>

ሙዚቀኛው ተዘራ ኃ/ሚካኤል "የዜማው ውቂያኖስ" (ደረጀ መላኩ)

ሙዚቀኛው ተዘራ ኃ/ሚካኤል “የዜማው ውቂያኖስ”

 ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች

እኔ ነኝ እኔ ነኝ እኔ ነኝ ተዘራ፣

የማጫውታችሁ ከጊታሬ ጋራ፡፡

የጣሊያን ሰፈሩ አራዳ፣ የዝነኛው የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ የሙዚቃ ዜማ ደራሲና ድምጻዊ ጋሼ ተዘራ ካለፈ አመታት እየተቆጠረ ነው፡፡ አንዲት ሴት ልጅ እንደርሱ አጭሬ፣ጸጉሯ አፍሮ ቢጤ፣ አይነ ከብላላ ደንቡሽቡስ ልጅ አንደነበረችው በከባድ ትዝታ አስታውሳለሁ፡፡ እንደ ዛሬው ሳይሆን እንደ ትላንቱ በአዲሰ አበባ የታወቁ የከፍተኛ ቀበሌ ጠኪነት ቡድኖች ነበሩ በተለይም መርካቶ ከፍተኛ አምስትና የካሳንችስ አካባቢ ከፍተኛ አስራ አምስት የኪነት ቡድኖች የታወቁ ነበሩ፡፡ እኔ እድሜ ልኬን የኖርኩበት ከፍተኛ አንድ የሙዚቃ ኪነት ቡድንም የታወቀ ነበር፡፡ ይህች ጣሊያን ሰፈር ቀበሌ 07 ትኖር የነበረችው ድንቡሽቡሽ የተዘራ ልጅ የቀድሞው ከፍተኛ አንድ የኪነት ቡድን ተውርግራጊ ነበረች፡፡ ነበርች ልበል ዛሬ የነበረው እንዳልነበረ በመሆኑ፡፡ በነገራችን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ቀበሌዎች የእግርኳስ ቡድኖች የበቀሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ተጫዋቾች እስከ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግርኳስ ቡድን ድረስ ተጫውተው እንደነበር የአሁንን ትውልድ ማስታወሱ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለማናቸውም ወደተነሳሁበት ዋነኛ ነጥብ ልመልሳችሁና ወደ ዜማው ውቅያኖስ ልመልሳችሁና የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ባንድ ጋሼ ተዘራ ሀይለሚካኤል ልመልሳችሁና  በትዝታ ፈረስ በወፍ በረር ጣፋጭ ትዝታውን በአጭሩ ላስታውሳችሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ተዘራ ኃ/ሚካኤል በ1930 ዓ.ም በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ነው የተወለደው። ተዘራ የስምንት ዓመት ልጅ ሳለ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ ሄዶ መኖር እንደጀመረ ከታሪኩ እንማራለን። 9ኛ ክፍል እስኪደርስም ትምህርቱን የተከታተለው አራት ኪሎ አምብርት ላይ በሚገኘው በዝነኛው  በዳግማዊ ምንሊክ ት/ት ቤት ነው። ተዘራ በጊዜው በጀነራል መንግሥቱ ንዋይ ይመራ በነበርው የክቡር ዘበኛ አባልነት የተመለመለው ገና የ13 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። በጊዜው የልዑል መኮንን ስካውት አባል የነበረው ታዳጊው ተዘራ በስካውትነት ከጓደኞቹ ጋር ወደ ተለያዩ ስፍራ ጉዞዎችን በማድረግ ፣ ሙዚቃ በመስማት፣ በማንጎራጎር እና በመደነስ ይዝናኑ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ተዘራ ለሙዚቃ የነበረው እምቅ አቅም መታየት የጀመረው። በስካውት ቡድኑ ውስጥ በማንጎራጎር ከሚያዝናኑት መካከል ተዘራ አንዱ ነበር። የስካውት ቡድኑ ሲበተን ተዘራ ወደ ዋናው የክቡር ዘበኛ ቡድን የመቀላቀል እድልን አግኝቶ የሙሉ ጊዜ ሰራተኛ ሆነ።

ለተዘራ ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ የሚወደውን የሙዚቃ ሞያ በደንብ የተማረበት እና ያዳበረበት ቤቱ ነው። በወቅቱ ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ እነ Nerses Nalbandian እና France Zelweckerን የመሳሰሉ የሙዚቃ ባለሞያዎች እና መምህራን የነበሩበት ትልቅ ተቋም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ለተዘራ ልምዳቸውን የሚያካፍሉ እነ ኢዩኤል ዮሐንስ፣ ሳህሌ ደጋጎ፣ ገ/አብ ተፈሪ፣ ገዘኸኝ ደስታ፣ ሰይፉ ዮሐንስ፣ ፍሬው ኃይሉ፣ እሳቱ ተሰማ፣ ብዙነሽ በቀለ እና ጥላሁን ገሠሠን የመሳሰሉ ሙዚቀኞች፣ ዜማ ደራሲያን፣ ግጥም ደራሲያን እና ድምጻዊያን የነበሩበት ቤት መሆኑ ለተዘራ ታላቅ አጋጣሚ ነበር። ከነዚህ ሰዎች የተለያዩ የሙዚቃ ባለሞያዎች ልምድ የቀሰመው ተዘራ እሱም ለወርቃማው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን የራሱን አስተዋጾ አበርክቶ አልፏል።

ዘውዳዊው ስረዓት ከወደቀ በኋላ ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተበትኖ በወታደራዊው መንግሥት “ማዕከላዊ ኦርኬስትራ” ተተካ። ተዘራም በማዕከላዊ ኦርኬስትራ በሊድ ጊታሪስትነት መስራቱን ቀጠለ። ለቀጣዮቹ ሃያ ዓመታት ገደማ በማዕከላዊ ኦርኬስትራ ከሰራ በኋላ እንደገና በሀገሪቱ የመንግስት ስረዓት ለውጥ ሲመጣ ልክ እንደ ክቡር ዘበኛው ሁሉ ማዕከላዊ ኦርኬስትራም የመበተን ጽዋ ደረሰው። ተዘራም ወደ እስር ቤት ወረደ።

ተዘራ የእንጀራ ምንጩን ማጣቱ ሳያንሰው እስር ቤት ሲወርድ ቤተሰቦቹ ከፍተኛ ችግር ላይ ወደቁ። ይሄኔ ነበር የተዘራ ባለቤት የልጆቿን የተራበ ጉሮሮ ለመድፈን የባለቤቷን ታሪካዊ ጊታር በሶስት መቶ ብር እዳ ያስያዘችው። በኋላ ተዘራ ከእስር ቢፈታም በእዳ የተያዘውን ጊታሩን ግን የሚያስመልስበት አቅም አልነበረውም። ይህን ጊዜ ነበር ተዘራ ሃዘን እና ተስፋ የተቀላቀለበትን ሙዚቃ ደርሶ ለማህሙድ አህመድ የሰጠው…..

በምድር ላይ መከራው ችግሩ፣

ቢበዛም ኑሮ ማስመረሩ፣

ሁሉንም ችለን ማለፍ ጥሩ።

በመንግሥት ስረዓት ለውጥ ምክንያት እንጀራቸውን ያጡት እነ ተዘራን የመሳሰሉ የሙዚቃ ባለሞያዎች የኋላ ኋላ በእነ ኮ/ል አምሳሉ ወረደ እና ጥላሁን ገሠሠ እርዳታ ተሰባስበው አንድ ባንድ በማቋቋም መስራት ጀምረው ነበር። በዚህ አዲስ ባንዳቸው አማካኝነትም “የክቡር ዘበኛ ቅርስ” የተሰኘ አልበም ለአድማጭ ማድረስ ችለዋል። ያለመታደል ሆኖ ይህ አዲስ የተቋቋመው የሙዚቃ ባንድም እጣው መበተን ሆነ፣ ተዘራም ወደ ቀደመ የድህነት ህይወቱ ለመመለስ ተገደደ። ግን እድል አሁንም ተዘራን ፊቷን አላዞረችበትም ነበር። አንድ አጋጣሚ የተዘራን ህይወት ዳግም ተስፋ እና ደስታ ዘራችበት።

➳ አጋጣሚው

ኃይሌ ከበደ የተባለ የክቡር ዘበኛ አድናቂ የነበረ ግለሰብ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ይመጣና ተዘራን አፈላልጎ ያገኘዋል። ኃይሌ ተዘራን ባገኘው ጊዜ ተዘራ የነበረበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ነበር። በተዘራ ሁኔታ ልቡ የተሰበረው ኃይሌም ተዘራን ምን ቢሆንለት እንደሚመኝ ይጠይቀዋል። የተዘራ ምኞት የነበረው በእዳ የተያዘች ጊታሩን ማስመለስ ነበር። በዚህ ጊዜ የጊታሯ እዳ 600 ብር ደርሶ ስለነበር ኃይሉ እዳውን ከፍሎ ጊታሩን ለተዘራ አስረከበው። የሚወዳት ጊታሩን መልሶ ያገኘው ተዘራ እጅጉን ተደሰተ። አዳዲስ ሙዚቃዎችን ለማምረትም በአዲስ ሞራል መስራት ጀመረ።

➳ የተዘራ ሥራዎች

ተዘራ ለጥላሁን ገሠሠ…. አመልካች ጣት፣ ፍቅር ደረሰብኝ፣ ልቦናሽ ቢፈርደኝ፣ ናፍቆቷ፣ ንግግር አላቸው፣ ምን ጥልቅ እርጎኝ፣ ምን ሊበጀኝ፣ ኑሮ አያረካኝም፣ ቂም ይዞ መታረቅ፣ የሕይወቴ አጥር ነሽ፣ ሰዎች አትንኩኝ፣ ተራመጂ፣ ተይ አታበሳጭኝ፣ ጠይም ናት፣ እና የኔፍላጎቴ የተሰኙ ሥራዎችን አበርክቷል።

ለብዙነሽ በቀለ…. አትራቀኝ፣ በዓይን የሚታይ ዕድል፣ እንራመድ፣ መሆኑ አሳዘነኝ፣ ትግል ነው፣ እና የሚሰረቅ ቢሆን የተሰኙ ሥራዎችን አበርክቷል።

ለማህሙድ አህመድ…..አንቺን ካልኩ፣ በፍቅር አትቀልጂ፣ ገብቷት ይሆን ፍቅሬ፣ ትዳር ለኑሯችን፣ የዓለም ባይተዋር ነኝ፣ እና የፍቅር ውሃ ጥም የተሰኙ ሥራዎችን አበርክቷል።

ተዘራ ሥራዎቹን ለሌሎች ሙዚቀኞች ከማበርከትም በተጨማሪ እራሱም በድምጹ ይጫወት ነበር። ከተጫወታቸው ዜማዎች መካከል ዝነኛ የነበረው “እኔ ነኝ ተዘራ ” የተሰኘ ስራው ነው።

እኔ ነኝ፣እኔ ነኝ፣እኔ ነኝ ተዘራ

የማጫውታችሁ ከጊታሬ ጋራ።

ሙዚቃ የመንፈስ ምግብ ናት አውቃለሁ፣

ደስ ብሎኝ በስሜት እኔ እጫወታለሁ።

ምንም ብታዩኝ ቁመቴ አጥሮ፣

ያለኝ ስሜት በተፈጥሮ።

ሙዚቃ ፈልስፎ ጭንቅላቴ፣

ሲሰማ ይረካል ሰውነቴ።

  እንደ መደምደሚያ

ጀግኖቹን የሚረሳ ወይም ታሪካቸውን ማወደስ የማይፈልግ ወይም ቋሚ የታሪክ ማስታወሻ ለማቆም የማይታትር እንደ ኢትዮጵያ ያለ ህዝብ ያለ አልመስልህ አለኝ፡፡ ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ ከዚች አለም ድካም ሲያርፍ የቀብር ስነስርአቱ እንኳን በኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡ ካረፈ በኋላ ለጥቂት አመታት በብሔራዊ ቲያትር ቤት በመጨረሻ ባለቤቱ አመሃኝነት በየአመቱ ስራዎቹ ይዘከሩ ነበር፡፡ ዛሬ ስሙን እንኳን የሚያነሳው ጠፍቷል፡፡ ሙዚቃዎቹም በመገናኛ ብዙሃን ብዙ ግዜ አይሰሙም፡፡ሀውልቱ በአደባባይ ይቆማል እየተባለ ብዙ ከተደሰኮረ በኋላ ከስሞ ቀርቷል፡፡ ጥላሁን ዘመን የማይሽረው የሙዚቃ ሰው ነው፡፡ ጣሊያን ለሙዚቃ ንጉሷ ሚሃኤል በአደባባይ ሀውልት አቁማለታለች፡፡ የጂብራልተሩ አለት ታላቁ ይደነቃቸው በሀገሩ አንድም ማስታወሻ ባይቆምለትም፣ ውለታውን የቆጠረችው ሞሮኮ በዋና ከተማዋ ራባት ታላቅ እስታዲዮም በስማቸው ሰይማለች፡፡ የኤደንብራው ምሩቅ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እድሜ ልካቸውን ሀገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት አገልግለው መጨረሻቸው በውህኔ ቤት ማለፍ ነበር ውጤቱ፡፡ በሰውነት ደረጃ ቆመው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ስለ ሀገራቸው መሰረታዊ ችግር እና መፍትሔው ጭምር በተለያዩ ዘዴዎች ያለመሰለስ የጻፉትና ያስተማሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አንዲት ማስታወሻ እንኳን አለመቆሙ ሲታሰብ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡

   በመጨረሻም ተዘራ እና የወርቃማው ዘመን የሙዚቃ ቡድን ጓደኞቹን ስናነሳ አሁን ድረስ ተተኪ ያልተገኘለትን የክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ኦርኬስትራን ታሪክ መዘንጋት ስህተት ነው፡፡ ይህ የሙዚቃ ቡድን ጋሼ ጥላሁን፣ብዙነሽ በቀለን፣ሻለቃ ሀድጎ፣ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ፣ጌታቸው፣ተፈራ፣የውዝዋዜ አሰልጣኙ ሃምሳ አለቃ ዘውገ፣ገዛሀኝ ደስታ፣ ዝነኛው የመድረክ አስተዋዋቂ ሥዩም ባሩዳ፣ጸጉረ ከርዳዳ፣ በድሉ፣ የቫዮሊኑ ንጉስ ሻምበል አየለ ማሞ፣ እሳቱ ተሰማ ወዘተ ወዘተ ያፈራ ታላቅ የሙዚቃ ቡድን ነበር፡፡ ነበር ልበል ዘረኛው የወያኔ ቡድን አዲስ አባባ በ1983 ዓ.ም. እንደተቆጣጠረ ካጠፋቸው የሀገር ቅርሶች አንዱ  በጥንት ዘመን የክቡር ዘበኛ በደርግ ዘመን ደግሞ የማእከላዊ እዝ ይባል የነበረውን የሙዚቃ ኦርኬስትራ ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. በሁኔታው የተበገኑና የተቆጩ በህይወት የተረፉ የቀድሞው የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ‹‹ የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ቅርስ›› የተሰኘ የሙዚቃ ቡድን አቋቁመው አንድ ሙሉ ካሴት የሙዚቃ ስራ ካወጡ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ይህ የሙዚቃ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከስሟል፡፡ ዛሬ ይህ የሙዚቃ ቡድን የሰራቸው እና ያቀረባቸው ዘመን አይሽሬ የሙዚቃ ስራዎች በኢትዮጵያዊ የሙዚቃ አፍቃሪዎች እዝነ ልቦና ወይም በብሔራዊ መገናኛ ብዙሃን ስቱዲዮ ( ዘመኑ በዋጀው ስቱዲዮ ውስጥ) አሊያም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ መጽሐፍት ውስጥ ነው፡፡ አውሮፓውያን በአባቶቻቸው ስራ ላይ እየጨመሩ ሲሄዱ እኛ አፍሪካውያን በተለይም ኢትዮጵያውያን የአባቶቻችንን ታሪክ በማጥፋት እንደ አዲስ ጀማሪዎች ስለሆንን ካለንበት መነሳት አልቻልንም፡፡

ለማናቸውም ጋሼ ተዘራ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚነሱ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው ተብሎ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ሰላም

መናደድ ሲበዛ ያስቀኛል፣

እንደው መናደዴ ይቆጨኛል፡፡

Filed in: Amharic