ለአምሓራ ህዝብ ኅልውና እንታገላለን የምንል ሁሉ ፤ ከአስመሳይ ታጋይ አታጋዮች መጠንቀቅ አለብን!
ብርሃኑ ድንቁ (ኖርዌይ ኦስሎ)
የዘመኑ ቴክኖሎጂ ወደ ህብረተሰቡ የመድረሻውን መንገድ አቅሎታል። ዩቲዩብ (YouTube)፣ ቲክቶክ (TikTok)፣ ፌስቡክ (Facebook)፣ ትዊተር (Twitter) – ምቹና ሠፊ ግልጋሎት ከመስጠታቸው አኳያ በብዙዎች ዘንድ እጅግ ተዘውታሪ ሆነዋል። እነኚህ ማህበራዊ መገናኛዎች ለትምህርት፣ ለመረጃ ልውውጥ፣ ለመዝናናት፣ ወዘተ፣ መጠቀምያ ከመሆናቸው በላይ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉ ማህበራዊ አንቂዎችም ሃሳቦቻቸውንና ዓላማዎቻቸውን ያንጸባርቁበታል።
በእርግጥ ማህበራዊ መገናኛዎች የመታገያውንና የመሰባሰቢያውን መንገድ እጅግ ቢያቀሉትም እንኳን በግንባር የመገናኘት ዕድልን ስለማይፈጥሩ የማህበራዊ አንቂዎቹን ማንነትም ሆነ የዓላማዎቻቸውን ሃቀኝነት በቅጡ ለመመርመር ያስቸግራል። ይህ ሁኔታ በአምሓራው የኅልውና ትግል ላይም ቢሆን ራሱን የቻለ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል።
የአምሓራው ህብረተሰብ ለትግል መነሳሳትን ተከትሎ ሁለት መሠረታዊ ልዩነቶች ያሏቸው ተጻራሪ ቡድኖች መከሰታቸው ነባራዊ ሃቅ በመሆኑ ሁለቱም አባላትን ወደየራሳቸው ጎራ ይጎትታሉ።
1ኛው ቡድን – ጥናትና ምርምር ተመርኩዞ፣ ነባራዊ ሁኔታውን አገናዝቦ፣ ማህበር አቋቁሞ ህብረተስቡን በንቃት በማሳተፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን – ቡድኑ መርሆችን የሚተገበርበት የፖለቲካ መድረክ (platform) አዘጋጅቶ ማህበረሰቡን በማንቃትና በማታገል ላይ የሚገኝ ነው።
2ኛው ቡድን – በሁለት ንዑስ ስብስቦች የተከፈለ ነው። አንደኛው የመንግስት እገዛ እየተደረገለት የአምሓራውን ህዝብ የትግል አቅጣጫ ለማሳት የሚሰራ ሲሆን ሌላኛው በማንነት አምሓራ ባልሆኑ ትግሉን ለማደናቀፍ ሰርገው በገቡ (infiltrate) ግለሰቦች በግልጽ ወይንም በስውር (surreptitiously) ደባ የሚፈጽም ነው።
እስኪ ዘርዘር አድርገን እንያቸው፤
በ1ኛው ቡድን ውስጥ የተካተቱት ሁለት አይነት የትግል ስልትን ያራምዳሉ።
– የመጀመርያው የትግል ስልት በማህበር ተድራጅቶ የሚከወን እንቅስቃሴ ሲሆን – ይህ ለአምሓራው ህዝብ ነፃነት ጉልህ ሚናን የሚጫወተው ነው። ቡድኑ ድርጅታዊ መርህን የታጠቀ ከመሆኑም ባሻገር አነሰም በዛም አባላት አሉት፣ መተዳደሪያ ደንብም አለው። ድርጅታዊ አሠራርና መድረሻ ግቡን (strategy) ነድፎ ስለሚንቀሳቀስና ተጠያቂነት ስላለበት ለአምሓራው ነፃነት ትግል ብቸኛ መንገድ ነው። በዚህ አይነት ከተደራጁት ውስጥ ለምሳሌ 51 ማህበራትን ያጠቃለለው የአለም አቀፍ የአምሓራ ንቅናቄ፣ በአሜሪካ ያለው የአምሓራ ማህበር፣ በካናዳ የሚገኘው የአምሓራ ማህበር፣ በአውስትራሊያ የሚገኘው የአምሓራ ማህበር፣ አሁን ሊቋቋም የታሰበው የአውሮፓ ማህበር እንዲሁም በሃገር ቤት የፋኖ አደረጃጀትና የአምሓራ ህዝባዊ ግንባር በጉልህ የሚጠቀሱ ናቸው።
– ሌላኛው የትግል ስልት በተነሳሽነት (initiative) የሚራመደው ነው። ግለሰቦች የየራሳቸውን የፖለቲካ መድረክ አዘጋጅተው ሰዉን በማነቃቃትና ለትግል እንዲነሳሳ በማድረግ ጠቃሚ ኢንፎርሜሽኖችን በማካፈል ምን መደረግ እንዳለብት አቅጣጫ ይጠቁማሉ። ይህ የትግል ስልት የሚናቅ አይደለም። በእርግጥ ውጤታማነቱ የድርጅትን ያህል ሠፊ ባይሆንም ጠቃሚነቱ ግን አጠያያቂ አይደለም። ይህን ዓይነቱን የትግል ስልት ከሚያራምዱት መካከል – አቻምየለህ ታምሩ፣ አበበ በለው፣ ዘመድኩን በቀለ በሰፊው ይጠቀሳሉ።
በ2ኛው ቡድን ውስጥ ያነሳኋቸው የአምሓራ ህዝብን የነፃነት ትግል ለማኮላሸት በየፊናቸው እየሰሩ ያሉትን ነው።
በዚህ ውስጥ የሚካተቱት “ሀ” እና “ለ” ብለን የምንሰይማቸው ንዑስ ስብስቦች፣ ዘርና ቋንቋን ሁለንተናዊና ወሳኝ መስፈርት ያደረጉ፣ የአምሓራ ህዝብ ትግል ያስደነገጣቸው ናቸው። ስለዚህ – በዚህም በዛም ብለው ትግሉ እንዲዳከም አልያም ጥርጣሬና መከፋፈል እንዲሰፋ ሳይታክቱ ይሰራሉ። የሁለቱም ፍላጎት ተመሳሳይ ነው፣ የአምሓራን የኅልውና ትግል ማዳፈንና የአምሓራውን ነገድ መቀመቅ መክተት።
በ “ሀ” ንዑስ ቡድን ውስጥ የተካተቱት ኮሎኔል አብይ አህመድ በሚመራው ገንዘብ እየተከፈለው በሚሰራው ስብስብ ውስጥ ነው። ይሄ ስብስብ የገንዘብ አቅም ስላለው በስፋት ይንቀሳቀሳል። ስብስቡ በየፈርጁ የተዋቀሩትን የአምሓራ ህብረተሰብ ውስጥ ስርጎ በመግባትና ብሎም በመቆጣጠር ማህበራትን ስንኩል ያደርጋል። ይህ መሰሪ ኃይል ስርጎ መግባት ባይችል እንኳን በየማህበራቱ ውስጥ ካሉት መካከል ጥቂቶችን በንዋይና በልዩ ልዩ ጥቅሞች በመደለል ለራሱ ዓላማ ያሰልፋቸዋል ወይንም ተለጣፊ ማህበር አቋቁሞ አባል ያደርጋቸዋል። ስብስቡ “ትንሽ ቆሎ ይዘህ አሻሮ ተጠጋ” በሚል ብልሃት ኢምንት እውነት ያዘለ እውቀት መሰል ነገር ያርከፈክፍና መላ ማህበሩን ምርኮኛ ያደርገዋል። ይህ ስብስብ ጠንካራ አቋም የለበሱ ታጋዮችን ስም በማጠልሸት ማህበሩን ጨርሶ በማዳከም ክፍፍል ለመፍጠር ይሞክራል። ለዚህ መሰሪ ኃይል ያደሩ ሰዎች አድፍጠው ይጠብቁና አመቺ ሁኔታ ሲገጥማቸው የድርጅቱን ሚስጥር ለመንግስት በማቀበል የተዘጋጀላቸውን አሞሌ ጨው ይልሳሉ።
በ “ለ” ንዑስ ቡድን ውስጥ የሚካተቱት የፖለቲካ ውታፎች ሲሆኑ “አምሓራ ከተደራጀ የመገንጠል ህልማችን ያከትማል፣ ስለዚህ አምሓራው ጠንካራ ድርጅት መመስረት የለበትም” ብለው ቀን ሌት የሚቃዡት ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች አማርኛ ቋንቋ ስለሚችሉ፣ “አምሓራው ይህን ያድርግ – ያን ይተው” እያሉ የአዛኝ ቅቤ አንጓች መላቸውን በመጠቀም በየሜዲያው ሲዘላብዱና ሲንጫጩ ይውላሉ። ይህ ችግር ከኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከዛሬ ሲከተለን የቆየ የንቃትና የመደራጀት ጠንቅ ነው። ብርሃነ መስቀል ረዳ አንድ ወቅት ላይ እንዲህ ተናግሮ ነበር።
“…እኛን መስለው፣ የእኛን ቋንቋ የሚናገሩ፣ የእኛን ልብስ የተላበሱ ከእኛ ጎን ሆነው በሥር ነቀል ደጋፊነት ስም የሚታወቁ…እፍኝ የማይሞሉ፣ ከባዕዳን ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው በጥንቃቄ መያዝ የሚገባቸው ናቸው…” ብርሃነመስቀል ረዳ፣ 1965 ዓም ቤይሩት
ግራም ነፈስ ቀኝ የአምሓራው ትግል በምንም አይነት ሁኔታ ወደ ኋላ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል። አምሓራ ስለ ማንነቱ፣ ኅያው ታሪኩና ኃይማኖታዊ ትውፊቱ ሲል በሥርዓት ይታገላል። መፍትሄው ወደፊት መግፋት ብቻ ነው። ሆኖም ግን በንዑስ ስብስቦች “ሀ” እና “ለ” ውስጥ በተካተቱት የክፋት ተልዕኮ ፈጻሚዎች ሳብያ ትግሉ ከሂደቱና ከእንድርድሪቱ (momentum) እንዳይስተጓጎል ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
ለአምሓራ ህዝብ እንታገላለን የምንል ሁሉ – “የትኛው የአምሓራ ማህበር፣ የትኛው ቡድን ወይንም የትኛው ማህበራዊ አንቂ – ለአምሓራው የኅልውና ትግል ትክክለኛውን አስተዋጾ ያበረክታል” – “፟የትኞቹስ የክፋትና የሴራ አገልጋዮች ናቸው” ብለን ጥልቅ በሆነ ሁኔታ ጉዳዩን በንፅፀር ማየት አዋቂነት ከመሆኑም ባሻገር ደግሞ ደጋግሞ በችግር ውስጥ ከመዘፈቅም ያድናል።