>

ኢትዮጵያዊ ዜግነት፤ በዓለማዊ ሕይወት እና በመንፈሳዊ ሥልጣን

ኢትዮጵያዊ ዜግነት፤ በዓለማዊ ሕይወት እና በመንፈሳዊ ሥልጣን

ከይኄይስ እውነቱ

በቅድሚያ የዜግነት ትርጕም ምንድን ነው? መንፈሳዊ ዜግነትስ?

‹‹ዜጋ፤ በቁሙ፤ ተገዥ፤ ገብር፣ ገባር፤ ጢሰኛ፣ ባላገር፡፡›› ማለት እንደሆነ ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በተባለ መጽሐፋቸው ፍቺ ሰጥተውታል፡፡

በቁሙ ሲወሰደ ‹ዜጋ› እንዳለ ዜጋ ማለት ነው፡፡ ገባርነቱ፣ ተገዥነቱ፣ ታዛዥነቱ ባላገር ለሆነበት ሀገረ መንግሥት ሲሆን፤ በባላገርነቱ ባለርስት የአገር ባለቤት ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል መንፈሳዊ ዜጋ ለእግዚአብሔር ተገዥ አገልጋይ የሆነ አማኝን ሲመለከት፣ ባላገርነቱ ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት (መንግሥተ ሰማያት) ባለርስት ወራሽ ባለቤት መሆኑን ያመለክታል፡፡ 

ዜግነት (ዜጋ መሆን) የአገር ባለቤትነት ሙሉ መብት እንደሚያስገኝ ሁሉ፤ ባለርስት ለሆነበት ሀገረ መንግሥት የገባርነት፣ የተገዥነት ወይም የታዛዥነት ግዴታንም ያስከትላል፡፡ ዓለማዊ ዜግነት በምድራዊ ሕግ የሚሰጥና የሚነፈግ ሲሆን፣ በግለሰቡ ዜጋ ፈቃድ ሊለወጥ/ሊቀየር ይችላል፡፡ መንፈሳዊ ዜግነት በእምነት እና የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዛት በማክበርና በመጠበቅ የሚገኝ የሰማያዊ አገር ዜግነት ነው፡፡ የአንድ ሰማያዊ አገር ዜግነት በመሆኑም አይቀያየርም፡፡ በሕግጋቱ የተቀመጡ መስፈርቶች እስከተሟሉ ድረስ ዓላማዊውም ሆነ መንፈሳዊው ዜግነት ዘር፣ ቀለም፣ ነገድ፣ ጐሣ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡

ዓለማዊው ዜግነት እንደ ሁናቴው በየአገሩ የበላይ ሕግና ዝርዝሩ በበታች ሕጎች የሚገዛ ነው፡፡ ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት ካቆሙበት ከ1922 ዓ.ም. (በ1948 ዓ.ም. ተሻሽሏል) ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ዜግነትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በሕገ መንግሥቷ አካትታ፣ ዝርዝር ጉዳዩን ደግሞ በ1922 ዓ.ም. ባወጣችው የኢትዮጵያ ዜግነት ሕግ (እንደተሻሻለ) ስትሠራበት ቆይታለች፡፡ ይህ ሕግ በ1996 ዓ.ም. በወጣው የኢትዮጵያ ዜግነት ዓዋጅ ቊጥር 378 ተተክቷል፡፡ በ1987 ዓ.ም. የወጣውና አሁን ሥራ ላይ ያለው የወያኔ ማስመሰያ የጐሣ ‹ሕገ መንግሥት› በዜግነት ላይ የተመሠረተ ባይሆንም በአንቀጽ 6 ላይ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማን እንደሆነና የውጭ አገር ዜጎች በሕግ የኢትዮጵያ ዜግነት ሊያገኙ እንደሚችሉ፣ ዝርዝሩም በሕግ እንደሚወሰን ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሠረት ወላጆቹ ወይም ከወላጆቹ አንዱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡ ይኸው አቋም በተጠቀሰው የኢትዮጵያ ዜግነት ዓዋጅ አንቀጽ 3 ላይ ዜግነት በመወለድ፤  እና በአንቀጽ 4 ደግሞ ዜግነት በሕግ (naturalization) እንደሚገኝ ደንግጓል፡፡ መሟላት ያላባቸውንም መስፈርቶቹ በተከታታይ ድንጋጌዎች አስቀምጧል፡፡ ይኸው ዓዋጅ ዜግነት ስለሚቀርበት ሁናቴም በአንቀጽ 20 ደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በራሱ ፈቃድ የሌላ አገር ዜግነት ካገኘ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን በራሱ ፈቃድ እንደተወ ይቆጠራል ይላል፡፡ በዚህም ሕጉ ጣምራ ዜግነትን (dual citizenship/nationality) ይከለክላል፡፡

ሌላው ተያያዥነት ያለው ሕግ ‹‹የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎችን በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ›› በዓዋጅ ቊጥር 270/1994 ዓ.ም. (እንደተሻሻለ) የወጣው ዓዋጅ እና ይህንን ዓዋጅ ለማስፈጸም የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቊጥር 101/1996 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ሕግ ከስያሜው እንደምንረዳው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ተፈጻሚ የሚሆን ሕግ ነው፡፡ የዚህ መብት ተጠቃሚ ለሚሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎች የሚሰጠውም የኢትዮጵያ ተወላጅነት የመታወቂያ ካርድ ‹ቢጫ ካርድ› የኢትዮጵያ ዜግነትን የሚያስገኝ ወይም ለጣምራ ዜግነት ዕውቅና የሚሰጥ አይደለም፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በትውልድ አገራቸው የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሕይወት ተሳታፊ በመሆን ለራሳቸው፣ ለትውልደ አገራቸውና ሕዝባቸው ዕድገትና ብልጽግና አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ዕድል የሚሰጥ ሕግ ነው፡፡ ዓዋጁ በአንጽ 6 ላይ የኢትዮጵያ ተወላጅ ለሆኑ የውጭ ዜጎች የሚሰጠው የተወላጅነት የመታወቂያ ካርድ የሚያሰገኘውን መብትና የሚጥለውን ገደብ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ተወላጅነት መታወቂያ ካርድ የያዘ የውጭ ዜግነት ያለው ሰው በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በሚካሔድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት የለውም፡፡ እንዲሁም በማናቸውም የአገር መከላከያ የአገር ደኅንነት ወይም በውጭ ጉዳይና መሰል የፖለቲካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመደበኛነት ተቀጥሮ መሥራት አይችልም፡፡ በዚህም ከሐሳብ የዘለለ ተግባራዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለዜጎች ብቻ የተሰጠ መብት መሆኑን ያመለክታል፡፡

ከፍ ብለን የጠቀስናቸው የኢትዮጵያ ዜግነት ዓዋጅም ሆነ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ አገር ዜጎች በትውልድ አገራቸው የአንዳንድ መብቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የወጣው ዓዋጅና ደንብ በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊ አገልግሎት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እኩል ተፈጻሚነት አለው፡፡ በዚህ ረገድ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን በተለይም በከፍተኛ ማዕርግ ያለ ኤጲስ ቆጶስ፣ ጳጳስ፣ ሊቀ ጳጳስ እና በትርያርክ የውጭ አገር ዜግነት ካገኘ በገዛ ፈቃዱ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ትቷል ማለት ነው፡፡ ታዛዥነቱ፣ ታማኝነቱ በሕግ ዜግነት ለተቀበለበት አገር ይሆናል፡፡ ለዚህም በአገሩ ሰንደቅ ዓላማ ሥር ተንበርክኮ ቃለ መሐላ ይፈጽማል፡፡ ይህን ድርጊት እንደተራ ጉዳይ ቆጥሮ ዋናው ልቤ/እምነቴ እንጂ በተግባር የያዝሁት የውጭ አገር ዜግነት አይደለም የሚል ሰው ካለ ራሱን የሚያታልል ግብዝ ሰው ነው፡፡ ለማናቸውም ተግባራዊ ጉዳይ በተለይም ለአገር ውስጥም ይሁን ዓለም አቀፍ ሕግ ዓላማ የውጭ አገር ዜግነት ያለው በትውልዱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይደለም፡፡ በሕግ የተመለከቱ ዓለማዊ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ እንኳን በኃላፊነት መደበኛ ተቀጣሪ ሊሆን አይችልም፡፡ 

በከፍተኛ መንፈሳዊ ኃላፊነት ቦታስ? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሁንም ሥራ ላይ ባለው የፍትሐብሔር ሕግ መሠረት ሕጋዊ ሰውነት ያላት መንፈሳዊ ተቋም ናት፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአባልነት የያዘች፣ በሥሯ በርካታ አድባራትና ገዳማትን የምታስተዳድር፣ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ የተዘረጋ አስተዳደራዊና መንፈሳዊ መዋቅር ያላት፣ የበርካታ ግዙፍና ግዙፍ ያልሆኑ መንፈሳዊ ቅርሶችና ሀብቶች ባለቤት የሆነች፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ጸንታ ከቆመችባቸው ዓምዶች ቀዳሚና ዋነኛው ሀገር-አከል ተቋም መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህች በነቢያትና በሐዋርያት ላይ የተመሠረተች ጥንታዊትና ኵላዊት አንዲት ቤተ ክርስቲያን ከውስጥ አገር አፍራሽ ቅጥረኞች፣ ከውጭ ታሪካዊ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ባንድነት ተነሥተውባት ህለውናዋን እየተፈታተኑ ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክህነቱም ሲኖዶሱም ‹ሰው ጠፍቶበት› መንፈሳዊነትና ቅድስና ከተለየው እነሆ 34 ዓመታት እያስቆጠረ ነው፡፡ ሁናቴው ያላማራቸው ጥቂት እውነተኛ አባቶች ቀደም ብለው ገዳም ገብተው በጸሎት ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶችም በዕርግናና በሕማም ዐረፍተ ዘመን እየገታቸው፣ ጥቂቶችም በመለካውያንና ክህነት በሌላቸው ተራ ካድሬዎች ታፍነው፣ ከሁሉም በላይ ዓለማዊ ምቾትና ድሎት አላላውስ ያላቸው ደግሞ ከምእመኑ ገንዘቡን ፈልገው ከቤተ መንግሥቱ ደግሞ በጥብዐት መጋደልን ፈርተው ብቻ ሳይሆን በ‹ነውርና ነቀፋ› ማስፈራሪያ ተይዘው በኹለት ልብ እያነከሱ ክርስቶስ የሞተላትን ቤተ ክርስቲያን የአውሬዎች መፈንጫ የጐሠኞች ተራ ሸንጎ አድርገዋታል፡፡ እነዚህ ራሳቸውን ማዳን የማይችሉ ‹ድኩማኖች› ቤተ ክርስቲያንን እና አገርን ሊታደጉ ቀርቶ ለቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ ለአገር ዕዳ ሆነዋል፡፡ ምእመኑ እና ሊቃውንት እንዳይንቀሳቀሱም እጅ ከወርች ጠፍረው ይዘዋል፡፡ በተለያየ አገላለጽ ‹አያገባችሁም› ብለውናል፡፡ ‹እረኞቹ› የማሰማርያውን በጎች አጥፍተዋል÷ በትነዋል፡፡ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ወዮላችሁ ተብለዋል፡፡ ከማሕፀን ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ ባለው በነቢዩ ኤርምያስ አድሮ በጎቹን ስላባረሩ፣ ስለበተኑ፣ ስላልጎበኙም እነሆ የሥራችሁን ክፋት እጎበኝባችኋል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ ከአድርባይነት የፀዱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን የአገርና የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ማንንም ሳይጠብቁ ጉዳዩን በእጃቸው ማስገባት ያለባቸው ጊዜ ዘግይቷል ካልተባለ በቀር አሁን ይመስለኛል፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና ከፍተኛ መንፈሳዊ ሹመትን እና ዜግነትን በሚመለከት መንፈሳዊው ሕግ (ካለ) ምን ይላል? በጥቁርና በነጭ የተጻፈ ደንብ ባይኖርስ ከአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቷ መሠረተ እምነት፣ ቀኖና እና ክርስቲያናዊ ትውፊት መንፈስ አኳያ፤ ደጋግሞ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያኒቷ አገር የሠራች ሀገር-አከል ኢትዮጵያዊ ተቋም ከመሆኗ አኳያ፤ ኢትዮጵያን ከቤተ ክርስቲያኗ ነጥሎ ማየት የማይቻል ከመሆኑ አኳያ፤ ‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይቻላልን?›› ከሚለውና ቀደም ሲል በተጠቀሰው ታላቅ ነቢይ ከተነገረው ቃለ እግዚአብሔር አኳያ ወዘተ. ሲታይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ስደተኛ ዜግነታቸውን በለወጡ ‹አባቶች› መመራት አለባት? ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን የቀየረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የውጭ አገር ዜጋ ወሳኝ በሆነው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሕይወት (በመንግሥት ተቋማት፣ በአገር መከላከያና ደኅነት ወዘተ.) እንዳይሳተፍ ገደብ የተጣለበት ከሆነ ለመንፈሳዊውማ ለሰማያዊው መንግሥትማ ለላቀ ምክንያት መለኪያው መመዘኛው (threshold/ bar) በእጅጉ ከፍ ሊል አይገባውም? የአመክንዮ ሕግስ አያስተምረንም? መቼም መንፈሳዊ አባት ዜግነት የለውም የሚል የማይረባ መከራከሪያ የሚያቀርብ ካለ ጉድ በል ሺዋ ከማለት ያለፈ የምለውም የለኝም፡፡ ይሄ ዓለምን ንቆ አጥቅቶ በምንኵስና ሕይወት የሚገኘውን ሰማያዊ ክብር ትቶ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ በማለት ለጽድቅ ምውት ለዓለም ሕያው የሆኑ፣ ከመንፈሳዊነት የተፋቱ ‹ዘመናዊ መነኰሳት› ደካማ የመከራከሪያ ነጥብ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ሊቃውንት አባቶቻችን ባንድ ወቅት በጾም ‹ዓሣ ይበላል/አይበላም› የሚል የእንብላ ባዮች ክርክር ተነሥቶ ‹አድልዑ ለጾም› (ለጾም አድልታችሁ ወስኑ) በማለት ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ 

አሁን በመንበሩ ላይ ያሉት በትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከገባችበት ማጥና ካጋጠማት ፈተና እንዴት እንደምትወጣ ተጠይቀው ከኹለተኛው በትርያርክ ሹመት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗ ከሥርዓት ወጥታለች በማለት አሁን ላይ የሚስተካከል ነገር የለም የሚል አንድምታ ያለው የተስፋ መቁረጥ የሚመስል አነጋገር መሠንዘራቸው ይታወሳል፡፡ ካፈርሁ አይመልሰኝ ይመስላል፡፡ በዚህም በዜግነት ጉዳይ የተለየ ሕግ ያስፈልጋል የሚል እምነት ባይኖረኝም አመዛኙ ተድላ ደስታ ያሸነፋቸው በመሆኑ ወደ ምቾት አድልተው እንደሚወስኑ አልጠራጠርም፡፡

በነገራችን ላይ ርእሰ ጉዳይ ስላደረግነው የኢትዮጵያ ዜግነት ጉዳይ ስንነጋር ቤተ መንግሥቱም ሆነ ቤተ ክህነቱ ሥራ ላይ ያለውን ሕግ ባለማክበር የማይታሙ መሆናቸውን መግለጽ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ 

ወደ ነጥቡ ስንመለስ አሁን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በውጭ ኖረው የውጭ አገር ዜግነት ይዘው ስለነበር በትርያርክ ለመሆን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያስፈልጋል የሚል መመሪያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንደዋለ ሰምተናል፡፡ በትርያርኩ ከሊቃነ ጳጳሳቱ ቀዳሚና የበላይ መሆናቸው እንጂ ነገ ተነገ ወዲያ በበትርያክነት የሚሰየም አባት ከሊቀ ጳጳሳቱ አንዱ ነው፡፡ በቤተ ክህነቱ፣ በሲኖዶሱ ያሉ መሠረታዊ ችግሮች በእግዚአብሔር ቸርነት በምእመናንና ሊቃውንት ትጋት ተቃልለው የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነትና ቀኖና በጠበቀ መልኩ እውነተኛ መንፈሳዊ አባቶች የመሰየሙ ተግባር ለወደፊቱ ይከናወናል በሚል ተስፋና እምነት ይዘን፣ በትርያርክ ሊሆን የሚችለው አባት ከሊቀ ጳጳሳቱ አንዱ ከሆነ ለበትርያርኩ የተቀመጠው የዜግነት መመዘኛ በእኩል ደረጃ ለሊቃነ ጳጳሳቱም ተፈጻሚ እንደሆነ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይገባውም፡፡ ለበትርያርክነት የሚሰጠው ምክንያት ለሊቀ ጳጳሱትም በእኩል ይሠራልና፡፡ ጥብዐቱ ያላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካላችሁ ሐዋርያት ከሠሯቸው የሐዲስ ኪዳን የሥርዓት መጻሕፍት ውስጥ ለዚህ የዜግነት ጉዳይ መልስ የሚሰጥ ቀኖና ሊኖር ስለሚችል ለምእመኑ ማሳወቅ የናንተ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ምሳሌው ሕፀፅ ቢኖርበትም ኢትዮጵያዊ መንግሥት ባለበት ሥርዓት አንድ ኢትዮጵያን ወክሎ በአምባሳደርነት ወደ ውጭ የሚላክ ዲፕሎማት በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ አገር ዜጋ ሊሆን አይችልም፡፡ ባለርስት ወይም ባላገር ያልሆነበትን አገር ሊወክል አይችልምና፡፡ ታማኝነቱ፣ ታዛዥነቱ ወይም ገባርነቱ ለኢትዮጵያና ለሰንደቅ ዓላማዋ አይደለምና፡፡ ከሁሉም በላይ ዲፕሎማሲ/ዓለም አቀፍ ግንኙነት የፖለቲካ ሥራ በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው ሰው የሚሠማራበት የሥራ መስክ አይደለምና፡፡ በተመሳሳይ መልኩ (አገልግሎቱ መንፈሳዊ ቢሆንም) ጳጳሳት ከአገር ውጭ ወዳሉ አኅጉረ ስብከቶች የሚላኩት ለሐዋርያዊ አገልግሎት ነው፡፡ ቆይታው ሥርዓት ተደርጎ የጊዜ ገደብ ሊበጅለት የሚችል ነው፡፡ ዘላለማዊ ሹመት አይለም፡፡ ለሐዋርያዊ ተልእኮ የሚቆይበትን አገር ዜግነት እንዲወስድ የሚያስገድደው አንዳች ምክንያት የለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን እንደያዘ አገልግሎቱን መስጠት የሚያግደው ነገር የለም፡፡ አምባሳደሩ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ጠብቆ ተልእኮውን እንደሚፈጽም ሁሉ፡፡ ለተልእኮ የሔደበትን አገር ዜግነት መያዙ ሥራን ለማቅለል ስለሚጠቅም የሚለው አሁንም ከሥጋዊ ምቾት ጋር የተያያዘ ስንኩል ምክንያት ነው፡፡ መነኵሴ እኮ በምድረ በዳ፣ ደጋ ወጥቶ ቆላ ወርዶ ቊሩንና ሐሩሩን ታግሦ ሐዋርያዊ ተልእኮውን ለመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን የፈጸመ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነው፡፡ ዛሬ ለተለያዩ ሥጋዊ ጥቅሞች (ለዘመድ አዝማድ ጭምር) ሲባል ካንድ በላይ የውጭ አኅጉረ ስብከቶችን ደርበው የያዙ፣ ይህ ሥልጣን እንዳይነካባቸው በዓላውያን አገዛዞች ደሙ እንደ ጎርፍ ለሚፈሰው የጥምቀት ልጆች ሳይጮኹ፣ ይህንን የሚፈጽመውን ርጕም ሰውና ሰይጣናዊ አገዛዙን ለመናገር ጥብዐቱ ሳይኖራቸው፣ አገርና ቤተ ክርስቲያን ከሚያፈርሱ ጋር በዝምታ በመተባበር አንዳንዴም በማገዝ ጭምር ያሉ የስም ‹አባቶች› የግል ጥቅማቸው ሲነካባቸው የሚያሰሙት ጩኸት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ መሰማቱ በእጅጉን የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ አምላኬን ምን ብንበድለው ነው ለእነዚህ ‹ምንደኞች› አሳልፎ የሰጠን በማለት አዝናለሁ፡፡ ባጭሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ መንፈሳዊ አባት በሕግ ተጻፈ/አልተጻፈ ከፍ ብዬ ባነሳኋቸው ምክንያቶች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከ1600 ዘመን በላይ ‹‹በቅኝ ስትገዛ›› የቆየችው ሊቃውንት አባቶቻችን እንደጻፉትና እንዳስተማሩን በሥርዋጽ (ሆን ተብሎ ተሰንቅሮ በተቀመጠ) ‹‹ከግብጻውያን አባቶች ሌላ እንዳይሾም›› ተብሎ በገባ ቃል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ እና በትጉሃንና መንፈሳውያን ሊቃውንት ጥረት ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ‹ባርነት› ተላቅቀን በራሳችን ልጆች ጳጳስ እንድንሾም ሲደረግ ሐሳቡ ከባላገሩ/ከባለርስቱ እንዲሾም መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ የአገር ባለቤት ደግሞ ዜጋ ነው፡፡ አለበለዚያማ በእምነት ከሚመስሉን አራቱ የኦርየንታል አኀት አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳትን አምጥተን መሾም የሚከለክን የለም፡፡ የአሜሪካን ዜግነት ያለው ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ነው፡፡ በመሆኑም ከግብጽ፣ ከሶርያ፣ ከአርመንና ከሕንድ ማላባር ጳጳሳትን መሾም ይቻላል የሚል አንድምታ ያለው አሠራር ውስጥ እንዳንገባ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡  

ይህን ሁለ ሐተታ ውስጥ የገባሁት የአገርና የቤተ ክርስቲያን  ጉዳይ በመሆኑ ከዋናው አጀንዳ እንዳልራቅሁ በማሰብ ነው፡፡ አሁን አሁን የመጣ ፈሊጥ አንድ ሰው ብዙዎች ከያዙት የተለየ አቋም ይዞ ሲገኝ የአገዛዙ ሰው መሆን አለበት፣ ሐሳቡ አገዛዙን የሚደግፍ ነው የሚለው ድምዳሜ ጥሩ አዝማሚያ አይመስለኝም፡፡ የሚነገረው እውነት ከሆነ ቢመርም መቀበል ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የሠለጠነውን ፋሺስታዊ አገዛዝ የሚደግፍ አንድም በጽኑ ደዌ የተያዘ አሊያም ኢትዮጵያዊነቱን የካደ አድርባይ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ንግግራችንም ሆነ ጽሑፋችን በማስተዋል ይሁን፡፡ 

ዛሬ በዓለማችን ብዙ ዓይነት ስደት አለ፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ከተወለዱበትና ዜጋ ከሆኑበት አገር ነፃነታቸውንና ሕይወታቸውን ላለማጣት የሚሰደዱ ሰዎች አሉ፤ ሥጋዊ ሕይወታቸውን ምቹ ለማድረግ ወይም ‹‹የተሻለ ዕድል›› ለማግኘት በመሻት በፈቃዳቸው አገራቸውን ለቅቀው የሚወጡ የኢኮኖሚ ስደተኞች አሉ፤ በጦርነት፣ በረሃብ፣ እንዲሁም በሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ምክንያት ለስደት የሚዳረጉ ሰዎች አሉ፡፡ 

በሌላ በኩል በክርስትና እምነት ለጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ሰዎች አሉ – መንፈሳዊ ስደት፡፡ ይህ ዓይነቱ ስደት የመንፈሳዊ ተጋድሎ መገለጫ በመሆኑ ከሰማዕትነት የሚቆጠር ነው፡፡ ይህን የኋለኛውን ስደት ባርከው ቀድሰው የሰጡን ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እና እናቱ ድንግል ማርያም ሲሆኑ፣ እመቤታችን ሕፃን ልጇን ወዳጇን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን አዝላ ከአገሯ ቤተልሔም (እሥራኤል) ተነሥታ ወደ ግብጽ ምድር ያደረገችው ስደት በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቧል፡፡ በርካታ ቅዱሳንም የመድኃኔ ዓለምን እና የወላዲተ አምላክን አሠረ ፍኖት በመከተል በዓላውያን ነገሥታት ተገፍተው በስደት እንዲኖሩ ተገድደዋል፡፡ ሰማያዊ ክብርንም አግኝተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ስደት (ዓለማዊም ይሁን መንፈሳዊ) ዜግነትን ለመቀየር አያስገድድም፡፡ ባዕድ ለሆነ አገር ለመሞት መሐላ የፈጸመ ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ በስደት ለተጠለለበት አገር ሰንደቅ ዓላማ የተንበረከከ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እንዴት የትውልድ አገሩ ስትፈርስ፣ ሀገር የሆነችው ቤተ ክርስቲያኑ በጐሣ ቆጠራ ተከፋፍላ ህልውናዋ እንዲጠፋ ሲደረግ፣ የጥምቀት ልጆች የዘር ፍጅት ሲፈጸምባቸው፣ ካህናት በመሠዊያው ሥር ሲታረዱ፣ ለመላው ዓለም በተለይም ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ዓርማ የሆነው ሰንደቅ ዓላማዋ ሲዋረድ ዝም ብሎ ይመለከታል? ዛሬ በቤተ ክህነቱና በሲኖዶሱ ተሰባስበው በሃይማኖት ሽፋን ያሉ አብዛኞቹ ‹‹አባቶች›› ከፍ ብለን የጠቀስነውን ለሰማይና ለምድር የከበደ ነውር የፈጸሙ ናቸው፡፡ አድርባይ ከሆነው በስተቀር ተራውን ትውልደ ኢትዮጵያዊ እየተናገርሁ አይደለም፡፡ ብዙዎች ላገራቸውና ለቤተ እምነታቸው የሚቻላቸውን ሁሉ ሳይታክቱ እያደረጉ ያሉ መኖራቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

በመጨረሻም ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ ሳለሁ የወንድሞቻችንን የዘመዴን እና የቀሲስ ሳሙኤልን ‹‹እውን ሲኖዶሱ ታፍኗል›› በሚል የተላለፈውን መርሐ ግብር በኢትዮ-ቤተሰብ ሚዲያ ለማዳመጥ ዕድሉን አግኝቼአለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ያስተላለፍሁት መልእክት ቁም ነገር እንዳዘለ የምታምኑ አንባብያን በውይይቱ የተንፀባረቁትን አቋሞች በመጠኑም ቢሆን ለመዳኘት ያስችላችኋል ብዬ አምናለሁ፡፡ 

Filed in: Amharic