>

አዲስ አበቤ ባርነትን የመረጠ ይመስላል (ከይኄይስ እውነቱ)

አዲስ አበቤ ባርነትን የመረጠ ይመስላል

ከይኄይስ እውነቱ

ኦነጋዊው የኦሕዴድ አገዛዝ አጥፍቶ ለመጥፋት አንድ ሐሙስ የቀረው ቢሆንም፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን መዲና ከጥቅም ውጭ በማድረግ ነዋሪውን ባይተዋርና ተንበርካኪ ማድረግ፣ ጐሣን መሠረት አድረርጎ በጅምላ ከማፈናቀሉና ተሳዳጅ ከማድረጉ በተጨማሪ ኅብረትና አንድነት አጥቶ ሁሉም በተናጥል እየደረሰበት ያለውንና የሚደርስበትን ግፍና መከራ ለመቀበል ዝግጁ ያደረገው ይመስላል፡፡ ከጅምሩ ከሕግና ሥርዓት የተፋታው የወረበሎቹ አገዛዝ ዐዲስ አበባን ለአጥፊ ዓላማው እንደሚመች አድርጎ የተቆጣጠረና ነዋሪውም እምቢኝ አሻፈረኝ በማለት ሊያደርግ የሚገባውን ተቃውሞ ባለማድረጉ አሁን ላይ ፈዝዞና ደንግዞ ቀሪ ጥፋቶችን ለመመከት የዘገየ የሚመስልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በመሆኑም በቁም የሞተበትን ሕይወት ዘንግቶ መሣሪያ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ፣ በአገዛዝ ስም አገርና ሕዝብን እያጠፉ ያሉ ሽፍቶችና አሸባሪዎች በጠራራ ፀሐይ የሚፈጽሙትን ወንጀል አሜን ብሎ እየተቀበለ ሙልጩን እስኪቀርና ህልውናው እስኪያከትም በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

ነዋሪው እየተጋፈጠ ያለው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ፣ መላው አገሪቱ በጦርነትና በሰላም እጦት እየታመሰች እያለ፣ በሚሊዮን የሚቈጠሩ ወገኖቻችን አገዛዙ በፈጠረው ምስቅልቅል ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የረሃብና በሽታ ሰለባ ሆነው እያሉ፣ አምራቹ ገበሬ ማምረት የማይችልበትና ተመጽዋች እንዲሆን በተገደደበት ሁናቴ፣ ሦስት አራተኛ የሚሆነው የከተማው ነዋሪ ሥራ አጥ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬን ቀምሶ ነገ ተነገወዲያ የሚላስ የሚቀመስ የሌለው በጠኔና በረሃብ የሚሰቃይ ሆኖ ሳለ፣ የመንግሥት ሥራ ብሎ በደመ ነፍስ የሚንከላወሰው ጥቂቱ የኅብረተሰብ ክፍልም ደመወዙ የቆመበትና አገዛዙም ሊከፍለው የማይችልበት ደረጃ ላይ መሆኑን እያወቀ፣ ቤትና ንብረቱን እያጣና በቀጣይም እንደሚያጣ እያወቀ፣ መንግሥት ያለ ይመስል ራሱን እያታለለ ስለ ልጆቹ ትምህርት÷ ስለ ዕለት አስቤዛው÷ ስለ አገልግሎት ክፍያ፣ ስለ ንግድ፣ ስለ ግብርና አገዛዙ ስለሚጭንበት ሌሎች ሕገ ወጥ ግዴታዎችና ‹ኑሮው› መጠመዱ የደረስንበትን ውርደትና ዝቅጠት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ አልሞትኹም ብዬ አልዋሽም አለ ‹የአርሙኝ› መጽሐፍ ገጸ ባሕርይው አቶ ተማቹ፡፡ 

ኅብረተሰብን በጥቅሉ መውቀስ ተገቢ ባይመስልም ባዲስ አበባችን በተለይ የምናስተውለው የአብዛኛው ነዋሪ አመለካከትና ጠባይ – የጐሠኞቹ አገዛዝ ያሳደረበት ተጽእኖ እንዳለ ሆኖ – በመሠረታዊ መልኩ በእጅጉ የተበላሸ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ጥቂት የማይባለው ለሆዱ ያደረ÷ አድርባይነትን ገንዘቡ ያደረገና ዘላቂውን የአገርና የሕዝብ ጥቅም ለጊዜያዊ ፍላጎቱ ያስገዛ÷ ዋስትና ለሌለው የዕለት ፍርፋሪ ባርነትን የመረጠ መሆኑ የየዕለት ትዝብታችን ነው፡፡ ለአብነት ያህል አገዛዙ ግልጽ በሆነ ዝርፊያ በዘዋሪ ደብዳቤ አማካይነት ኅብረተሰቡ ላይ ከጫነው የቤት ግብር ጋር ተያይዞ ባለፉት ሁለት ወራት ባዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ የምናየው ጠባይ እጅግ አሳፋሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በቅድሚያ የግብሩ ማሻሻያ ኅብረተሰቡ አልተሳተፈበትም፤ 2ኛ/ ግብሩ በዓዋጅ ወይም በደንብ ወጥቶ ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው አልተደረገም፤ 3ኛ/ የግብሩ ክፍያ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሆነ ሳይታወቅ ቅጣት በሚል ዘረፋ ሲፈጽሙ ከፋዩም አሜን ብሎ መቀበሉ፤ 4ኛ/ አብዛኛው ነዋሪ አገዛዙ ቤት ንብረቴን ይወስድብኛል ብሎ ሕገ ወጡን ግብር ለመክፈል የሚያደርገው መሽቀዳደም ሳያንስ የአገልግሎት ተብሎ በዝርፊያ መልክ የሚጫንበትን ክፍያ መክፈሉ (በዚህ ረገድ ለፋይል ማውጫ ተብሎ – የግብር ከፋዮች ማኅደር ከመደርደሪያ ላይ አውጥቶ ለማስተናገድ እና ለምሕንድስና አገልግሎት ተብሎ የሚፈጸመው ክፍያ ለማመን የሚከብድ የዝርፊያው አንዱ መገለጫ ነው)፤ 5ኛ/ ከሁሉ የሚገርመው ግን ነዋሪው በሙሉ ግብሩን ተቃውሞ አልከፍልም ማለት ሲገባው፣ ጥቂቶች ቢያጉረመርሙም አብዛኛው ለተቃውሞው አለመተባበሩ ለመብት የምንሰጠውን ግምት ከማሳየቱም በላይ ምን ያህል ከዕውቀትና ሥልጣኔ የተራቆትን መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ 

አንዳንዱ ዛሬ ‹ነግዶም› ይሁን ዘርፎ ወይም ውጭ ከሚኖር ዘመዱ ባገኘው ርጥባን መክፈል ቢችልም ይህ ወንጀለኛ አገዛዝ ነገ የበለጠ ቀንበር ጭኖበት ባዶውን እንደሚያስቀረው አለመረዳቱ ይገርመኛል፡፡ አገዛዙ ላለፉት 5 ዓመታት ዕለት ዕለት እያደረሰ ያለውን አገራዊ ጥፋት እያየ ዛሬ ያለው የመሰለው ሰው ነገ መናጢ ደሀ እንደሚሆን አለማስተዋሉ የሕማም ምልክት ነው፡፡ በተለይም በልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ረገድ በወላጆች ዘንድ የሚታየው የከረመ ነውረኛ ጠባይ የኅብረተሰባችንን ብሉሽነት በእጅጉ ጎልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ጥቂቶች አገዛዙ የሚጭንብንን ክፍያ መክፈል የለብንም፡፡ ዐቅማችንም አይፈቅድም፡፡ የግል ትምህርት ቤቶችም ባመዛኙ የንግድ ተቋማት በመሆናቸውና ትምህርቱም ጥራት የሌለው በመሆኑ ለጥቂት ጊዜም ተቸግረን ቢሆን (የልጆች ትምህርትን እስከማቆም ደርሰን) የተሻለ ሥርዓት እንዲመጣ አገዛዙን መታገል ይኖርብናል ሲሉ፣ አሁንም ከወረዳ ጀምሮ በየዕርከኑ ያሉ የአገዛዙ ኃላፊዎችና ካድሬዎች በዝርፊያ የሚያገኙት ገንዘብ እንኳን ለልጆቻቸው ት/ቤት ለውስኪም የሚያጠፉት በመሆኑ መክፈል የማይችሉትን አትበጥብጡን በማለት ሲዘልፉ፤ በሌላ በኩል ዳያስፖራ የሚባለው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዶላር በመላክ የዚሁ ተልካሻ ድርጊት ተባባሪ እየሆነ ነው፡፡ እዚህ ላይ ውጭ የሚገኙ ወገኖቻችን ቤተሰባቸውን አይርዱ እያልሁ አይደለም፡፡ አገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁናቴ ሁሉም ለጊዜው ተቸግሮም ቢሆን ይህን ፋሺስታዊ አገዛዝ ለማስወገድ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ለማሳሰብና የዕለት ጉርስ የሌላቸው ወገኖችንም ሕይወት ማሰብ ተገቢ እንደሆነ ለማመልከት እንጂ፡፡ እስከ መቼ ነው ዛሬ ቀምሶ ነገ የሌለው የኅብረተሰባችን ክፍል በሚያደርገው ተጋድሎ ነፃ ለመውጣት የምናስበው? ይልቁንም ለዓመትም ሆነ ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የሚያግደረድረው ጥሪት ያለውና በውጭ ወገኑ የሚረዳው ዜጋ በመጠኑ በመኖር ለትግሉ የበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ የለበትም?

አገር መንግሥት በሌለበት ስለ ዕለት ኑሮአችን የምንጨነቅበት ጊዜ ነው? ጎበዝ ኧረ እናስተውል! ይህ ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ ባሠማራቸው ሽብርተኞች አማካይነት እገሌ ከእገሌ ሳይል የእያንዳንዱን ቤት ንብረትና እና በባንክ አለኝ የሚል ጥሪቱን እንደሚዘርፈው ጥርጥር የለም፡፡ አሁንም እያደረጉት ነው፡፡ ሁሉም እንቅስቃሴ የሚቆምበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም፡፡ ጨርሶ ከመዘግየታችንና ተያይዘን ከመውደቃችን በፊት ስግብግብነታችንና ቅጥ ያጣ ራስ ወዳድነታችንና እንዲሁም ቦቅቧቃነታችንን አስወግደን በኅብረት ድምፃችንን ለማሰማት ጊዜው በእጅጉ ዘግይቷል ከሚባል በቀር አሁን አይደለም ወይ?

ድኅረ መልእክት

ይህ አጭር መልእክት ከዚህ ቀደም ደጋግሜ ያሳሰብኹት ዐቢይ አገራዊ ጉዳይ ቢሆንም በየመጣጥፌ ማስታወስ ሰላለብኝ ያቀረብሁት ነው፡፡

መልእክቴ ለዐምሐራ ሕዝባዊ ግንባር፣ ለሕዝባዊው ኃይልና ባጠቃላይ የህልውና ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው የዐምሐራ ሕዝብ ነው፡፡ ለህልውና ትግሉም ሆነ መዳረሻችን ለሆነው የኢትዮጵያ አንድነት ቀዳሚ ጠላቶቻችን የብአዴን አመራሮችና ተላላኪዎቻቸው መሆኑን እያወቅን እነሱን ከዐምሐራ ምድር ለማስወገድ የተቸገርንበት ምክንያት አሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ ነው፡፡ ዐዲስ አበባ ለሚልከሰከሱት ኃላፊነቱ የዐዲስ አበባ ሕዝብ ሲሆን፤ በዐራቱ ክ/ሀገራት (በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋ እና በወሎ) ደግሞ ኃላፊነቱ የየአካባቢው ነዋሪና ሕዝባዊ ኃይል መሆኑን ሳንዘነጋ፣ እነዚህን ከሀዲዎችና ከሰውነት የዘቀጡ ነውረኞች ማስጠንቀቂያ መስጠቱ አብቅቶ፣ ጎጠኝነትና ዝምድና ከሕዝብ ህልውናና ከአገር ደኅንነት እንደማይበልጥ ተረድተን አስተማሪ የሚሆን ርምጃ ለመውሰድ ጊዜው በእጅጉ ዘግይቷል የሚባል ካልሆነ በቀር አሁን ነው፡፡ እንደ ፖለቲካ ማኅበራት መግለጫ በማውጣት ጊዜአችንን ማባከኑን ትተን ለጠቅላላው ጥቅም ስንል ጥብዐት (ለበጎ መጨከን) የተሞላበት ርምጅ መውሰድ ይኖርብናል፡፡

Filed in: Amharic