>

መንግስት እንደ አህያ ባልም'፣ እንደ ጅብም ... ሕዝብ በመንግስት ላይ ለምን እምነት አጣ? ( ያሬድ ሀይለማርያም)

መንግስት እንደ አህያ ባልም’፣ እንደ ጅብም …

ሕዝብ በመንግስት ላይ ለምን እምነት አጣ?

ያሬድ ሀይለማርያም

‘If people lose fath in their government the result is the same whether or not the loss of confidence is justified “ John Kennedy

የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም’ እንደሚባለው ብልጽግና መር የሆነው የአብይ አስተዳደርም ከከፋ እልቂት፣ ከጅምላ በማንነት ላይ ያተኮረ ጭፍጨፋ፣ ከመፈናቀል፣ ከርሃብ፣ ከስደት፣ ከእርስ በርስ ግጭት፣ ከከፋ የኑሮ ውድነት፣ ከዝርፊያ፣ የሻርክ ጥርስ ካበቀሉ ሙረኞች፣ ከመጥፎ የመንግስት አስተዳደር፣ ከተበላሸ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ከትራንስፖርት እጥረት፣ ከነዳጅ መወደድና መጥፋት፣ በየቀኑ ከሚንር የቤት ኪራይ፣ ከውሃና ኤሌክትሪክ መቋረጥ፣ ወዘተ ከመሰሉ ሕዝብ አማራሪ ጉዳዬች፣ ታፍኖ ከመሰወርና የመንደር ታጣቂዎች መፈንጫ ከመሆን ሕዝብን ለመታደግ የማይችልበት ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን በርካታ ማሳያዎችን መዘርዘር ይቻላል። ከአህያ ባል ከሚያመሳስለው መገለጫዎችም አልፍ በአንዳንድ ሁኔታዎች የጅቡንም ገጸ ባህሪ ተላብሶ ይታያል። ለዚህም በመንግስት የሚፈጸሙ አስከፊ የመብት ጥሰቶችን ማንሳት ይቻላል።

አዎ፤ የአብይ አስተዳደር በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ወደ ሕዝብ የሚወነጨፉ አደጋዎችን መከላከል ካቃተው ውሎ ያደረ ከመሆኑም በላይ አብዛኛዎቹ አደጋዎች ደግሞ የሚመነጩት ከራሱ ከመንግስት ጥናት የጎደላቸው ፖሊሲዎች፣ ማስተዋል የራቃቸው ግልብ እርምጃዎች፣ ጥንቃቄና ሰብአዊነት ከጎደላቸው ግብረ ምላሾች የመነጩ መሆናቸው public confidence ወይም የሕዝብ መተማመኛ እንዲያጣ ያደረገው ይመስለኛል።

እጅግ በለየለት የአገዛዝ ሥርዓትም ውስጥ ቢሆን እንኳ ሕዝብ በተወሰኑ ጉዳዬች ዙሪያ መንግስት ላይ የሚያሳድረው መተማመን አለ። ለምሳሌ ደርግ የለየለት አንባገነናዊ አስተዳደር ቢሆንም በአገር ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ጸጥታን በማስከበር፣ ሙስናን በመከላከልና ድሆችን ያማከለ የኑሮ ዋስትናን በማረጋገጥ እረገድ በሕዝብ ዘንድ መተማመንን የፈጠረ ነበር። ከቀበሌ ራሸን አንስቶ የዳቦ ግራምን መቆጣጠር ከብዙ ማሳያዎች ይጠቀሳሉ። 

በወያኔ የአገዛዝ ዘመንም ምንም እንኳን ብሔርን ያማከለ አንባገነናዊና አፋኝ ሥርዓት ቢሆንም እንዲሁ በተወሰኑ ጉዳዬች ላይ በመንግስትና በሕዝብ መካከል መተማመን ነበር። ቢያንስ ያለምንም ስጋት አንድ ሰው ከአንድ ያገሪቱ ጫፍ እስከ ሌላ ጫፍ በነጻነት መጓዝና መንቀሳቀስ ይችል ነበር። ጠንካራ የጸጥታ መዋቅር ስለነበር አንጻራዊ የሆነ ሰላም ነበር። እንዳሁኑ ዘጠኝ ሳይሆን አንድ ጉልበተኛ ብቻ ነበር፤ እሱም መንግስት ነው። ሌሎች ነፍጥ አንጋቢዎች ኤርትራ፣ ሱዳንና ኬኒያ ተቀምጠው ይፎክሩ ነበር እንጂ አንዲት ቀበሌ እንኳ ሳይቆጣጠሩ ነው የተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ የዛሬ አምስት አመት ከስደት የታደጋቸው።

በተቃራኒው የአብይ ብልጽግና መር የሆነውን የአገዛዝ ሥርዓት የተመለከትን እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ የእምነት ቃብድ የሰጠው መንግስት ነው። ጠቅላዩ ወደ ስልጣን እንደመጡ ያለፈ ሥራቸውን እንኳ ሳያይ ንግግራቸውን ብቻ በመስማት ‘እንዳረጉ ያርጉን፣ ምሩን፣ አሻግሩን፣ ወዘተ…’ ብሎ ተስፋ የጣለባቸውና ፎቷቸውን ደረቱ ላይ ለጥፎ በአደባባይ የደገፋቸው። በዚህ ረገድ ብቸኛ መሪ ይመስሉኛል። ጠቅላዩ የተሰጣቸውን የሕዝብ መተማመኛ ቃብድ ማንጠባጠብ የጀመሩት ድጋፍ የሰጣቸው ሕዝብ ያጠለቀውን ምስላቸው ያለበት ቲሸርት ሳያወልቅ ነበር። ከቡራዩ እልቂት ጀምሮ በየቀኑ የታዩት ክስተቶች የሥልጣን መሠረት በሆናቸው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንኳ ወዲያው ነው ምስላቸው መቃጠል፣ መጽሐፋቸውም ተቀዶ በየአስፋልቱ መጣል ጀመረው። 

ዛሬ ላይ የአብይ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ የሕዝብ መተማመኛ ወይም የቅቡልነት ማጣት አደጋ ውስጥ የወደቀ ይመስለኛል። የዚህ ደግም ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም የተወሰኑትን ለመጠቆም ያህል፤

– ሕዝብ በተለያዩ አጥጋቢ ምክንያቶች በመንግስት ተሿሚ ባለስልጣናት ላይ እምነት ማጣት (Untrustworthy politicians)፣ የአቅም ማጣትና ሙስና

– በመንግስት አቋምና ብቃት ላይ እምነት ማጣት (Pervasive distrust of government)፣ የፖሊሲዎች መጣረስ፣ ወጥ አቋም ያለመያዝ፣ ቁርጠምነት አለመኖር፣ ወዘተ…

– የመንግስት ተሿሚዎች ቅቡልነት፣ እውነተኝነት፣ ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ መግባት (Questioned acceptance of public officials)፣ በችሎታ ያለመሰየም፣ ከንግግር መግደፍ፣ በአቋም ያለመጽናት፣ ሕዝብን መናቅ፣ ጥላቻን መስበክ፣ የሃሰት መግለጫ፣ ወዘተ…

– ሌሎች በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

የአንድ መንግስት በሕዝብ ዘንድ ያለው ቅቡልነት የሚረጋገጠው በሚቀርጻቸው ፖሊሲዎች፣ በሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ ፍልስፍና እና በአተገባበሩ የሕዝብን ቀልብ የሳበና መተማመንን የገነባ ሲሆን ነው። መንግስት ለእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ሲጨነቅ፣ ሲጠነቀቅና መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን ሲያከብር እና ሲያስከብር ብቻ ነው የሕዝብ መተማመኛን መፍጠር የሚችለው። በዚህ እረገድ የአብይ አስተዳደር አልተሳካለትም ብቻ ሳይሆን ከአፋፍ ላይ ተፈጥፍጦ በአፍንጫው የተደፋ ይመስላል።

ሕዝብ በጠቅላዩም ሆነ በሌሎቹ አመራሮች ላይ እምነት ያጣ ለመሆኑ ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ ጎዳና ብቅ ብሎ አላፊ አግዳሚውን እየጠየቁ ጥናት ማድረግ ይቻላል። በቅርቡ የተደረገ አንድ በቪድዬ የተደገፈ social study አይቻለሁ። ተጠያቂዎቹ ለጠቅላዩ ደረጃ ስጧቸው ሲባሉ ከ10 ከዜሮ በታች ቁጥር እየጠሩ መተማመን ማጣታቸውን ይገልጹ ነበር።

አገር እየመሩ የሕዝብ መተማመኛ legitimacy or public confidence ማጣት ወደ ከፋ ደረጃ ሲደርስ የሚወልዳቸው ሌሎች አደገኛ ነገሮች አሉ። መንግስትንና ባለስልጣናትን የስጋት ምንጭ አድርጎ መውሰድና መፍራት (fear of officialdom)፣ አመጽና ሁከትን እንደ አማራጭ መውሰድ (Acceptance of violence)፣ የሕዝብ መተማመኛ መሸርሸር (erosion of public trust)፣ በመንግስት ተቋማት ላይ ጥርጣሬን ማሳደር (Suspension of bureaucracy)፣ ለመንግስት አካላት ትብብር መንፈግ (lack of cooperation with officials) እና ሌሎች አደጋዎችን ይጋብዛል።

በባለሥልጣናትና የመንግስት ተቋማት ደጋግመው የሚነገሩ ውሸቶች፣ በሴቶች ለሚፈጸሙ ጽዎታዊ ጥቃቶች መንግሥት ዳተኛ ሆኖ መታየት፣ የፖለቲካ ሽረባዎች (Political scandal)፣ የኢኮኖሚ መዋዠቅና ግሽፈት፣ የመረጃዎች ፍሰት ላይ የሚደረጉ ገደቦች፣ ተቋማዊ ቅጥፈት (Institutional lying)፣ በመንግስት ተቋማቶች መካከል የሚታይ አለመናበብና ሲከፋም መጣረስ፣ የአመራር ብቃት ማነስ (Governmental incompetence)፣ የተካዱ በመንግስት የተገቡ ቃሎች (Broken government promises)፣ በሕግ የተጣሉ ግዴታዎችን ወደጎን ችላ ብሎ መተውና ተጠያቂነት መጥፋት Avoidance of legal obligations by politicians and absence of accountability) እና ሌሎች ተደራራቢ የመንግስት ስህተቶች ሕዝቡ እንኳን በመንግስት ላይ አይደለም ተደግፈውት በቆሙ እንደ ኢዜማና አብን በመሰሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ እምነት ያጣ ይመስላል።

ይሀህ አይነቱ አደጋ በጊዜ መቀልበስ የሚችልበት ደረጃ አለ። ያንን ደረጃ ሲያልፍ ግን የአገዛዝ ሥርዓቱ ሰማይ ቢቧጥጥ፣ ምድርን ቢያካልል የሕዝብ አመኔታን መልሶ ሊያገኝ የሚችልበት እድል አይኖርም። ያኔ ተያይዞ ገደል ነው የሚሆነው።

በዛሬዋ ኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝብን ከብዙ አደጋዎች መታደግ ያልቻለበትና ለአንዳንዶቹ ችግሮችም ዋነኛ ተጠያቂ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ብዙዎች በአንድ ጀንበር ተገለው ቢያድሩ፣ ሃምሳዎች ከመንገድ ታፍነው ቢወሰዱ፣ ሕጻናት ታርደው ሲጣሉ፣ መቶ ሺዎች ከቄያቸው ሲፈናቀሉ፣ የድሆች ቤት በጅምላ ሲፈርስ፣ ሚሊዬኖች ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ሲወድቁ ፈጣን እና አጥጋቢ ምላሽ ያልሰጠ፣ ወደለየለት ዝርፊያ የተቀየረውን ሙስናም መቆጣጠር ያቃተው መንግስት ወደብ አስመልሳለሁ የሚል ቅዠት የመሰለ ፕሮፖጋንዳ ውስጥ ቢገባ፣ ቅንጡ ቤተመንግስት ቢገነባ፣ መዝናኛ ሥፍራዎችን ቢያስውብ፣ የሹሞችን ቢሮ ቢያዘምን  ያጣውን  የሕዝብ መተማመ ድጋፍ ማግኘት የሚችል አይመስለኝም። 

ሕዝብና መንግስት በማይተማመኑበትና በማይደጋገፉበት አገር ሰላም አይኖርም፣ ብልጽግናውም ህልም ነው። ተማሪም ብዕሩን፣ ገበሬም ሞፈሩን ጥሎ ነፍጥ በያዘበት አገር አመጽና ሁካታ የዕለት ተዕለት ዜናዎች ይሆናሉ። የብልጽግና አመራሮች ለሕዝብ ስሜት፣ ጉዳት፣ በደልና እሮሮ ግድ ያላቸው አይመስሉም። ግፍ በበረታበት አገር መንግስት እንደማይጸና የተረዱት አይመስለኝም ወይም እረስተውታል።

ለማንኛውም እንደ ሀገር አደጋ ውስጥ መሆናችንን የሚያሳይ ትልቅ ክፍተት መሆኑን ተረድቶ በጊዜ የጋራ ትብብር የታከለበት እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ በሕዝብና በመንግስት መካከል የተፈጠረው ያለመተማመን ገደል ሁላችንንም ዋጋ ያስከፍለናል። ይህን አደጋ በሚመጥን ደረጃ የሚደረግ አገራዊ ምክክር የግድ ይላል።

 

መልካም ሰንበት!!

Filed in: Amharic