>

በምናምንቴዎች ላይ የወደቀች አገር

 

በምናምንቴዎች ላይ የወደቀች አገር

ከይኄይስ እውነቱ

ሊቁ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ‹‹ዐዲሰ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› በሚለው ሥራቸው ምናምንቴ የሚለውን ቃል ከንቱ፣ የማይረባ፣ ነውረኛ፣ ልክስክስ፣ ጣዖት በማለት ይተረጕሙታል (ገጽ 786)፡፡ አንድም ምናምንቴ የሚለው ቃል የሚያስተላልፈው አሉታዊ መልእክት ለሚገባቸው (‹ገ› ጠብቆ ይነበብ) ክፍሎች መዋረድን መናቅን የሚያመለክት በዘለፋነት የሚነገር ቃል ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ አሁን በምትገኝበት አስከፊ ሁናቴ በማናቸውም ምክንያት ከሕዝቧና ብሔራዊ ጥቅሟ በተጻራሪ የቆሙ ኃይሎች (ግለሰቦችን ጨምሮ) በሙሉ በርእሱ በተጠቀሰው ስም ቢጠሩ አካፋን አካፋ ማለት በነቀፌታ የተጠቀከምሁበት ቃል እንደሆነ አንባቢዎች በሙሉ በቅድሚያ እንድትረዱልኝ በማክበር እጠይቃለሁ፡፡ በእኔ አረዳድና እምነት እነዚህ ምናምንቴዎች ባገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም የሚገኙ ሲሆን፣ እነማን ናቸው ለሚለው የተጠናቀቀ ዝርዝር ማቅረብ ባይቻልም ጎላ ያሉትን ግን መጠቆም ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህል፤

  • ብአዴን እና ታናሽ ወንድሙ አብን፤
  • ርጉም ዐቢይ፣ ፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝ አመራሮቹና ተወራጆቹ (ኦነግ/ኦሕዴድ)፤
  • ወያኔ ሕወሓት፣ አመራሮቹ እና ደጋፊዎቹ፤
  • የዘር ፖለቲካ የተጣባቸው በሙሉ፤
  • የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በውስጥ በአፍኣ የሚያፈርሱ ኃይሎች በሙሉ፤
  • ‹‹የብልጽግና ወንጀል›› በሚባለው ባዕድ/ሰይጣናዊ አምልኮ ውስጥ ማኅበርተኞች የሆኑ ጉዶች በሙሉ፤
  • በቤተ እምነቶች ውስጥ ተሸሽገው በእምነት ሽፋን፣ የፋሺስታዊው አገዛዝ አባሪና ተባባሪ በመሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገር በማፍረስ፣ በማኅበረሰብ መካከል ዘረኛነትና ጥላቻን በማራገብ እልቂትን የሚደግሱ ብሎም በገዳይ ቡድን መዋቅር ውስጥ ተደራጅተው በገዳይነትና አስገዳይነት የተሰማሩ ነውረኞች በሙሉ፤
  • ‹‹አገራዊ ምክክር›› በሚል ፌዝ በአጋንንታዊው አገዛዝ ሥር ተደራጅተው የአገርን መከራ፣ የሕዝብን ሰቆቃ ለማራዘም የሚዶልቱ ቡድኖችና ግለሰቦች በሙሉ፤
  • ለፋሺስታዊው አገዛዝ ቀኝ እጅ በመሆን በመደበኛም ሆነ ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ሆነው ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ 24/7 የሚቀጥፉና የሚዋሹ፣ ባገር ጥፋትና በሕዝብ እልቂት ግምባር ቀደም ተባባሪ የሆኑ ቅጠረኛ ቡድኖችና ግለሰቦች፤
  • የአገር ጉዳይ አያገባኝም ብለው ተዘልለው የተቀመጡ፣ ያለው ሁናቴ እንዳለ እንዲቀጥል በመመኘት የ‹ምቾት› ጥጋት ፈጥረው በአድርባይነት የተቀመጡ በሙሉ፤
  • የበኩላቸውን አንዳች አስተዋጽኦ ለማድረግ ፍላጎቱ ሳይኖራቸው በሌላው ዜጋ መሥዋዕትነት ነፃነት ለመውጣት የሚቋምጡ ሰነፎች፣ ዝርፊያና ንቅዘትን ቋሚ ተግባራቸው ያደረጉ ቡድኖችና ግለሰቦች በሙሉ፤ 
  • የወገን ተቆርቋሪ መስለው፣ የኢትዮጵያዊነት ካባ አጥልቀው፣ አንዳንዶቹም የእምነት ሰው መስለው፣ የዕውቀትና የማስተዋል ጨዋ ሆነው፣ የቀድሞ ወራዳ ማንነታቸው አገርሽቶባቸው፣ የአገርን ጉዳይ ‹‹የልጆች ጨዋታ›› በማድረግ፣ መነሻቸውንም ሆነ መድረሻቸውን ገንዘብ አድርገው፣ ለታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ቅጥረኞች ሆነው፣ መንጋ ተከታይ አለን በሚል በነውር በተሞላ አንደበትና ጽሑፍ ልዩነትን ብቻ የሚያራግቡ ቡድኖችና ግለሰቦች፤ወዘተርፈ፡፡

ምናምንቴዎቹ በመብዛታቸው ወይም ያለ ኀፍረት በድፍረት አየሩ ላይ ስለናኙ፣ ዐዋቂዎች እንደ ሰጎን ራሳቸውን አሸዋ ውስጥ ቀብረው በሚያስደነግጥ ዝምታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አንድም የምናምንቴዎቹን ተራ ስድብና ዘለፋ ሽሽት፡፡ አንድም ሥልጣን በአቋራጭ ፈላጊዎች የሚል የምናምንቴዎቹን ከንቱ ክስ በመፍራት፡፡ ወዲህም አድምጦ ተግባራዊ የሚያደርግ በመጥፋቱ ዝምታን የመረጡ አሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ አቋም ባገር ደረጃ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለን በመሆኑ፣ ከዚህም ብዙ ሳይረፍድ አገርንና ሕዝብን በመታደግ ታላቅ ተግባር ውስጥ የበኩላችሁን እንድታበረክቱ በዚህ አጋጣሚ እንደ አንድ ዜጋ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡ እኛ ዘለፋና ነቀፋ ፈርተን የምንሸሽ ከሆነ ከፋሺስቶች ጋር ፊት ለፊት ገጥመው እየተፋለሙ ውድ ሕይወታቸውን የሚገበሩትን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን ለአፍታ ማሰብ እንዴት አቃተን? ፋሺስታዊውን አገዛዝ ለማስወገድ በተጀመረው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በዕውቀታችሁ፣ በሕይወት ተሞክሯችሁ፣ በዳበረ ልምዳችሁ ሜዳ ላይ ያለውንና የሕይወት መሥዋዕትነት እየተከፈለበት፣ ወገኖቻችን በገፍ እያለቁ ያሉበትን የህልውናና አገርን የመታደግ ትግል በምትችሉት ሁሉ (በዕውቀት፣ በማንቃት፣ በምክር፣ አደረጃጀታዊ ጥበብን በማካፈል ወዘተ) መስመር የማስያዝ እና ትግሉ ባጭሩ እንዲቋጭ የማድረግ ኃላፊነት የለባችሁም?

አሁን አሁን ላገርና ለሕዝብ ቆመናል በሚሉ አንዳንድ የትግል ሚዲያዎች ጭምር፤ የዘመኑ ቴክኖሎጂ አመቸን በሚል ትንሹም ትልቁም ተነሥቶ ባገር ጉዳይ ላይ ወሳኝ ሆኖ አካኪ ዘራፍ ሲል ይደመጣል፡፡ ይህን አድርጉ፤ ይህን አታድርጉ፤ ይህን ተናገሩ፤ ይህን አትናገሩ፤ ይህንን ካሟላችሁ የትግሉ አካል ናችሁ፤ ካላሟላችሁ የትግሉ አካል አይደላችሁም ወዘተ. እያሉ እንደ ሐኪም መድኃኒት የሚያዙልን፣ እንደ ወታደር ሥርዓት የዕዝ ሰንሰለት አበጅተው የሚያዙን በዝተዋል፡፡ 

ባገር ጉዳይ እንኳን የአገሩ ባለቤት የሆነው ዜጋ ቀርቶ ዜግነት የሌለውም ተወላጁ (መንግሥት ባለበት አገር በሕግ የሚኖረው ገደብ እንደተጠበቀ ሆኖ) ያለጥርጥር በደምብ ያገበዋል፡፡ የማያገባቸውም እንኳን ጉልበታቸውን ተመክተው ዝፍቅ ብለው ገብተው እያመሱን ይገኛሉ፡፡ ከግለሰብ እስከ ቡድኖች፣ የተደራጁም ሆነ ያልተደራጁ አካላት ስለ አገር ጉዳይ የራሳቸው አመለካከትና አቋም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አመለካከቱ ገንቢም ይሁን አፍራሽ፤ አቋሙም ጠቃሚ ይሁን ጎጂ፣ ጊዜያዊም ይሁን ዘላቂ ዳኝነቱ ለሕዝብ የሚተው ሆኖ፣ ለሚንፀባረቀው አመለካከትና ለተያዘው አቋም ግለሰብም ይሁን ድርጅት ኃላፊነት የሚወስዱበት ይሆናል፡፡ ሚዲያዎች መደበኛዎቹም ሆነ ኢ-መደበኛዎቹ በራሳቸው ከሚቀርቡ ዝግጅቶች በተጨማሪ ላገርና ለጠቅላላው ሕዝብ በሚጠቅም ጉዳይ (የአገር ህልውናን፣ የሕዝብ ደኅንነትን፣ ዘላቂ ሰላምንና ጸጥታን፣ አንድነትን፣ አብሮነትን፣ ፍቅርን፣ ፍትሕና ርትዕን፣  የጋራ ዕድገትና ልማትን ወዘተ. በሚያመጡ ጉዳዮች) ማንቃት፣ መምራትና መስመር የማስያዝ ኃላፊነት አለብን ካሉ በሕይወት ልምድና በዕውቀት የለዘቡ አገርና ሕዝብ ወዳድ ምሁራን፣ሊቃውንትን እና ዕድሜ ያስተማራቸው ጠቢባንን በቋሚነት በመጋበዝ ተከታታይነት ያላቸው መርሐግብሮችን ሊያስተላልፉ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ በታሪካዊ የውጭ ጠላቶች አይዞህ ባይነት በኢትዮጵያችን ላይ የሠለጠነው ፋሺስታዊ የኦነግ/ኦሕዴድ አገዛዝ፣ ቋሚ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው ወያኔ ሕወሓት እና የኹለቱም አጋንንታዊ ቡድኖች ቋሚ ዘላለማዊ አሽከር ብአዴን እንዲሁም ውገናቸውን ከነዚህ ፋሺስታዊው ኃይሎች ጋር ያደረጉ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች አመለካከታቸውና አቋማቸው አገርን ማፍረስ፣ ሕዝብን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ በማንነቱና በእምነቱ መጨፍጨፍ፣ ከቤት ንብረቱ ማፈናቀል፣ ማሳደድ፣ ማደህየት፤ ቤተ እምነቶችን ከአማኒዎቻቸውና ቅርሶቻቸው ጋር ማጥፋት፣ ሥርዓተ አልበኝነትን ማንገሥ፣ አገራዊ ሀብትን መዝረፍና ማሸሽ፣ ብሔራዊ ቅርሶችንና መለያዎችን ማጥፋት፣ ባጠቃላይ አገርና ሕዝብን በማዋረድ ለባርነት መዳረግ መሆኑን ደግመው ደጋግመው ለሕዝብ ይፋ በማድረጋቸው ከፍ ብለን ለተናገርነው አሳብና አቋምን ባግባቡ ማስተናገድ ለሚለው አጠቃላይ አነጋገር ወይም ደንብ (general rule) እንደ ልዩ ሁናቴ (exception to the general rule) ስለምናያቸው እነሱን አይመለከቱም፡፡ ምክንያቱም አገርም ሕዝብም በሌሉበትና በማይከበሩበት መደማመጥ ስለማይኖር፣ ቅድሚያ እነዚህን ምናምንቴዎች አፅድቶ የታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ መጣል ግድ ይለናል፡፡ ለኢትዮጵያችን በመጀመሪያው ረድፍ የምናየው አንገብጋቢ ጉዳያችንም ይኸው ነው፡፡

የዛሬው አስተያየቴ ባቢሎናዊ ጠባይ ስላለው ለረዥም ጊዜ በውስጤ ሲመላለሱ የቆዩ አንዳንድ ጥያቄዎችን (መልስ ባለገኝላቸውም) ለማንሣት ወደድሁ፡፡ ባለፉት አምስት ዐሥርታት ለክህደት፣ ለኑፋቄ፣ ለአድርባይነት፣ ለሆድ፣ ለክፋት፣ ባጠቃላይ ለነውር ሁሉ ቅርብ የሆኑ ምናምንቴዎች ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የበዙበት ምክንያት ምንድን ነው? በአእምሮ በአስተሳሰብ የቀነጨረ፣ አገሩን ወገኑን አምርሮ የሚጠላ ስንኩላነ እና ድውያነ አእምሮ እንደ አሸን የፈላበት ምክንያት አጋንንታዊ አገዛዞች ስለሠለጠኑብን ብቻ ነው? ሥር የሰደደው ማኅበራዊ ድቀት (የግብረ ገብ መንኮታኮት፣ የሥነ ምግባር መላሸቅ) ከየት መጣ? ቤተ እምነቶች፣ መሪዎቻቸውና አማንያኑ ጭምር በአመዛኙ አስመሳዮች ስለሆንን ነው? ቤተ እምነቶችን ከተራ የንግድ ተቋምም በታች ስላደረግናቸው ነው? የሐሰት ጳጳሳቱና ኤጲስ ቆጶሳቱ ጉዳይ ብዙ ስለተባለበት ወረድ ልበልና ቀጣፊ የደብር ጸሐፊ፣ ወስላታ ‹ሰባኬ ወንጌል› እና ሌባ የደብር አለቃ ‹ክቡር› እየተባባሉ ርስ በርሳቸው የሚሸነጋገሉበት ምክንያት ምን አመጣው? በሽንገላና በማስፈራራት ምእመኑን ለምን ይዘርፉታል? ለመሆኑ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል አገርና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙበትን ዓውድ እና ተጨባጭ እውነታ መሠረት አድርገው ጊዜውን የዋጀ ትምህርትና ስብከት ይሰጣሉ? ቊጥራቸው ቀላል የማይባል ምእመናን ነውር ኃጢአታቸውን በንስሓ ከማንፃት ይልቅ ለምን በገንዘብ ለመሸፈን ይጥራሉ? ለምን ሰንበት ት/ቤቶች በአብነት ትምህርቱ ተተኪ ትውልድ የሚፈራባቸው መንፈሳዊ ተቋማት ከመሆን ይልቅ ወጣቶች  በዓል ለማድመቅ ‹ለጭፈራ› ብቻ የሚተራመሱባቸው ቦታዎች ሆኑ? ታላቁ ታናሹን እንዳያንፅ ሰንበት ት/ቤቶች ለምንስ  የዕድሜ ገደብ ሊጣልባቸው ተፈለገ? ሊቃውንት አባቶች በረሃብ በሚጠበሱበትና በሚሰደዱበት አገር አንድ ተራ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን (ከአለቃ እስከ አናጕንስጢሱ፣ መነኮሳትን ጨምሮ) ከየት በመጣ ሀብት ነው ባለ ቪላ ቤት፣ ያማረ መኪና ወይም የተንደላቀቀ ሥጋዊ ሕይወት ሊኖረው የሚችለው? የተለያየ የገቢ ምንጭ ያላቸው አድባራትና ገዳማት ምእመኑን በገንዘብ ውትወታ የሚያስጨንቁት እሰከ መቼ ነው? ምእመኑስ እውነተኛ አገልጋዮችን ከአስመሳዮቹ በመለየት የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል ብሎ (ጽድቅ እየመሰለው) ገንዘቡን ለ‹ሌቦች› የማይበትነው? ሀብት፣ ንብረትና፣ ቅርሶችን በኃላፊነት ስሜት የሚቆጣጠረው? 

ከመንፈሳዊው ጉዳይ ወጣ ብለን ደግሞ ሁለት ሰዎች በየትኛውም ዓለማዊ ይሁን መንፈሳዊ መመዘኛ በጎ በሚባል ነገር ላይ መተባበር የተሣናቸው በምን ምክንያት ነው? ወላጆች በልጆቻቸው የትምህርት ጉዳይ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናገሪ ሊሆኑ ያልቻሉበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ስለምን ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ ዓመፀኛና ‹አውሬ› ትውልድን አፈራን? የልጆቹን ውሎ የማይጠይቅ፣ የቅርብ ጓደኞቻቸውን የማያውቅ ወላጅ እንዴት ነው ልጆቹን ባግባቡ አሳደግሁ ማለት የሚችለው? የሞያን መሠረታውያን ማወቅ፣ ሞያን አከብሮ መሥራትና ለሞያ ሥነ ምግባር መገዛት (ፕሮፌሽናሊዝም) ለምን ጨርሶ ጠፋ? ላንድ ዓላማ እየተዋጋንና ጎን ለጎን እየሞትን እንኳን በልዩ ልዩ ውስጣዊ ፍትወት ምክንያት የጋራ ግብን እስክናሳካ ለመታገሥ ለምን አቃተን? በሕይወት ቆይተን ልዩነታችንን መፍታት አንችልም? እምነት አለን የምንል ከሆነ ተሸንፈን ማሸነፍ አንችልም? ከእኛ ከንቱ ፍትወት ሕዝብና አገር አይበልጥም? በመጨረሻም ምናምንቴዎቹ እንደሚመኙት ለመሆኑ እንደ ኅብረተሰብ ጨርሶ ጠፍተናል/ወድቀናል?

Filed in: Amharic