>

የህልውናው ትግል በውስጥም በውጭም ብርቱ ጥንቃቄ ይፈልጋል!

የህልውናው ትግል በውስጥም በውጭም ብርቱ ጥንቃቄ ይፈልጋል

ከይኄይስ እውነቱ

በኢትዮጵያ ላይ ላለፉት 5 ዓመታት የሰፈነው በሥጋዊው ሕይወት ሠልጠንሁ ከሚለው ዓለም በእጅጉ ያፈነገጠ ድንቁርናና ዕብደትን ገንዘቡ ያደረገ የመጨረሻ ኋላ ቀር አገዛዝ ነው፡፡ 16ኛውን ክ/ዘመን ወደ 21ኛው ክ/ዘመን በከፋ መልኩ ጎትቶ ያመጣ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አገዛዝ ባሕርይው ለድርድር የተሠራ አይደለም፡፡ 

የፋሺስታዊው አገዛዝ መሠረትና ጉልላቱ ቅጥፈትና ማጭበርበር ነው፡፡ የሞራልና ሥነ ምግባር መቅኒ ከሌለው አጋንንታዊ ኃይል ጋር ነው ውጊያ የገጠምነው፡፡ እንኳን እግዚአብሔርን መፍራት ያህል ተቀዳሚውን ጥበብ ቀርቶ እምነት አልቦ ከሆኑ ሰዎች የሚጠበቅ ተራ ጨውነትና ሰብአዊነት ያልፈጠረባቸው ‹አካይስቶች› ናቸው የገጠሙን፡፡ ሥጋ ከለበሰ ጋኔን ጋር ድርድር ማድረግ ቀርቶ ስለ ድርድር ማንሣት የህልውና ትግል በማድረግ ላይ የሚገኘውን የዐምሐራን ሕዝብ በየትኛውም መመዘኛ አይመጥንም፡፡

እንደሚታወቀው የብዙኃን መገናኛ ተቋማት የመንግሥትም ይሁኑ የግል፤ መደበኛም (main stream medias) ይሁኑ ማኅበራዊ (social medias) የሕዝብን አስተያየት ቅርፅ ከማስያዝ አኳያ ትልቅ ተጽእኖ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም መደበኛ የብዙኃን መገናኛዎች በይፋ የሚገለጽ የአርትዖት ፖሊሲ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በግልጽ በጽሑፍ ባይቀመጥም በተግባር የሚያስጠብቁት ወይም የሚቆሙለት ዓለማና ጥቅም፣ የፖለቲካ ዝንባሌና አቋም አላቸው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ቢሆኑ እንደዚሁ፡፡ በተለይም የሕዝብ ትግል አካል ሆነው የተቋቋሙ ሚዲያዎች ደግሞ ለበለጠ ምክንያት ከእውነትና ፍትሕ ጎን ቆመው የትግል መሣሪያ በመሆን እንዲያገለግሉ ይጠበቃል፡፡ ባጭሩ አሁን ባለንበት በጉልበት የሚታመንበት ዓለም ውስጥ ከውግንና የጸዳ የሚዲያ አሠራር አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከዘመነ ብሉይ አንሥቶ እስከ ዘመነ ሐዲስ በዘለቀው የእስራኤልና የፍልስጤማውያን ጦርነት ዘመናዊ ሚዲያዎች የሚሰጡት ሽፋን የቊጥራቸውን ያህል የተለያየ ብቻ ሳይሆን በይፋ ካንዱ ወይም ከሌላው ጋር ጥብቅና የቆመ ነው፡፡ ባገራችንም ዓውድ የአገር ውስጥና የውጭ (በተለይም የምዕራባውያን) ሚዲያዎች በወያኔ ሕወሓት እና በኦሕዴድ/ኦነግ ጦርነት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝባችን ካስፈጁ በኋላም በምዕራባውያን ስፖንሰር ለተደረገው ‹ድርድር› ላሉት ቀልድ  የሰጡትና እየሰጡት ያለው ሽፋን እና አሁን የዐምሐራው ሕዝብ በፋሺስታዊው አገዛዝ በይፋ ጦርነት ታውጆበት የዘር ማጥፋት ሲፈጸምበት ምን ዓይነት ሽፋን እየተሰጠው ስለመሆኑ መናገር የዐደባባዩን በጆሮ ይሆንብኛል፡፡

ባገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በተለያየ ጊዜ በጉልበት በሠለጠኑ መሪር አገዛዞች ለመናገር የሚያስቸግር ግፍና በደል ሲፈጸምበት የቆየው የዐምሐራ ሕዝብ ከአምስት ዓመታት ወዲህ በተነሣው በርጉም ዐቢይ በሚመራው ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ በይፋ ጦርነት ታውጆበት የሞት ሽረት የህልውና ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ አገዛዝ የእምየ ምንይልክ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥሮ ስላለ ብቻ አንዳንዶች እንደ ‹መንግሥት› ቢቆጥሩትም በዚህ መልኩ ሊጠራ የማይገባውና የማይበቃ መሆኑን ከበቂ በላይ በተግባር ያሳየ የተራ ዱርዬዎችና አሸባሪዎች ቡድን ነው፡፡ በየትኛውም መለኪያ ከአገሩ ብሔራዊ ጥቅም፣ ነባር የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ባህል፣ የጋራ እሤቶች በተቃራኒ በመቆም ሌት ተቀን ለማፍረስ የሚሠራ፣ ተሠርቶ ያደረን አገር አፍርሼ በነባሩ ፍርስራሽ ላይ አንድ ወጥ የሆነ ጐሣ ያለበት አገር በመመሥረት ዓላማ ላይ እሠራለሁ የሚል ቡድን፣ በተለይም እገዛዋለሁ የሚለውን ሕዝብ በፍጹም ኢሰብአዊነት የሚጨፈጭፍ የባለጌ ስብስብ በዓለም ታሪክ ውስጥ ‹መንግሥት› ተብሎ ተጠርቶ አያውቅም፤ ሊጠራም አይገባውም፡፡ ጦርነቱ በይፋ ከመታወጁ በፊትም ይሁን በኋላ የውጮቹንም (ለጀግኖቻችንን ቃለ መጠይቅ ያደረገው የቢቢሲ ዐማርኛው ክፍልን ጨምሮ) ሆነ የአገር ውስጥ መደበኛና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለሰጡት ሽፋን (ካለ) ሆነ ስለያዙት አቋም ለአንባቢ ትዝብት ትቼዋለሁ፡፡ 

ከፍ ብዬ ያመለከትኋቸውን ሐሳቦች በመግቢያነት ያነሣሁበት ምክንያት ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹በየቀኑ መንኮታኮቱ የቀጠለው የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ እና ድል የሠመረለት የዐምሐራ ሕዝብ ትግል! ›› (ከ2 ሰዓት 15 ደቂቃ ጀምሮ ያድምጡ) በሚል ርእሰ ጉዳይ በኢትዮ 360 ሚዲያ የዕለቱ መርሐ ግብር ላይ ወንድማችን ሀብታሙ ከፋኖ አደረጃጀቶች መካከል ‹የዐምሐራ ሕዝባዊ ፋኖ› በሚባለው ውስጥ አመራር የሆነው ፋኖ አስረስ ዳምጤ ከኹለት ወራት ገደማ በፊት ለቢቢሲ የዐማርኛው ክፍል የሰጠው ቃለ ምልልስ ሰሞኑን መውጣቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያና መወዛገቢያ በመሆኑ ምክንያት ለፋኖ አስረስ ዳምጤ በቀጥታ ያቀረበለትን ጥያቄዎችና እሱም የሰጠውን መልስ መሠረት በማድረግ አጠር ያለ አስተያየት ለመስጠት የሚያስገድደኝ ሁናቴ በመፈጠሩ ነው፡፡ ይኸውም፤

1ኛ/ ፋኖ አስረስ ዳምጤና ሌሎች ጓዶቹን ቃለ መጠየቅ ያደረገው ዓለም አቀፍ የዜና አውታር ቢቢሲ (የዐማርኛው ክፍል) ከኹለት ወራት በፊት ያስተናገደውን ቃለ መጠይቅ አሁን ላይ መልቀቁ አጋጣሚ ወይስ ሆን ብሎ የተደረገ? ፍላጎቱስ ምንድን ነው?

2ኛ/ ጦርነት በታወጀባቸው አራቱም የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት (ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃምና ጎንደር) የዐምሐራን ሕዝብ በደጀንንት ከጎኑ አሰልፎ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኘውን የዐምሐራ ሕዝብ በድጋፍነት ይዞና የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ተቀባይነት አግኝቶ ለህልውናው ብሎም የጋራ ቤታችን ለሆነችው ኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና የሕዝብ አንድነት በአጥንትና በደም መሥዋዕትነት እየተፋለመ የሚገኘው የዐምሐራ ፋኖ አንድ ወጥ አደረጃጀትና አመራር ሳይኖረው በዓለም አቀፍ ሚዲያ ቀርቦ፣ የአራቱንም ክፍላተ ሀገራት ፋኖ አመራሮችን አሳትፎና ይሁንታ አግኝቶ÷ በዘርፉ በዕውቀትና ልምድ የለዘቡ የዐምሐራ ተወላጆችን (በውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙትን) አማክሮ በጥናት ላይ ተመሥርቶ አቋም ሊያዝበት የሚገባውን እጅግ አንኳር አጀንዳ በተናጥል ማቅረብ በትግሉ ላይ የሚኖረው አንደምታ በሚገባ ታስቦበታል ወይ የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ በጥንቃቄ መመልከት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

ከፍ ብዬ ያነሳኋቸውን ኹለት ነጥቦች ከመመልከቴ በፊት በየትኛውም አደረጃጀት ሆነው የዐምሐራን ሕዝብ ህልውና ብሎም በጐሣ ፋሺስታዊ አገዛዝ ሥር ወድቃ የግዛትና የሕዝቧ አንድነቷ፣ ሉዐላዊነቷና ብሔራዊ ክብሯ በቋፍ የምትገኝ አገራችን ኢትዮጵያን ለመታደግ በፊት ለፊት ረድፍ ተሰልፈው ውድ ሕይወታቸውን እየሰጡ ላሉ (ወንድማችን ፋኖ አስረስን ጨምሮ) የዐምሐራ ፋኖዎች በሙሉ በቃላት የማይገለጽ ከልብ የመነጨ አክብሮት÷ ፍቅርና ኩራት ያለኝ መሆኑን ለመናገር እፈልጋለሁ፡፡ ዐቅሜ የፈቀደውን ከማድረግ ጋር በጸሎት ሁሌም ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡ እውነትንና ፍትሕን በመያዛችሁ የኢትዮጵያ አምላክ ከናንተ ጋር መሆኑን ለአፍታ አልጠራጠርም፡፡ 

በመቀጠል በተራ ቊጥር 2 ካነሣሁት ወንድማችን ፋኖ አስረስ ዳምጤ ለቢቢሲ የዐማርኛው ክፍል ከኹለት ወር ገደማ በፊት ሰጥቼዋለሁ ያለውን ቃለ መጠይቅ መሠረት አድርጎ ወንድማችን ሀብታሙ አያሌው ላቀረበለት ጥያቄዎች የሰጠውን መልስ እንመለከታለን፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን አስተያየት የምንሰጠው ፋኖ አስረስም ይሁን ጓደኞቹ ለምን ቃለ መጠይቅ አደረጉ ፣ የተደራጁበትን ክፍል ወክለው ለምን ሐሳባቸውን ሰነዘሩ በሚል ለመውቀስ አይደለም፡፡ ዓላማው በእንዲህ ዓይነቱ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ላይ (ቋንቋው ዐማርኛ ቢሆንም) የሚሰጡ አስተያየቶችና አቋሞች በህልውና ትግሉ ላይ የሚኖራቸው ጥልቅ አንደምታ በጥንቃቄ መረዳት ስለሚያሻ፣ ከትግሉ በተቃራኒው የተሰለፉ ክፍሎች በተዛባ ሁናቴ ሊተረጕሙ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል በመኖሩና የኹሉም ፋኖዎች አቋም ተደርጎ ሊወሰድ ስለሚችል ብዥታ፣ ውዥንብር እና ከከፋም ክፍፍልን ሊፈጥር ስለሚችል ለወደፊቱ ጥንቃቄና እርምት እንዲወሰድበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ወንድማችን ሀብታሙ ጥያቄውን በምን ዓይነት ትህትናና ጥንቃቄ እንዳቀረበ፣ ፋኖ አስረስ ካነሳቸው መልሶች ተነሥቶ ወይም ከዛ ውጭ ጠንካራ ጥያቄዎችን ማቅረብ እየቻለ ማለፉ ለፋኖዎች ያለውን ስሱነት፣ በዚህም ምክንያት ጠላቶች የሚፈልጉት ማናቸውም ዓይነት ስንጥቃት እንዳይኖር ያለውን ሥጋት በእጅጉ ያሳያል፡፡ ያም ሆኖ በየትኛውም ደረጃ ያለ መሪ ግለሰብ ወይም ቡድን (ፊደል የቆጠረ ይሁን ምሁር ወይም በሕይወት ተሞክሮ የበሰለ ሰው) ፍጹምነት ስለማይኖረው ዕውቀቱና ልምዱም ውሱን ሊሆን ስለሚችል ለምን ተሳሳትሕ አይባልም፡፡ ሆኖም የምንናገርበት ዓውድ በሕዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ብቻ ሳይሆን የዘር ማጥፋት ዘመቻ በመሆኑና የአገር ህልውናም አደጋ ላይ በመውደቁ፣ ፈጻሚውም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተነሡ አገዛዞች አንዳች የመንግሥትነት ጠባይ የሌለው አረመኔያዊ ቡድን በመሆኑ በቀላሉ ልናልፈው የማይገባ መሆኑን ለማሳሰብ ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም ትንሽ ጨከን ብዬ ብናገር እኔም ለፋኖ የህልውና ትግል ካለኝ ስሱነትና ፈጣሪ ያዘጋጀልን ከባርነት መውጫ የመጨረሻ መንገድ ነው ብዬ ስለማምን ማናቸውም ስሕተት በእጅጉ እንዳያስከፍለን ከመሥጋት መሆኑን ፋኖ አሰግድና ጓዶቹ እንደሚረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አ/ አሁን የዐምሐራ ሕዝብ የገጠመው የህልወና አደጋና ኢትዮጵያ እንደ ሉዐላዊ አገር ለመቀጠል የገጠማት ውስብስብ ችግር ከመደበኛው የወጣ እጅግ ልዩ ሁናቴ በመሆኑ፤ ከተለመደው መንገድ ወጣ ያለ ልዩ መፍትሄ የሚሻ ነው (an extraordinary situation/exceptional circumstance to be addressed with or warranting an extraordinary measure)፡፡ ከመደበኛ ወጣ ያለ የሚለው አገላለጽ በዋናነት ጦርነቱንም ሆነ አገዛዙን ይመለከታል፡፡ ባጠቃላይ አገራችን በአራቱም ማዕዝናት የምትገኝበትንም ውስብስብ ሁናቴ ይመለከታል፡፡ አገዛዝ ነኝ የሚል አካል በየትኛውም አገር ቢሆን አሁን በምናየው ደረጃ የገዛ ሕዝቡ ላይ (ሕዝቤ ነው ብለው ባያምኑም እንኳን) ጦርነት ዓውጆ ዘር በማጥፋት ዓላማ የውጭ ጠላትን በሚፋለምበት መጠን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በከፋ መልኩ የሕዝቡን ሀብት ተጠቅሞና ለትውልድ የሚተርፍ ብድር ተበድሮ በሚገዛ መሣሪያ ለማጥፋት መነሣት በየትኛውም መመዘኛ መደበኛ ሁናቴ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ይህንንም የሚፈጽመው ኃይል ሆነ ሠራዊቱ ‹መንግሥትና የመንግሥት መከላከያ ኃይል› ነው ብሎ መውሰድ ጤናማ አስተሳሰብ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ነባር አገርና ሕዝብ አጥፍቶ ዐዲስ አገር በነባሩ ፍርስራሽ ላይ እገነባለሁ የሚል ኃይል ከወራሪ ጠላት የከፋ ፋሺስታዊ ወይም ናዚያዊ የጥፋት ቡድን ከሚል ስያሜ በቀር መደበኛ በሆነ አጠራር ‹መንግሥት› ተብሎ እውቅና ሊሰጠው አይችልም፡፡ በቅድሚያ ‹‹ድርድር›› የምንለውን ኹለት ወይም ከዚያ በላይ ባሉና በጠላትነት በሚተያዩ አካላት መካከል አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረግ ውይይትን ከፍ ብለን በገለጽንው ከተለመደው እጅግ ወጣ ባለው ሁናቴ ማዕቀፍ ውስጥ ማየትን ይጠይቃል፡፡ 

አንድ ሕዝባዊ መሠረት እና በአብዛኛው ሕዝብ ድጋፍና ተቀባይነት ያለው ኃይል ከውጭ ጠላት በከፋ መልኩ የአገር ሥልጣን ይዞ ሆን ብሎ በሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመ፣ አገርን ለማጥፋት ቀን ተሌት እየሠራ፣ ሃይማኖት÷ ባህልና እነዚህን መሠረት አድርገው ለዘመናት የተገነቡ ቅርሶችና እሤቶችን እያጠፋ፣ የአገር ሀብት እየዘረፈና እያወደመ ወዘተ. ያለን ኃይል አስወግዶ ለሁሉም የሚሆን በእኩልነት ላይ የተመሠረት ዐዲስ ሥርዓት ከመገንባት ውጭ ከእንዲህ ዓይነቱና ቋሚ ባሕርይው ከሚታወቅ ወንበዴ ጋር ድርድርን እንደ መፍትሔ ማስቀመጥ በየትኛውም መመዘኛ ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ ኹሉ የእልቂትና የውድመት ዓመታት በኋላ የአገዛዙን ባሕርይ ተረድተናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አንድ በሽታ ነቀርሳ ደረጃ ከደረሰ (እንደ ነቀርሳው ዓይነትና መስፋፋት) ብቸኛው መፍትሔው ነቀርሳውን ከሰውነት ለይቶ ማስወገድ ነው፡፡ አለበለዚያ ነቀርሳው በመላ አካላችን ናኝቶ ዕጣ ፈንታችን ሞት ይሆናል፡፡ 

በ/ የአገዛዙ ደጋግሞ በተግባር የተመሰከረ ቋሚ ባሕርይ

የፋሺስታዊው አገዛዝ መሠረትና ጉልላቱ ቅጥፈትና ማጭበርበር ነው፡፡ የሞራልና ሥነ ምግባር መቅኒ ከሌለው አጋንንታዊ ኃይል ጋር ነው ውጊያ የገጠምነው፡፡ እንኳን እግዚአብሔርን መፍራት ያህል ተቀዳሚውን ጥበብ ቀርቶ እምነት አልቦ ከሆኑ ሰዎች የሚጠበቅ ተራ ጨውነትና ሰብአዊነት ያልፈጠረባቸው ‹አካይስቶች› ናቸው የገጠሙን፡፡ ሥጋ ከለበሰ ጋኔን ጋር ድርድር ማድረግ ቀርቶ ስለ ድርድር ማንሣት የህልውና ትግል በማድረግ ላይ የሚገኘውን የዐምሐራን ሕዝብ በየትኛውም መመዘኛ አይመጥንም፡፡ አገዛዙ በየትኛውም መለኪያ የማይታመን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሕዝብ መካከል ክፍፍልን፣ መለያየትንና አለመተማመንን ከመፍጠር ባሻገር አንድ ዓይነት ዓላማ አለን የሚሉ ኃይሎች እንኳን በጋራ ተባብረው መሥራት የማይችሉበት ደረጃ እንደደረሱ አስተውለናል፡፡ 

ገ/ ከጉልበተኞች አደራዳሪዎች የተለየ መንገድ

እምንነጋገረው ስለ ልዩ (exceptional) ሁናቴ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የገጠማት በሌላ ዓለም ላይ ከሚታየው መደበኛ ወይም የተለመደ ሒደት በእጅጉ የተለየና ወጣ ያለ እንደሆነ ከተስማማን፣ መውጫ መንገዱም የተለየ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ይህንን ከተረዳን ወንድማችን አስረስ፤ ጉዳዩ ድርድር እጅ የመስጠት ወይም የመሸነፍ ምልክት ነው/አይደለም የሚለው አይደለም፡፡ ወይም የድርድርን አስፈላጊነት ለዜና አውታሩ ከዲፕሎማሲ አኳያ ማሳወቁ አይደለም፡፡ ዘር እያጠፋ አገር እያወደመ ካለ ፋሺስታዊው አገዛዝ ጋር ለድርድር የሚያበቃ ሰጥተን የምንቀበለው አንዳች የጋራ ነገር የለንም፡፡ ያለን ብቸኛ ምርጫ ሕዝብ ድል አድርጎ ህልውናውንና አገርን መታደግ ነው፡፡ ከዚህ መለስ ያለ ‹መፍትሔ› (እንደ መፍትሔ የሚቆጠር ከሆነ) አገዛዙ እንዲቀጥል ዕውቅና መስጠትና እንደ እባብ አፈር ልሶ እንዲነሣ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በደም በሕይወት የታተመው መሥዋዕትነት ከንቱ ሊሆን ነው፡፡ ማሰብ ያለብን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መፍትሔ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ አገዛዝ ‹የሽግግር ሥርዓት› ይኑር ብሎ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ አንድም ስለማይቀበለው ተግባራዊ አይሆንም፤ ባንፃሩም አገዛዙ የፈጸማቸው ወንጀሎች እጅግ ግዙፍ ከመሆናቸው የተነሣ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎች መለኪያ የሽግግር ሥርዓቱ አካል እንዲሆን አይፈቅድለትም፡፡ በመሆኑም ብልጫ የምናገኝበትን ዐቅምና ኃይል (leverage) የምንፈጥረው ለድርድር ሳይሆን አገዛዙን አስወግደን ለሃምሳ ዓመታት ቁም ስቅሉን ሲያይ ለኖረው ሕዝባችን እፎይታ ለመስጠትና ፈረንጆች እንደ መድኃኒት የማያዙልን ሀገር በቀል እሤቶችን መሠረት ያደረግ ለአብሮነት የሚበጅ የእኩልነት ሥርዓት ለመፍጠር መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከግል ጥቅምና የሥልጣን ፍትወት ርቆ አገርንና ሕዝብ ለሚያስቀድም ኹሉ ይቻላል፡፡ 

ደ/ ሌላው ድርድርን በሚመለከት ተደጋግሞ እንደ ዶግማ ሲነገር የምሰማው አባባል አለ፡፡ ሁሌም የጦርነት ወይም ሌሎች ግጭቶች መደምደሚያ ድርድር ነው የሚል፡፡ ማን ነው ያለው? በሥነ ጽሑፍ የተቀመጡ ሰው ሠራሽ መፍትሔዎች እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ቃል የማይለወጡና የመጨረሻ (hard and fast rule) አድርጎ መውሰድ ስሕተት ነው፡፡ በዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እንደ አጠቃላይ ደንብና ልማዳዊ አሠራር (general rule and customary practice) ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ የጦርነት መቋጫው የግድ ድርድር ነው የሚል አመለካከት ግን አያስኬድም፡፡ ሁሌም ለጠቅላላው ደንብ ልዩ ሁናቴ (exception) ሊኖር እንደሚችል መዘንጋት የለብንም፡፡ በተራ ቊጥር ‹አ› እንደገለጽሁት አሁን ያለንበት ሁናቴ ከተለመደው ወይም መደበኛው ወጣ ያለ በመሆኑ ልዩ መፍትሔን የሚሻ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ላይ ላለፉት 5 ዓመታት የሰፈነው በሥጋዊው ሕይወት ሠልጠንሁ ከሚለው  ዓለም በእጅጉ ያፈነገጠ ድንቁርናና ዕብደትን ገንዘቡ ያደረገ የመጨረሻ ኋላ ቀር አገዛዝ ነው፡፡ 16ኛውን ክ/ዘመን ወደ 21ኛው ክ/ዘመን በከፋ መልኩ ጎትቶ ያመጣ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አገዛዝ ባሕርይው ለድርድር የተሠራ አይደለም፡፡ ፈረንጆቹ በታዛቢነት ወይም በአዛዥነት ስለሚገቡበት ሳይወድ በግዱ ይቀበላል ወይም ለድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎች ተገዢ ይሆናል የሚል አስተሳሰብ ካለ የክፍለ ዘመኑ ትልቅ የዋህነት ሳይሆን ጅልነት ይሆናል፡፡ ወገኔ ሲጀመር ምዕራባውያኑ ለእኛ አስበው እውነትና ፍትሕ ፈልገው ጣልቃ አይገቡም፡፡ በየትኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሲገቡ የሚከተሉት ብቸኛ መርህ ብሔራዊ ጥቅማቸው መሆኑ የፖለቲካ ሀ ሁ ነው፡፡ በመሆኑም ውገናቸው ከጥቅማቸው ጋር እንጂ ከየትኛውም ቡድን ጋር አይደለም፡፡ በምዕራባውያኑ የሚዘወረው ዓለም አቀፋዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥርዓት ኢ-ፍትሐዊና ሰይጣናዊ መሆኑን ለአፍታ ልንዘነጋ አይገባም፡፡ በመሆኑም ድርድር የምንለው ጉዳይ ለአንጋሽነት ሚናቸው በራችንን ብርግድ አድርገን የምንከፍትበት መንገድ መሆኑን እናስተውል፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን ደግሞ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሸፍጥ የተሞላበት ‹ድርድር› ተደጋጋሚ ሰለባ መሆኗን ግምት ውስጥ አስገብቶ ከታሪክ መማር ያስፈልጋል፡፡

ሀ/ አሁን ደግሞ በርጉም ዐቢይ የሚመራው ፋሺስታዊው የጐሣ አገዛዝ በዐምሐራ ሕዝብ ላይ የአስቸኳይ ጊዜና ጦርነት በይፋ ባወጀበት ባለፉት 6-7 ወራት ውስጥ የዐምሐራ ፋኖ አደረጃጀት በየጊዜው ከታች ወደ ላይ የሆነ ተፈጥሮአዊ ዕድገት (bottom up organic growth) እያሳየ መምጣቱ እሙን ነው፡፡ አገዛዙ እያደረሰ ካለው ጥፋት አኳያ ፍላጎታችን በአራቱም ክፍላተ ሀገራት የወታደራዊውም ሆነ የፖለቲካው አመራር አንድ ወጥ አደረጃጀት ኖሮት በማዕከል እንዲፈጸምና መሥዋዕትነቱን በቀነሰ ሁናቴ ድሉን ለማቅረብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምድር ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁናቴ ደግሞ በልዩ ልዩ አደረጃጀት ያሉ የፋኖ አመራሮችና የፋኖ ሠራዊት አባላት በተሻለ ያውቁታል፡፡ ያም ሆኖ  ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸውን በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያሉ የዐምሐራ ተወላጆችን ድጋፍና እገዛ በተጨማሪነት የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ ካንድ ብርቱ ኹለት መድኃኒቱ እንደሚባለው፡፡ ይህንንም ስል ምክሩ መምጣት ያለበት ራሱ ካልተመከረው ዮናስ ብሩን ከመሳሰሉት ፊደል ቆጥረናል ከሚሉ የአእምሮ ድውያን መሆን የለበትም፡፡ 

ወንድማችን ፋኖ አስረስ የሚገኝበት ድርጅት በፋኖ እንቅስቃሴ ውስጥ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ፣ ከጦርነቱ በፊት ረዘም ላለ ጊዜ ልምድና ተሞክሮ እንዳለው፣ የድርድር ነጥቦችንም በሰነድ እንዳዘጋጀ፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያው ጋር ቀርበው የሰጡት ቃለ ምልልስም ድርጅታቸውን ብቻ ወክለው እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ይህ ዝግጅት ለአጠቃላዩ የፋኖ አደረጃጀት እንደ ግብዐት ስለሚያገለግል መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከታላቅ አክብሮት ጋር በእኔ እምነት ዋናው ቁም ነገር እነዚህ ወንድማችን የጠቀሳቸው ነጥቦች ቃለ መጠይቁን በተናጥል ለማድረግ በተለይም ስትራቴጂካዊ ጉዳይ ላይ አቋም ይዞ ለመናገር በቂ ምክንያት አይሆኑም፡፡ ወንድማችን አስረስና የትግል ጓዶቹ ለሚዲያው ከመቅረባቸው በፊት አገዛዙ በሕዝባችን ላይ በይፋ ጦርነት ዓውጆ በአራቱም ክፍላተ ሀገራት ልዩ ልዩ የፋኖ አደረጃጀቶች ተፈጥረው ትግሉን እየመሩ፣ ሕዝቡን እያደራጁና እያስተባበሩ፣ በየጊዜው በየአካባቢአቸው ያለውን የዓውደ ውጊያ ውሎ ለሚዲያዎች መረጃ እየሰጡ እንደሚገኙ በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ጎን ለጎንም ፋታ በማይሰጠው ጦርነት ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ ወጥ አደረጃጀት ለመፍጠር አብዛኛውን ተግባራት እያገባደዱ እንደሆነ በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንንም በግንባር ቀደምትነት እያስተባበሩ ከሚገኙና የትግሉ ምልክት ከሆኑ ጀግኖች መካከል ጀግና ወንድሞቻችን አንዱ ፋኖ አስረስ በምትገኝበት የዐምሐራ ፋኖ ሕዝባዊ ኃይል መሪ የሆነው ፋኖ ዘመነ ካሤ ነው፡፡ ሲሆን የዓውደ ውጊያ ውሎዎች መረጃዎችም አንድ ወጥ ሆኖ መሰጠት ይገባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የሕዝባችንን ሞራል ከፍ የሚያደርጉ የድል ዜናዎች የትግሉን መንፈስ በግለት እንዲቀጥል ስለሚረዳና የሕዝቡንም ተሳትፎ ስለሚጨምር በልዩ ልዩ የፋኖ አደረጃጀት መሪዎች መረጃው መፍሰሱ ለጊዜው አስፈላጊና ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ስትራቴጂክ በሆኑና የሁሉም ፋኖ አደረጃጀቶች አንድ ወጥ አደረጃጀትና መዋቅር ፈጥረው የጋራ አቋማቸውን የሚያሳይ መግለጫ ሰነድ እስኪዘጋጅ ድረስ በተናጥል (ድርጅትን ወክሎም ቢሆን) አንኳር በሆኑ ጉዳዮች ያውም ለዓለም አቀፍ ሚዲያ ቃለ ምልልስ መስጠት ተገቢና ለትግሉ የሚጠቅም ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሚዲያው ስለ ድርድር ጉዳይ ሲያነሣ ወንድማችን ፋኖ አስረስ አምኜበታለሁ ያለውን ቢገልጽም ‹ይህን ጉዳይ በሚመለከት ለመናገር ሕጋዊ ውክልና የለኝም፡፡ ሁሉንም የፋኖ አደረጃጀቶች የሚወክል ድርጅት ሲቋቋም መልስ የሚሰጥበት ይሆናል› ብሎ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ማለፍ ይቻል ነበር፡፡ ይህን የምለው ለመማማር ነው፡፡

ለአንድ ዓላማ እስከተሰለፍን ድረስ አደረጃጀቶች በተናጥል የሚሰጡት መግለጫና ቃለ መጠይቅ በጦር ሜዳ ሽንፈት እየገጠመው ላለው ጠላት የመከፋፈያ አጀንዳ ማቀበል ይሆናል፡፡ ሥርዓት በማክበር የሚታወቅና ያስመሰከረ ሕዝብ መገለጫም አይሆንም፡፡ ፋሺስታዊው ኃይል ደግሞ በዚህ እኩይ ተግባር የተካነ መሆኑን ስለምናውቅ ለወደፊቱ ጥንቃቄ ማድረጉ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለጠው የጠላት ኃይል ጥንካሬ መሠረቱ የኛ ድክመት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ዋናውን መሥዋትነት በሕይወት በደም እየከፈላችሁ በመሆኑ ሌላውን አንድ ወጥ አደረጃጀት ከፈጠርን በኋላ እንደርስበታለን፡፡ በዚህ ረገድ ጥቃቅን ልዩነቶች ካሉ በቶሎ ፈትቶ በጉጉት የሚጠበቀውን አደረጃጀት እውን በማድረግ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ያለንን ብቃት በዓለም ፊት ማስመስከር እንችላለን፡፡ 

ለንጽጽር እያቀረብኹ ባይሆንም ‹ትሪፕል ኤ› የተባለው በውጭ የሚገኝ ድጋፍ ሰጭ ‹የዐምሐራ ድርጅት› ያለ ሕጋዊ ውክልና የፈጸመው ስሕተት ብዙ አቧራ እንዳስነሣ ኹሉ የጀግንነቱ ቦታ ባላችሁት በዋኖቻችን ተመሳሳይ ስሕተት ሲፈጸም ማየትም ትክክል አይሆንም፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል!!! ልንል ይገባል፡፡

ሌላውና ከፍ ብዬ በተራ ቊጥር አንድ ያነሣሁት የቢቢሲ የዐማርኛው ክፍል ቃለ መጠይቁን አሁን ላይ መልቀቁና አንዳንድ መረጃዎችንም (የፋኖ አስረስ ዳምጤ ኃላፊነትን እና እሱ ‹የዐምሐራ ፋኖ ሕዝባዊ ኃይል› የተባለውን ድርጅት ብቻ ወክሎ መቅረቡ እየታወቀ አጠቃላይ በአራቱም ክፍላተ ሀገራት ያለውን የዐምሐራ ፋኖ እንደሚወክል አድርጎ ማቅረብ) አዛብቶ ማቅሩቡ ሆን ብሎ ይሁን በስሕተት ግልጽ አይደለም፡፡ ድብቅ አጀንዳ ኖሮት ወይስ ሌላ ምክንያት?

አንባቢያን! በጽሑፌ መግቢያ ላይ ስለ ሚዲያዎች የሰጠሁትን አስተያየት በሚገባ አስተውሉ፡፡ በዚህ ረገድ ርእሰ መጻሕፍቱ ‹‹የጥፋትን ርኵሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል›› የሚለውን ከማስታወስ ባለፈ ብዙ መናገርን አልፈቅድም፡፡ 

ድል ለዐምሐራ ፋኖ! ድል ለኢትዮጵያ! አምላከ ኢትዮጵያ የዐምሐራ ፋኖን ኅብረትና አንድነት ያጠንክርልን፡፡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ያድርግልን፡

Filed in: Amharic