>

አጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች

አጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች

“The Study of history is the best medicine for a sick mind!” Livy
የታሪክ ጥናት ለሕሙም አእምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው።

በእደ ማርያም እጅጉ ረታ

ኢትዮጵያ ጥንታውያን ከሚባሉት ሀገሮች አንዷ ስትሆን፣ ከአምስት ሺህ ዓመት ያላነሰ ታሪክ አላት። በእነዚህ ዘመናት፣ ቀደምት አባቶቻችን ሠርተው፣ ትተውልን ካለፉት ሥራዎች መካከል የአክሱምሐውልት፣ የላሊበላ ቤተ መቅደስ ሕንፃዎች፣ የጎንደር ቤተ መንግስቶች ለምስክርነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ባለፉት በእነዚህ ዘመናት ሀገራችን የእርስ በርስ ጦርነትና ከውጭ በመጡ ወራሪዎች፣ ብዙ ቅርሶች ወድመዋል፣ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ከእዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ፣ በዐሥራ ስምንተኛውና ዐሥራ ዘጠነኛው ምዕት ዓመት፣ ሀገራችን ዘመነ መሳፍንት በመባል የሚታወቀው ጊዜ ውስጥ ገባች። ያ ወቅት ደግሞ አውሮጳውያን አፍሪቃን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመከፋፋል ወስነው ዘመቻቸውን የጀመሩበት ወቅት ነበር።
በዚያ ወቅት፣ ይህች በዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ኀይሏ የተዳከመችውን ሀገር መልሶ አንድ ለማድረግ፣ የቋራው አንበሳ ካሣ ኀይሉ፣ በኋላ ዳግማዊ ዐጤ ቴዎድሮስ ተብለው የነገሡት ተነሡ። ዐጤ ቴዎድሮስም በእነዚህ መሳፍንት ላይ በመዝመት ድል አድርገው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ተመልሳ እንደ ቀድሞው አንድ እንድትሆን መንገዱን ከፈቱ። ባደረጉትም ዘመቻ፣ አንድም ቀን ድል ሆነው
የማያውቁት ንጉሠ ነገሥት፣ ከአውሮጳውያኑ ጋር በተፈጠረው ችግር፣ የእንግሊዝ ጦር እስረኞቹን ለማስፈታት በዘመተባቸው ጊዜ፣ እጃቸውን ለወራሪው ጦር መስጠትን እንደ ውርደት ቆጥረውት መቅደላ አፋፍ ላይ ሽጉጣቸውን ጠጥተው የክብር ሞትን ጽዋ ተቀብለዋል።
ይሁን እንጂ፣ ዐጤ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ የተነሡት ነገሥታት እሳቸው የጀመሩትን ዓላማ በመከተል ኢትዮጵያ ተመልሳ አንድ እንድትሆን አድርገዋል። ከዐጤ ቴዎድሮስ ቀጥለው የነገሡት ዐጤ ዮሐንስ 4ኛ ሲሆኑ፣ በእሳቸው ዘመን የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ እና የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች,  ግዛቶቻቸውን እንደያዙ የዐጤ ዮሐንስን የበላይነት አሜን ብለው ተቀብለው ዕውቅና ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ በየበኩላቸው በቀጥታ ከውጭ ሀገር መንግሥታት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያደርጉ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
አውሮጳውያን የአፍሪቃን ምድር፣ እንደ ቅርጫ ሥጋ በሚቀራመቱበት በዚያ ወቅት፣ ኢጣሊያ በበኩሏ፣ በባህረ ነጋሽ በተባለው፣ እነርሱ ግን በኋላ ኤርትራ የሚል ስም የሰጧት፣ የቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ እግሯን ተክላ ነበር። እንደልቧ ለመስፋፋት ግን፣ ዐጤ ዮሐንስ እንቅፋት ስለሆኑባት፣ የወሰደችው አማራጭ ከሌሎቹ ነገሥታት (ንጉሥ ምኒልክ እና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት)ጋር ጥሩ
የወዳጃነት ግንኙነት መፍጠር ነው። ይኽም ኢጣሊያ ወደፊት ዐፄ ዮሐንስ ላይ ስትዘምት እንዲተባሩዋት ለማድረግ በማሰብ ነበር።

ዋናው ሐሳብ ይህ ሆኖ ሳለ ነገር ግን በአሰብ ወደብ ስለሚገቡ ዕቃዎች ቀረጥና በሸዋ ስለሚኖሩ ኢጣሊያኖች ሁኔታ ለመነጋገርና ፔትሮ አንቶኔሊ መልእክተኛ ሆኖ ወደ ንጉሥ ምኒልክ በ21 ሜይ 1883 ዓመተ ምሕረት በመምጣት ውል ተፈራረመ።

ንጉሥ ምኒልክም ወደፊት በዐጤ ዮሐንስ ላይ ለመዝመት እንዲያስችላቸው የጦር መሣሪያ እንዲገዙ ተስማሙ። ኢጣሊያኖችም በእውነት ንጉሥ ምኒልክ በዐፄ ዮሐንስ ላይ ይዘምታሉ ብለው ስላመኑ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ በመስጠትና እንዲሁም ብዙ ብድር በመፍቀድ የንጉሥ ምኒልክ ጦር ይበልጥ እንዲጠናከር አደረጉት። በዚህ መኸል፣ ዐጤ ዮሐንስ፣ እንግሊዞች በስምምነታቸው መሠረት፣ ምፅዋን ለኢትዮጵያ በማስረከብ ፈንታ ለኢጣሊያ መስጠታቸውን ንጉሥ ምኒልክ እንዲያወቁ አደረጉ። ንጉሥ ምኒልክ አንቶኔሊን በአስቸኳይ ጠርተው፣ ሁኔታውን እንዲያስረዳ ለጠየቁት የሰጣቸው መልስ ስላላረካቸው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጣሊያኖች ላይ ጥርጣሬ አደረባቸው። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ)ሚያዚያ 1889 ንጉሥ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ወሎ ላይ ውጫሌ በሚባለው ቦታ ሳሉ እያሉ ዐጤ ዮሐንስ መተማ ላይ መሞታቸውን ሰሙ። በአጋጣሚ ሆኖ አንቶኔሊ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ይዞ ሲመጣ ንጉሥ ምኒልክ እንጦጦ ስላልነበሩ፣ ውጫሌ ሄዶ አገኛቸው።

አንቶኔሊ ንጉሡ ወደ መናገሻ ከተማቸው እስኪመለሱ ድረስ መታገስ አቅቶት ወደ ውጫሌ የሄደው፣ በኢጣሊያኖች የተረቀቀውን ውል ለማስፈረም ነበር። ሃያ አንቀጽ ያለውን ይኽን ውል ንጉሥ ምኒልክና እንዲሁም በንጉሥ ኡምቤርቶ ስም አንቶኔሊ ሆኖ ፈረሙ። ይህ ውል፣ በተፈረመበትን ቦታ ስም <<የውጫሌ ውል>> ተባለ። ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ውል ውስጥ 17ኛው አንቀጽ አማርኛው፣ <<የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮጳ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል>> ሲል፣ የኢጣሊያንኛው ደግሞ <<የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮጳ ነገሥታት ለሚፈልጉት ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካይነት ማድረግ ይገባቸዋል>> ይላል። ይህ አንቀጽ ውሎ አድሮ በሁለቱ ሀገሮች መካካል የአድዋ ጦርነት ተብሎ ለሚታወቀው መነሻ ምክኒያት ሆኗል።
ንጉሥ ምኒልክ የውጫሌ ውል ሮም ላይ ሲፀድቅ በቦታው እንዲገኙ ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤልን ወደ ኢጣሊያ ላኳቸው። እሳቸውም ሮም ደርሰው በቬኒሲያ ቤተ መንግሥት ተገኝተው፣ ውሉ ከመጽደቁ በፊት፣ እ.አ.አ ኦክቶበር 1 ቀን 1889፣ <<የኢጣሊያ ግዛት ድንበር የሚጸናው በዚያች ቀን የኢጣሊያ ጦር ባለበት ቦታ ላይ ነው>> የሚል ተጨማሪ ውል እንዲፈርሙ አደረጓቸው። የኢጣሊያን
መንግሥት ይህን ያደረገውም በዚያ ወቅት፣ በጦርነት ተዳክሞ የነበረው የራስ መንገሻ ሠራዊት ዐቅም

ሙሉ ጽሑፉን ለማንበብ ቀጥሎ ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።  Atse Menelik

Filed in: Amharic