>
5:16 pm - Sunday May 24, 0820

“ሆሣዕና” የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት።

“ሆሣዕና” የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት።

መ/ር ጌታቸው በቀለ
                                                                             መግቢያ
ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መገቢያ ዋዜማ ነው። ሆሣዕና አስቀድሞ ካለው ረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ስም በዚሁ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ “ሆሣዕና በአርያም’’ ‘”ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ “ዕለተ ሆሣዕናሁ አርዓየ…” ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር፣ በውዳሴና ቅዳሴ “ሆሣዕና በአርአያም” እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።
ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሃት፣ በረዐድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት ጌታ፤ በአህያና በውርንጫይቱ በትሕትና ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡
ሆሣዕና ሆሣዕና ማለት “አድኅነነአ፤ አድነና፣ አድነንኮ፤ እባክህ አድነን” ማለት ነው፡፡ ትርጓሜውም “መድኃኒትነት ወይም መድኃኒት መኾን ማለት ነው፡፡ የበዓል ስም የሥላሴን በዓል፣ሥላሴን ይዘው እያመሰገኑ የሚያወድሱበት ለብሉይ የመጸለት ሰባተኛ ቀን፤ ለሐዲሱ ግን ከትንሣኤ በፊት ያለ እሑድ ነው” ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(1948)፡፡ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡ (አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት)፤ ገጽ 373፡፡ በዓለ ሆሣዕና ከዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት አንዱና የዐቢይ ጾም ስምንተኛው እሑድ ነው፡፡
ሆሣዕና የሚለው ቃል ትርጉም መድኃኒት ማለት ነው፡፡ በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደሆነ አወቅን›› ዮሐ. ፬÷፵፪ ተብሎ እንደተፃፈው፡፡ ይኸውም መድኃኒት ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ሱባኤ የቆጠሩለት በዳዊት ከተማ የተወለደው፣ ከጽዮን የወጣውና መዳንን ለሚሹ ሁሉ የተሰጠ መድኃኒት ነው፡፡ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ “አቤቱ እባክህን አሁን አድን፤ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” እንዲል /መዝ. ፻፲፯÷፳፭—፳፮/፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በአህያዋና በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት በመንገዱ ዘንባባና የልዩ ልዩ ዛፍ ዝንጣፊ እየጎዘጎዙ ልብሳቸውን እያነጠፉ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት ነው፡፡ ይህ ዕለት “የጸበርት እሑድ” /Palm Sunday/ በመባልም ይታወቃል፡፡
የዘንባባው እሑድ /Palm Sunday/ ይህ ዕለት የጸበርት እሑድ /Palm Sunday/ በመባል ይታወቃል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ሆኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸውም ሣራ የወላድነት ዕድሜዋን ጨርሳ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ የጎበኟትን አምላክ አመስግነዋል፡፡ እስራኤልም ከግብጽ በወጡ ጊዜ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ አመስግነዋል /ዘሌ ፳፫÷፵—፵፪፤ ዮሐ. ፲፪÷፲፫ /፡፡ በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት፣ ከሲኦል ባርነት ለማውጣት ወደ መስቀሉ በተጓዘ ጊዜ /ሉቃ.፳፪÷፲፰/ ሕፃናትና አእሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እነርሱ ሳያውቁ እግዚአብሔር ባወቀ ዘንባባ በመያዝ “ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል” እያሉ ዘምረዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን አስቀድሞ በነቢዩ ዘካርያስ “እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ኾኖ በአህያይቱም፤ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ/ዘካ.፱÷፱/፡፡ እስራኤል ዘንባባ በመያዝ እንዳመሰገኑት እኛም አስራኤል ዘነፍስ ዕለቱን ዘንባባ (ጸበርት) በግንባራችን በማሰር በዓሉን በየዓመቱ እያስታወስን እናከብራለን፡፡ በዚህ ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡
ለምን ዘንባባ ያዙ ቢባል? ይስሐቅ በተወለደ ጊዜ አብርሃም ደስ ብሎት ዘንባባ ይዞ እግዚአብሔርን አመስግኖበታል የደስታ መግለጫ በመሆኑ አንተ ደሰታ የምታስገኝ ሐዘናችንንም የምታርቅ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ ደርቆ እንደገና ሕይወት ይዘራል፤ የደረቀ ሕይወታችንን የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ እሾሃም ነው፤ አንተም ህያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ በሌላም በኩል ዘንባባ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ አይበላውም አንተም ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ፤አንድም ዘንባባ ረጅም /ልዑል/ ነው አንተም ባሕርይህ ልዑል ነው ሲሉ ዘንባባ ይዘው ተቀብለውታል፡፡ ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው የሰላም አምልክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ የነፃነት ምልክት ነው ከባርነት ነፃ የምታወጣን አንተነህ ሲሉ ነው አኛም ይህን በማሰብ ዘንባባ ይዘን ሆሣዕና በአርያም እያልን ዕለቱን እናስባለን፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
Filed in: Amharic