>

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ፓትርያርክ የአቢይ ጾምን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እነሆ፦

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤ 

• በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም ኢትዮጵውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ! 

እንደ ስሑትና ደካማ ሰብአዊ ባሕርያችን ሳይሆን እንደ አባታዊ ቸርነቱ ሁል ጊዜ በምሕረቱ የሚጐበኘን አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለጾመ ኢየሱስ አደረሰን፤ አደረሳችሁ! 

• “ንጹም ጾመ፣ ወናፍቅር ቢጸነ፣ እስመ ከማሁ አዘዘነ፡- ጾምን እንጹም፣ ባልንጀራችንንም እንውደድ፣ እንዲህ አዞናልና” (ቅዱስ ያሬድ)  

እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ስንኖር፣ እንድናደርገው ያዘዘን ዓቢይ ነገር ቢኖር ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ እየመገበ የሚገኘው በፍቅር ነው፡፡ እኛንም ከፍዳ ኃጢአት ያዳነን በፍቅር ነው፡፡ ሕይወታችንና ንብረታችን ተጠብቆ የሚኖረው ፍቅር ሲኖር ነው፡፡  

ግላዊና ማኅበራዊ ኑሮአችን እንዲሁም ሃይማኖታዊ አምልኮአችንና የተግባር እንቅስቃሴአችን በሙሉ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ፍቅር ሲኖር ነው፡፡  

በፍቅር ውስጥ በረከት እንጂ ጉድለት የለም፤ በፍቅር ውስጥ ጤና እንጂ በሽታ የለም፤ በፍቅር ውስጥ ጽድቅ እንጂ ኃጢአት የለም፤ በፍቅር ውስጥ እግዚአብሔር እንጂ ዲያብሎስ የለም፡፡ ይህም በመሆኑ ቅዱስ መጸሐፍ ፍቅርን ‹‹የሁሉም ነገር ማሰሪያ ነች›› በማለት ይገልጻታል፡፡  

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሁሉም የምትበልጠው ታላቋ ትእዛዝ ‹‹ፍቅር›› እንደሆነች ከመግለፁም በላይ ኦሪትና ነቢያት ሁሉ በእሷ እንደሚጠቃለሉ አስተምሮናል፡፡ 

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት! 

ፍቅርን እንደ ዓይን ብሌን ስንጠብቃት በእጅጉ የምትጠቅመንን ያህል ጣል ጣል ስናደርጋት ደግሞ በእጅጉ ትጎዳናለች፡፡ በፍቅር እጦት የሚደርሰው ጉዳት በተወሰነ ነገር ብቻ ሳይሆን በነፍስም ሆነ በሥጋ፣ በምድርም ሆነ በሰማይ እጅግ በጣም የገዘፈና የሰፋ ነው፡፡  

በሀገራችን የሆነውና እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ ፍቅርን ባጣንባቸው ዓመታት ከየት ወዴት እንደደረስን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚገነዘበው ነው፡፡ ያተረፍነው ነገርም ምን እንደሆነ የምናውቀው ነው፡፡  

ይሁንና የፍቅር እጦት ምን ያህል እንደጎዳን ራሳችን ተገንዝበን ወደ ሰላሙ መንገድ መመለሳችን የተሻለ አማራጭ መሆኑን ሳንመሰክር አናልፍም፡፡ የተጀመረው የፍቅርና የሰላም ጉዞም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ልባዊ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው፡፡ 

ይህንን ሰላም እንዲመጣ ያደረጉ ወገኖችም ሁላቸውን ሳናመሰግን አናልፍም፡፡ ምክንያቱም በሰዎች መካከል ፍቅርንና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ ብሎ ጌታ እንደ አስተማረን ብፅዕና ይገባቸዋልና ነው፡፡  

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት! 

የፍጹም ፍቅር መገኛ የሆነው ቅዱስ ወንጌል የሚያስተምረው ፍቅር፣ ራስን ማፍቀር ወይም መውደድ ሳይሆን ራስን መጥላት ባልንጀራን ግን መውደድ ነው፡፡ ወንጌላዊ-ፍቅር ፍጹም ነው የሚያሰኘውም ቅሉ ይህ ነው፡፡  

ለሁለት ሺሕ ዘመናት ያህል በቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ ላይ የተገነባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ባህልም ይህን ፍቅር ጠብቆ የሚጓዝ ነው፡፡  

ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ አበው መነኮሳት ከነበራቸው ፍቅርና ትሕትና የተነሣ፣ የሹመት ሽሚያ አያውቁም ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ትልቁን ሥልጣን ይቅርና የአንድ ገዳም መሪ ለመሆንም በእግር ብረት ታስረው በግድ ካልሆነ በቀር እሺ ብለው በፈቃደኝነት ሹመትን አይቀበሉም ነበር፡፡ 

ራሱን በራሱ መሾም ወይም እኔን ሹሙኝ ብሎ መናገርና የሌላን ድጋፍ መጠየቅ ለኢትዮጵያውያን መነኮሳት ጭራሽ ነውርና ጸያፍም ነበር፡፡  

ያም በመሆኑ ነው ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ለሦስት ሺሕ ዘመናት የዘለቀው ሃይማኖታችን ምንም ዓይነት መለያየት ሳያጋጥመው አንድ ሆኖ ሊዘልቅ የቻለው፡፡ 

ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ጠንካራ አንድነት ለሕዝቡም በመትረፉ የሀገሪቱን አንድነትና ነጻነት አስጠብቆ እስከ ዘመናችን ሊደርስ ችሎአል፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን የሕዝብንና የሀገርን አንድነትና ነጻነት ለማስጠበቅ ያደረገችውና የምታደርገው ጥረት ሊያስመሰግናት እንጂ ሊያስወቅሳት አይገባም፡፡  

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት! 

ከቅርብ ቀናት ወዲህ በቤተ ክርስቲያናችን ተከሥስቶ የነበረውን ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት የቤተ ክርስቲያናችንን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ባሕላዊ መርሕን የናደ፣ እንደዚሁም በኢትዮጵያ ይቅርና በዓለም ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ድርጊት እንደሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ስትገልጽ ቆይታለች፡፡ 

ይህንን የቤተ ክርስቲያን ድምፅ በመስማትና በመቀበል ሕዝበ ክርስቲያንና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር ባቀረቡት ኃዘንና ጸሎት እንደዚሁም ባደረጉት መጠነ ሰፊና ዙርያ መለስ የሆነ የድጋፍ ርብርብ ስሕተቱ ሊታረም ችሏል፡፡  

ለተገኘው መንፈሳዊ ውጤትም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትርና መንግሥታቸውን፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲከበር ከፍተኛ መሥዋዕትነት ለከፈለው መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲሁም ይህ ስሕተት እንዲታረም ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን ተሰልፈው ድምፃቸውን ላሰሙ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርብላቸዋለን፡፡ 

በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ግልፅ ማድረግ የምንፈልገው ከቤተ ክርስቲያናችን ዶግማ፣ ቀኖና እና ሥርዓት መከበር እንደዚሁም ከሉዓላዊ አንድነቷ መጠበቅ በመለስ ያለው ጥያቄ ለማስናገድ ቤተ ክርስቲያናችን ዝግጁ መሆኗን ነው፡፡  

ቤተ ክርስቲያናችን ሕዝቦች በቋንቋቸው የመማር፣ የማስተማርና የማምለክ እንዲሁም የመተዳደር መብትን ካሁን በፊትም፣ አሁንም፣ ካሁን በኋላም የምትነፍግበት መሠረት እንደሌለም ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡  

ይህም በመሆኑ በቋንቋ የመጠቀም መብት በሕገ ቤተ ክርስቲያናችን ምዕራፍ 2 አንቀጽ 5 ከቁጥር 1-3 ባለው አንቀጽ በሚገባ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በቋንቋ የመጠቀም ጥያቄ በሕግ ደረጃ ተመልሶ በተግባር እየተሰራበት የሚገኝ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡  

የተወዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤ 

ዛሬ ታላቁን ጾማችን በፍቅር ሆነን የምንጾምበት ወቅት ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ጾም ማለት ስጋዊ ፈቃድን በመግታት ከእግዚአብሔር ጋር ጥብቅ ግንኙነት ለማድረግ የሚካሄድ መንፈሳዊ ተጋድሎ ነው፡፡  

በጌታችን ጾም በተግባር እንዳየነው ጾም ማለት ዲያብሎስ የሚሸነፍበት በአንጻሩ ደግሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ አሸናፊዎች የሚሆኑበት ኃይል ነው፡፡  

ስለሆነም ጾም የተጋድሎና የሙዓት ሜዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የምንታገለውም ልቡሰ ሥጋ ሰውን ሳይሆን ረቂቅ ፍጡር የሆነው ሰይጣን በሰው አድሮ የሚነዛውን አጥፊ ሐሳቡንና ድርጊቱን ነው፡፡  

ከዚህም ጋር ሰውነታችን ለዚህ ክፉ መንፈስ ታዛዥ እንዲሆን የሚገፋፉ ጥሉላት መባልዕትን መተው፤ ኃይለ ሥጋን መቈጣጠር፤ ኃይለ መንፈስን ደግሞ ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ በጾም ወቅት የተራቡትን ማጉረስ የታረዙትን ማልበስ የተበደሉትን መካስ፣ ፍትሕና ርትዕ በማኅበረ ሰብ ውስጥ ማንገሥ ያስፈልጋል፡፡

በጾም ወቅት ኅሊናችን ማሰላሰል ያለበት ሰው ምን አለ? ወይም ምን አደረገ? በሚለው ሳይሆን እግዚአብሔር በፊቱ ምን ዓይነት ሰው እንድንሆንለት ይፈልጋል? በሚለው ላይ ነው፡፡ 

ስለዚህ ጾማችን በዚህ መንፈስ የተቃኘ ፍቅረ፣ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ማእከል ያደረገ፣ መጠራጠርንና አለመተመማንን ያስቀረ፣ የተለያዩትን ያቀራረበ፣ የተሳሳቱትን ያረመ በአንጻሩ ደግሞ ሁላችንን በሰላምና በፍቅር አንድ አድርጎ ያስተሳሰረ ይሆን ዘንድ በዚህ መንፈስ ተነቃቅተን እንድንጾመው አባታዊ ጥሪያችንን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናስተላልፋለን፡፡  

በመጨረሻም፤ 

በሀገራችን እየታየ ያለው የሰላም ጭላንጭልና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ዝንባሌ በእጅጉ ጠቃሚና ለሁለንተና ልማታችንና ለዕድገታችን እንደዚሁም ለተሟላ አንድነታችን ጠቃሚነቱ የጎላ ስለሆነ እግዚአብሔር ለዘለቄታው እንዲያሳካልን ከልብ እንድናዝንና ወደ አምላካችን በተመሥጦ እንድንጸልይ በአጽንዖት በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡  

መልካም የጾም ወራት ያድርግልን! 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!! 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን 

አባ ማትያስ ቀዳማዊ 

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስምወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 

የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. 

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ


Filed in: Amharic