አቤ ጉበኛ አምባዬ ሲታወስ
ጌታ በለጠ ( ደብረ ማርቆስ፣ ከውሰታ ወንዝ ዳር)
አብዮተኛው ጸሐፊ አቤ ጉበኛ አምባዬ ልክ በዛሬው ቀን (ሰኔ 25 ቀን 1925 ዓ/ም) አቸፈር ውስጥ ኮረንች አቦ ተወለደ፡፡ ገና በልጅነቱ እናቱን (ወይዘሮ ይጋርዱ በላይን) ሞት የሚባል ክፉ ጥላ ቀማው፣ በአባቱ በአቶ ጉበኛ አምባዬ እቅፍ ውስጥ አደገ፡፡ ዕድሜው ለፊደል ቆጠራ ሲበቃ የቤተክህነት ትምህርት ለመሸመት ከእነ “የንታን” ጓሮ ተገኘ፡፡ የንታ የቤተክህነት ትምህርት የሚያስተምሩ የቀለም አባቶች የወል ሥም ነው። አቤ ፊደል አጥንቶ ቀለም ገባው። ፈጣን ነው። በመምህሮቹ ተወዳጅ ነው።
በቤተ ክህነት ትምህርት ቤት በቅኔ ዋዜማ ( ከቅኔ በፊት) የሚሰጡ ትምህርቶችን አጠናቅቆ ቅኔ ለመማር ይስማላ ጊዮርጊስ ከሚገኙት ከመሪጌታ ገሠሠ ቅኔ ቤት ተመዘገበ፡፡ በቅኔ ችሎታው አግራሞት ላይ የወደቁት መሪጌታ ገሠሠ “ይኼ አቤ ጉበኛ ሳይኾን አቤ ጉደኛ ነው” ማለታቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
አቤ ጉበኛ በቤተ ክህነት ያገኘውን እውቀት በዘመናዊ ትምህርት ማጎልበት ፈለገ። ፍላጎቱን እውን ለማድረግ ወደ ዳንግላ ከተማ በመኼድ ከቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ ተምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ተማረ፡፡ በ1946 ዓ/ም ከዳንግላ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ፡፡ አዲስ አበባ ሃና ማርያም ቤተክርስቲያን በመሪጌታነት ተቀጠረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የምርግትና ሥራውን ትቶ ጎጃም ጀምሮ የነበረውን ትምህርት ጀመረ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ ውስጥ አጠናቀቀ፡፡ በትርፍ ጊዜው አንድ ትንሽ ሱቅ ከፍቶ ይነግድ ነበር፡፡
አቤ የሥነ ጽሑፍ ጥበበ አፍ አውጥታ የጠራችው ገና በማለዳ ነው። ግጥም እየጻፈ ያስቀምጥ ነበር። የአቤ ሥራዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከህትመት ጋር የተገናኙት ሚያዚያ 12 ቀን 1949 ዓ/ም ነው፡፡ በዚኽ ወቅት አቤ ጉበኛ አንድ ግጥም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አወጣ፡፡ ሕዝብ ወደደለት፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1933 ዓ/ም ንጉሡ ከስደት እንደተመለሱ ነው ነው መታተም የጀመረችው፡፡
በ1949 ዓ/ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይጽፋቸው ከነበሩ ግጥሞች መካከል የሚከተሉት ስንኞች ይገኙበታል።
የበቀለው አረግ በጫካና በዱር፣
ስበው ካላመጡት አይሆንም ለማገር።
ወገኑን ሰብስቦ እንጀራ ሲያበላ፣
ያጠግበው ነበረ ጠላቱን በጠላ።
አንድ ኹነን ካላሰብን ለጠላቶቻችን፣
አይገባም ተስቦ ክፉ በሽታችን።
በውድ ከምንፈልግ የባሕር ቅመም፣
የእኛን ጥቁር አዝሙድ እናልማት በጣም።
አቤ ጉበኛ ግንቦት 10 ቀን 1949 ዓ/ም የጃንሆይ ኃይለሥላሴ ልጅ (ልዑል መኮነን) በመኪና አደጋ መሞታቸውን አስመልክቶ አንድ ግጥም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አስነብቧል፡፡ ግጥሙ የሚከተለው ነበር፡፡
ያገርህን ትምህርት ጠንቅቀህ ስታውቅ፣
የውጪ አገር ትምህርት ጠንቅቀህ ስታውቅ፣
መምጣቱን ሳታውቀው ሳትጠነቀቅ፣
በመጣው ፈተና በድንገት ብትወድቅ፣
ወገንህ ይታያል በጣም ሲደነቅ፡፡
ግጥሙ ብዙ መልዕክት አዝሏል፡፡ “መምጣቱን ሳታውቀው ሳትጠነቀቅ” የሚለው ሞት የንስሃ ጊዜ የማይሰጥ መኾኑን፣ ምንም እንኳ በዓለማዊ ሕይወታችን ጎበዞች ብንኾንም ሞት መምጫ የማናውቅ መኾኑን ያሳያል፡፡ በመጣው ፈተና በድንገት ብትወድቅ- ወገንህ ይታያል በጣም ሲደነቅ” የሚለው የልዑሉን ሚስጥራዊ አሟሟት ነው፡፡ ልዑል መኮነን በመኪና አደጋ ሞተ ይባል እንጅ ከአሟሟቱ ጀርባ የሚወራ የጥርጣሬ ወሬ ስላለ ያንን ለመጠቆም ነው፡፡
በ1949 ዓ/ም መገባደጃ ላይ አንድ የግጥም ስብስብ አሳተመ፣ ርዕሱን “ ከመቅሰፍት ሠራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት” አለው፡፡ መጽሐፉ በተባይ የተወከሉ የመንግሥት ሹማምንት በድሃው ሕዝብ ላይ ያደርሱ የነበረውን በደል የሚኮንን ነበር፡፡ አቤ ለድሃ መጮኽ አይሰለቸውም፣ መንግሥት ሚዛኑን በሳተ ቁጥር የአቤ ስል ብዕር ቁንጥጫቸውን አይተውም። በደልን አይወድም፣ ፍትኀ አልባነትን አጥብቆ ያወግዛል።
እኔ ጌታው ቅማል ከእድፍ ተወልጄ፣
ሕዝብን እፈጃለሁ እንደ በግ አርጄ።
ስደፋው የምኖር የኔ እኮ ነው ጀብዱ፣
ስረግጠው ዝም የሚል ሴቱም ኾነ ወንዱ።
በተባይ ( ቅማል) የተመሰሉት ባለጌ ባለሥልጣናት ናቸው። ግብር አላግባብ የሚሰበስቡ፣ ድሃውን የሚበድሉ፣ አስራት የሚጥሉ፣ ግፍ መሥራት የማይሰለቻቸው ሹመኞችን ነው አቤ የሚኮንነው። “ስረግጠው ዝም የሚል” በሚለው ሐረግ ውስጥ የመብት ተጠያቂነት መንፈስ መላላትን ያሳያል። አቤ “ስትገፉ ዝም አትበሉ፣ በደልን አውግዙ፣ ስለነጻነት ተጋደሉ፣ መብታችሁን ጠይቁ እንጅ አትለምኑ” የሚል ዘመን የሚራመድ መልዕክት ነው ማጋባት የፈለገው።
አቤ ጉበኛ በነበረው የሥነ ጽሑፍ እውቀት በ1951 ዓ/ም በማስታወቂያ ሚኒስትር ስር በጋዜጠኛነት ተቀጠረ፡፡ 1953 ዓ/ም በእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ተሞክሮ የከሸፈው መፈንቅ መንግስት ከመደረጉ ቀደም ብሎ “የሮም አወዳደቅ” የሚል የተውኔት ጽሑፍ አሳትሞ ነበር፡፡ ጽሑፉ የኢትዮጵያን መንግስት እጣ- ፈንታ የተነበየ በመኾኑ ደራሲውን “ትንቢት ተናጋሪው ደራሲ”አሰኝቶታል፡፡ “የሮም አወዳደቅ” የሚለው መጽሐፍ አቤን መዘዝ አመጣበት፡፡በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከሰሰ፣ የሚወለደውን የጋዜጠኛነት ሥራ አስለቀቁት፡፡ በኋላ ነገሮች ተረጋግተው መልክ ሲይዙ በጤና ጥበቃ ውስጥ ተቀጠረ፡፡
በወርኀ መስከረም 1955 ዓ/ም አቤ ጉበኛ “የአመጽ ኑዛዜ” የተሰኘ አንድ ልብ ወለድ ጻፈ፡፡የአመጽ ኑዛዜ መጽሐፍ ፖለቲካዊ ይዘት ቢኖረውም በድሃ እና በባለጸጐች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ያትታል፡፡ “ባለጸጋ ድሃውን አይዘንጋ” የሚል ይዘት ተላለፎበታል፡፡ በዚኹ ዓመት ( 1955 ዓ/ም) አቤ ጉበኛ “አልወለድም” የተሰኘውን ድንቅ መጽሐፍ ጻፈ፡፡ የፍትኅ፣ የእኩልነት፣ ሰው የመኾን፣ የሥርዓት ሚዛናዊነት ጥያቄዎች ተነሱ፡፡ አቤ በአልወለድም ታውቆበታል፣ ታስሮበታል። የአልወለድም ጭብጥ የአንድ ዘመን ክስተትን ብቻ አያሳይም። ዘመን ይሻገራል።
ደራሲ መስፍን ማሞ በአልወለድም መጽሐፍ ላይ በሰጡት አስተያየት ” በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የአልወለድም ጭብጥ እውነት ነበር። በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የኮሚኒስት አገዛዝ አልወለድም እውነት ነበር። በአቶ መለስ ዜናዊ አገዛዝ አልወለድም እውነት ነው” ይላሉ። እኔም እላለሁ ” አልወለድም ማለት ያለብን በዓብይ አህመድ አገዛዝ ነው።” አልወለድም በጃንሆይ ሹማምንት ዘንድ አልተወደደም ነበር። 800 ቅጅዎች እንደተሸጡ መጽሐፉ ተለቅሞ ተቃጠለ፡፡ አቤ ጉበኛ ጥርስ ተነከሰበት፡፡ ንጉሡ በቤተ መንግሥታቸው ጠሩት፡፡ ጃንሆይ አቤን አነጋግረው የተቃጠለውን የመጽሐፍ ዋጋ ሰጥተው ለወደፊቱ አፉን ይዘጋ ዘንድ ማስጠንቀቂያ ሰጡት፡፡
እልኸኛ አቤ መጽሐፉን በድብቅ ማሳተም ጀመረ፡፡ የካቲት 28 ቀን 1955 ዓ/ም የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ተከፈተበት፡፡ ክትትሉ ቀጠለ፡፡ ሞገደኛው አቤ ግን መጻፉን አላቆመም፡፡ በ1956 ዓ/ም የፍጡራን ኑሮ፣ መልክአ ሰይፈ ነበልባል፣ የአመጽ ኑዛዜ እና The Salvage Girl የተሰኙ መጽሐፍትን ለንባብ አበቃ፡፡
ዘመን በዘመን ሲተካ የአቤ ብዕሮች ጉልበታቸው እየጠነከረ ኼደ፡፡ በ1957 ዓ/ም የራሔል እንባ እና ከልታማዋ እህቴ የተባሉ ሥራዎችን እንካችሁ አለ፡፡ ከጽሑፍ ተጋድሎው በተጨማሪ አቤ ጉበኛ በ1957 ዓ/ም ለሚደረገው የእንደራሴነት ምርጫ ራሱን አዘጋጀ፡፡ የምረጡኘ ቅስቀሳ ወቅት ተይዞ የወር ቀለብ 50 የኢትዮጵያ ብር እየተከፈለው ኢሊባቡር፣ ጎሬ ውስጥ ታሰረ፡፡ ከአራት ወራት እስር በኋላ ከጎሬ ወደ ሞቻ አዛውረው አሰሩት፡፡ ከጎሬ ወደ ሞቻ የተዛወረበትን ምክንያት እንዲኽ ነው፡፡
ጎሬ እስር ቤት እያለ የኢሊባቡር አስተዳዳሪ ደጃዝማች ወርቁ እንቁሥላሴ ነበሩ፡፡ ደጃዝማች ወርቁ እንቁሥላሱ የደጃዝማች ጸሐዩእንቁሥላሱ ወንድም ናቸው፡፡ በአንድ ዕለት ደጃዝማች ወርቁ አቤ ጉበኛን “በብዕር ሥም መንግስታችንን የሚነቅፍ ጽሑፍ አውጥተኻል” ሲሉ አቤን ይጠይቁታል፡፡ አቤም “ይኼንን የወደቀ ሥርዓት ለመንቀፍ በብዕር ሥም መጻፍ አያስፈልገኝም፣ ይልቁንም አቤ ጉበኛ የተሰኘ ወርቅ ሥም አለኝ” ሲል መለሰ፡፡ ደጃዝማች ወርቁ “ አንተ ልጅ ጠግበኻል፣ ጥጋብኽን እናስታግስኻለን” ባሉት ጊዜ “ የእኔ የወር 50 ብር ካጠገበ፣ እርስዎ በሚከፈልዎ አንድ ሽህ ብር ላይ ጨምሬለወታለኹ” በማለቱ ከጎሬ ሞቻ ወደሚባል እጅግ ቀዝቀዛ ቦታ ሰደዱት፡፡ ደጃዝማች ወርቁ እንቁሥላሴን ደርግ ነው የገደላቸው፡፡
አቤ ጉበኛ ከእስር የተለቀቀው በመስከረም 1961 ዓ/ም ነው። ከእስር እንደተለቀቀ ብዕሩን አጠንክሮ ቀጠለ፡፡ ከ1961- 1965 ዓ/ም ድረስ አንድ ለናቱ፣ የሐሜት ሱሰኞች፣ መስኮት፣ ዕድል ነው በደል፣ የሕይወት ተርጓሚዎች፣ የረገፉ አበቦች፣ እሬትና ማር እና የደካሞች ወጥመድ የተሰኙ መጽሐፍትን አስነብቧል፡፡ አቤ በ1962 ዓ/ም ምስኮት ሲል ባሳተመው መጽሐፍ እናቱ በ17 ዓመታቸው መሞታቸውን ጠቆም አድርጓል። እንዲኽ ይላል።
እናቴ በድንገት ተነስተሽ ባይሽ፣
ማሚቱ ልልሽ ነው እማማ ልልሽ፣
አንቺ አስራ ሰባትን ሳትደርሽ ቀረሽ።
በ1965 ዓ/ም አቤ International Writing Revolution ስልጠና ለመውሰድ ወደ አገረ አሜሪካ ጉዞውን አደረገ፡፡ አሜሪካ እያለ አብዮቱ ፈነዳ፡፡ አቤም አገሩ ተመለሰ፡፡አቤ ጓደኞቹ ኢትዮጵያ መግባት እንደሌለበት መክረውት ነበር። አልሰማም። “ከሕዝቤ ጋር የመጣውን እቀበላለሁ” አለ። በመጀመሪያ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን የደርጎች መፈክር ወዶት ነበር። ደርጎች ያነገቡትን መፈክር አሽቀንጥረው ጥለው አይፈስስም ያሉትን ደም ማፍሰስ ጀመሩ።
የደርግ መንግሥት አካኼድ ያላማረው አቤ ጉበኛ (በ1968 ዓ/ም) “ፖለቲካና ፖለቲከኞች” የሚል ተውኔት በሐገር ፍቅር ቲአትር ቤት ለሰፊው ሕዝብ አቀረበ፡፡ መልዕክቱ ግልጽ ነበር፡፡ ፖለቲከኞች ሊመሩበት የሚገባውን መርኽ ነው የጠቆመው፡፡ አፈንጋጮች ፖለቲከኞችን ብብዕሩ ይቆነጥጣል፡፡ ደርጎች ጠሉት፡፡ እሱ ግን አልቦዘነም፣ የመንግሥት ጉድፎች አዲስ ዘመን ላይ ማስጣት ቀጥሏል፡፡
አቤ ብዕሮቹ ብርቱ ናቸው፡፡ አቤ ሐያሲም ነበር፡፡ “ጎብላንድ አጭበርባሪው ጦጣ” የሚለው የአቤ ጉበኛ ሥራ ሒስ ነው፡፡ ጎብላንድ የዝንጀሮ ዝርያ ነው፣ የሚታወቀው በማስመሰል ነው፡፡ ዝንጀሮ ሲያገኝ ዝንጀሮ፣ ጦጣ ሲያገኝ ጦጣ የመምሰል ልዩ ባሕርይ አለው፡፡ አቤ ጉበኛ የእነ ሰሎሞን ደሬሳ እና ዳኛቸው ወርቁን የወቅቱ የአጻጻፍ ዘይቤ ላይ ትችት ሰንዝሯል። የቃላት ስሪያን አጥብቆ ይቃወማል። የግዕዙን ቃላት ከአማርኛ ቃላት፣ የአማርኛውን ከእንግሊዝ ቀላቅሎ ማቅረብ በአቤ ዕይታ የቃላት ስሪያ ነው። በውብ ቃላት ተሽሞንሙኖ ጭብጥ አልባ ጽሑፍ ካየ “ከንቱ የቃላት ኳኳታ” ይላል አቤ።
አቤ “ዝናን የተራበ ዝነኛ አይኾንም” የሚል ዕሳቤ አለው። አስመሳይ እና ከንቱ ውዳሴ የሚፈልጉ ሰዎችን “ጎብላንድ” ይላቸዋል፣ አስመሳይ ማለቱ ነው። አቤ ጉበኛ አስመሳዮችም “በምላሳቸው የሚራመዱ ውርጋጦች” ብሎ ነው የሚጠራቸው። እውነቱን ነው። አሁንም ሐገሪቱን የማትወጣው አዙሪት ውስጥ የከተቷት በምላስ ተራማጅ ሸንጋዮች ናቸው።
“የደካሞች ወጥመድ” በሚለው መጽሐፉ ዘመነ መሳፍንትን ተችቷል። ” ጀግኖች በደካሞች እየተገደሉ እስከመቼ እንዝለቅ ይላል”?” አቤ ጉበኛ ” ዕድል ነው በደል” በሚለው ሥራው ማሕበራዊ ሒስ ላይ ተመስርቶ ኋላቀርነትን ሚዛናዊ አመክንዮ ይዞ አውግዟል። በዚኽ መጽሐፍ ሚስቱ ሞታ፣ ልጆቹን መመገብ የማይችል ግለሰብ “ትዝካር” ያወጣ ዘንድ በቄሶች ታዝዞ የደረሰበትን መከራ ያሳያል። ያልተገባ እና የተንዛዛ ድግሥ ማሕበረሰቡ ላይ እያደረሰ የነበረውን ጣጣ አሳይቷል። የሐይማኖት መሪዎች ሚና ምን መምሰል እንዳለበት መክሯል።
The Savage Girl ሲል በእንግሊዝ ቋንቋ በጻፈው ሥራው ነጻነት ጠያቂ ሴቶችን አሳይቶናል። ሴቶች በደልን ፈንቅለው አደባባይ ይወጡ ዘንድ አበክሮ ይመክራል። ተሟጋች፣ ሞገደኛ፣ ጠያቂ ሴቶችን እንዴት ማፍራት እንዳለብን መክሮናል። አቤ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ነበር። ከአውሮፓውያኑ ቅኝ ግዛት ማግስት የኮንጎ መሪ ስለነበረው ፓትሪንስ ሉቡምባ አሳዛኝ አሟሟት ” የፓትሪንስ ሌቡምባ አሟሟት” የሚል ድንቅ መጽሐፍ ጽፏል። በዚኽ ድርሰቱ አቤን ኢትዮጵያን ተሻግሮ ለአፍሪካ ሲያስብ እናገኘዋለን።
አቤ ስለ አብሮነት አቀንቅኗል፣ ስለ ሰላም ዘምሯል፡፡ “ሰዎች ሁሉ ከአራዊት ባሕርይ ተዛምዶ ያለውን ያለውን አካላቸውን ከመለኮት ተዛምዶ ባለው መንፈሳቸው ሥልጣን ስር ሲያውሉት፣ በጎ ምግባር ክፉ እና ትቢተኛ ፍላጎትን ድል ሲያደርግ ብቻ ነው ሰላማዊ ኑሮ የምንኖረው” ይላል፡፡ ስለ አጋርነት፣ ስለ ሰዎች አስፈላጊነት፣ አንዳችን ያለ አንዳችን ምንመ መኾናችንን አቤ እንዲኽ ይነግረናል፡፡ “ ከዘጠን ወራት በላይ በሰው ሆድ የቆየን፣ ከሦስት ዓመታት በላይ በሰው ጀርባና ክንድ የሰነበትን፣ ስንሞት በሰዎች እንባና ኀዘን ታጅበን ከመጨረሻው ቦታችን ያረፍን የሰው ባለዕዳዎች ነን፡፡”
አቤ ጉበኛ የመንግሥት በትር ያልሸበበው፣ በንዋይ ያልታለለ፣ የብርቱ መንፈስ ባለቤት፣ ብዕሩ ስለፍትኀ፣ ስለ እኩልነት ተናግረው የማይደክማቸው ሞገደኛ ጸሐፊ ነው፡፡ ገና ጥንት መወለድ ወንጀል አይደልም ሲል ሞግቷል፡፡ ለዚኽ ሃሳብ ማጠንከሪያ “ መወለድ ወንጀል አይደለም እንጅ ቢኾን እንኳን ወንጀለኞች ወደ ምድን ያመጡን አንጅ እኛ አይደለንም” ይላል፡፡ አቤ ዛሬ ኖሮ ቢኾን ለማለት አይታክተኝም። ለነገሩ አለ፣ ኀያው በኾነው መጽሐፉ ዘላለም ሥሙ ሲነሳ ይኖራል።
አቤ ጉበኛ ማታው ያሳዝናል፡፡ ከትላንት እስከ ዛሬ ጎበዞች በሰነፎች የሚገደሉባት ሃገር ኢትዮጵያ አቤ ጉበኛን አስገድላለች። አቤ ወደ ባሕርዳር ከተማ ገብቶ በንግድ ሥራ የተሰማራው በ1969 ዓ/ም ነበር። በ1972 ዓ/ም ለአንድ ጉዳይ አዲስ አበባ ኼደ፡፡ የካቲት 1 ቀን 1972 ዓ/ም አዲስ አበባ ውስጥ፣ ጎጃም በረንዳ አካባቢ በድንጋይ ተቀጥቅጦ ተገደለ፡፡ አሟሟቱን በተመለከተ ምርምር አድርጎ አንድ መጽሐፍ የጻፈው ኤልያስ አያልነህ “የአቤ ጉበኛ ብሔራዊ ተጋድሎ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሐፍ አቤ ጉበኛ ስለት በሌለው (ድልዱም) መሳሪያ ጭንቅላቱ ላይ ተመትቶ እንደሞተ የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልን የአስክሬን ምርመራ ዋቢ አድርጎ ፅፏል።
ብዐረኛው አቤ ምድርን 50 ዓመታት እንኳን ሳይኖርባት በተወለደ በ47 ዓመቱ አልፏል፡፡ አጭር የምድር ቆይታውን ያሳለፈው ስለ እውነት ሲሟገት፣ ስለሕዝቦች ነጻነት ተጋድሎ ሲያደርግ፣ መንግሥታዊ ውስልትናን ሲቃወም እና ፍትኅ ትሰፍን ዘንድ ሲለፋ ነው፡፡ ያ የሥነ ጽሑፍ ቆሌ፣ የመብት ተሟጋች፣ ሞገደኛ ጸሐፊ የካቲት 4 ቀን 1972 ዓ/ም ጎጃም ውስጥ፣ ቅኔ ተምሮ ባደገበት ይስማላ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጸመ፡፡አቤ በሕይወት ዘመኑ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆችን አፍርቷል፡፡ ሚካኤል አቤ፣ ፅጌማርያም አቤ እና ፍቅርተ አቤ ይባላሉ።
ስለ አብዮተኛው ደራሲ አቤ ጉበኛ ማወቅ የሚፈልግ ቢኖር የሚከተሉትን ሰነዶች ይፈትሽ፣
- ፍጹም ወልደማርያም፣ ያልተዘመረላቸው
- ኤልያስ አያልነህ፣ የአቤ ጉበኛ ብዕራዊ ተጋድሎ
- አንተነህ አወቀ፣ ዳግም ንባብ በአልወለድም
- እንዳለጌታ ከበደ፣ ማዕቀብ
- Antenehe Awoke, The representation of Ethiopian Politics in Selected Amharic Novels: 1910- 2010