ካሲናው ጎጃም- በእኔ ዕይታ
ጌታ በለጠ ( ጎጃም፣ ደብረ ማርቆስ)
ሔንሪች “ቃላት ካቆሙበት ሙዚቃ ይጀምራል” የሚለው አባባል አለው፡፡ ሙዚቃ ቃላት ካላቸው ጉልበት በላይ መልዕክት ያስተላልፋሉ ማለቱ ነው፡፡ነገሩ እውትነት አለው፣ የዘፈን ጉልበት ኃያል ነው፣ ግዙፍ መልዕክት ነው የሚያሻግረው፡፡ እንደ አስቻለው ፈጠነ አይነቶች ሲዘፍኑት ደግሞ ጉለበቱ ውበት ይጨምርበታል፣ አድማጭ ምርኮኛ ይኾናል፡፡
የሐገር ፍቅር ስሜት የሚያነሳሱ፣ትዝታን የሚቀሰቅሱ፣ ወኔ የሚያላብሱ እና ልብን የሚያሞቁ ዘፈኖችን በመዝፈን የሚታወቀው አርቲስት አስቻለው ፈጠነ “ካሲናው ጎጃም” በሚል ርዕስ አዲስ ዘፈን ለአድማጭ አድርሷል፡፡ ዘፈኑን ትላንት ማታ ደጋግሜ ሰማሁት፡፡ ጎጃምን ያየሁበት ዘፈን ነው፣ ዘፈኑ ሚስጥር ይበዛዋል፡፡
በመሰረቱ አንድ ዘፈን የሚለካው በዘፈን አላባውያን ነው፡፡ ዜማ፣ ቅኝት፣ ግጥም፣ ምት እና ቅንብር የዘፈን አላባውያን ናቸው፡፡ እኔ የማቀርበው ምልከታ የግል ስሜት እንጅ ሂስ አይደለም፡፡ ሂስ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሚዛናዊ ግምገማ መኾኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ከዚኽ አንጻር ሙያውም እውቀቱም የለኝም፡፡ ሙያው ላይ ያሉ ግለሰቦች ሚዛናዊ ግምገማ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡
አስቻለው ዘፈኑን የሚጀምረው “አገራችን ጎጃም፣ ወንዛችን ዓባይ” ብሎ ነው፡፡
አገራችን ጎጃም ወንዛችን ዓባይ፣
እንደ መስቀሏ ወፍ ብቅ አትይም ወይ፡፡
ተክለማርያም ፋንታዬ “አምሳለ ገነት” ሲል በሰየመው መጽሐፉ “ጎጃም የባሕር ጠረፍን ከማጣቱ በስተቀር ከአካባቢ ጠቅላይ ግዛቶችና ሐገሮች ጋር እንደ ልቡ ለመነገድ የሚችል ከመኾኑም በላይ ታላቁን የዓባይ ወንዝና የጣናን ባሕር በብዙ ሊጠቀምባቸው ተፈጥሯዊ መብት ፈቅዶለታል።” ይላል። ጎጃም የታላቁ የግዮን ወንዝ መነሻ ነው። ግዮን ከጎጃም፣ ሰከላ ተነስቶ ጎጃምን ይዞራታል።
“የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ፣
ዓባይ ሌጋሲ ነው ለዚያ ለበርሃ።”
እያለች እጅጋዬሁ ሽባባው የግብጽ ሲሳይ መኾኑን በቁጭት ያንጎራጎረችለት የግዮን ወንዝ መነሻው ጎጃም መኾኑን ነው አርቲስቱ የሚነግረን፡፡
አገሩን ከእነ ወንዙ ሥም የተናገረው አርቲስት አዘውትራ መምጣት የተወችውን ጉብል እንደ መስቀል ወፍ በዓመት እንኳን ትመጣ ዘንድ “እንደ መስቀሏ ወፍ ብቅ አትይም ወይ” እያለ ይማጸናታል፡፡ የመስቀል ወፎች ውዶች ናቸው፣ መገኛቸውም አፍሪካ ብቻ ነው፡፡ የመስከረምን ወር ቆጥረው ነው የሚታዩት የመስቀል ወፎች ጥቁር ወርቃማ ቀለም አላቸው፡፡ ለእነዚህ ወፎች ወርኀ መስከረም የመራቢያ ጊዜ በመኾኑ ደምቀው አና አብበው ለጾታዊ ግንኙነት ይወጣሉ፡፡
ግምባሯን ቶ መስቀል የተነቀሰችው፣
ያያ ወንዳለ ልጅ ነብሮን አገባችው፡፡
አሁን አሁን ቀረ እንጅ የጎጃም ጉብሎች ግምባራቸውን ቶ ምልክት ይነቀሱ ነበር፡፡ በ ቶ ምልክት የመነቀሳቸው ምስጢር ጥናት ይጠይቃል፣ በደመ ነፍስ ( በግምት) የተደረገ ግን አይመስለኝም፡፡ ቶ ሰባተኛ ተራ ላይ የምትገኝ የግዕዝ ፊደል ናት፡፡በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ሰባተኛው ቀን ሰንበት ነው፡፡ ስለ ቶ ምልክት ደራሲ አስቻለው ከበደ “ከርከቤዴል፣ የኢትዮጵያ የሰማይ ኃያላት” ሲል በሰየመው መጽሐፉ ላይ ትቂት ማብራሪያ ጽፏል፡፡ የዚኽ መጽሐፍ የገጽ ሽፋን (cover) ላይ ያለው ምልክትም ቶ የሚል ነው፡፡ የዚኽ ግጥም ሁለተኛው ስንኝ ያያ ወንዳለ ልጅ ( የአያ ወንዳለ ልጅ) የተባለችው ሴት ማንነትን አልደረስሁበትም፡፡
አርቲስቱ ትዝታ ቀስቃሽ ነው፡፡ “ሎሚ ተራ-ተራ” የሚለውን የጥንት የሕዝብ ዘፈን በመሐል አምጥቶ ዶል አድርጎታል፡፡ “ሎሚ ተራ ተራ” በሚለው ሐረግ ውስጥ ነፍጠኛዋን አርቲስት ጠለላ ከበደ አስታወስሁኝ፡፡አርቲስት ጠለላ (የከበደ ወርቄ ልጅ) የደርግ መንግስት በገባ ማግስት ” ሎሚ ተራ ተራ- እምዬን አደራ” ስትል ለእነ ደጃዝማች ጸሐዩ እንቁሥላሴ፣ ጃንሆይ ኃይለሥላሴ እና ለኢትዮጵያ አቀንቅና ነበር፡፡በዚህም የደርግ መንግስት አስሯት ነበር፡፡ አርቲስት ጠለላ ከበደ ማለት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ መስከረም 10 ቀን 1987 ዓ/ም በወያኔ መንግስት ሲታሰሩ በማመጻቸው ከታሰሩት 1500 ግለሰቦች አንዷ ናት፡፡
አታሞው ሲመታ መሬቱ አረገደ፣
ያያ ኩታ ለብሶ ዝናብ አወረደ፡፡
ያያ ( እያያ) የአጎት ወይም የትልቅ ወንድም መጠሪያ ነው( ክንዴ፣ ወንድምጋሼ፣ መከታዬ እንደምንለው)፡፡ በዚህ ስንኝ ውስጥ ዝናብ አወረደ የሚለው ሐረግ ሁለት ትርጓሜ አዝሏል፡፡ በአንድ በኩል “ዝናብ እንቅጥቅጥ” የተሰኘውን ቱባ የኾነ የጎጃም ድለቃ የሚያሳይ ሲኾን በሌላው ገጽ ጠጅ እና ጠላ እንደ ዝናብ ያለመጠን ቀዳ ማለት ነው፡፡
ድግሱ አማረላት ታተይ ተመናሸች፣
መቀነቷን ታጥቃ ዋንጫ ለቀለቀች፡፡
ታተይ (እታተይ) ጎጃም አካባቢ ልጅ እናቱን የሚጠራበት ሥም ነው፡፡ “መቀነቷን ታጥቃ ዋንጫ ለቀለቀች” ቅኔ ለበስ ስንኝ ነው፡፡ አንደኛው ትርጉም “ዋንጫ ልቅለቃ” የተሰኘውን ጎጃም ውስጥ የተለመደውን የድለቃ (እስክስታ) አይነት ለመግለጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል “ዋንጫ ለቀለቀች” ማለቱ ባሕላዊ የጠጅ መጠጫ (ብዙ ጊዜ ከቀንድ የሚሰራ ዋንጫ) አጠበች/ አጸዳች ማለት ነው፡፡
ያለ ዛሬ ቤቴን አታውቀውም ብሎ፣
ጠሪ አክባሪ ድሷል አቆልቋይ ጨምሮ፡፡
ጎጃም አንድ ውብ ባሕል አለው፣ ወጪ/ ሸክም መጋራት የሚሉት፡፡ ሰው ልጁን ቢድር፣ተዝካር ቢያወጣ፣ቤት ቢሰራ ዘመዶቹ፣ ጎረቢቶቹ እንዲሁም ወዳጆቹ የድግሱን ወጪ ያግዙታል፡፡ ይኼ ሥርዓት አቆልቋይ ይባላል፡፡ በእኔ የትውልድ ቦታ ( እነብሴ ሳር ምድር) አቆልቋይ “ሌማት” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ አንድ ሌማት ማለት 120 እንጀራ እና ሁለት እንስራ ጠላ ነው። አንድ ግለሰብ ብዙ ጊዜ የሚያዋጣው የሌማት ዕኩል ( ግማሽ ሌማት) ነው። ሰዎች ያላቸው የቀደመ ወንፈን እና ግንኙነትን መሰረት በማድረግ አንዳንድ ሰዎች ሩብ ሌማት ይይዛሉ። ታዲያ አስቻለው ፈጠነ ይኼንን ውብ ባሕል ነው በዘፈኑ ያንጸባረቀው፡፡
ድግሱን ደግሶ አይነግርም አዋጅ፣
መንገደኛው ሁሉ ሰተት ነው እንጅ፡፡
ጎጃም ውስጥ የዓመት በዓል ድግስ ቢኖር ሰው ተመርጦ አይጠራም፡፡ ዘመድ፣ ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ አበልጅ፣ ተጋብ ተብሎ በሰዎች መካከል ልዩነት አይደረግም፡፡ ቤቱ ክፍት ነው፡፡ እግር ያደረሰው፣ ዕድል የጣለው ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ ነው፡፡
ጋኑን እጠቢና በጋምቢሎ ጭስ፣
በጥብጠሽ ጠብቂኝ ገምብሃ ድረስ፡፡
ከእንጨት ጥቅሞች አንዱ ለማጥንትነት ማገልገል ነው፡፡ጠላ ከመጠንሰሱ በፊት ጋኑ ( ከሸክላ የተሰራ ባሕላዊ ዕቃ) ማዕዛው ውብ በኾነ እንጨት ይታጠናል፣ ይታጠባል፡፡ ጋምቢሎ እናቶች ዕቃ ለማጠብ እና ለማጠን ከሚገለገሉባቸው እንጨቶች አንዱ ነው፡፡ ገምብሃ አገር ነው፣ አገው ምድር ውስጥ ያለ የቦታ ሥም፡፡ ገምብሃ ተራራ ነው፣ ለዓይን ማራኪ የኾነ መልክአምድር፡፡ ገምብሃ ነጻነት የተጻፈበት ምድር ነው፣አባት አርበኞች የታገሉበት የጦር ሜዳ፡፡
ኩራትሽ ኩራትሽ ኩራትሽ ኩራትሽ፣
ዶቅማ መቅመስሽን አወቅሁ በምላስሽ፡፡
ዶቅማ ጣፋጭ ፍሬ ያለው የዛፍ ዓይነት ሲኾን በብዛት የሚበቅለው መተከል፣ አሶሳ እና ከማሽ ዞን አካባቢ ነው፡፡እኔ ዶቅማን የማውቀው ቤኒሻንጉል ክልል፣ከማሽ ዞን በነበርሁት ዘመን ነው፡፡ ዶቅማ ፍሬዎቹ ጥቋቁር ኾነው በመጠን አነስ ያሉ ናቸው፡፡ ፍሬዎቹ ጥቋቁር ከመኾናቸው የተነሳ ምላስ ያቀልማሉ፣ ለዚህም ነው አርቲስቱ “ዶቅማ መቅመስሽን አውቅሁ በምላስሽ” የሚለው፡፡
ፍጥረት መጀመሪያው
የአፍላጋት መፍለቂያ የዮቶር ሞገድ፣
ካሲናው ጎጃም ነው ምድሪቱ ምጣድ፡፡
አፍላጋት ማለት ወንዞች ማለት ነው፡፡ጎጃም የአፍላጋት (የወንዞች) መፍለቂያ ነው፡፡ ገነትን ያጠጡ ከነበሩት አራቱ ወንዞች መካከል ከጎጃም ሰከላ የሚነሳው የግዮን ወንዝ አንዱ ነው፡፡ ዮቶር የሙሴ አማት ነው፣ ሴት ልጁን ለሙሴ የዳረ የሞርያም ካህን ነው፡፡ ሞርያም የጣና እና ዓባይ ዙሪያ የቀደመ መጠሪያው ነው፡፡ ሙሴ እና የዮቶር ሴት ልጅ የተያዩት የሙሴ ሴት ልጅ ከብቶችን ከዓባይ ወንዝ ስታጠጣ ነው፡፡
የዘፈኑ ፍጻሜ ምርቃት ነው፡፡ ጃንሆይ ኃይለሥላሴ “ሽምግልናችንን ያልናቀች ወጣትነታችን የተባረከች ትሁን” ይላሉ ስለ ሽምግልና በረከት ሲናገሩ፡፡ የሽምግልና አንዱ በረከት ምርቃት ነው፡፡ ለሞተ ጽድቁን፣ ለታመመ ምህረቱን፣ላለው ስምምነቱን፣ ላጣ ማግኘቱን እንዲያድለው የተመኙት ሽማግሌ የተቸገረ የሚያበድር፣ የተጣላ የሚያስታርቅ አለኝታ ሽማግሌ አያሳጣን ብለው ተመኝተዋል፡፡ ፍትኅ ተጓደለ፣ ድሃ ተበደለ የሚል አስተዳደር ለሰፊው ሕዝብ ይስጥልን ነው እያሉ ያሉት ሽማግሌው፡፡ አገሩን አማን፣ ገበያውን ጥጋብ ያደርገው ዘንድ ምኞታቸውን ገልጸው መርሐ ግብሩን አሳርገዋል፡፡
በአጠቃላይ
“ካሲናው ጎጃም” የተሰኘውን የአስቻለው ፈጠነ ዘፈን መስማት አያሌ የፎክሎር መጽሐፍትን እንደ ማንበብ ይቆጠራል። ከአራቱ የፎክሎር ዘርፎች ውስጥ “ሐገረሰባዊ ትተውን ጥበባት” አንዱ ነው። ሐገረሰባዊ ትውን ጥበባት ባሕላዊ ዘፈኖችን፣ ዳንሶችኛ ጭፈራዎች፣ብሎም ድራማዎችን ይይዛል። ሐገረሰባዊ ልማዶች የተሰኘው ሌላው የፎክሎር ዘርፍ ደግሞ አንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ከባሕል፣እምነት እና ዕሳቤ ጋር በተያያዘ የቡድኖች የአንድ ወቅት ክንውን ነው። ሁለቱም የፎክሎር ዘርፎች “በካሲናው ጎጃም” ውስጥ በጉልህ ይታያሉ።
አስቻለው ፈጠነ በዋናነት ሁለት የዘፈን ( የዜማ) ስልቶችን ተጠቅሟል፣ “መላዬ ነይ መላ እና አሸበል ገዳዮ”። ሁለቱም የዘፈን ስልቶች ላይ አውጭ እና ተቀባይ ጉልህ ተሳትፎ አለው፣ ዜማ አውጭው ግጥሞችን እየሰደረ ሲዘፍን ተቀባዮች ( ታዳሚዎች) ይቀበላሉ። ከአንደኛው የዘፍን ስልት ወደ ሌላው የዘፈን ስልት የተሻገረበት አካኼድ የዘፈኑን ለዛ አላጠፋውም። የጥንቱ የባሕል ሙዚቃ ማድመቂያ የኾነው የአታሞ ምት ልዩ ውበት አለው።
የዘፈኑ ቅንብር እና ሚክሲንግ የተዋጣለት ነው። ግጥሞቹ ምታቸውን የጠበቁ፣ምጣኔያቸው የተስተካከለ፣ ቁጥብ እና የተዋዛ ዜማ ያዘሉ ናቸው፡፡ የአልባሳት ምርጫው የጎጃምን ባሕል ገላጭ ነው፡፡ እናቶች ራሳቸውን በሻሽ ሸብ አድርገዋል፣ ወገባቸው ላይ ወፍራም መቀነት አደግድገዋል፡፡ ሙሉ ሽንሽን እና እንክርት የተሰኙ የባሕል አልባሳት ቀረጻውን አድምቀውታል፡፡ ድሪ እና ጠልሰም የእናቶችን አንገት አስውቦታል፡፡ ወንዶች በውብ የጎጃም ጋቢ ተውበዋል፣ሻሽ የጠመጠሙ አሉ፡፡ ሞሰብ፣ ቆለምሸሽ፣ዋንጫ፣ወስከንባ፣ዋርማ፣ አታሞ፣ ድስት እና ሌሎችም ባሕላዊ ቁሶች ምስሉን የበለጠ ውብ አድርገውታል፡፡
ባሻዬ:- ድለቃው ላይ ሲገማሸሩ የነበሩት የዲማ እና አካባቢ ጎጃሜዎች ናቸው። ስሙት እና አትርፉ!!