>

መንግሥትም ሆነ እኛ ከልብ ልንጸጸትበት እና ይቅርታ ልንጠይቅበት የሚገባን የ2ቱ ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት!!

መንግሥትም ሆነ እኛ ከልብ ልንጸጸትበት እና ይቅርታ ልንጠይቅበት የሚገባን የ2ቱ ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

‘‘እኔ ግን የእነዛን ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኩ ብዬ ደስ አይለኝም…’’
(ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከዐድዋ ድል በኋላ ለአውሮፓውያን መንግሥታት ከጻፉት ደብዳቤ የተቀነጨበ)

1. እንደ መንደርደሪያ

ባለፉት ሁለት ዓመታት ‘በፌዴራል መንግሥቱ’ እና ‘በሕወሓት’ በኩል የተደረገውን መቶ ሺሕዎች ያለቁበትን የእርስ በርስ ጦርነት ለመዘገብ ግንባር ላይ የሰነበተ፤ በአንድ የግል መገናኛ ብዙኃን ላይ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ ጋዜጠኛ ወዳጄ- የጦርነቱ ክፉ ዳፋ መልሶ መላልሶ የጎበኛቸው ወለዬዎች ስለነዛ ‘ክፉ ቀናት!’ እንዲህ መቀኘታቸውን አጫወተኝ፤

‘‘አንተ ቃሉ መጀን

ኧረ ጦሳ መጀን

ኧረ አዝዋ መጀን

ኧረ ወሎ መጀን

… እኮ ምን ይዋጠን

እውነት ምን ይበጀን…!?

ሲተኮስ ተወልደን ሲተኮስ አረጀን!

በንጉሥ ተፋጀን!

በአብዮት ተፋጀን!

ለኢያሱ ተዋግተን!

ለተፈሪ ሞተን!

በሕወሓት ጃጀን!

እውነት ምን ይበጀን…!?

ኧረ ጢጣ መጀን

ቧንቧ ውኃ መጀን

ሆጤ ሜዳ መጀን…

… ይኼው ጫት ታቅፈን

ፍቅርን ብለን አርፈን

ከኒህ ነጃሳዎች…!

የአህመድ ዓሊ ልጅ

ለውጥ ብሎ አፋጀን!!’’

2. ጸጸት እና ኀዘኔታ የሌለን ስለ ለምን ሆንን…?!

‘‘እኔ ግን የእነዛን ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኩ ብዬ ደስ አይለኝም…’’

(ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከዐድዋ ጦርነት በኋላ ለአውሮፓውያን መንግሥታት ከጻፉት ደብዳቤ የተቀነጨበ)

ባሳለፍነው ሳምንት ዕለተ-ሰንበትን በተለያዩ ምክንያቶች በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚኖሩ የውጪ ሀገር ሰዎች ጋር አንድ የትውውቅ ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ ነበርኩ እናም በዚህ ዝግጅት ላይ ከአንድ ጎልማሳ ጋር የትውውቅ ወግ ጀመርን፡፡ በመዲናችን አዲስ አበባ በግል ቢዝነስ ላይ የተሰማራ ይህ ጎልማሳ ስሙንና ከሀገረ ቱርክ የመጣ መሆኑን ነግሮኝ ከተዋወቅን በኋላ አንገቱን ዝቅ አድርጎ – ጸጸትና ኀዘኔታ በተሞላበት ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆኖ እንዲህ አለኝ፤

‘‘ሀገሬ ቱርክ በሀገራችሁ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት የድሮን ሽያጭ በማድረጓና ስለተፈጠረው ሞት፣ እልቂትና መፈናቀል… ከልብ ማዘኔን ልገልጽልህ እወዳለኹ፤’’ ብሎኝ ከጥቂት የዝምታ አፍታ በኋላ ወደ ሌላ የጨዋታችን ርእስ ተሸጋገረ፡፡

የዚህ ቱርካዊ የጸጸትና የይቅርታ መንፈስ የተላበሰ ንግግሩ በመብረቅ የተመታሁ ያህል ነበር ያስደነገጠኝ፡፡ እናም ራሴን እንዲህ ለመጠይቅ ተገደድኩ፤ ለሺሕ ዘመናት የዘለቀ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባህልና ሥልጣኔ ያለን ሕዝቦች ነን የምንል እኛ እንደምን በዚህ ልክ ከሰብአዊነት ልእልና፣ ከሞራል ሕግ፣ ከሃይማኖት የይቅርታ አስተምሮ ልንጎድል ቻልን… ለመሆኑ መንግሥትም ሆነ እኛስ እንደ ሕዝብ እስከ መቼ ይሆን ለጸጸትና ለይቅርታ የጨከነ እኩይ ማንነትን ይዘን የምንዘልቀው… የሚል ጥያቄ አእምሮዬን ሰቅዞ ያዘው፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት ባደርግነው የእርስ በርስ ጦርነት በታሪካችን ከውጪ ወራሪ ኃይሎችም ሆነ እርስ በርሳችን ባደርግናቸው ጦርነቶች ከደረሰው እልቂት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደት… ወዘተ አንጻር አቻና ተወዳዳሪ ያለው አይደለም፡፡

ከሃይማኖት አባት እስከ ሀገር ሽማግሌ፣ ከአፈ ነቢብ እስከ ምሁራን፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በሆንበት በዚህ የእርስ በርስ ዘግናኝ ጦርነት የደረሰው እልቂት (ገና ባይረጋግጥም በዚህ ጦርነት አንድ ሚሊዮን የሚያህል ሕዝብ ለሞት መዳረጉ ይነገራል)፣ መፈናቀል፣ የመሠረተ ልማት ውድመት… በአጠቃላይ ሰብአዊና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊውና ፖለቲካዊ ቀውሱ ከምንገምተው በላይ ነው፡፡

ያለፉት ሁለት ዓመታት የዐመፅና የጦርነት ጐዳናዎች ብዙ ስብራት አምጥተውብናል፡፡ ጦርነቱ ይቍም እንጂ፣ ጦሱ ቀላል አይደለም፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቈጠሩትን ሕይወት አሳጥቷል፤ በርካቶችን አካለ ስንኵላን አድርጓል፡፡ ከ4.1 ሚሊዮን በላይ ዜጐችን አፈናቅሏል፤ ከእጥፍ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለከፍተኛ ምግብ ዕጠረት አጋልጧል፡፡ ልጆችን ያለወላጅ፣ ወላጆችን ያለ ልጅ አስቀርቷል፤ ሚስቶችን መበለት አድርጓል፤ ሕፃናትን ሳይቀር ማግዷል፡፡ አገራችን አረጋውያኗ ከመጽናናት በላይ ልባቸው የተሰበረባት ምድር ሆናለች፡፡

በዚህ ጦርነት ውስጥ፣ ልጆቻችን፣ እኅቶቻችንና እናቶቻችን ዘግናኝ በሆነ መልኩ ተደፍረዋል። የአካል ጉዳታቸውና የሥነ-ልቡና ስብራታቸው ከቃል በላይ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገራችን ስም ጠልሽቷል። ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሣ ጥላቻ ተዘራቷል፡፡ የምዕራቡ ዓለምም ፊቱን አዙሮብን ከርሟል፡፡ በርካታ የጤና፣ የትምህርትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፈርሰዋል። አኮኖሚያችንን አድቅቋል፣ ዕዳችንንና ኑሯችንን አክብዷል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሁሉ ረገድ አክስሮናል፤ አጠቃላይ በሀገሪቱ በጦርነቱ የደረሰው ውድመት 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ወይም 28 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ይገመታል፡፡ ለመልሶ ግንባታ ብቻ ከ 20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልገናል። ከሁሉም በላይ፣ ሊፈታ ከሚችል ግጭት ውስጥ የተወለደ የወንድማማቾች ጦርነት እንደመሆኑ መጠን፣ በታሪካችን ትልቅ ጥቍር ጠባሳ ትቶ አልፏል፣ ገናም እያለፈ ያለ ነው፡፡

3. ይህንኑ የጦርነቱን ዳፋ የሚገልጽ አንድ ሌላ የግል ገጠመኜን ለአብነት ልጨምር፤

በምሠራበት መስሪያ ቤት በጥበቃ ሥራ ተቀጥሮ የሚሠራ አንድ ኢትዮጵያዊ የቀድሞ ወታደር ነበር፡፡ ይህ የመስሪያ ቤታችን ባልደረባ ከሁለት ዓመት በፊት መንግሥት ያወጀውን “የህልውና ዘመቻ ጥሪን!” ተቀብሎ ወደ ሰሜን ግንባር ዘመቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ወራት በፊት ይህ ኢትዮጵያዊ ወገናችን በሰሜን ግንባር እስከ ወዲያኛው መቅረቱን የሚያስረግጥ የሞቱ መርዶ ለሚስቱና ለሰባት ዓመት ልጁ ተነገረ።

ገና በሠላሳዎቹ መጀመሪያ የምትገኘው ሚስቱ እርሟን/ኀዘኗን ከጎረቤት፣ ከዘመድ ወዳጆች ጋር ካወጣች በኋላ- መቼም ሕይወት ይቀጥላልና ያለ አባት የቀረውን ልጇን ለማሳደግ ስትል ከመርግ ከከበደው የሀገራችን ኑሮ ጋር ትግሏን ቀጠለች። ቀድሞ በባለቤቷ ገቢ ትተዳደር የነበረችው ይህች ሴት አሁን ብቻዋን ኑሮን መጋፈጡ አልሆንላት አለ። እናም የዚህችን ሴት ችግር የተመለከተው መስሪያ ቤታችን ቀድሞ ባለቤቷ በጥበቃ ሥራ ሲሠራ ይከፈለው የነበረውን የወር ደመወዝ ታሳቢ ሆኖ እየተከፈላት በፅዳት ሠራተኝነት ቀጠራት።

ታዲያ ባለፈው ሰሞን ትምህርት ቤት ዝግ በመሆኑ ይህች ከላይ እስከ ታች ጥቁር ከል የለበሰች ሴት ለሥራ ወደ መስሪያ ቤታችን ስትመጣ ልጇን ቤት ብቻውን መተው ባለመቻሏ ወደ ሥራ ቦታ ይዛው መምጣት ትጀምራለች፡፡ ታዲያ ይህ ልጅ መቼም ልጅ ነውና የቢሮችን ሕንጻ አካባቢ መሯሯጥና መጫወት በማዘወተሩ ከአንዳንድ ሰዎች ቅሬታ መቅረብ ጀመረ። ታዲያ ይህን ጉዳይ ምን መፍትሔ መስጠት ይቻል ይሆን? በሚል ያነጋገርናት የልጁ እናት በእንባና በሰቀቀን ሆና እንዲህ አለችን፤

‘‘… ልጄን ምን ላድርገው…?! ቤት ጥዬው እንዳልመጣ ቤቱ ውስጥ ሰው የለ… ምን ትመክሩኛላችሁ፤ አይ ዕድሌ፣ እስቲ ፍረዱኝ አለ አባት የቀረውን ልጄን ምን ላድርገው…?!’’ ብላ አንገቷን ደፍታ መንሰቅሰቅ ጀመረች፡፡

‘‘አለ አባት የቀረውን ልጄን ምን ላድርገው…?!’’ ይህ ልብን በኀዘን የሚሰብር ምሬትና ሰቆቃ በዚህ ጦርነት ወላጆቻቸውን ያጡ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ዕጣ ፈንታ ነው…!! ይሄ መራርና አሳዛኝ እውነታ በዚህ ጦርነት ባላቸውን፣ አባታቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ እኅቶቻቸውን ያጡ  የብዙዎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከመርግ የከበደ መከራቸውና ሰቀቀናቸው ማሳያ ነው።

ወደ ቀደመ ሐሳቤ ስመለስም፤ ይህን ዓለምን በአግራሞትና በድንጋጤ እጁን በአፉ ላይ እንዲጭን ያደረገው የእርስ በርስ ጦርነት- በአፍሪካ ኅብረት፣ በአሜሪካና በሌሎች የውጪ ሀገራት ግፊትና ጫና- በንግግርና በሰላማዊ ድርድር ይቋጭ ዘንድ ከተደረገ በኋላ በሁለቱም ወገን የጸጸትና የኀዘንና ስሜት ሳይሆን ያየነው የተገላቢጦሽ “ድሉ የእኛ ነው!!” ወደሚል ፉክክርና ብሽሽቅ እንዲሁም የድል የአበባ ጉንጉን ወደ መሸላለም ነበር የተገባው። በዚህ ጦርነት ስለደረሰው ከፍተኛ የሆነ እልቂት፣ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መጸጸቱንና ኀዘኑን የገለጸ አንድም የመንግሥት ባለ ሥልጣን አላየሁም፤ አልሰማሁም።

እንደው የሆነስ ሆነና እንዴት ነው ወደዚህ ዓይነቱ የሞራል ውድቀት/ልሽቀትና ደንታ ቢስነት የተሸጋገርነው። ለገዛ ሀገራችን፣ ለገዛ ሕዝባችን በመግቢያዬ ላይ ያነሳኹትን የባዕዱን ቱርካዊ ያህል ጸጸትና ርኅራኄን ስለምን አጣን…?! ይህን ከመንግሥት እስከ የሃይማኖት ተቋሞቻችን እንዲሁም እያንዳንዳችን ቆም ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን የጊዜው ጥያቄ ነው።

4. ለመውጫ ያህልም፤

ታሪካችንን ስንፈትሽ- ከዐድዋው ጦርነት ድል በኋላ ዐፄ ምኒልክ ለአውሮፓ መንግሥታት በጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ነበር ያሏቸው፤

‘‘… ጦርነት ይቅር ብላቸው እምቢ ብለው በጥጋባቸው ዐድዋ ላይ ድል ሆኑ፤ እኔ ግን የእነዛ ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ መፈሰሱን እያየሁ ድል አደረግኩ ብዬ ደስ አይለኝም…፤’’ በማለት የኢትዮጵዊነትን የሞራል የበላይነትንና ሰው የመሆን ከፍ ያለ የመንፈስ ልእልናቸውን ለተቀረው ዓለም አሳይተውበታል፡፡

ታዲያ እንዴት ነው ከመቶ ዓመታት በኋላ ለባዕድ እንኳን ባይተርፍ እንዴት እርስ በርሳችን ለተገዳደልንበት፣ ምድሪቱን፣ ኢትዮጵያን አኬልዳማ/የደም-ምድር ላደረግንበት፣ የብዙዎችን ሕይወትና ኑሮ ክፉኛ ላመሳሰቃቀልንበት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን ወላጅ አልባና ተስፋ አልቦ ላደርግንበት ጦርነት/ዘግናኝ እልቂት ጥቂት እንኳን እንጥፍጣፊ መጸጸት፣ ኀዘንና ሃፍረትን እንደምንና ስለምን አጣን!?

እናም … በርግጥም ላለፉት ሁለት ዓመታት ያደረግነው የእርስ በርስ ጦርነት፤ የኢትዮጵያ አንድነት መሠረትና ዋልታ የኾኑ ሕዝቦችን ደም ያቃባ፣ ኢትዮጵያን ወደኋላ የመለስና በብዙ የከሰርንበት- መንግሥትም ሆነ እኛም እንደ ኢትዮጵያዊ ልናፍርበት፣ ከልብ ልንጸጸትበት እና ይቅርታ ልንጠይቅበት/ልንጠያየቅበት የሚገባን ጦርነት ነው!!

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

Filed in: Amharic