>

የመጀመሪያዎቹ የአማርኛ ቋንቋ ምሩቃን ቻይናውያን ተማሪዎች በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ!!

የመጀመሪያዎቹ የአማርኛ ቋንቋ ምሩቃን ቻይናውያን ተማሪዎች በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ!!

ተረፈ ወርቁ ደስታ

 

ከጥቂት ሳምንት በፊት በቻይና/ቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ለ4 ዓመት አጥንተው በመጀመሪያ ድግሪ ስለተመረቁ ቻይናውያን ተማሪዎች በዋልታ ቴሌቪዥን/የ”ካሪቡ አፍሪካ” ሾው ትናንትና ማምሻውን አንድ ዝግጅት ቀርቦ ነበር።

በዚህ ዝግጅት ላይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ፕሮፌሰርና የፕሮግራሙ አስተባባሪ የኾኑት ስንቅነሽ አጣለ (ዶ/ር)፤ የአማርኛ ቋንቋ በቻይና ቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር የተጀመረበትን ሂደቱንና ቋንቋ በሀገራት ግንኙነት፤ በባህል ልውውጥና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት/Public Dipolmacy ረገድ ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያዊ ስማቸው ቴዎድሮስና ቤዛዊት የተባሉ ቻይናውያን የአማርኛ ቋንቋ ተመራቂ ተማሪዎችም ስለ አማርኛ ቋንቋ ግሩም የሆነ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት፤ አማርኛ የጽሑፍ ቋንቋ ሆኖ ብቅ ያለው መጀመሪያ ላይ በአፄ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ከ1297-1327 ለንጉሡ በተገጠመ ግጥም እንደሆነ ያሳያሉ። ይህ ማለት የዛሬ 789 አመት ነው።

ከዚያም ለሁተለኛ ጊዜ በተገኘ የፅሁፍ ማስረጃ በአማርኛ ቋንቋ የተፃፈው በአፄ ይስሃቅ ዘመን መንግስት በተፃፈ ግጥም ነው። ሦስተኛው ደግሞ በአፄ ዘርአያዕቆብ ዘመን መንግስት ከ1399-1414 ዓ.ም  በተፃፈ ፅሁፍ ነው። እንዲሁም ለአፄ ገላውዲዮስ/አፅናፍ ሰገድ 1540-1559/ የተገጠመው ግጥም ተገኝቷል። ግጥሙ ንጉሡ ከግራኝ አህመድ ጋር ያደረጉቱን ጦርነት እና ያገኙትን ድል የሚያወሳ ነው። አማርኛ በየ ስርዓተ መንግሥቱ እየጐለበተ መጣ።

በመሠረቱ የአማርኛ ቋንቋ በውጩ ዓለም/በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ የረጅም ዘመናት ታሪክ ያለው ቋንቋ ነው። በተለይ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ አንድ ክስተት ተፈጠረ። አባ ጐርጐሪዮስ የሚባሉ አባት በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ከቤተ-አምሐራ ይሰደዱ እና ወደ አውሮፓ ይሔዳሉ። እዚያም ሂዮብ ሉዶልፍ የተባለ የቋንቋ ተመራማሪ ጋር ይገናኛሉ።

አባ ጐርጐሪዮስ የአማርኛ ቋንቋን ሥርዓት ባጠቃላይ ስዋሰውን ለሂዮብ ሉዶልፍ ያስረዱታል። እርሱም አባ ጐርጐሪዮስን እንደ መረጃ አቀባይ (informant) ቆጥሮ የአማርኛ ቋንቋ ሰዋሰው መዝገበ ቃላት እ.ኤ.አ በ1698 ዓ.ም አሣትሞ አስወጥቷል። ከዚህ ዘመን ጀምሮ የአውሮፓ ሊቃውንት በአማርኛ ቋንቋ እና በኢትዮጵያ ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ ጀመሩ በማለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና የሥነ-ጽሑፍ ሊቅ የነበሩት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ጽፈዋል።

ስለ አማርኛ ቋንቋ መስፋፋት ምክንያት የሆኑ ነጥቦችን ስንጠቅስ አንድ ታላቅ ጀርመናዊ እፊታችን ድቅን ይላል። ይህ ሰው ዮሐን ፖትከን ይባላል። የኮሎኝ ሠው ነው። ይህ ሰው በቫቲካን በቅዱስ እስጢፋኖስ ከሚገኙ መነኮሳት የዳዊት የግዕዝ ግልባጭ አግኝቶ በሕትመት እንዲወጣ አድርጓል ይባላል። ይህም የሆነው በ1513 ዓ.ም ነው።

ጀርመናዊው ጉተንበርግ የመጀመሪውን የሕትመት መሣሪያ እንደሰራ ከታተሙ የአለማችን መፃሐፍት አንዱ ይህ ኢትዮጵያዊ መጽሐፍ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያን መፃሕፍት በአውሮፓ ማሣተም የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1513 ዓ.ም. በዮሐን ፖትከን አማካይነት ነው።

የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሐፊ ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለ ሕትመት ታሪክ ባዘጋጁት ግሩም መጽሐፋቸው ውስጥ ሌላ ጀርመናዊን ይጠቅሳሉ። ይህ ሰው ፒተር ሃይሊንግ ይባላል። ሙያው ሕክምና ነው። ግን ከፍተኛ የቋንቋ ችሎታ ያለው ሰው ነበር። ጐንደር ላይ ገናና መሪ ከነበሩት ከአፄ ፋሲል/1632-1667/ ጋር ጥሩ ጓደኝነት ይፈጥራል።

በወቅቱ ሃይማኖትን ለማስፋፋት ይፈልግ የነበረው ይኸው ጀርመናዊ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የዮሐንስ ወንጌልን እ.ኤ.አ በ1647 ዓ.ም. ወደ አማርኛ ተርጉሞ በማሳተም በብዛት ማሠራጨቱ ተጽፏል።

ለአማርኛ ቋንቋ መስፋፋት አስተዋጽኦ ካደረጉ ሰዎች መካከል ኢዘንበርግ የተባለው ሚሲዮናዊ ተጠቃሽ ነው። ይህ ሰው እ.ኤ.አ በ1841 ዓ.ም የጂኦግራፊ መጽሐፍ አሳትሟል። አማርኛው ግን ያው የፈረንጅ አማርኛ ነበር። ይህ ሰው ትግራይ አድዋ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱም በትግርኛ ቋንቋም አሳትሟል።

እ.ኤ.አ በ1835 ዓ.ም ደብተራ ማቴዎስ የተባለ ኢትዮጵያዊ ቀጥሮ ሐዲስ ኪዳንን ወደ ትግርኛ ቋንቋ መተርጐሙን ዶ/ር አምሣሉ አክሊሉ አጭር የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ በተሠኘው የጥናትና ምርምር መጽሐፋቸው ላይ ገልፀዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን በኢትዮጵያ ቋንቋ የመተርጐምና የማሠራጨት ስራ ተስፋፍቶ ነበር። በ1870 የሉቃስ ወንጌል፣ በኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሟል። ከሦስት ዓመት በኋላ መዝሙረ ዳዊት እና ኦሪት ዘፍጥረት ቀጥሎም ኦሪት ዘፀአት እ.ኤ.አ. በ1877 በኦሮምኛ ታትሟል።

ይኸው ኢዘንበርግ የተባለው ሚሲዮናዊ ከጂኦግራፊ መፅሐፍ ሌላ የአማርኛ ንባብ ማስተማሪያ መፅሐፍ “የትምህርት መጀመሪያ” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ1941፤ “የዓለም ታሪክ መጽሐፍ” እ.ኤ.አ በ1842 ደርሶ አሳተመ።

ከዚያም ኢትዮጵያዊ መፃሕፍት በአውሮፓ ውስጥ ይታተሙ የነበሩት በብዛት ጀርመን እና ስዊዝ ውስጥ ነበር። በተለይ በስዊዝ አገር በቅዱስ ክሪቮና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማተሚያ ቤት ተቋቁሞ ስለነበር ከስዊዝ እስከ ኢትዮጵያ መፃሕፍት ይጓጓዙ ነበር። በሰው፣ በእንስሳት፣ በባህር ላይ እየተጓጓዙ በአማርኛ ቋንቋ ለማደግ ሁሉም ተረባርቧል። አማርኛ ቋንቋ የሁሉም ነው ማለት ይቻላል።

ለመውጫ ያህል፤

1955 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ቋንቋ ምን ይሁን የሚል ጥያቄ በምሁራን ዘንድ ተነስቶ ነበር። ያነሱት ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም። ከቅኝ ግዛት የተላቀቁት የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ምሁራን ናቸው። እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ፖርቹጋልኛ የአፍሪካ ቋንቋዎች አይደሉም፤ የቅኝ ገዢዎቻችን ቋንቋዎች ናቸው። ስለዚህ አፍሪካዊ የሆነ ቋንቋ ያስፈልገናል ተባባሉ።

አፍሪካዊ ፊደል ያለው የጽሑፍ ቋንቋ የሆነው ብዙ ታሪክ ያለው አማርኛ ቋንቋ በዋናነት ታጭቶ ነበር። ምክንያቱን በውል ባለተረዳሁበት እና መረጃም ያጣሁለት ነገር ቢኖር ይህ እጩነት እንዴት ገቢራዊ እንዳልሆነ ነው። አማርኛ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት የልሣን  ቋንቋ እንዲሆን መታሰቡ ግን የቋንቋውን ግዙፍነት ያሳያል። የቻይናውያኑን የአማርኛ ቋንቋ ተምፕራቂ ተማሪዎችና የመምህራቸውን ቃለ-መጠይቅ ከዚህ በታች በተቀመጠው ማስፈንጠሪያ/ሊንክ ያገኙታል።

https://youtu.be/qw1CG_ktGfM?si=5b-PmUaNH7Vop-wd

Filed in: Amharic