>

በዐምሐራ የህልውና ትግል ውስጥ የባለ ድርሻዎች ሚና

በዐምሐራ የህልውና ትግል ውስጥ የባለ ድርሻዎች ሚና

ከይኄይስ እውነቱ

መዳረሻው በመላው ኢትዮጵያውያን በጉጉት የሚጠበቀው የዐምሐራ የህልውና ትግል ተአምራት በሚያሰኙ ድሎች ታጅቦ እየገሰገሰ ይገኛል፡፡ እውነት፣ ፍትሕና ሰብአዊነትን ይዘው የተነሡ ጀግኖቻችንን እና ደጀን ሕዝባችንን ለረዳ ሰማያዊ አምላክ ምስጋናችንን በየዕለቱ እናቀርባለን፡፡ መጨረሻውንም እንዲያሳምርልን የዐቅማችንን ከማድረግ በተጨማሪ እንደየ እምነታችን በጸሎታችን እንተጋለን፡፡ 

ያለ መከራ ጸጋ አይገኝምና የድል ዜናው እንደሚያስደስተን ኹሉ ተገደን የገባንበት ጦርነት ከኃይለ አጋንንት ጋር ነውና ጀግኖቻችንና ሕዝባችን ከፍተኛ መሥዋዕትነት እየከፈሉ እንደሚገኙ ለአፍታ መዘንጋት የለብንም፡፡ ፋሺስታዊው አገዛዝ ተስፋ በቆረጠ መጠን ጥላቻውና ጭካኔው እየበረታ እንደሚሔድ እያስተዋልን ነው፡፡ ሰላማዊ ወገኖቻችንን በድሮንና በከባድ መሣሪያ መጨፍጨፉን ቀጥሎአል፡፡ ጀግኖች የዋሉበት ለመገኘት ሳይሆን ንጹሐንን ለመጨፍጨፍ የደፈጣ ውጊያም ጀምሮአል፡፡ የገጠመን ጠላት ከጥልያን ፋሺስትም የከፋ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም ከሁሉም በቅድሚያ በአገር ቤት የማይተካ ሕይወቱን እየሰጠ ያለው የዐምሐራ ፋኖ/ተዋጊው ኃይል፣ አመራሩና ሕዝቡ ባጠቃላይ ድርጅታዊ አሠራሩን አጠናክሮና ወጥ አድርጎ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተነጋሪ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ አሁንም ፈተና ሆኖ የቀጠለ የባንዳ ኃይል ስላለና እስከ መጨረሻውም ሊዘልቅ ስለሚችል ዋነኛ ጠላት አድርጎ ያለ ርኅራኄ መፋለም ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ አንድ የጸና አቋም ሊያዝ ይገባል፡፡ ጅምሩ መልካም ነው፡፡ ደጋግሞ በጀግኖቻችን እንደተነገረው ሕዝባችንን አሳምኖ በባንዳዎች ላይ (ከትግሉ በአፍኣ ያለ የብአዴን ኃይል፣ ሚሊሽያ፣ የዐድማ ብተና የሚባለው ኃይልና ከጠላት የኪስ ገንዘብ እየተቀበለ የጆሮ ጠቢነትና ወገንን ለማስጠቃት የምሪት ሥራ ላይ የተሰማሩ በሙሉ) የማያዳግም ርምጃ መውሰድ ይኖርብናል፡፡ ፊት ለፊት በመዋጋት ከጀግንነት ጋር የማይተዋወቀው ጨካኙና የአገዛዙ ሠራዊት በተለይም በጥላቻ የተሞላው ኦሕዴዳዊ/ኦነጋዊ ኃይል ንጹሐን ወገኖቻችንን በከባድ መሣሪያ ከጨፈጨፈ በኋላ በምርኮ ጊዜ መረጃ ስለሌለኝ ሳላውቅ ተሳስቼ ነው የሚለውን የተደጋገመ ወሬ መስማት ትተን (የውጊያውን ጥበብና ስልት ለናንተ በመተው) ቢቻል መደምሰስ ያስፈልጋል፡፡ ከጠላት የሚላከው ዐዲስ ኃይልም ሊማር የሚችለው የማያዳግም ርምጃ ሲወሰድ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ባንፃሩም የሚማረከውን ኦሕዴዳዊ/ኦነጋዊ ሠራዊት በሚመለከት (ለቀባሪው አረዱት ባይሆንብኝ) ብርቱ ክትትልና ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ እግረ መንገዴን ለጀግኖቻችንና ደጀን ለሆነው የዐምሐራ ሕዝብ አንድ ቀለል ያለች መልእክት እንዳስተላልፍ ፍቀዱልኝ፡፡ ወያኔና ኦነግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ‹ክልል› ብለው ባጠሩልን የአትድረሱብኝ አጥር አካባቢያችንን ላለመጥራት ካሁኑ ልምምዱን ብናደርግ፡፡ አልፎ አልፎ መልካም ጅምሩን እንደሰማሁት ክፍለ ሀገር ወይም የኢትዮጵያ ግዛት ብለን ብንጠራ መልካም ይመስለኛል፡፡

ይህን ካልሁ በኋላ የህልውና ትግላችን ግብ ፋሺስታዊውን የጐሣ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ምድር ነቅሎ በቅድሚያ የኢትዮጵያን አገራዊ ህልውናና አንድነት ማረጋገጥ ብሎም ከቀሪው ኢትዮጵያውያን ጋር በእኩልነትና በፍትሕ እንደ አንድ ሕዝብ የምንኖርባትን አገር እውን ማድረግ በመሆኑ በዚህ ትግል ውስጥ ከጠላት ኃይል በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ አለው፡፡ 

1ኛ/ ከወያኔና ከፋሺስታዊው አገዛዝ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያኖች በሙሉ

ዛሬ ተዘልሎ የተቀመጠ የመሰለው ክፍለ ሀገር ነገ በጠላት ኃይል ቁም ስቅሉን የሚያይ ተረኛ እንደሚሆን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በመሆኑም ኹላችንም በኢትዮጵያ ዕድል ፈንታ እንደ ማኅበረሰብ ህልውናችንን የማስከበር፣ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የጋራ ቤታችንን ባንድነት ለማነፅ መነሣት ይኖርብናል፡፡ ዛሬ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልጽ እንደሆነው ሁሉን ‹ኬኛ› የሚለውና እንደ ፖሊሲ የሚከተለው የጠላት ኦሮሙማ ኃይል በቅዠት ለሚያልመውና በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ እገነባዋለሁ ለሚለው ‹ኦሮሚያ› የሚባል አገር ካርታ ሠርቶ፣ ባንዲራ አዘጋጅቶ የተስፋፊነቱን ተግባር በኃይል ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዛሬ በዚህ ፋሺስታዊ ኃይልና በጭካኔ የመስፋፋት ዘመቻ ያልተነካ የኢትዮጵያ ክፍልና ማኅበረሰብ የለም፡፡ በመሆኑም በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን የወራሪነት መንፈስና ዓላማ ከሚንቀሳቀሰው ‹የገዳ ወራሪ ኃይል› አካባቢውን መጠበቅ መከላከል ለነገ የማይባል ሥራ ነው፡፡ አገዛዙን ከሰላማዊ የእምቢተኝነት ትግል እስከ ትጥቅ ትግል አላላውስ በማለት አለመታዘዙን ማሳየት ዛሬውኑ መጀመር ይኖርበታል፡፡ የመዳን ቀን ዛሬ ነው እንዲል ርእሰ መጻሕፍቱ፡፡ ትግሉ በየቦታው ከተቀጣጠለ አገዛዙ የሚይዘው የሚጨብጠውን አጥቶ ስለሚባክን ዕድሜውን ብሎም የሕዝብ ሰቆቃ በእጅጉ ማሳጠርና መቀነስ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ በየማኅበረሰቡ ያላችሁ ምሁራን፣ ፊደል የቆጠራችሁና ጥሪት የያዛችሁ ባለሀብቶች የየማኅበረሰባችሁን የትግል እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት የማገዝና የማስተባር ኃላፊነትና ግዴታ አለባችሁ፡፡ ነገ ሁሉም ነገር ከእጃችሁ ተነጥቆ ሽባ ከመሆናችሁ በፊት ራስችሁንም ሆነ ማኅበረሰባችሁን ከኦሮሙማው አውሬ ታደጉ፡፡ 

ባንፃሩም ፋሺስታዊውን የኦነግ/ኦሕዴድ ኃይል ለመገርሰስ በዐምሐራው ለተጀመረው ትግል አጋርነትን በማሳየት ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ 

2ኛ/ የዐምሐራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ኃይል

ግንባሩ አገር ቤት ካለው ሕዝባዊ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ ወጥነት ያለው አደረጃጀት ለመያዝ እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በውጭ የሚገኘው የድጋፍ ኃይል እንደ ስሙ አገር ቤት ላለው የዐምሐራ ፋኖ የህልውና ትግል እና መዳረሻ አድርጎ ያስቀመጠው ዓላማ ይሳካ ዘንድ ሚናው ሁለንተናዊ ድጋፍ/እገዛ ማድረግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ከአገር ቤቱ አመራር ጋር የተናበበ አሠራር ይኖረዋል፡፡ እዚህ ላይ ጎላ አድርጌ ማንሣት የምፈልገው በግንባሩ የውጭ ድጋፍ ኃይል አመራሮች ውስጥ በእጅጉ የምናከብራቸው በዕውቀትም በልምድም የበለጸጉና የበሰለ ተሞክሮ ያላቸው (seasoned) ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አሉ (ዶ/ር ልዑል ዐሥራተ ካሣ፤ ሻለቃ/ጋሼ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፤ አቶ ዑመር ሽፋውና ሌሎችም)፡፡ እነዚህ በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በዲፕሎማሲ፣ በአካባቢያዊ ግጭቶች አፈታት፣ በሥራ አመራር ወዘተ. ጎምቱ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን ሳያሰሙ ትልቅ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ባስብም (የማይነገርበት በቂ ምክንያት ከሌለ በቀር) ክንዋኔዎች በሪፖርት መልክ ቀርበው መስማት የምንችልበት ዕድል ቢኖር መልካም ይመስለኛል፡፡ እነዚህን በመልካም ሰብእናቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ ዋስ ጠበቃ በመሆናቸው ባብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው ኢትዮጵያውያን ላይ ባለጌው አገዛዝና ስድ አደግ ግለሰቦች ባልታረመ አንደበት ጥላሸት ለመቀባት ውር ውር ሲሉ አንድ ሰሞን አድምጬአለሁ፤እየተናነቀኝም  አንብቤአለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ትልቁን አገራዊ ሥዕል በማየት ነውረኞቹን ንቀዋቸው ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ እየተወጡ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን ባለፉት ግማሽ ምዕት ዓመታት ቋያ በቅሎባት የተፈታችው የዐዋቆችና እውነተኛ ሽማግሎች መካር በማጣት እንደሆነ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት በጣት የሚቈጠሩ ዕንቊ ኢትዮጵያውያንን በጥንቃቄ መያዝ ይኖርብናል፡፡ ዘመንን የዋጀ ምክራቸው ለኢትዮጵያ በእጅጉ ያስፈልጋታልና፡፡ 

3ኛ/ በውጩ ዓለም የሚገኘው ኢትዮጵያዊም ሆነ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የዐምሐራ ማኅበረሰብ እና ቀሪው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ

በውጩ ዓለም የምትኖሩ የተደራጃችሁም ሁኑ በግለሰብ ደረጃ ያላችሁ የዐምሐራው ተወላጆች ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርሻ/ሚና አንድ ሲሆን÷ ነገር ግን የማይናቅና ታላቅ ነው፡፡ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ ብቻ፡፡ ሁለንተናዊው ድጋፍ የሚገለጽባቸውን ሁናቴዎች ከመዘርዘሬ በፊት በሁሉም ዘንድ በማያሻማ መልኩ ግልጽ ሊሆን የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ይኸውም በውጩ ዓለም በዐምሐራው ማኅበረሰብ ስም የሚገኙ ማናቸውም ዓይነት አደረጃጀቶች እንዲሁም የዐምሐራ ተወላጅነት ያላቸው ግለሰቦች ባገር ቤት በሚካሔደው የዐምሐራ ህልውና ትግል መሪዎች አይደሉም፤ ሕጋዊ ተወካዮችም አይደሉም፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ በሚያደርገው የህልውና ትግል ስም ከየትኛውም አካላት ጋር ድርድር ወይም ማናቸውንም ስምምነት በፍጹም ማድረግ አይችሉም፡፡ እነዚህ አደረጃጀቶችም ሆኑ ግለሰቦች ሚናቸው ድጋፍ በማድረግ ላይ ብቻ የተመሠረተ ይሆናል፡፡

የተቀረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወገናችንም ተሳትፎው አገር ቤት ለሚካሔደው የህልውና ትግል ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ብቻ የተመሠረት ይሆናል፡፡

ሁለንተናዊ ድጋፍ በሚከተሉት መልኩ ይገለጻል፤

ሀ/ አገር ቤት ካለው የዐምሐራ ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀትና ተቋማዊ በሆነ አሠራር በዘላቂነት የዐምሐራ ፈንድ በማቋቋም በገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ፤ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መልሶ ማቋቋም፤ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን (ት/ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ወዘተ.) ዐቅም በፈቀደ መጠን ማሠራት፤ ለትምህርት የደረሱ የዐምሐራ ልጆችን ከሙዓለ ሕፃናት እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ አስፈላጊውን እገዛ የማድረግ፤

ለ/ በወያኔ ትግሬ ላለፉት 27 ዓመታት፤ በፋሺስታዊው አገዛዝ ላለፉት 5 ዓመታት በዐምሐራው ሕዝብ ላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች በተለይም በወለጋ፣ በጎጃሙ መተከል፣ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በሰየመው ክፍል እና በዐዲስ አበባ የተፈጸሙና እየተፈጸሙ ያሉ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ፣ የዘር ማፅዳት፣ የዘር ማጥፋት፣ የጦርና ሌሎችም ወንጀሎችን በሚመለከት ማስረጃዎችና መረጃዎች በጥንቃቄ መሰነድ፣ በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ጥረቶች ጋር በማቀናጀት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበትን ሁናቴዎች ማመቻቸት፤

ሐ/ በተቀናጀ መልኩ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ከሚመለከታቸው መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የዐምሐራውን ሕዝብ ፍትሐዊ የህልውና ትግል  ተሰሚነት እንዲያገኝ ጥረት ማድረግ፤ ሕዝቡ በፋሺስታዊው አገዛዝ ከዘር ማጥፋት እስከ ጦር ወንጀል፣ ሆን ተብሎ በገፍ ከመፈናቀል በረሃብና በበሽታ እስከ መርገፍ እየደረሰበት ያለውን ሰቆቃ ማጋለጥ፣ ማሳወቅ፤ ስለ መብቱና ነፃነቱ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን ጨምሮ በየትኛውም መድረኮች መከራከርና መከላከል፤ ትግሉ መዳረሻዬ ብሎ ያስቀመጠው ዓላማ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዓላማ መሆኑን እና ለነሱም ጥቅም ሥጋት እንዳልሆነ ማስረዳት፤ፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝ ተወግዶ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያቆሙት መንግሥት የምዕራቡ ቅጥረኛ የሆነ ተላላኪ እንዳይሆን ብርቱ ክትትል ማድረግ፤

መ/ የሜዲያ ነፃነት ባለበት በአሜሪካና በአውሮጳ የምትገኙ ወገኖች ትግሉ ከደረሰበት ደረጃ ጋር የሚመጥን የሜዲያ ሥራ መሥራት፤ ፋሺስታዊው አገዛዝ በዐምሐራ ወገናችን በተለይ÷ ባጠቃላይ ባገራችን ላይ እየፈጸመ ያለውን የማይጠገን ጥፋት እግር በእግር እየተከታተሉ ማጋለጥ፤ ለዐምሐራ ፋኖ ድልና እንቅስቃሴ ሰፊ ሽፋን መስጠት፤ በተቻለ መጠን አገዛዙ ትኩረት ለማስቀየር በየጊዜው ለሚሰጣቸው አጀንዳዎች ማስተጋቢያ ላለመሆን መጠንቀቅ፤ ትግሉን ለማዳከም ከፋፋይና አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን የሚያደረጉ አደረጃጀቶችም ሆኑ ግለሰቦች ካሉ በቅድሚያ በውስጥ እንዲመከሩ ማድረግ፤ እምቢተኛ ሆነው በአፍራሽ ድርጊታቸው ከቀጠሉ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ÷ማጋለጥ፤

ሠ/ ምሁራን ጥናትና ምርምር በማድረግ ኢትዮጵያውያኖች በጋራ ለሚያቋቁሙት ሥርዓተ መንግሥት በግብዓትነት የሚያገለግል ሰነዶች ማዘጋጀት፤ ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ፤

ረ/ ባገር ቤት በዐውደ ውጊያዎች ላይ በሚገኘው ተዋጊው የዐምሐራ ፋኖም ሆነ በየደረጃው ያሉ የፋኖ አመራሮች አሠራር እንዲሁም በሕዝቡ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ማናቸውንም ከፋፋይ ሥራ ከመሥራት መቆጠብ፤ አፍራሽ አካባቢያዊ (የመንደርተኛነት) ዝንባሌዎችን ከማሳየት መቆጠብ፤

በነገራችን ላይ በአራቱም ክፍላተ ሀገራት መሬት ላይ ያለው የዐምሐራ ፋኖ÷ አመራርና ደጀኑ ሕዝብ ተግባብቶ፣ ጽሙድ እንደ ገበሬ ቅኑት እንደ በሬ ሆኖ ለህልውናው ተጋድሎ ከማድረግም አልፎ ነፃ ያወጣቸው ግዛቶቹ ላይ ፍትሐዊ አስተዳደር እየዘረጋ ነው፡፡ ለአሉባልታና ለንቁሪያ ጊዜም ፍላጎትም የለውም፡፡ በዋሻው መጨረሻ ላይ የሚታየውን መዳረሻ ወጋገን ብርሃን ራሱም ሕዝቡም እንዲያይ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ንቁሪያው ወሬው አሉባልታው ስንጥቁ ክፍተቱ እየተባለ የሚነገረው ውጭ በሚገኘው በዐምሐራ ስም የተቋቋመው ቊጥሩ በውል የማይታወቅ አደረጃጀት ነው፡፡ አንዳንዱን ማኅበራት የሚያምሱ በውስጣቸው ለፋሺስታዊው አገዛዝ ያደሩ አፍራሽ ሆዳም ኃይሎች አሉ፡፡  አገር ቤት ያለው ባንዳ ተለይቶ የታወቀ በመሆኑ ጀግኖቹ እያፀዱት ነው፡፡ ባንዳነቱ ካገር ቤቱ ይልቅ በውጩ ያይላል፡፡ ሌሎችም ፍላጎቶችና ጥቅሞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ በግልጽ ማሳወቅ የምንፈልገው የዐምሐራውም ሆነ የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የናንተን ንቁሪያና አሉባልታ ለመስማት ጊዜውም ሆነ ፍላጎቱ የለውም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ከንቱ ወሬ በሚዲያ እያነሣችሁ በሀገር ቤት በሚደረገው ትግል ላይ ክፍተት ለመፍጠር ምክንያት እንዳትሆኑ አጥብቃችሁ ልታስቡበት ይገባል፡፡ ሚናችሁ ድጋፍ ነውና ይህንን ባግባቡ ለመፈጸም ከፈለጋችሁ የውስጣችሁን ትርምስና ጉሽሚያ (ትልቅም ይሁን ትንሽ) እዛው በጓዳ ጨርሳችሁና ተስማምታችሁ ድጋፋችሁን ቀጥሉ፡፡ በሳንቲም ምክንያት በጀግኖቻችን መካከል ስንጥቃት ለመፍጠር የምታልሙ ካላችሁ ባትሞክሩት ይሻላል፡፡ እውነት እላችኋለሁ የኢትዮጵያ አምላክ ያለጥርጥር ይሰነጥቃችኋል፡፡ ድጋፋችሁ ቢቀር እንኳን ቢያንስ እንቅፋት እንዳትሆኑን አደራችሁን፡፡ ልመና አይደለም፤ ብርቱ ማስጠንቀቂያ እንጂ፡፡ ዐምሐራው ለይተው ከታወቁት ጠላቶቹ ይልቅ መከራውን ያራዘሙት በድርጅትም ይሁን በግለሰብ ደረጃ ያሉ ከውስጡ የበቀሉ እንክርዳዶች ናቸውና፡፡ ነገራችን የምጣዱ ሳለ የዕንቅቡ ተንጣጣ እንዳይሆንብን፡፡ 

4ኛ/ የ‹‹ፖለቲካ ማኅበራት›› 

በእኔ እምነት በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ባለው የቃሉ መመዘኛ በኢትዮጵያ ውስጥ የ‹ፖለቲካ ማኅበራት› የሉም፡፡ ባጭሩ በአራት ምክንያት፡፡ 1/ በጐሣ በተደራጀ ፖለቲካ ውስጥ በተግባር የጐሣ እንጂ የፖለቲካ ማኅበራት ሊኖሩ ስለማይችል፡፡ 2ኛ/ የፋሺስታዊው አገዛዝ ተፈጥሮ ስለማይፈቅድ፤ 3ኛ/ በስብስቦቹ የዓላማ፣ አደረጃጀት፣ በአመራሮች ሰብእና ችግር፣ ጥቂት በማይባሉ አባላት ጭፍን ተከታይነት፣ በጽሑፍ የሰፈረ ዓላማና መግለጫ ቢኖርም እንኳን እስከ ሞት ለመታመን ዝግጁ ያለመሆን ወዘተ. ችግሮች፡፡ 4ኛ/ በ1960ዎቹ የተነሣውና ‹ያ› የሚባለው ትውልድ በጥላቻና በመጠላለፍ ላይ የመሠረተውና አሁን ድረስ የዘለቀው ቆሻሻ የፖለቲካ ባህል፡፡ ይህ ማለት ግን ፋሺስታዊው አገዛዝ በወረቀት ላይ የመዘገባቸው፤ በፈለገው ጊዜ ከወረቀቱ የሚሠርዛቸው፤ በተግባር የተቋቋሙበትን ዓላማ ማስፈጸም የማይችሉ፣ በአመዛኙ ለአገዛዙ ያደሩና ለሥልጣኑ የሐሰት ሕጋዊ ድጋፍ ወይም ተቀባይነትን (legitimacy) እንዲያሰጡት የሚፈልጋቸው የጥቅም ስብስቦች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ ለሕዝባችን ዕዳ እንጂ ሀብት ለመሆን ያልቻሉ ናቸው፡፡ 

እነዚህ የጥቅም ስብስቦች ዐምሐራው ማኅበረሰብ በማንነቱ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ለመናገር እንኳን የሚሰቅቅ መከራ ሲፈራረቅበት፣ ሲታረድና ሲፈናቀል ሕዝብን አስተባብረው በሰላማዊ ሰልፍ እንኳን ተቃውሞ ለማድረግ ያልቻሉ ሲሆኑ፣ የተለመደውን ባዶ መግለጫ በማውጣት ለማውገዝ እንኳን አንድ ሁለት ከሚባሉ ስብስቦች በቀር የውግዘት መግለጫ ለማውጣት የማይችሉና የማይፈልጉ መሆኑ በተግባር ታይቷል፡፡ ሕዝብ በምሬት ትግል ሲጀምር ግን የትግሉ አካል ሆኖ መሥዋዕትነት ለመክፈል ወይም ለማገዝ ሳይሆን ትግሉን ለመጥለፍና ሥልጣን ባቋራጭ ለማግኘት የሚቋምጡ ወይም ግዳይ ጥሎ ለአገዛዙ አሳልፎ ለመሰጠት የሚሯሯጡ ወይም ባይችሉም ትግሉን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ኃይሎች ናቸው፡፡ እውነቱን ለመናገር ብዙዎቹ ስብስቦች አገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም ውር ውር ከሚሉ አቋም አልባ፣ ትኩረት ፈላጊዎችና በሐሰተኛ ኢትዮጵያዊነት ካባ ከተጀቦኑ ጥቂት ግለሰቦች በቀር ይህ ነው የሚባል የሕዝብ መሠረት ያላቸው አይደሉም፡፡ በመሆኑም በተቃዋሚ ‹ማኅበራት› ስም ባገዛዙ ተመዝግበው ባገር ውስጥ የሚገኙም ይሁኑ ሳይመዘገቡ በውጩ ዓለም የሚገኙ ስብስቦች ካሉ በዐምሐራው የህልውና ትግል ረገድ  የምንጠብቀው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የለም፡፡ ምናልባትም ከእነዚህ ስብስቦች ጥቂቶቹ ባፍም በመጣፍም ሆነ በተግባር ከፋሺስታዊው አገዛዝ ጋር ካልተባበሩ ወይም በሕዝባዊ ትግሉ ጣልቃ ገብተው እንቅፋት ካልሆኑ እንድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡

ድል ለዐምሐራ ፋኖ! ድል ለኢትዮጵያ! አምላከ ኢትዮጵያ ጀግኖቻችንን ባንድነት ያጠንክርልን፡፡ ሕዝባችንን ከኃይለ አጋንንቱ ይታደግልን፡፡

Filed in: Amharic