>

የዐድዋ ድልን፤ ያለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ማስብ ፈጽሞ የማይቻል ነው!!

ስለ ዐድዋው ጦርነት እና ድል በኢትዮጵያ ቤ/ክ አባቶች/ሊቃውንቶች አስቀድሞ ትንቢት መነገሩን እናውቅ ይሆን?! 

የዐድዋ ድልን፤ ያለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ማስብ ፈጽሞ የማይቻል ነው!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

በኢ.ኦ.ተ. ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ማኅበረ ቅዱሳን የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛ የሆነችው፤ እኅታችን መስከረም ጌታቸው፤ ከሰሞኑን ለዐድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሆን በታነጸው ቤተ-መዘክርን/ሙዚየምን ምርቃት መሠረት በማድረግ በ‹ድሬ ቲዩብ› ላይ፤ ‹መፍትሔው ራስን ማግለል ወይስ መጋፈጥ?!› በሚል አርእስት ቁጭት አዘል ጽሑፍ አስነብባናለች፡፡ የመስከረምን ቁጭት መነሻ አድርጌ ከዚሁ ቁጭት ጋር የሚሰናሰል አንድ የታሪክ እውነታ ለማንሳት ወደድኹ፡፡

በኢትዮጵያ ቤ/ክ ላይ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ለሚነሳው ወቀሳ፣ ሐሜታና ውግዘት ታሪክን በሚገባ መርምሮና መዝኖ ዘመኑን የዋጀ ተገቢውን መልስ በመስጠት ረገድ በቤተክህነቱ አካባቢ ባሉ ሰዎች ዘንድ ያለውን ስር የሰደደ ችግርና ግዴለሽነት ለጊዜ እንተወውና- ለመሆኑ፤ ‹የኢትዮጵያ ቤ/ክ ሊቃውንት/አባቶች ስለኢጣሊያ ወረራና ስለዐድዋው ድል ምን ትንቢት ተናግረው እንደነበር› በጣም በአጭሩ ታሪክን በማጣቀስ ለማስረዳት ልሞክር፡፡

የቀደሙት የእግዚአብሔር ነቢያት ከጓዳ እስከ እልፍኝ ከአደባባይ እስከ ሀገርና ዓለም አቀፍ ድረስ- ሊሆን፤ ሊመጣ ያለውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ ተረድተው ትንቢት/ቃል የሚያመጡ፣ ነገሥታትን/መንግሥታትን የሚገሥጹ፣ የሕዝብን ልብ ለንስሓ የሚያዘጋጁ ነበሩ፡፡ የቀደሙት ነቢያት እንደዛሬዎቹ ነቢያት ነን ባዮች፤ ሕዝብን ሰብስበው፤ ‹‹ስምህን፤ ስልክ ቁጥርህን፣ ዛሬ ማለዳ የበላኸውን… ወዘተ. ጌታ ገለጸልኝ…›› በማለት በሰው ሕሊና/አእምሮ የሚጫወቱ ደፋሮች፣ ማሃይምናን፣ ፍቅረነዋይ አቅላቸው ያሳታቸው፣ ሸቃጮች አልነበሩም፡፡

ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስም፤ ‹ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የመውረሯ ነገር አይቀሬ መሆኑንና ግን በዐድዋው ጦርነት ተሸንፋና የሃፍረት ሸማን ተከናንባ ኢትዮጵያን እንደምትለቅ፤› አለቃ ለማ ኃይሉ የተባሉ የቤተክርስቲያናችን ሊቅ የሚከተለውን ትንቢታዊ ቅኔ መቀኘታቸውን ልጃቸው አብዬ መንግሥቱ ለማ፤ ‹‹መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም፤ ‹‹በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን አምላክ ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም፤›› (አሞጽ 3፤7) እንዲል፡፡ እንሆ ቅኔው፤

‹‹ምኒልክ ግበር ላዕለ ሮምያ/ሮማ መጠነ እዴከ ትክል፣

አምጣነ ለአጺድ በጽሐ ማእረራ ወመዋዕሊሃ ለኃጉል፣

ዓዲ ተዘከር ውስተ ወንጌል፣

ላዕለ ሮምያ በለስ ኢሀሎ አስካል፣

በከመ ይቤ ወልደ ያሬድ ቃል፡፡››

ትርጉም፡-

‹‹ምኒልክ በሮማ ላይ እጅህ እንደቻለ መጠን አድርግ፣

መከሯ ለመታጨድ፣ ቀኗም ለጥፋት ቀርቧልና፡፡

ዳግመኛ በወንጌል ያለውን አስብ፣

በሮምያ/በበለስ ላይ ፍሬ የለም እንዳለ ወልደ ያሬድ/ቃል፤››

ምኒልክ በቤተስኪያን የሉም ይኸ ሲባል፡፡ ይኸ ጥንቆላ ነው፤ ያድዋ ጦርነት ሳይደረግ ነው፡፡ ኸጣልያን ጋር ስምም ናቸው ያን ጊዜ አጤ ምኒልክ፡፡ አለቃ ወልድ ያሬድ ‘መልካም መልካም!’ አሉና፣ እሑድን ዋልነ፡፡ ሰኞ ጉባዔ አለ፤ አለቃ ተጠምቆ ናቸው እሚያኼዱ፡፡ አለቃ ወልደ ያሬድ እርሳቸው እልፍኝ አጠገብ ቤት ሰጥተውናል፡፡ እርሳቸው መጥተው ይቀመጣሉ ኸጉባዔ ለመስማት፡፡

የኔታ ተጠምቆ

አቤት!

ኸኒያ ክፉዎች ጋር እኮ ጠብ ላይቀርልን ነው፤ አሉ፡፡

እንግዴህ ትግሬ ናቸው አለቃ ተጠምቆ እነ ራስ አሉላ፣ እነ ራስ መንገሻ አሉ ኸኒያ መስሏቸው፤

ኸነማን ጌታዬ? ኸነማን? አሉ ደንግጠው አለቃ ተጠምቆ፡፡

ኸነጮቹ፤

ምነው፣ ምነው? አሉ፡፡

እንዴ! የልጅዎን ቅኔ በቀደም አልሰሙትም?

በለማ ቅኔ ሆነ እንዴ ጦርነት? አሉ አለቃ ተጠምቆ፡፡

አናጋሪው ማን ይመስልዎታል?! አሉ፡፡

እንደ መውጫ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ፤ ከአገራችን ነጻነትና አንድነት፤ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፤ ስለ ነጻነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር ‹በቃልም በተግባርም› ጭምር ያስተማረች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ተቋም ናት፡፡ ቤተክርስቲያናችን ከሀገራችን ከኢትዮጵያ አልፎም፤ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራትና የነጻነት ትእምርት መሆኗ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

ለአብነትም የነጻነት ታጋዩ፣ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንቶች የነበሩት ኔልስን ማንዴላና ታቦ እምቤኪ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግራቸው፤  ‹‹… የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ነጻነት ክብርና ዓርማ፤ ለአፍሪካ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ማከማቻ፣ ማእከል መሆኗን እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት፤

‹‹… the Ethiopian Church would be the authentic African church that serves as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity, and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church.›› 

ሰላም!

Filed in: Amharic