>
5:26 pm - Monday September 17, 7759

አዲስ አበባ እና የቆዩ ቅርሶችዋ አሳዛኝ ዕጣ (ብርሃኑ ድንቁ)  

አዲስ አበባ እና የቆዩ ቅርሶችዋ አሳዛኝ ዕጣ

ብርሃኑ ድንቁ

አዲስ አበባ ቀድሞ የነበረው የከተማነት ማዕዛዋ ጠፍቶ እምቅ ከተማ ሆናለች። የከተማዋ ውበት ጠልሽቷል። ቅርሶችዋ ወድመው ሊያልቁ ነው። አዲስ አበባ የከተማ አስተዳደር ሙያን በተካኑ ተመራጭ መተዳደር ካቆመች ቆይታለች።

አዲስ አበባ በኢጣልያ ወረራ ዘመን

ቅዳሜ – ቅዳሜ – ከሚውለው ከ 30000 እስከ 50000 ገበያተኞች ከሚያስተናግደው ትልቁ የገበያ ሥፍራ፣ አርመኖችና ህንዶች ከገነቧቸው ሠቀላ ቤቶች እንዲሁም የእንጦጦን ተዳፋት ተከትለው እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣልያና ሩስያ ከሠሯቸው ቆንስላዎቻቸው በቀር ኢጣልያ አዲስ አበባን ሲወራት ሁነኛ የከተማ ቅያስ አላገኘባትም ነበር። በእርግጥ በዳግማዊ ሚኒልክ ዘመነ መንግሥት በኢጣልያና ግሪክ ሥነ-ሕንጻ አዋቂዎች የተሠራው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን ውብ ነበር።

ኢጣልያ አዲስ አበባን እንደተመለከታት መጀመርያ ያሰበው የከተማ ዕቅድ መንደፍ ነበር። በዚሁ መሠረት የጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን (S. Giorgio) አካባቢ የአምልኮ ቦታን ማስዋብ፣ የሚኒሊክ ቤተ መንግሥትን (አሮጌ ግቢ – vecchio ghebi) ማስተካከል፣ ለኢጣልያ ቅኝ የአስተዳደር አዲስ ሠፈሮችን (አዲስ ግቢ – nuovo ghebi) መገንባት፣ አረንጓዴ መስኮችንና (zone verdi) የመኖርያ ቦታዎች (quartiere indigeno) መቀየስ እንዲሁም የገበያ ቦታዎች (quartiere commerciale) እና የኢጣልያኖች መኖርያ ሠፈርና የአስተዳደር/ፖለቲካ ማዕከል (quartiere italiano – centro politico) ማዘጋጀት ነበር።

ፒያዛ፣ ፖፖላሬ፣ ካዛንቺዝ፣ ጣልያን ሠፈር፣ ብሄራዊ ቴዓትር አካባቢ፣ ወዘተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ዳር ዳር ሠፈሮች የምንመለከታቸው ጠንካራ ምሽጎችን ጨምሮ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ የሚሄዱት መንገዶችና ጠንካራ ድልድዮች – ኢጣልያ በአምስቱ ዓመታት የወረራ ዘመን የገነባችው ዛሬ ላይ እንደ ቅርስ የሚያታዩ ግንባታዎች ናቸው።

አዲስ አበባ ዛሬ አልተመቻትም። በየክልሉ በተዘረጋው የዘር አድሎ ምክንያት ሕዝብ ይጎርፍባታል (ethnicity and migration)። በመላ አገሪቱ መልካም አስተዳደር ባለመኖሩ አድሎና ሥራ አጥነት ያማረራቸው ወይንም መስፈርቱን እያማሉ በቋንቋ ምክንያት መቀጠር ያልቻሉ ተመራቂዎች ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ከመሰደድ ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም። በመሆኑም ከተማዋ ታምቃለች፣ ዘራፊዎችና ቀጣፊዎች ይተራመሱባታል፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች በቂ አይደሉም። አልፎ ተርፎም  ታሪክ ጠል ዘረኞች – ቅርሶችዋን – በማፈራረስ የከተማዋን የቆየ ውበት እያበላሹ ነው።  ከሹመኞች መካከል አዲስ አበባ በታሪካዊ ከተማነት በቅርስ እንድትቆይ የማይፈልጉ አሉ። እስኪ ችግሩን በጥቂቱ እንመልከት።

ሀ. እምቅ ከተማ (suffocating city) – አዲስ አበበ አምቡላንስና እሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪ የማይላወሱባት በመንገዶች ጥበት የምትሰቃይ እምቅ ከተማ ሆናለች። ከማህል አዲስ አበባ ወጣ ያሉ ሠፈሮች ለመድረስ ከአንድ እስከ ሁለት ሠዓት  በግል መኪና ወይንም ታክሲ ውስጥ እንደ ሰርዲን መታጨቅ ያስፈልጋል። ይህ በአዘቦት ቀናት ነው። የውጭ አገር መሪ ለጉብኝት ሲመጣ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲንቀሳቀሱ አልያም መኪና ከተጋጨና ፖሊስ መንገዱን ከዘጋ ደግሞ አበሳው እጥፍ ድርብ ነው። ሹፌርነት ቅጣት በሆነባት ዋና ከተማ እግረኛውም ይሰቃያል። እግረኛው ከአሮጌ መኪኖች የሚወጣውን ጭስ እየማገ ከስድስት ሠዓት ሲቃ በኃላ እኮንዶሚየሙ ይደርሳል።

ለ. የከተማ ውበት መጠልሸት (depressed urban area) – የአዲስ አበባ ከተማ ብልሹ (delinquency) ነገሮች እየሞሉባት ነው። የከተማው ጥበቃ በመላላቱና ሙስና በመናሩ የተደራጀ (organized crime) እና አሰቃቂ ወንጀል (violent crime) ተበራክቷል። በከተማዋ አሳፋሪ ጸረ-ማህበረሰብ (anti-social behaviour) ጠባዮችና (criminal damage) ያልተገባ ምግባሮች (disorderly conduct) ሲንጸባረቁ ይታያሉ።  በአዲስ አበባ ከተማ – ቤት የለሽ ጎዳና ተዳዳሪዎች (vagrancy)  ቦዘኔዎች  (loitering) እና ዕጽ-ተጠቃሚዎች እንደ አሸን ፈልተዋል።  ዛሬ ላይ አደገኛ ዘራፊዎችና ነፍሰ ገዳዮች በበዙባት አዲስ አበባ ጠዋት ሳይነጋም ሆነ በየምሽቱ ለታክሲ ወረፋ ረዥም ሠልፍ የሚይዘው ነዋሪ መንግሥት ደህንነቱን በተገቢው አይጠብቅለትም። ጎህ ሳይቀድ ለሥራ ሲወጡ አልያም ምሽት ላይ ወደ ቤት ሲመለሱ በጅብ የተበሉ ሰውችም እንዳሉ ይነገራል። ዛሬ ላይ ጅቦች የሰው ልጅ ስጋን እየለመዱ በመሄዳቸው አውሬነታቸው አስጊ ሆኗል።

ሐ. ቅርሶችን ማፈራረስ (damaging antique buildings) – የአዲስ አበባን ታሪክ ለማበላሸት ወይንም አዲሱ ትውልድ እንዳያውቀው ለማድረግ የመለስ ሃሳብ የወለደው ቅርሶችን የማፈራረስ ወያኔዊ ክፋት ዛሬም ቀጥሏል። ትላንትና የጀግናው ራስ አበበ አረጋይ መኖርያ ቤት መፍረስ ሲገርመን ዛሬ ደግሞ ከብሄራዊ ቴዓትር ፊት ለፊት ኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ ቆሞ የነበረው ኢጣልያ የሠራው የበጎ አድራጎት ሕንጻ ፈርሷል። ለነገሩ አዲስ አበባን – ማንስ ይሟገትላት? ሊሟገቱላት የቆሙትን በሸፍጥና በሴራ ያርቋቸዋል። አዲስ አበባ ልጆቿም ተሰደውባታል። ስደት ውጤቱ ይህ ነው። ስደት ተቆርቋሪዎችን ማራቅ ማለት ነው። ጊዜ በባለጊዜዎች እጅ ስትወድቅ ስደተኛው ከሩቅ ይጮሃል። ጩኸት በረከተ እንጂ ቅርሶች ፈርሰው ሊያልቁ ነው። በአደጉ ከተሞች ታሪካዊ ቅርሶች የህግ ጥበቃ አላቸው (protection and preserving of antiques law)።

መ. ከተማ የማስተዳደር ሙያ አለመካን – አዲስ አበባ ሁለት ነገር ይጎድላታል። አንደኛ – ውስጧን፣ ከተማዋን በቅጡ የሚያውቅ አስተዳዳሪ  ስለሌላት ማዘጋጃ ቤቷ ደካማ ነው  (weak municipality)። ሁለተኛ ሊመሯት በማዘጋጃ ቤት የተሰበሰቡት ምናልባት የዘር ፖለቲካን ከመንተራስ ውጭ ሠፊ ከተማ የማስተዳደር ሙያዊ ክህሎት መሸከማቸው ያጠራጥራል (perform duties on a non-professional basis) ። የማዘጋጃ ቤቱ ተመራጮች ሙያን የተካኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቢሆኑ ኖሮ የከተማዋን ታሪክ ከማጥፋት ይልቅ የተሻለ አስተዳደራዊ ክህሎቶችን ይጠቀሙ ነበር። ቅንነቱ ቢኖር እኮ አዲስ ከተማ መቆርቆርም በተቻለ። ገንዘብ ካላግባብ መዛቅ የሚፈልግ ሁሉ ዓይኑ የሚያርፈው አዲስ አበባ ላይ ነው። ቤት ገንቢዎችና የሪል ስቴት ባለቤቶች ወቅቱን ተገን አድርገው ድንጋይ በድንጋይ ላይ ይቆልላሉ እንጂ ስለ ከተማ ደህንነትም ይሁን አካባቢ ጥበቃ ለማሰብ ጊዜም የላቸው። ገንዘብ እየዛቀ ወደ ውጭ ማሸሽ የሚፈልግ ሁሉ በአዲስ ፕሮጄክት ግንባታ ስም ብቅ የሚለው አዲስ አበባ ላይ ነው። ሙሰኛ ባለሥልጣናት ነዳጅ እንደሚወጣበት ጉድጓድ ካለርህራሄ የሚቆፍሯት አዲስ አበባን ነው። እንዳው በደፈናው የከተማው አስተዳዳሪዎች ዕቅድ የሚባል ነገር አያውቁም፣ አንድ የሚችሉት ነገር የነበረውን ቤት እያፈረሱ እማይረባ ኮንዶሚኒየም መስራት ነው። ታዲያ እነዚህን መሪዎች ነው ሰው ዝም ብሎ ማየት ያለበት ወይስ በቃችሁ ሊባሉ ይገባል? ፍርዱን ለነዋሪው እተወዋለሁ።

አዲስ አበባና የፈረሱ ቅርሶችዋ

የአዲስ አበባን ታሪካዊ ቅርሶች ማዳን እንችላለን? አይመስለኝም! ምን አቅም አለንና። ቢሆንም ይህን እናደርጋለን። የፈረሱ ቅርሶችን ዳግም መመልሰ አንችልም። አንድ ቀን ግን አምላክ ሲፈቅድ – ቅርሱ ፈርሶ አዲሱ የሙስና ሕንጻ በተሰራበት አጠገብ – የቀድሞውን ታሪካዊ ቅርስ የሚያስታውስ ምስል አቁመን – የተሰራበትን ቀን ታሪኩንና የፈረሰበትን ቀን – እንዲፈርስ ትዕዛዝ የሠጠውን ሹመኛ ስም ጭምር ጽፈን – ለትውድል ማስተላለፍ እንችል ይሆናል።

የቀድሞ ቅርሶች ፈርሰው፣ በፈረሰው ቅርስ ምትክ አዲስ የተገነባው ሕንጻ ወደፊት ሕዝባዊ አገልግሎት ሠጪ መሆኑ ያጠራጥራል። የአዲሱ ህንጻ “ባለቤት” የሆናችሁ ሁሉ በግፍ በተደረመሰው ታሪካዊ ቅርስ ምትክ ዘመን የሚቆጥር የሠማዕት ሃውልት መቆሙን ከወዲሁ ልታውቁት ይገባል።  ፍርዱ የእግዚአብሄር ነው።

ኢጣልያ ከገነባችው ሕንጻ ምስሎች መካከል ጥቂቶች

  1. በቅርቡ የፈረሰው – የበጎ አድራጎት ሕንጻ – ይህ ነበር። እታች በግራ በኩል ዳር ላይ የነበረው ታዋቂው አንበሳ ባር ምድር ቤቱ ዝነኛ ከረምቦላ ቤት ነበረው። ሕንጻው ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ወራ ይዛ በነበረበት አምስቱ የአርበኞች ትግል ወቅት የተገነባ ነው። ይህ ሕንጻ ከኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ ይገኝ ነበር።
  1. የበጎ አድራጎት ሕንጻ ከመፍረሱ በፊት – ፊት ለፊቱ የሚታየው ሕንጻ የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት – የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ነው። ይህ ከታች የሚታየው ውብ ሕንጻ በኢጣልያ የተሠራ ነው። ከቴአትር ቤቱ በታች ምድር ላይ የተለያዩ ሱቆች ነበሩ።  ሹመኞቹ መተላለፍያውን ለጊዜው አስቀርተው ሱቆቹን አፈራርሰዋቸዋል።
  1. አሁን ከፈረሰው ከበጎ አድራጎት ሕንጻ ጎን (መኪና መንገዱን ተሻግሮ) ያለ – በወረራው ዘመን በኢጣልያ የተገነባ ነው። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ እንዲሁም ከኢጣልያ ሽንፈት – ከ1933 ዓም ጀምሮ – ከሌተና ጄነራል (ራስ) አበበ አረጋይ  እስከ ሌተና ጄነራል አዲስ ተድላ 1983 ዓም ድረስ፣ ለተወሰነ ዘር ሳይሆን – ለኢትዮጵያ አንድነት በጽናት የቆመው – የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት – የተመራበት ይህ – የአገር መከላከያ ሚኒስቴር – ታሪካዊ ሕንጻ – በሕንጻ አራጆች ግብዓተ-መሬቱ ይፈጸም ይሆን?

በአንድ ላይ ቆመን ታሪካዊ ቦታዎችን አታፍርሱ ብለን ልንሞግታቸውና ልንጠይቃቸው ይገባል!

Filed in: Amharic