>

መንቆረር የአቡነ ቴዎፍሎስን የመታሰቢያ ሐውልት ልትተክል ነው- (ጌታ በለጠ)

መንቆረር የአቡነ ቴዎፍሎስን የመታሰቢያ ሐውልት ልትተክል ነው-

 ጌታ በለጠ (ደብረ ማርቆስ፣ ጎጃም)

ወርኅ ሚያዚያ በኢትዮጵያ ታሪክ አሉታዊ ብሎም አወንታዊ ታሪኮች ተገምደውበታል፡፡ በዳግም ጣሊያን ወረራ ወቅት የማዕከላዊ መንግስት መሪ ሐገር ጥለው ሲሸሹ የውስጥ አርበኞች የሐገርን ዳር ድንበር አስከብረው ነጻ ሐገር ያስረከቡን በወርኀ ሚያዚያ ነው፡፡ንጉሡ ከስዴት ተመልሰው የኢትዮጵያን ሰንደቅ በታላቁ ቤተ መንግስት ያውለበለቡት ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ/ም በመኾኑ ዕለት የአርበኞች ቀን ተብሎ ሲታሰብ ይኖራል፡፡የካሳ ኀይሉ (አጤ ቴዎድሮስ) ቀኝ እጅ እና የጦር ፊታውራሪ የኾኑት ፊታውራሪ ገብርዬ (ገብረሕይወት ጎሹ) ስለ ሐገር እና ሕዝብ ሲሉ መስዋዕትነት የተቀበሉት በወርኀ ሚያዚያ ነው፡፡ በአምስቱ የአርበኝነት ዘመን ማግስት ጃንሆይ ኀይለሥላሴ ጦር  በደጃዝማች በላይ ዘለቀ እና ወንድሞቹ ላይ ጦር በማዝመት ጀግኖችን ለእልቂት የዳረጓቸው በሚያዚያ ወር ነው፡፡ ወቅቱ እልፍ የታሪክ ክንውኖች የተካኼዱበት ነው ወር ነው፡፡

ዛሬ የ2015 ዓ/ም የወርኀ ሚያዚያ የመጨረሻው ቀን ነው። እንሆ እኔም የሐዋርያው እባ ሰማዕቱ ቅዱስ ማርቆስ የዕረፍት ቀን የሚታሰብበትንና በየዓመቱ ሚያዚያ 30 ቀን  እልፍ ምእመናን በሚታደሙበት፣ የቤተ ክርስቲያን ስርአት ባልተበረዘ መልኩ በሚንጸባረቅበት በታላቅ ድምቀት በሚከበረው የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ተገኝቶ ምስጋናዬን አድርሼ ተመልሻለሁ፡፡የእኔዋ ደብረ ማርቆስ በታላቁ የጎጃሙ መስፍን ንጉሥ ተክለሃይማኖት ሥም የሰየመችው አደባባይ ነጭ በለበሱ፣ የቤተክርስቲያን አልባሳት በደረቡ፣ ሰንደቅ በሚያውለበልቡ፣ ኮርቻው እና ግላስ  ባደመቀው ፈረስ ላይ ተቆናጠው በሚንጎባለሉ ሰዎች ተሞልቷል።

የጎጃሙ መስፍን ከዛሬ 143 ዓመታት በፊት ያስደበሩት የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን እንደ ደረጃቸው (ድቁና፣ ቅስና እና ክህነት ለመቀበል የተሰበሰቡ የቤተክህነት ሰዎች፣ ቤተክርስቲያኑን ለመጎብኘት ያለሙ ሰዎች፣ ታቦተ ህጉን ለማንገስ ከገጠር እና ከተማ የተሰበሰቡ ምእመናን ተከቧል፡፡ ስለ ክብረ በዓል ትርጓሜ የሰማሁትን ልንገራችሁ፡፡ ክብረ በዓል ከአንድ ዘመን ወደ ሌላ ዘመን፣ ከአንድ የሕይወት ደረጃ ወደ ሌላ የሕይወት ደረጃ መሸጋገሪያና የታሪክ ድርጊት፣ እንዲሁም የቅዱሳን፣ የጻድቃን፣ የሐዋርያት እና ሰማዕታት ልደትና ሞት መታሰቢያ ድርጊቶች ተምሳሌታዊ በኾነ መንገድ የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ከዚህ አንጻር ሚያዚያ 30 የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የዕረፍት ቀን ነው፡፡ ጣኦት አምላኪዎች ቅዱስ ማርቆስን በበሬ ጎትተው ያስገደሉት በዛሬዋ ዕለት ነው፡፡ ስለሆነም በየዓመቱ በዚህ ዕለት በድምቀት ይከበራል፡፡ካህናቱ ከበሮ፣ ጽናጽልና መቋሚያ የተሰኙ ንዋያተ ቅዱሳት ታጅበው በዜማ እና ሽብሸባ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፣ ግሩም ነው ለሚሰማው፡፡

ሌላም ጎጃሞች ደጃች ተድላ ጓሉ የዛሬዋን ደብረ ማርቆስ ከተማ ከዛሬ 170 ዓመታት በፊት “መንቆረር” ሲሉ የሰየሙበትን ቀን እየዘከሩ ነው። በዚህ ዕለት ታዲያ የታሪክ ስንቅ የሚኾን ግሩም ሥራ ተሰርቷል፣ የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የመታሰቢያ ሐውልት በደብረ ማርቆስ ከተማ፣ በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ለማቆም  የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

አቡነ ቴዎፍሎስ ማን ናቸው?

አቡነ ቴዎፍሎስ የተወለዱት ሚያዝያ 16 ቀን 1899 ዓ/ም በጎጃም ክፍለሀገር፣ ደብረ ማርቆስ አውራጃ፣ ደብረ ኤልያስ ከአባታቸው ከሻቃ ጀንበሬ ውቤ እና እናታቸው ወይዘሮ ዘርትሁን አደላሁ ተወለዱ፡፡ የትውልድ ዘመናቸውን በተመለከተ ዲያቆን መርሻ አለኸኝ “ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን” ሲል በ1996 ዓ/ም በጻፈው መጽሐፍ ገጽ 33 ላይ የአቡኑን የውልደት ዘመን ሚያዚያ 1902 ዓ/ም እንደሆነ ጽፏል፡፡ነገር ግን የአቡነ ቴዎፍሎስ ታናሽ ወንድም ልጅ የሆነው እና አቡኑ ራሳቸው ያሳደጉት መምህር ታምራት አበራ ጀንበሬ ውቤ የተባለ ግለሰብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የአቡነ ቴዎፍሎስ የትውልድ ዘመን ሚያዚያ 16 ቀን 1899 ዓ/ም እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ታምራት አበራ ጀንበሬ  “ቀዳማዊ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ (የሕይወት ታሪክ)” በሚል ርዕስ የአቡኑን የሕይወት ታሪክ ለንባብ አብቅቷል። መጽሐፉን ማንበብ ትርፋማ ያደርጋል፡፡ ሻቃ ጀንበሬ ውቤ ወታደር ስለነበሩ እስከ ጅማ እና ከፋ ድረስ  በመኼድ ሐገራቸውን አገልግለዋል፡፡በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ደብረ ኤልያስ ተመልሰው እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ኖረዋል፡፡ሻቃ ጀንበሬ  አቡነ ቴዎፍሎስን የወለዷቸው ከከፋ ወደ ትውልድ መንደራቸው ደብረ ኤልያስ ከተመለሱ በኋላ ነው።

የአቡነ ቴዎፍሎስ የልጅነት ሥም ይታዬው ነበር፡፡ ይታዬው የሚለውን ሥም ያወጡላቸው አባታቸው ሻቃ ጀንበሬ ውቤ ናቸው፡፡ አቡኑ ገና በልጅነታቸው ከዚያው ደብረ ኤልያስ ደብር ንባብና ዳዊት ከመርጌታ ረዳኸኝ ዘንድ ተማሩ። ንባብና ዳዊት ሲጨርሱ የዜማ ትምህርት እዚያው ደብር ካሉ መምህር ግራጌታ ሣህሉ ዘንድ አጥንተዋል። ከዚያ በኋላ ቅኔ፣ቅዳሴ፣ ውዳሴ ማርያም እና የወንጌል ትርጓሜ ከየኔታ ገብረሥላሴ ዘንድ ተማሩ።የኔታ ገብረሥላሴ ለህፃኑ ይታዬው (በኋላ አቡነ ቴዎፍሎስ)  መልእክቱ የሚል ሥም አወጡላቸው፡፡ 

አቡነ ቴዎፍሎስ በ1920 ዓ/ም (በ1922 ዓ/ም) አዲስ አበባ ከሚገኙት ሊቀ ሐዲስ ተክሌ ዘንድ በመኼድ መጻሕፍተ ሐዲሳትና እና የፍትሐ ነገሥትን ትርጓሜ አጠኑ። ከአስር (አስራ ሁለት) ዓመታት በኋላ (1930 ዓ/ም) ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመኼድ የምንኩስና ማዕረግ ተቀበሉ። አባ መልእክቱ ተብለው ተጠሩ። በጣሊያን ወረራ ወቅት አቡነ ቴዎፍሎስ ከመምህራቸው ሐዲስ ተክሌ ሳይለዩ  ረዳት መምህር በመሆን የቤተክርስቲያን ትምህርት እንዳይቋረጥ በትጋት ሲያስተምሩ ቆይተዋል። 

በ1934 ዓ/ም  ጃንሆይ ኃይለሥላሴ ለተለያዩ ምሑራን ዘመናዊ የትምህርት ዕድል ሲሰጡ አቡነ ቴዎፍሎስ አንዱ የዕድሉ ተጠቃሚ ስለነበሩ በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት( በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)  ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠኑ፡፡በ1935 ዓ/ም የመካነ ሥላሴን ገዳም በአለቅነት እንዲያስተዳድሩ  መምህር ተብለው ተሾሙ፡፡መካነ ሥላሴ ተሰርቶ መንበረ ጸባኦት ቅዱስ ሥላሴ ካቴድራል ሲሰኝ በ1938 ዓ/ም የመጀመሪያው አለቃ በመሆን ሊቀ ስልጣናት ተብለው ተሾሙ፡፡ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ/ም ለመዓርገ-ጵጵስና ተመርጠው ሊቀ ጳጳስ ተባሉ። በ1953 ዓ.ም የመጀመሪያው ፓትሪያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንደራሴ ሆነው በመሾም እስከ 1963 ዓ/ም ድረስ በተለይ የውጭውን ጉዳይ ኃላፊነት ተሸክመዋል፡፡ ግንቦት 1 ቀን 1963 ዓ/ም የኢትዮጵያ ፓትርያርክና ዕጨጌ ዘመንበረ-ተክለሃይማት ሆነው በኢትዮጰያ ምድር ተሹመዋል፡፡በዚህም በኢትዮጵያ ምድር የተሾሙ የመጀመሪያው ፓትርያርክ  ለመሆን በቅተዋል፡፡ 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አንዳፍታ ላውጋችሁ ሲሉ በሰየሙት መጽሐፍ “ብጹዐነታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤተክርስቲያኗን በመወከል ማንም አይመስላቸውም፡፡ ግርማቸው እኛን ተከታዮቻቸውን ሲያኮራ ሌሎችን ያፈዝ ነበር፡፡ ከሰሯቸው ሥራዎች አንዱ ትልቅ ጉዳይ የብራና ጽሑፎችን በማይክሮፊልም እንዲሰራ ማድረጋቸው ነው” ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ አቡነ ቴዎፍሎስ ለቤተክርስቲያን አስተዳደር ሆነ ልማታዊ ሥራዎች ላይ ያላቸውን ጉልህ ድርሻም ያመሰግናሉ፡፡

አቡነ ቴዎፍሎስ የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ/ም በዕለተ ማክሰኞ ከመኖሪያ ቤታቸው በምሽት በደርግ መንግስት ታፍነው ወደ ቤተ መንግስት ተወስደው ታሰሩ። ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ/ም በዕለተ ቅዳሜ  ተገደሉ። የደርግ መንግስት አቡነ ቴዎፍሎስን ያለ ፍርድ ነው የገደላቸው፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ያለ ፍርድ መግደሉ ብቻ ሳይሆን ከገደላቸው በኋላ ሥማቸውን ለማጥፋት የኼደበት ርቀት ነው፡፡ የደርግ መንግስት ምክትል ፕሬዘዳንት የነበረው ሌ/ኮሎኔል  ፍስሐ ደስታ “አብዮቱ እና ትዝታዬ”  ሲል በሰየመው መጽሐፉ ገፅ 199 ጀምሮ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ አያያዝ እና አገዳደል የጻፈውን እንመልከት፡፡

ሌ/ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ መንግስት የተያዙበትን ምክንያት ሲገለጽ “ፓትርያርኩ የራሳቸውን ዘመዶች ይሾማሉ፣በመንግስት ላይ  አሻጥር ይሰራሉ፣ለዲያቆናት እና ቀሳውስት ደመወዝ ጭማሬ ከልክለዋል፣በጣሊያን ወረራ ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያን ሲገደሉ እጃቸው አለበት የሚል የተፈረመበት ክስ ደርሶናል”ይላል፡፡እያንዳንዳቸው ክሶች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን እንመልከት፡፡

የመጀመሪያው ክስ አቡነ ቴዎፍሎስ የራሳቸውን ዘመዶች ይሾሙ ነበር የሚል ነው፡፡ በእርግጥ የደርግ መንግስት ስልጣን በያዘ ማግስት አቡነ ቴዎፍሎስ ለአቡነ ጳውሎስ፣ ለአቡነ ባስልዮስ እና አቡነ ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ሹመት ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ሦስቱም አቡኖች አይደለም የአቡነ ቴዎፍሎስ ዘመድ ሊሆኑ ቀርቶ የአንድ አካባቢ  ሰዎች እንኳን አልነበሩም፡፡ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ይኼንን ክስ ሲያቀርብ አቡነ ቴዎፍሎስ የትኞቹን ዘመዶቻቸውን እንደሾሙ ያቀረቡት ማስረጃ የለም። ይኼ ደረቅ ውንጀላ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ የቀረበባቸው ክስ በመንግስት ላይ ያሴራሉ የሚል ነው፡፡ ይሄ ክስ መሰረተ ቢስ ነው፡፡ሌ/ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ በጠቅላላው አቡኑ በመንግስት ላይ ያሴራሉ ከማለት ውጭ መቼ እና እንዴት እንዳሴሩ ያቀረቡት ማስረጃ የለም፡፡ይሄንን አስመልክቶ በወቅቱ ከኃይለሥላሴ ባለስልጣናት ጋር በታላቁ ቤተ መንግስት እስር ቤት ለስምንት ዓመታት ያኽል ታስሮ የተፈታው አበራ ጀምበሬ “የእስር ቤቱ አበሳ በታላቁ ቤተ መንግስት (1966-1974)” ሲል ባሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 141 ጀምሮ ያዬውን ሃቅ አስቀምጧል፡፡ አበራ ጀምበሬ በዚህ መጽሐፍ ገጽ 144 ላይ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊያሳስራቸው የቻለው አቋማቸው ከደርግ ፖሊሲ ጋር የማይስማማ በመሆኑ እና የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስከበር ያላቸው የማይታጠፍ አቋም እንደሆነ ጽፏል፡፡

የአበራ ጀምበሬን ሃሳብ በሚያጠናክር መልኩ መስፍን በቀለ “ስኳዶቹ- ገዳይ ጓዶች” በተሰኘው መፅሐፉ የወቅቱ የዘመቻና ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ የነበረው ሻለቃ (በኋላ ኮሎኔል) ዳንኤል አስፋው  አቡኑ መጋቢት 10 ቀን 1968 ዓ/ም ለደርጉ መንግስት የፃፉትን ማመልከቻ ተቀብሎ ያልፃፉትን እንደፃፉ አድርጎ፣ በደብዳቤውም አቡኑ አዲሱን መንግስት እንደሚወነጅሉ አድርጎ ለደርግ ቋሚ ኮሚቴ የሕዝብ ደህንንት ጥበቃ ኃላፊዎች ደብዳቤ እንደፃፈ አስፍሯል።የአቡነ ቴዎፍሎስ ማመልከቻ ከሥርዓት ውጭ መታሰራቸውን እና የመንግስት አካኼድ የቤተ ክርስቲያንን ሕግ የሚፃረር መሆኑን የሚያሳኝ ነበር። አቶ መስፍን በቀለ ለአቡነ ቴዎፍሎስ መገደል የኮሎኔል ዳንኤል አስፋው ተንኮል ከፍተኛ አስተዋጽኦ  እንዳደረገ በዚሁ መጽሐፉ ላይ ይጠቅሳል፡፡

ኮሎሌል ፍሰሐ ደስታ በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ ያቀረቡት ሌላው ክስ “ለዲያቆናት እና ቀሳውስት የደመወዝ ጭማሬ ከልክለዋል፣ በዚህም ቅሬታ ቀርቦባቸዋል” የሚል ነው፡፡ ይኼ በጣም አስቂኝ ቀልድ ነው፡፡ደርግ ራሱ  መንግስትና ሐይማት የተለያዩ ናቸው ባለበት አፉ በቤተክርስቲያን የውስጥ አሰራር የሚገባበት ምክንያት አግባብ አይደለም፡፡ ቅሬታ ቀርቧል ቢባል እንኳን አቡኑን ለመግደል የሚያደርስ አልነበረም። 

ሌ/ኮሎኔል  ፍስሐ ደስታ የአቡነ ቴዎፍሎስን አሟሟት በተመለከተ ግርምንትን በሚያጭር መልኩ “…ፓትርያርኩ ለብቻቸው ታስረውበት ከነበረው የእድሚራል እስክንድርያ መኖሪያ ቤት (ብሔራዊ ቤተ መንግስት ውስጥ) አምልጠው እንደገና በመያዛቸው ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር እንዲታሰሩ ተደረገ፡፡ በ1971ዓ/ም በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ከሌሎች ስምንት ሰዎች ጋር ተገድለው  አስክሬናቸው ራስ አስራት ካሳ ግቢ መገኘቱ ተረጋግጧል” ይላል፡፡ ይኼ  ታሪክ ይቅር የማይለው ወሸት ነው፡፡

እውነታው ሌላ ነው፡፡አበራ ጀምበሬ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፉ ፓትርያርኩን ከእስር ቤት አስወጥተው የወሰዱበትን ድባብ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡”ፓትርያርኩ  በሦስት መንፈሳዊ ልጆቻቸው ግራ ቀኝ ታጅበው፣ ጥቁር ቀሚሳቸውን ለብሰው፣ ካባቸውን ደርበው፣ አክሊል እንደደፉ፣ አርዌ ብረት እንደያዙ፣ ነጠላ ጫማ እንደተጫመቱ ሲሄዱ ፅዋ መስዋዕትነትን ለመቀበልና ሕይወታቸውን ለቆሙለት ዓላማ አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጁ እንጅ ምንም ዓይነት ሥጋት የሚታይባቸው አልነበሩም”ይላል። የአበራ ጀምበሬን ሃሳብ የሚያጠናክርልን ሌላ ማስረጃ አቶ መስፍን በቀለ “ስኳዶቹ- ገዳይ ጓዶች” ሲል 2011 ዓ/ም ያሳተሙት መፅሐፍ ነው፡፡ይኼ መጽሐፍ በገጽ 56 ላይ እንዲህ ይላል።

“…የሞቱን ውሳኔ ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ስላሴ እንዲያስፈፅሙ ታዘዙ።… ኮሎኔል ተስፋዬ የአቡነ ቴዎፍሎስን የሞት ፍርድ ውሳኔ ባስቸኳይ እንዲፈፀምና መፈፀሙም በፍጥነት እንዲገለፅላቸው የማእከላዊ ምርመራ ድርጀት ሹም ለነበሩት ለሻለቃ (አሁን ብ/ጄኔራል)  ለገሰ በላይነህ ትእዛዝ ሰጡ።ሻለቃ ለገሰም ውለው ሳያድሩ በጓድ ዘሪሁን አጋፋሪ በሚታዘዙ ወታደሮች ግድያው በልኡል አስራት ካሳ ግቢ እንዲፈፀም ጓድ ዘሪሁን አጋፋሪን አዘዙ። ጓድ ዘሪሁንም በታዘዙት ዕለት አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በሚያዟቸው ወታደሮች አማካኝነት ግድያውን አስፈፀሙ። የቀብሩ ሥርዓትም በልዑሉ ግቢ ውስጥ ወዲያው ተከናወነ።”

የአቡነ ቴዎፍሎስ አፅም የት እና እንዴት ተገኘ?

የደርግ መንግስት ከተወገደ በኋላ በ1984 ዓ/ም የአቡኑን አፅም የሚፈልግ በአቡነ ባርናባስ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቶ ነበር፡፡ በአንድ ዕለት አማረ ደጀኔ የሚባል በደርግ ሰዓት ወታደር የነበረ ሰው የጡረታ መብቱን ለማስከበር ወደ ኮሎኔል አስራት አየለ (ኮሎኔል አስራት አየለ በኢህአዴግ የመጀመሪዎቹ ዓመታት የደህንነት ባለሙያ የነበረ ሰው ነው) ቢሮ ይመጣል፡፡በዚያን ጊዜ ወታደሩን ደህንነቱ የሚጠበቅለት መሆኑን ነግረው በልዑል አስራት ካሳ ግቢ ውስጥ በደርግ ወታደሮች የተገደሉትን ሰዎችን አስክሬን የተቀበረበትን ቦታ እንዲያሳይ ይጠየቃል፡፡ እሱም ፍቃደኛ በመሆኑ ቀድሞ ተቋቁሞ ለነበረው ኮሚቴ እና ለአቡነ ቴዎፍሎስ ቤተሰቦች  ተደውሎ አፅሙ እንዲወጣ ተደረገ፡፡

በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራስን መቻል ከፍተኛ ሥራ የሰሩ፣ ሐዋርያዊ ትምህርት እንዲስፋፋ ያደረጉ፣ የኢትዮጵያንን ቤተ ክርስቲያን ከዓለም አብያተ ክርስቲያን ጋር ለማቀራረብ የተጉ፣የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትን ያጸኑ አባት ነሐሴ 4 ቀን 1984 ዓ/ም ሥርዓተ ፍትኅት ተደርጎ አፅማቸው በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴደራል በክብር አረፈ።

ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ፣ በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ሐውልት ለማሰራት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን ስናይ ደስታችን ወደር የለውም፡፡

Filed in: Amharic