) ችግር ካልሆነ በቀር በተርሚናሎቹ ውስጥ ያሉት የ‹አጥሮች› ብዛት ከሠራተኞቹ ድክመት ላይ ሌላ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ይሄ የቊጥጥርና ሰው ኹሉ አጥፊ ነው የሚል፣ ይህንንም ተከትሎ የማጠር፣ የመዝጋትና የመከልከል አመለካከት በብዙ ተቋማት፣ በልዩ ልዩ መሠረተ ልማቶች አካባቢ በእጅጉ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ የባቡር ሐዲድ በተዘረጋባቸው መስመሮች ለተጓዦች ተብሎ የተዘጋጁ መግቢያና መውጫ በሮች አሉ፡፡ ሁሉም በገመድ/በሽቦ ታጥረዋል፡፡ የማያስፈልጉ ከሆነ ለምን ተሠሩ? የከተማውን ውበት ምን ያህል እንዳበላሹ ያስተዋለ አለ?
2ኛ/ በመስተንግዶ ላይ የተሰማሩት አብዛኛው ሠራተኞች (ፆታ ሳይለይ) እንደ ወረደ ከገጠር የመጡ ይመስላሉ፡፡ ይህም በዐደባባይ/ሰው ፊት የሚያቀርብ ውጫዊ ሰብእና (presentable personality) አይታይባቸውም፡፡ አየር መንገዱ ደግሞ ይሄንን ይፈልጋል፡፡ በዋናነት ደግሞ በቂ ሥልጠና ሳይሰጣቸው የተሰማሩ ወይም ቢሰጣቸውም ዘልቋቸው ያልገባ ስለሚመስሉ ከፍተኛ የብቃት ችግር ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት መስተንግዷቸው እጅግ የተንቀራፈፈ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከመንገደኛው ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ ግንኙነት በፍጹም ያልተረዱ፣ ንግግራቸው ያልታረም፣ የሚያመናጭቁና ወደ ብልግና ያዘነበለ ጠባይ (rude behavior) የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱ እንዲሉ ፊታቸው ላይ የጥላቻና ኩርፍያ ገፅታ እንጂ ባንዳቸውም ፈገግታ አታይባቸውም፡፡ ትህትናና ቅንነት የሚባሉት ሠናይ ጠባያት መኖራቸውን እስከነ አካቴው የሚያወቁ አይመስሉም፡፡ መንገደኛውን ኹሉ በጠላትነት የሚመለከቱ ይመስላሉ፡፡
3ኛ/ በነገራችን ላይ የከፋው መስተንግዶ (ማመናጨቁ፣ ስድብ ቀረሽ ንግግሩ) የሚጀምረው ሀ/ ወደ ውጭ ጉዞ ለመሄድ መንገደኞች ከመኪና ወርደውና ጓዛቸውን ይዘው ከሸኚዎቻቸው ጋር ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከድርጅቱ የጥበቃ ሠራተኞች የሚጠብቃቸው ማመናጨቅ የት ነው የመጣሁት የሚያሰኝ ነው፡፡ አዛውንት የለ፣ ጎልማሳ የለ፣ ወጣት የለ ሕፃናት ሲያጉላሉ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ አልፎ ተርፎም አንዳንድ መንገደኞችንና ሸኚዎችን ሲገፈትሩ ይስተዋላል፡፡ ሸኚ የት ድረስ መግባት እንደሚፈቀድለት ግልጽ ምልክት/ጽሑፍ ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ እነዚህ ሥርዓት አልባ ጥበቃዎች መረጃ ሲጠየቁ ለማናገርም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ መሣሪያ ስለያዙ የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ እንደሚችሉ የሚያምኑ ጥበቃዎች አየር መንገዱ ውስጥ ምን ይሠራሉ? ለ/ መንገደኛው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ከአውሮፕላን ከወረደ በኋለ ወደ ተርሚናሎች ለመሄድ የአየር መንገዱን አውቶቡሶች ከሚይዝበት ጊዜ ጀምሮ የሚጠብቀውም መስተንግዶ ከጥበቃ ሠራተኞች ጋጠ ወጥ ጠባይ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነት ‹ሠራተኞች› አየር ማረፊያው ውስጥ ምን ይሠራሉ? እባካችሁ ለሁላችን ያለን አንድ አገር ነው፡፡ አየር መንገዳችን መልካም ስሙን ጠብቆ መዝለቁ ጥቅሙ የጋራ ነው፡፡ ከብቃት ውጭ ለመጠቃቀም የሚደረገው ቅጥር በየትኛውም የሥራ መስክ ተገቢ ባይሆንም ቢያንስ ዓለም አቀፍ ጠባይ ያለው ድርጅት ጋር ጥንቃቄ ብታደርጉ መልካም ይመስለኛል፡፡ በጥቂቱ ማስተዋል ካለ እነዚህን ልጆች የምታሰማሩ ኃላፊዎች ከዚህ ቀደም ልምዱ ካላቸውና በመልካም መስተንግዶ ከሚታወቁ የቆዩ ሠራተኞች ጋር በማዳበል አገልግሎቱን እንዲረዱ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ መቼም መንገደኛውን አጉላሉ፣ አገጣብራችሁና ከፍ-ዝቅ አድርጋችሁ እዩ የሚል ኃላፊ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡
3ኛ/ ዓለም አቀፍ መንገደኞች መዳረሻቸው ሲገቡ ጓዛቸውን ማስፈተሽ እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ አልፎ አልፎ ሕገ ወጥ ዕቃዎችን የሚይዙ መንገደኞች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚስተናገድበት ሕጋዊ አግባብና ሥርዓት አለ፡፡ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. (Feb.6,2023) ከዱባይ አ.አ. በምሽት የገባው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መንገደኞች መካከል አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ጓዙን ሲያስፈትሽ ላፕ ቶፑ ውስጥ የሚታይ ‹ባዕድ› ነገር አለ በማለት ሥርዓት ከሌላቸው አስተናጋጆች መካከል አንዷ፣ ግለሰቡን (በዕድሜ ትልቅ ሰው ነው) እያመናጨቀች ላፕ ቶፑን ትወስዳለች፡፡ ጉዳዩን እየታዘበ ያለው መንገደኛ ባለሙያ ጠርታ ላፕ ቶፑ እንዲከፈት ታደርጋለች ብሎ ሲጠብቅ ላፕ ቶፑን ከላይና ከታች ፈልቅቃ በመክፈት ከጥቅም ውጭ አድርገዋለች፡፡ በጥርጣሬ አየሁ ያለችው ‹ባዕድ› ነገር ወይም ‹ዕፅ› የለም፡፡ የተገኘ ሕገ ወጥ ነገር የለም፡፡ የሚገርመው ግለሰቡ (በፍራቻም ይሁን በሌላ ምክንያት) የተሰበረበትን ላፕ ቶፕ ተቀብሎ ምንም ሳይናገር ወጥቷል፡፡ ሌላውም መንገደኛ የግለሰቡን ሁናቴ ተመልክቶ ጣልቃ ከመግባት ተቆጥቧል፡፡ በዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት ማነው ኃላፊነት መውሰድ ያለበት? ጋጠ ወጧ ሠራተኛ? አየር መንገዱ? በነገራችን ላይ ይህንን መረጃ ያገኘሁት በዚሁ በረራ ውስጥ ከነበረች የቅርብ ቤተሰቤ ነው፡፡ ወዴት እያመራን ነው?
ባጠቃላይ ላገር ስምና ብሔራዊ ጥቅም ሲባል እንጂ ይህ በአየር መንገዱ ሠራተኞች (ከጥበቃ እስከ አስተናጋጆች) የሚታየው ሕገ ወጥ አሠራር ባስቸኳይ የማይታረም ከሆነ ለሚመለከተው ዓለም አቀፍ አካል ለማስታወቅ የምንገደድ መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡